Print this page
Saturday, 06 July 2019 14:05

የኢትዮ-እስራኤላዊው ወጣት መገደሉ የቀሰቀሰው ተቃውሞ ቀጥሏል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የ18 አመቱ ኢትዮጵያዊ እስራኤላዊ ሰለሞን ተካ ባፈለው እሁድ ሃይፋ ከተባለችው ከተማ አቅራቢያ በአንድ እስራኤላዊ ፖሊስ በጥይት ተደብድቦ መገደሉን ተከትሎ፣ ድርጊቱ ያስቆጣቸው ቤተ-እስራኤላውያንና ደጋፊዎቻቸው ሰኞ ዕለት አደባባይ በመውጣት የጀመሩት ተቃውሞ ላለፉት ቀናትም ተባብሶ መቀጠሉ ተዘግቧል፡፡
በስራ ገበታው ላይ ባልነበረ ፖሊስ የተፈጸመውን ግድያ ተቃውመው በተለያዩ የእስራኤል ከተሞች ሰልፍ የወጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተ-እስራኤላውያንና ደጋፊዎቻቸው በፖሊሶች ላይ ድንጋይ በመወርወርና በጎዳናዎች ላይ እሳት በማቀጣጠል ተቃውሟቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ፖሊስ በበኩሉ ሰልፈኞችን ለመበተን አስለቃሽ ጢስና ተኩስ መጠቀሙንና በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰልፈኞችን መጉዳቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ወጣቱን ገድሏል የተባለው ፖሊስ በቁጥጥር ስር እንደዋለ የዘገበው የእስራኤሉ ሃሬትዝ ጋዜጣ፣ ግድያው ከዘር ጥላቻ የመነጨ ነው የሚል አቋም የያዘው ተቃውሞ ግን ባለፉት ቀናት ቴል አቪቭን ጨምሮ ወደተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች መስፋፋቱንና በሺህዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች የመኪና መንገዶችን በመዝጋትና መኪኖችን በማቃጠል ግድያውን ማውገዝ መቀጠላቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የእስራኤል ፖሊስ ሰልፈኞችን ለመበተን ባደረገው ጥረት በተፈጠረው ግጭት 111 ያህል ፖሊሶች መቁሰላቸውንና 136 ያህል ሰልፈኞች መታሰራቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ተቃውሞው መባባሱን ተከትሎ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በወጣቱ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን በመግለጽና ግድያውን በተመለከተ ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝ በመጠቆም፤ ሰልፈኞች ግን ህገወጥ ድርጊት ከማድረግ እንዲቆጠቡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የ18 አመቱ ኢትዮ-እስራኤላዊ የሰለሞን ተካ የቀብር ስነስርአት ባለፈው ማክሰኞ መፈጸሙን የዘገበው አልጀዚራ፣ ተቃዋሚዎቹ ወጣቱን የገደለው ፖሊስ በአፋጣኝ ፍርድ ቤት ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ መጠየቃቸውንና ቤተ-እስራኤላውያን ከዘር ጥቃትና ግድያ ነጻ የሚሆኑባትና ያለስጋት የሚኖሩባትን እስራኤል ለመፍጠር የሚያደርጉትን ትግል በዘላቂነት እንደሚገፉበትም ተናግረዋል፡፡
የእስራኤል ፖሊሶች በቤተ-እስራኤላውያን ወጣቶች ላይ ድብደባና ግድያ ሲፈጽሙ ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ከአራት ወራት በፊትም አንድ ኢትዮ-እስራኤላዊ ወጣት በፖሊስ ጥይት ተመትቶ ለሞት መዳረጉን አስታውሷል፡፡


Read 1871 times Last modified on Saturday, 06 July 2019 15:42
Administrator

Latest from Administrator