Saturday, 06 July 2019 13:55

በአሜሪካ ተቀምጠው “የጥላቻ ንግግር” የሚያሠራጩትን ለህግ ለማቅረብ እንቅስቃሴ ተጀምሯል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

 ፌስቡክ በአማርኛ የሚሰራጩ መልዕክቶች የምትቆጣጠር ኢትዮጵያዊት ቀጥሯል


            በአሜሪካ ተቀምጠው የጥላቻ ንግግር የሚያሠራጩ ኢትዮጵያውያንን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጐች ም/ቤት ያስታወቀ ሲሆን፤ ትልቁ የማህበራዊ ሚዲያ ፌስ ቡክ በበኩሉ፤ በአማርኛ ቋንቋ የሚሠራጩ የጥላቻ ንግግሮችን ለመቆጣጠር ኢትዮጵያዊት የአማርኛ ቋንቋ አርታኢ ቀጥሯል፡፡
የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጐች ም/ቤት የተሰኘውና መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ተቋም ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፤ በአሜሪካ ተቀምጠው የጥላቻ ንግግር በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚያሰራጩ መበራከታቸውንና ጉዳቱም እየሰፋ መምጣቱን በመጠቆም፣ ከእንግዲህ በመሰል ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን በሀገሪቱ ፍ/ቤት ለማቅረብ እገደዳለሁ ብሏል፡፡
በአሜሪካ የጥላቻ ንግግር ለማህበረሰብ ማሠራጨት፣ በዚህም ሞትና መፈናቀልን ማስከተል በህግ እንደሚያስቀጣ የጠቆሙት የም/ቤቱ አመራሮች፤ ይህን ህግ ተጠቅመን አሜሪካ ተቀምጠው ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥላቻን የሚያሠራጩትን ለህግ ለማቅረብ ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡
በአሜሪካ ህግ ግድያን ማበረታታት፣ ዛቻና ማስፈራሪያ መሰንዘር፣ ጐሣን ከጐሣ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጭ ንግግር ማቅረብ የጥላቻ ንግግር ተብሎ እንደሚበየን ያስረዱት ሃላፊዎቹ፤ እንዲህ ያሉ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ወገኖችን በመጠቆም ብቻ ለህግ ማቅረብ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡
ቅጣቱም ከእስር ጀምሮ ወደ ሀገር ቤት ተጠርንፎ እስከ መባረር እንደሚደርስ ጉዳዩን እየተከታተሉ የሚገኙ የህግ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
በአሜሪካን ሀገር ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገራት የሚኖሩትም ተመሳሳይ የህግ ተጠያቂነት እንዲኖራቸው በመሰል አላማ ከሚንቀሳቀሱ ተቋማት ጋር ምክክር እየተደረገ መሆኑንም ም/ቤቱ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ፌስቡክ የተሰኘው የማህበራዊ ትስስሮች ገጽ በአማርኛ ቋንቋ የሚሰራጩ የፌስቡክ መልዕክቶችን የምትቆጣጠር ኢትዮጵያውያት የአርትኦት ባለሙያ መቅጠሩ ታውቋል፡፡
በፌስ ቡክ የገበያ ጥናት ባለሙያነት የተቀጠረች ወጣቷ ትንቢት በገፃ ባስተላለፈችው መልዕክትም፤ በአማርኛ ቋንቋ የሚሠራጩ መልዕክቶችን በመቆጣጠር በህብረተሰቡ ላይ የሚደርስን ጉዳት ለመቀነስ እጥራለሁ ብላለች፡፡
በጉዳዩ ላይ ከሰሞኑ ጠንከር ያለ መልዕክት ያስተላለፉት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው እናንተ በተንደላቀቀ ኑሮ ውስጥ ሆናችሁ ድሃ ወገናችሁን በአሉባልታ የምታጋጩ እግዚአብሔር ይፍረድባችሁ ሲሉ በምሬት ተናግረዋል፡፡ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችና መልዕክቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ህግም ተረቅቆ በውይይት ላይ መሆኑም ይታወቃል፡፡

Read 8720 times