Saturday, 06 July 2019 12:44

ኢትዮጵያዊነት ወይስ ብሔርተኝነት?

Written by  ታምራት ደሳለኝ የሜ
Rate this item
(3 votes)

በረዥሙ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ እንደ ዛሬው የጎሳ ክፍፍል በማይታወቅበትና የሃገራችን ህዝቦች አሰፋፈር የአሁኑን መልክ ከመያዙ በፊት፣ በአብዛኛው ዘመን፣ መንግስት መስርቶ የመስፋፋቱ ሂደት፣ ከሰሜን ተነስቶ ወደ ደቡብ አቅጣጫ የሚያጋድል ነበር፡፡
በዚህ የአሁኗን ኢትዮጵያ የመመስረት ሂደት ውስጥ ዛሬ የማናውቃቸው፣ ቋንቋቸው የጠፋና ዛሬም የምናውቃቸው ህዝቦች በተለያየ ደረጃ  የተሳተፉበት ነው፡፡ ከነዚህ ህዝቦች መካከል የአማራ ህዝብ ተጠቃሽ ነው፤ አሁን በምናውቀው የአሰፋፈር፣ የስነልቦናና የማንነት ሁኔታ ውስጥ ሳይሆን ማለት ነው፡፡ የአማራ ህዝብ (በቀድሞው አመለካከት አማርኛ ተናጋሪና ክርስቲያን የሆነ) በተለይም ከ700 ዓመታት በላይ በዘለቀው የክርስቲያን ሰለሞናዊ ስርወ መንግስትን የጀርባ አጥንት በመሆን ያቆመው ህዝብ ነው፡፡
“እኔ አማራ ነኝ፣ከሌላው የተለየሁ ነኝና ለራሴ ብቻ” ሳይል ነገስታትን እየተከተለ ደጀን እየሆነ፣ እያነገሰ፣ ሲሳሳቱ እያረመ፣ ከጠላት ጋር እየተዋጋ፣ ለሃይማኖቱና ሃገሬ ለሚለው ግዛት እየሞተ የነገስታት የቀኝ እጅ ሆኖ የዘለቀ ህዝብ ነው፡፡ ይሄ ሲፈጸም ግን ሌሎች ህዝቦች አልነበሩም ማለት አይደለም፤እንደውም  ግዕዝ ተናጋሪዎች፣ ትግሬዎች፣ አገዎች፣ ኦሮሞዎች፣ ቅማንቶች እንዲሁም እንደ ጋፋት ያሉ የተዋጡና የጠፉ ህዝቦች ጋር በመሆን ነው፡፡ ሆኖም የሰለሞናዊው ስርወ-መንግስት ባለቤት አማራ እንደሆነ ሊታሰብ የቻለበት ትልቁ ምክንያት ነገስታቱ ስለጠቀሙት ወይም ከሌሎቹ ህዝቦች ለይተው ስለሰሩለት አይደለም ፤ትልቁ ምክንያት ሀገሪቱን በመመስረት ሂደት ውስጥ የነገስታቱ የቀኝ እጅ ሆኖ በመዝለቁ ነው፡፡ በዚህ የታሪክ ጉዞ ውስጥ ከራሱ አብራክ ለወጡትም ሆነ ከሌላ ህዝብ ለመጡት ነገስታት መታመኑ አተረፈ እንጂ አልከሰረም፡፡ ያተረፈው ትልቁ ነገርም አማራ ማለት ሀገር ገንቢ፣ ሃገር የሚያቀናና ሌሎች ህዝቦችን አቅፎ ማስተዳደር የሚችል፣ የተከበረ ታሪክ ያለው ህዝብ መሆኑን እንዲመሰከርለት አድርጓል፡፡
ይሄ  ሂደት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የቀጠለና ለኢትዮጵያ ህልውና አሁንም ሆነ ወደፊት የሚያስፈልግ ነው፡፡ ነገር ግን በህውሐት/ኢህአዴግ  የሚመራው መንግስት፤ ሃገሪቷን በጎሳዎች ሲከፋፍል ለኢትዮጵያዊነት እንጂ አማራ ነኝ ብሎ በአንድ ጎጥ ተሰብስቦ የማያውቀውን ህዝብ “አንተ አማራ ነህ፣ ወሰንህ ይሄ ነው፣ ባንዲራህ ይሄ ነው፣ ከሌሎች ህዝቦችም በዚህ በዚህ ትለያለህ፣ታሪክህ ይሄ ነው፣ ኢትዮጵያዊ ሳትሆን የራስህ ማንነት ያለህ ነህ” ወዘተ በሚል ፍረጃ፣ አማራነትን ወደ አንድ ሳጥን ውስጥ በማጠቃለል ገድቦት ቆይቷል፡፡ መገደብም ብቻ ሳይሆን ግልጽ የሆኑ በደሎችንም አድርሶበታል:: በዚህም የተነሳ ለመጀመሪያ ጊዜ ይመስለኛል የአማራ ህዝብ በብሄር ደረጃ ተደራጅቶ ኢትዮጵያን ከሚያስተዳድረው መንግስት ጋር በተቃራኒ ሊቆም የቻለው፤ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች አስተዳደሩ የወደቀ ቢሆንም የብሄርተኝነት ስሜቱ ግን ተከትሎ በመጣው ኢትዮጵያን የሚያስተዳድር መንግስት ላይም ተጠራጣሪነት እንዲያድረበት ያደረገው ይመስለኛል፡፡
ይህ በአንድ ስርአት በተሰራ ግፍ ምክንያት ተከትለው የሚመጡ ሌሎች የኢትዮጵያ መንግስታትን በተመሳሳይ አይን መመልከት ግን ተገቢ ነው ብዬ አላስብም፡፡ የአማራ ህዝብ በታሪኩ ከአብራኩ ሳይወጡ ተቀብሎ ከየት እንደመጡ ዘርና ጎሳቸውን ሳይቆጥር ያነገሳቸው ሌሎች መንግስታትም ነበሩ፡፡ በዚህም አማራነትን አክብረው፣ ኢትዮጵያን ጠብቀው ለተከታዩ ትውልድ አስተላለፉ እንጂ ክብሩን አልነኩትም፡፡ የአማራን መብትና ክብር ማስጠበቅ እንዳለ ሆኖ፣ ነገር ግን ኢትዮጵያን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል አክራሪ ብሄርተኝነት ላይ መሳተፍ፣ ያለፈው ህዝብ ለኢትዮጵያዊነት ከከፈለው መስዋዕትነት በተቃራኒ ተሰልፎ ሃገር እንደ ማፍረስ ነው፡፡ የውጤቱም ምልክት ሰሞኑን የተመለከትነው አይነት ሲሆን ምልክቱ ሲከፋ ደግሞ እርስ በርስ መጨራረስ ነው፡፡
ስለዚህም እውነት እላችኋለሁ፤ ዛሬም ኢትዮጵያዊነት ብቻ ይሻለናል፡፡ የትኛውም አይነት መንግስት ይምጣ ከየትም ይምጣ፣ በኢትዮጵያዊነት ሚዛን ላይ ብቻ አስቀምጠነው ልንደግፈውና ልናርመው ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን የሃገሪቱን መንግስትም ወደ መጣበት ህዝብ እንዲጠብ እንጎትተዋለን፡፡
ከኢትዮጵያ መንግስታት ጋር ቆመው ጠላትን የተጋፈጡ፣ ለኢትዮጵያዊነት የታመኑ ግለሰቦችና ህዝቦችም አላፈሩም፤ይልቁንም ሀገር የካዱ ባንዶች ለጊዜው ተደሰቱ፤ ግን ለዘለቄታው አፍረውበታል፡፡ ኢትዮጵያ እጆቿ ወደ ፈጣሪ የተዘረጉ ስለመሆናቸው ጠቋሚ ሊሆነንም ይችላል፡፡
በአጠቃላይ ግን የቀድሞው ኢህአዴግ መር መንግስት፣ በብሄር እየከለለ፣ ለይቶ ባደረሰው መከፋፈል ምክንያት ትውልዱ የስነልቦና ቀውስና ለኢትዮጵያዊ ስሜት ያደረበትን መጠራጠር አስወግዶ፣ ዛሬም የአማራ ወጣትም ሆነ ቀሪው የኢትዮጵያ ወጣት፣ ለኢትዮጵያዊነት ቢያደላ ድል እንጂ ሽንፈት አይደርስበትም፡፡ ብሄርተኝነት አሸናፊ የለውም፤ አሸናፊ ቢኖረው እንኳን ድሉ በሌሎች ላይ ቆሞ በመሆኑ እንደ ሾህ የሚዋጋና የሚኮሰኩስ ነው:: ለኢትዮጵያዊነት መታገል ግን ድል እንጂ ሽንፈት የለውም፡፡
ቸር ያሰማን! ቸር ይግጠመን!

Read 2092 times