Saturday, 06 July 2019 12:37

“የትምህርት ፍኖተ ካርታ” ላይ፣ የማስጠንቀቂያና የመፍትሄ ምክር - ከአዋቂዎች!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)


            Dr. Helen Abadzi የኒሮሳይንስ እና የትምህርት ተመራማሪ ናቸው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት ውስጥ፣ በትምህርት ላይ፣ ዋና ተዋናይ የሆኑት ተቋማት፣ ማለትም፣…. የአለም ባንክ፣ ዩኤስኤአይዲ፣ ዩኔስኮ፣…. የተሳሳተ ቅኝታቸውን እንዲያስተካክሉ፣ ዶ/ር ሄለን በተቆጣጣሪነት፣ በአማካሪነትና በጥናት መሪነት መክረዋል። ካላስተካከሉ፣ በተለይ የድሃ አገራት ተስፋ ይጨልማል፡፡ የዛሬዎቹ ‹‹ተማሪ ህፃናት››፣ ነገ… ‹‹ማንበብ የማይችሉ ወጣቶች›› ይሆናሉ ሲሉ ለአመታት አስጠንቅቀዋል።
የትምህርት ይዘትንና የትምህርት ዘዴን ያካተተ፣ ትክክለኛውን መንገድ የሚያሳይ መፍትሄም አቅርበዋል። ከደርዘን በላይ መጻሕፍትና ጥናቶችን አዘጋጅተውም፣ ለአለም ባንክ እንዲሁም GPE፣ EFA ለመሳሰሉ ዓለማቀፍ ተቋማትና ፕሮጀክቶች አበርክተዋል።
Literacy for all in 100 Days … በሚል ርዕስ ያሳተሙትን መፅሐፍ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በጥናት የተረጋገጠ፣ ለዚያው በድሃ አገራት ያለብዙ ወጪ በቀላሉ ተግባራዊና ስኬታማ ሊሆን የሚችል የመፍትሄ መንገድን ያሳያል መፅሐፋቸው፡፡
የአንደኛ ክፍል ሕጻናት፣ በግማሽ ዓመት ውስጥ ማንበብን ተምረው የሚለምዱበት ዘዴ፣… ፊደል በፊደል፣ ቃል በቃል በዝርዝር የሚተነትነው የምሁርዋ መጽሐፍ፣ ለስኬት የሚያበረታታ ነው።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው?
ዶ/ር ሄለን አባዝ ምክራቸውን የለገሱት፣ ስህተትን በመተቸትና በማስጠንቀቅ ብቻ ሳይሆን፣ መፍትሄውን በማሳየትና ለስኬት በማነሳሳትም ጭምር ነው፡፡
ትችት የሚሰነዝሩት፣ መፍትሄም የሚያቀርቡት፣ ከርቀት በባላንጣነት ስሜት አይደለም፡፡ የዓለም ባንክ የትምህርት ዘርፍ ዋና የጥናት መሪና የኦዲት ተቆጣጣሪ የነበሩት ዶ/ር ሄለን፣ የማስጠንቀቂያ ትችትን ከነመፍትሄው በይፋ ያቀረቡትና የታተመው በራሱ በዓለም ባንክ በኩል ነው፡፡ ሌሎቹ መፃህፍትና ጥናቶች የታተሙትም፣ ከዩኤን ጋር በሚዛመዱ፣ ከዩኔስኮ ጋር በተቆራኙ ተቋማት፣ እንዲሁም በUSAID  አማካኝነት ነው፡፡ በቀጥታ ለተቋማቱ ነው ምክራቸውን ያቀረቡት፡፡ ያሳተሙትም በተቋማቱ፡፡
አሳዛኙ ነገር፣ ምክር የቀረበላቸው አብዛኞቹ ተቋማትና ኢትዮጵያን የመሳሰሉ በርካታ የአፍሪካ አገራት፣ ሰምተው እንዳልሰሙ ሆነዋል። እናስ ውጤቱ ምን ሆነ? ይሄውና ማንበብ ሳይችሉ ወደ 4ኛ ክፍል በሚዛወሩ ተማሪዎች የተሞሉ ትምህርት ቤቶችን እያየን ነው!
 እነ ኢትዮጵያ፣ ‹ትምህርት፣ እውነተኛ መረጃዎችን ማንቆርቆር አይደለም› እያሉ እውነትን እንዳያጣጥሉ ሲነገራቸው፣ ‹ትምህርት፣ በእውቀት ማጨቅ አይደለም› በሚል ፈሊጥ እውቀትን እንዳያጥላሉ ሲመከሩ፣…. የጥፋት መንገድ ይቅርብን ብለው ወደ ህሊናቸው ለመመለስ አልፈቀዱም። እህስ?   
የአገራችንን የትምህርት ሚኒስቴር መመልከት ትችላላችሁ፡፡ ለትምህርት የሚመደበው በጀት፣ በየጊዜው እየጨመረ ቢመጣም፣ ከጠቅላላው የፌደራልና የክልል በጀት ሩብ ያህሉ ለትምህርት እየዋለ ቢሆንም፣ ለህፃናት እውቀትን ከማስጨበጥ ይልቅ፣ ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎችን ለማበራከት ነው የዋለው፡፡
ደግሞስ፣ “ፊደሎችን መማር አያስፈልግም”፣ “ተጨባጭ እውነት የለም፡፡ ትርጉሙ ለእያንዳንዱ ሰው ይለያያል፡፡ ተጨባጭ እውቀት የለም፡፡ እያንዳንዱ ተማሪ የየራሱን እውቀት ይፈጥራል” ብሎ የሚሰብክ “ኮንስትራክቲቪስት” የተሰኘ ፍልስፍና፤ ትምህርትን ማፍረስ፣ ከእውቀት ጋር ማጣላት፣ ከንባብ ጋር ማራራቅ እንጂ ሌላ ምን አይነት ውጤት ሊያመጣ ይችላል?
አሁን የመጣው የትምህርት ፍኖተ ካርታስ?
ያንኑን የጥፋት ፍልስፍና ይበልጥ ለማስፋፋትና፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ የመጣውን ትምህርት ይባስ ቁልቁል የውድቀት ጉዞውን ለማፋጠን “የሚያገለግል” እቅድ ነው - ፍኖተ ካርታው፡፡ ዋና ፀቡም፣ ከእውነትና ከእውቀት ጋር ነው፡፡ በአንድ በኩል እውቀት አልባ “ተግባር”፣ በሌላ በኩል ደግሞ እውቀት የለሽ “ፈጠራ”፣ በፍጥነት እንዲስፋፋ ነው እቅዱ፡፡
ታዲያ፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ፣ ለእውነት ደንታ እየጠፋ፣ የ“ፈጠራ” ወሬና አሉባልታ፣ ያለማቋረጥና በየእለቱ እየተራባ አገር ሁሉ ቢጥለቀለቅ ይገርማል?
በየክልሉ፣ በየዩኒቨርሲቲው፣ ለማመዛዘንና ለማገናዘብ የሚጠቅም ቅንጣት እውቀት ጠፍቶ፣ ጭፍን “ተግባር” በየቦታው እየተበራከተ፣ ከብሽሽቅና ከስድብ ጀምሮ፣ እስከ አምባጓሮና ድብድብ፣ መንገድ ከመዝጋትና ከግርግር ጀምሮ እስከ ዝርፊያና ቃጠሎ፣ ከዚያም አልፎ ከኑሮ የማፈናቀልና የግድያ ወረርሽኝ ቢበራከት ይገርማል?
ህፃናት ትምህርት ቤት ገብተው ከእውነትና ከእውቀት ጋር እንዲጣሉ፣ ከዓመት ዓመትም የዘፈቀደ ንግግርንና ጭፍን ተግባርን እንዲለማመዱ የሚመደበው “የትምህርት በጀት” እየጨመረ ሲሄድ፣ መዘዙ እየከፋ መምጣቱስ ምን ይገርማል?
በየጊዜው አገሬው በአሉባልታና በውሸት ውንጀላ፣ በጭፍን የጥፋት ቅስቀሳና ዘመቻ መቃወሷ በጭራሽ አይገርምም፡፡
በእርግጥ አገርን ከለየለት ትርምስ ለማዳንና የሰዎችን እልቂት ለመከላከል፣ ለሳምንት ለሁለት ሳምንት፣ ኢንተርኔትን መዝጋት፣ ለጊዜውም ቢሆን ሊጠቅም ይችላል፡፡ ለእውነትና ለእውቀት ክብር መስጠት እንደሚያስፈልግ፣ በአፅንኦት  መናገርም ተገቢና ጠቃሚ ነው፡፡
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ፣ ካሁን በፊት በተደጋጋሚ እንደተናገሩት፣ ሰሞኑን ለፓርላማ ሲናገሩም፣ ለእውነትና ለእውቀት ቀዳሚ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ መግለፃቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡ ይሄ ቢሳካላቸው መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን ከንቱ ድካም ሊሆን ይችላል፡፡ የአገሪቱ የትምህርት ቅኝት፣ ህፃናትን ከእውነትና ከእውቀት ጋር ለማጣላት ታጥቆ የተነሳ ስለሆነ፣ በፍጥነት ካልተገታ፣ “ፍኖተ ካርታ” የተሰኘው ማባባሻ እቅድ ገና በእንጭጩ ካልተለወጠ፣ ሌላው ሌላው ጥረት ሁሉ፣ ከንቱ ልፋት ይሆናል፡፡
እና ምን ይሻላል?
ጠ/ሚ ዐቢይ፣ ቢያንስ ቢያንስ አንድ ቀላል ነገር ማድረግ ይችላሉ፡፡ አማራጭ የትምህርት ማሻሻያ ሃሳቦችን ለማድመጥ፣ አንድ ቀን መመደብ አይከብድም፡፡ ፍኖተ ካርታው፣ አማራጭ ሃሳብ የሌለ የሚያስመስል ሆኖ መዘጋጀቱን በማየት ብቻ፣ መስጋትና መጠርጠር ያስፈልጋል፡፡ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ፣ አንድ ሁለቴ ፍራንሲስ ፉክያማን ማነጋገር፣ ጥቅም እንጂ ጉዳት እንደሌለው ሁሉ፤ በትምህርት ጉዳይም፣ በአለማቀፍ ደረጃ የመፍትሄ ሃሳብ ያቀረቡ ሌሎች አዋቂዎችንና ጠቢባንን ማነጋገር ተገቢ ነው፡፡
እውነት ለመናገር፣ “ፍኖተ ካርታው” ከፀደቀና ተግባራዊ ከተደረገ፣ ከድጡ ወደ ማጡ ወደ ረመጡ የሚያወርድ፤ ትልቁ የመንግስት ታሪካዊ ጥፋት ይሆናል፡፡ “በኮንስትራክቲቪስት”  ፍልስፍና የተቃኘ የትምህርት አቅጣጫ፣ የትም አገር ውጤት አላስገኘም፤ ውድቀትን እንጂ፡፡
እንደዚያ ባይሆንም እንኳ፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ “ፍኖተ ካርታው” ከመፅደቁ በፊት፣ አማራጭ መፍትሄ ያቀረቡና በተጨባጭም ስኬታማ ውጤት በማስመዝገብ ያስመሰከሩ ምሁራንንና ጠቢባንን ለማማከር ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ Dr Helen Abadzi ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው፡፡   

Read 853 times