Print this page
Sunday, 07 July 2019 00:00

በምሬት፣ በቁጭትና በተስፋ የተሞላው የጠ/ሚኒስትሩ ማብራሪያ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)


             ስለመፈንቅለ መንግስት ሙከራ
የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ነው የተባለው ክስተት አወዛጋቢነቱ በቀጠለበት ሁኔታ በፓርላማ ተገኝተው የመንግስትን አቋምና ወቅታዊ ጉዳዮች ያብራሩበትን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2011 ዉሎ በርካቶች በአንክሮ ተከታትለውታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፋት ከሣምንት በፊት በባህርዳርና በአዲስ አበባ የባለስልጣናትና ወታደራዊ መኮንኖች ግድያ የሀዘን ስሜት ውስጥ አለመውጣታቸውን በሚያረጋግጥ መልኩ ስለ ክስተቱ በምሬት፣ በቁጭት፣ በእንባ እንዲሁም በተስፋ ውስጥ ሆነው ሰፊ ማብራሪያ ሠጥተዋል፡፡
ሰኔ 15 ቀን 2011 በባህርዳር ያጋጠመው ክስተት መፈንቅለ መንግስት የመሆኑን ጉዳይ አጥርተው እንዲናገሩ የተጠየቁት ጠ/ሚኒስትሩ ጉዳዩ ግልጽ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መሆኑን ድርጊቱ ሲፈፀም የክልሉ መንግስት ተቋማት ላይ ጥቃት መፈፀሙን፣ በሶስት አካባቢዎችም የጥፋት እንቅስቃሴዎች መደረጋቸውን አስገንዝበዋል፡፡ በባህርዳር ባለስልጣናትን መግደል፣ በአዲስ አበባም የመከላከያ ኢታማዦር ሹምና ባልደረባቸውን የመግደልና በቤኒሻንጉል ጀም ጀም በተባለ አካባቢ በርካታ የሠራዊት እንቅስቃሴ መደረጉን በማስረዳት፣ ድርጊቱ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዝርዝር ጉዳዮችም በምርመራ የሚጣሩ መሆኑን ያስገነዘቡት ጠ/ሚኒስትሩ፣ በቁጭትና በሲቃ በታፈነ ድምጽ “የፌደራል መንግስቱን የማስወገዱ ጉዳይ ስላልተሳካ፣ እንዴት መፈንቅለ መንግስት ነው ይባላል ይሉናል ብለዋል፡፡
የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድራጊዎቹ ምን ለመፍጠር አስበው ድርጊቱን እንደፈጽሙ የሚያውቁት ራሣቸው ናቸው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ አሁን ባለው የኢትዮጵያ መንግስት ሁኔታ መፈንቅለ መንግስት ማድረግ የሚሳካ አይሆንም፤ የሚሆነው እልቂትን የሚፈጥር አጋጣሚ ነው  ብለዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ መንግስታቸው ከሰኔ 16 ቀን 2010 እስከ ሰኔ 16 ቀን 2011 ባለው ጊዜ ውስጥ በብዙ አይነት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች መፈተኑንም አብራርተዋል፡፡
የሁለት ዜጐችን ነፍስ ቀጥፎ ከ150 በላይ የሚሆኑትን ቁስለኛ ባደረገው የሰኔ 16 ቀን 2010 የመስቀል አደባባይ የቦንብ ጥቃት የጀመረው ሙከራ፤ ከሁለት ወር በኋላ ወታደሮችን ወደ ቤተ መንግስት በመላክ መቀጠሉን ያወሱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ይህም ተገቢው ምላሽ ተሰጥቶት ወደመጣበት ሲመለስ፣ በምዕራብ ኢትዮጵያ ደግሞ በሶስት ወራት ውስጥ መንግስት እሆናለሁ የሚል ሃይል ነው የተነሳብን ብለዋል፡፡ ይህም ተገቢው ምላሽ ሲሰጠው፤ ወዲያው ደግሞ ዜጐችን እንደ በግ ወዲያና ወዲህ እየነዱ የማፈናቀል ድርጊት ተፈፀመ፤ የተፈናቀሉትንም ስንመልስ “አስገድደው መለሷቸው የሚል ዘመቻ የተከፈተብን ብለዋል፡፡  
ሌላው መንግስታቸውን ያጋጠመው ፈተና፤ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ መሆኑን ያወሱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ይህም ሴራና አሻጥር የተሞላበት ነው ብለዋል፡፡ ይህ ሁሉ ፈተና ቢቀርብልንም እውነት ከእኛ ጋር ስለሆነ፣ ምንም አንሆንም ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የማይተኛ የማያንቀላፋ አምላክ ስላለን ይጠብቀናል ብለዋል፡፡
የፌስቡክ አሉባልታዎች
በፌስቡክ የሚቀርቡ አሉባልታዎችም ሀገሪቱንና መንግስታቸውን እረፍት እንደነሳው ጠ/ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ በውጭ ሀገር በተንደላቀቀ ሊሞዚን እየሄዳችሁ እዚህ ለአውቶብስ መሣፈሪያ እንኳ የሌለውን ወገን እርስ በእርሱ የምታጫርሱ፣ የምታዋጉ ሃይሎች፣ ፈጣሪ የእጃቸውን ይስጣችሁ” ሲሉም በምሬት ተናግረዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
የኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ
ሌላው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተነሳላቸው ጥያቄ ክልል ልሁን የሚሉ አካላትን የተመለከተ ነበር:: አንድ ብሔረሰብ ክልል ልሁን ብሎ መጠየቁ ህገመንግስታዊ መብት መሆኑን በአጽንኦት የተናገሩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ይህን ህገመንግስታዊ መብት በህገ መንግስታዊ መንገድ ማቅረብ እንደሚገባ፣ በህገ መንግስታዊ መንገድ ለቀረበው ጥያቄም በህገ መንግስቱ መሠረት ምላሽ እስኪሰጥ በትዕግስት መጠበቅ ተገቢ እንደሆነ አሳስበዋል፡፡
የአንድ ክልል ራሱን ችሎ መዋቀር በሌሎች ላይ ሊፈጥር የሚችለው ተጽዕኖ ምንድን ነው የሚለው መጠናት እንዳለበት ያስገነዘቡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በህገመንግስቱ አንቀጽ 46 መሠረትም አንድ ክልል መሆን የሚፈልግ አካል፣ በህገ መንግስቱ ዝርዝር ውስጥ ለመካተት የሌሎች ክልሎችን ህገመንግስቱ እንዲሻሻል ያላቸውን ፍቃድ ማግኘት እንደሚሻ በመጠቆም ፤ጉዳዩ ውስብስብ መሆኑን አስረድተዋል:: ከዚህ አንፃር “የክልል እንሁን” ጥያቄዎች በሰከነና በተጠና መልኩ ምላሽ ሊያገኙ እንደሚገባና ጠያቂዎችም ትዕግስት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ከህግ አግባብ ውጪ የሚደረግ ሙከራን የፌደራል መንግስት ፈጽሞ እንደማይታገስ በማስጠንቀቅ ጭምር የገለፁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “መንግስት በኢትዮጵያ አንድነት አይደራደርም” ብለዋል ጠንከር ባለ ድምፀት፡፡
ስፖርት በተይም እግር ኳስ የፖለቲካ መድረክ እየሆነ መምጣቱንና መንግስታቸው በዚህ ጉዳይ ምን አቋም እንዳለው ተጠይቀውም ሲመልሱ፤ “ስፖርቱ አለማቀፋዊ መርህና ዲስፒሊንን ተከትሎ እየተከናወነ አለመሆኑን ጠቁመው፤ የፖለቲካ ሀሳቦች ማራመጃ መድረክ እየሆነ መምጣቱን በመግለጽ፣ የሰው ህይወትም እየጠፋበት ነው ብለዋል፡፡
ራሱን ለአደጋ ያጋለጠው ስፖርት
“ስፖርቱ ራሱ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፤ ስፖርቱ ኖሮን እንኳ ችግሩ ቢኖር፣ ከስፖርቱና ከችግሩ ብለን አማራጭ እንወስድ ነበር አሁን ስለ ችግሩ የምንነጋገረው በሌላ ስፖርት ነው፤ መንግስት እጁን ቢሰበስብ እያንዳንዱ ክለብ አንድ ወር መዝለቅ አይችልም” ሲሉ፤ ለመንግስት መፍትሔው ቀላልና በእጁ ያለ መሆኑን አስገንዝበዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
መንግስት በስፖርቱ ላይ ብዙ ሃብት እያፈሰሰ መሆኑን በመግለጽም፤ ስፖርቱን ከፖለቲካ ጋር አደባልቆ ለማካሄድ የሚደረገው ጥረት በጊዜ መፍትሔ አግኝቶ ስፖርቱ ወደ ትክክለኛ አላማው ካልተመለሰ፤ መንግስታቸው የሀገር ደህንነትን ለማስጠበቅ ያለውን አማራጭ እንደሚወስድ በማያወላውል አቋም ገልፀዋል፡፡
ስለ ህገመንግስቱ፤
ህገመንግስቱን በተመለከተም መሻሻል ካለበት በውይይትና በሃሳብ እንጂ በሃይል እንደማይሆን አስገንዝበው በአጠቃላይ መንግስትን በጉልበት ለማንበርከክ የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት እንደሌለው በማስረዳት፤ የሀገር አንድነትን ለማፍረስ የሚደረገውን ተግባርም መንግስታቸው ከእንግዲህ እንደማይታገስ በሃይለ ቃል ተናግረዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ከቃላትም ከነፍስም በላይ ናት! ለኢትዮጵያ አንድነት ዛሬም ነገም ግንባራችንን እንሰጣለን፣ በኢትዮጵያ ህልውና የሚመጣ ካለ እስክሪብቶ ሣይሆን ክላሽ ይዘን ለመዋጋት ዝግጁ ነን” ሲሉም ጠ/ሚኒስትሩ ሳይለሳለሱ ቁርጡንና ሃቁን ገልፀዋል፡፡


Read 1304 times