Saturday, 06 July 2019 12:46

መማር ምኑ ላይ ነው ጥቅሙ?!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 መሰረታዊ የሰው ልጅ ድህነትና የብዙ ችግሮቹ ምክንያት የዕውቀት እጦት ሆኖ ይታያል፡፡ ሰውን ከማይምነት የሚመነጩ ብዙ ጎጂ ነገሮች አግኝተውታልና፡፡ ብርሃን በሌለበት ጨለማ እንደሚነግስ ሁሉ፣ የዕውቀት ብርሃን በሌለበትም ጥፋት ይበዛል በሽታ፣ ድህነት፣ ጦርት … ሌላም ብዙ ጉዳቶች ይበረክታሉ፡፡ በርክቶም እያየን እየሰማን እየደረሰብንም ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ይመስላል ፕላቶን፡- “ሰው ትክክለኛውን ትምህርት ያገኘ እንደሆነ ለስላሳና እግዜርን የሚመስል ፍጥረት ነው፡፡ ትምህርት ያላገኘ እንደሆነ ግን በምድር ላይ ካሉት አራዊት ሁሉ የባሰ ነው” ሊል የቻለው፡፡ ሰው ያለ ዕውቀት በብዙ ነገሩ ደሀ ነው፡፡
ከሁሉ የባሰ ጎጂ የሚሆነው ደግሞ የአዕምሮ ብቻ ሳይሆን የመንፈስ ድንቁርና ሲታከልበት ነው፡፡ የመንፈስ ድንቁርና አደገኛነቱ በዓለማችን ላይ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ድንቁርና እጃችንን ይዞ እየመራን የምንፈፅማቸው አደገኛ ወንጀሎች በርክተዋል፡፡ ፈንድቶ እስከ ማፈንዳት የሚዘልቅ ተስፋ ቢስ የሚያደርግ ድንቁርና ከፍቷል፤ በተገለጠላቸው ጨለማ ዕውቀት እየተነዱ የዓለም ስጋት ሆነዋል፡፡ የሚገድል ሁሉ እግዚአብሔርን የሚያውቅና የሚያገለግልም የሚመስለው፣ ዕውር ድንብሩ የጠፋ ኃይማኖተኛ በዝቷል “ኃይማኖቴን ካልተቀበልክ አንገትህን በገመድ ፈጥነህ አስገባ” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ የሚያስተላልፍ ዳርቻ የሌለውን የደንቆሮ ክፋት እያየን ነው፡፡
ባለፉት ዘመናት በዓለምም በሀገራችንም የተፈፀሙትን ጦርነቶች አልፈን ዛሬ በልማት በኃይማኖት፤ በዘ፣ በጎሳ፤ … ስም ጥፋትን፤ ሽብርን፤ ውድመትን … እጅግ ተጠምተው ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉትን ስናይና ስንሰማ፣ የሰው ልጅ ሰላሙን ከበጠበጠ፣ የገነባውን መልሶ ከደረመሰ፣ እራሱን ከደመሰሰ ሁኔታው በዕውቀት መጎልበቱ ሳይሆን ለክፋት፤ ለልማት ሳይሆን ለጥፋት፤ ለሰላም ሳይሆን ለብጥብጥ ከዋለ … አለመማር ምኑ ላይ ነው አሳፋሪነቱ ያሰኛል፡፡
የተማረ ለችግር መፍትሔ ፈላጊ ሳይሆን ይልቁኑ የችግር ምንጭ ከሆነ፣ ከማይሙ ይልቅ ምሁሩ ወደር የለሽ ጥፋት ሲፈፅም ከተገኘ፣ መማር ችግርን፣ ድንቁርናን፣ ክፋትን፤ ጠማማነትን፤ ዘረኝነትን፤ ወገንተኝነትን፤ ኃይማኖታዊ አክራሪነትን … ካላስወገደ፤ ለሰው ዘር ሁሉ እኩል ክብር መስጠት ካላስቻለ፣ የውስጥ እድፍን ቆሻሻን ካላጠበ፤ ነፍስን ካላስዋበ፤ ተንኮል የማያውቀውን ገራገር የገበሬ ልብ ሁሉ የሚያሻክረው፣ ለጥፋት የሚቀሰቅሰው፣ የሚያሸፍተው ከሆነ፤ መማር ምኑ ላይ ነው ጥቅሙ? በደንብ ያስብላል፡፡

Read 1512 times