Saturday, 06 July 2019 13:18

የማይሰበረው ኤርሚያስ አመልጋ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

በአዳዲስ የቢዝነስና የስራ ፈጠራ ሃሳቦች አፍላቂነታቸውና በፈር-ቀዳጅ ኢንቨስተርነታቸው በሚታወቁት ኢትዮጵያዊው ኢኮኖሚስትና ባለሃብት በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ የሕይወት ታሪክና ስራዎች ዙሪያ የሚያጠነጥነውና በደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው የተጻፈው “የማይሰበረው - ኤርሚያስ አመልጋ” የተሰኘው የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ በገበያ ላይ ይውላል፡፡
አጠቃላይ ዝግጅቱ ከስድስት አመታት በላይ ፈጅቶ የተጠናቀቀው መጽሐፉ፤ ከወላጆቻቸው የኋላ ታሪክ አንስቶ የአቶ ኤርሚያስ አመልጋን የልጅነት ሕይወትና አስተዳደግ፣ የወጣትነት ዘመንና የትምህርት ቆይታ እንዲሁም ወደ አሜሪካ አቅንተው ከጥበቃ ሥራ እስከ የዩኒቨርሲቲ ተማሪነት እንዲሁም እስከ ግዙፉ የአለማችን የፋይናንስ ማዕከል ዎልስትሪት የኢንቨስትመንት ባንኪንግ ስመጥር ባለሙያነት የዘለቁበትን የረጅም አመታት ጉዞ የሚያስቃኝ ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ከ20 አመታት በላይ የተጓዙበትን በስኬትና በውድቀት የታጀበ፣ ፈተናና ውዝግብ ያልተለየው ረጅም የሕይወት ጎዳናም በዝርዝር ይዳስሳል፡፡   
አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በተለይም ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ የወጠኗቸውን አዳዲስና ሰፋፊ የፋይናንስ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕቅዶቻቸውን ከዳር ለማድረስ ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ጉዞ ውስጥ ያጋጠሟቸውን እሾህ አሜካላዎች፣ የተጋፈጧቸውን ፈተናና እንቅፋቶች በዝርዝር የተረኩበት መጽሐፉ፤ ከባለታሪኩ የግልና የስራ ሕይወት ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ተሰምተው የማይታወቁ በርካታ አጓጊና አነጋጋሪ መረጃዎችን አካትቷል፡፡
በሁለት ክፍሎች ተከፋፍሎ የቀረበውና 12 ዋና ዋና ምዕራፎች ያሉት “የማይሰበረው - ኤርሚያስ አመልጋ” የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ፤ “ማረፊያ አንቀጾች” እና “ድህረ-ታሪክ” የሚሉ ንዑሳን ክፍሎችን ጨምሮ በአጠቃላይ በ394 ገጾች የተቀነበበ ነው፡፡ “የማይሰበረው - ኤርሚያስ አመልጋ” በአዲስ አበባና በሁሉም የክልል ዋና ዋና ከተሞች በሚገኙ የመጽሐፍት መደብሮችና በአዟሪዎች፣ በአዲስ አበባ በሁሉም የዳሽን ባንክ ቅርንጫፎችና በሸዋ ሱፐር ማርኬቶች፣ በስልክ ትዕዛዝ የቤት ለቤት ዕደላና በአማዞን ድረ-ገጽ አማካይነት ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ለገበያ የሚቀርብ ሲሆን የመሸጫ ዋጋውም 300 ብር እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የታሸገ ውሃ “ሃይላንድ” ለገበያ በማቅረብ እንዲሁም “ዘመን ባንክ” እና “አክሰስ ሪል እስቴት”ን ጨምሮ ባቋቋሟቸው የተለያዩ ኩባንያዎች የሚታወቁት አነጋጋሪው የኢኮኖሚ ባለሙያ  አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ ከብረታ ብረት ኮርፖሬሽን የሙስና ክስ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ከወራት በፊት በቁጥጥር ስር መዋላቸውና በአሁኑ ወቅትም በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሆነው የፍርድ ሂደታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ በእስር ላይ በቆዩባቸው ወራትም፣ በተለይ ሥር በሰደደ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግሮች የሚተነትንና ዝርዝር የፖሊሲ ማሻሻያዎችን የሚያቀርብ Ethiopia:Tipping Point የተሰኘ መጽሐፍ አዘጋጅተው በAmazon.com አማካኝነት በኦንላይን እየተሸጠ ይገኛል፡፡ በዚህ መጽሐፍ በምዕራፍ ሦስት ላይ Ethiopian Economy at Cross Road  በሚል ርዕስ የቀረበውን ጥናታዊ የኢኮኖሚ ትንተና፣ ከ10 ወራት በፊት፣ ለጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ መንግስት፣ መላካቸውን አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በመጽሐፋቸው ይገልጻሉ፡፡   
“የማይሰበረው - ኤርሚያስ አመልጋ” የተሰኘውን የህይወት ታሪክ መጽሐፍ ያዘጋጀው ደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው፤ ከዚህ ቀደም “መልስ አዳኝ” እና “ባቡሩ ሲመጣ” የተሰኙ የአጫጭር ልቦለድ ስብስብ መጽሐፍትን ለንባብ ያበቃ ሲሆን፣ ለ54 ተከታታይ ሳምንታት በፋና ኤፍ ኤም 98.1 የተላለፈውንና “ስውር መንገደኞች” የተሰኘውን ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ በደራሲነትና በተዋናይነት ለአድማጭ ማብቃቱም ይታወሳል፡፡

Read 9120 times