Saturday, 06 July 2019 11:53

እስፖርትን የመስራት ጥቅም

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

 እርግዝና….ልጅ መውለድ…ሕጻን… በሚል ርእስ ለንባብ የበቃው መረጃ በተለይም ከእርግዝና ቀደም ካለ ወቅት ጀምሮ እስፖርትን መስራት ምን ይጠቅማል በሚል ዝርዝር ሁኔታውን እንደሚከተለው ያስነብባል፡፡
Women health የተባለው ድረገጽ ከእርግዝና በፊትም ሆነ በእርግዝና ወቅት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው እና በተለይም በእርግዝና ወቅት መሰራት ያለባቸውንና የሌለባቸውን የእስፖርት አይነቶች በዝርዝር አስቀምጦአል፡፡
አንዲት ሴት ጤነኛ ከሆነችና ውስብስብ የሆነ የጤና ችግር ከሌለባት በእርግዝናዋ ወቅት እስፖርት ብትሰራ አለአግባብ ከመወፈር ትድናለች ፤ ጠንካራ ትሆናለች ፤ የአካል ብቃትዋ የተሟላ ይሆናል፤ የስነልቡናዋ ጤንነት አስተማማኝ ይሆንላታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ልጅ ለመውለድ ጊዜው ሲደርስ ማለትም ምጥ ሲጀምራት በፍጥነት ባልተራዘመ ምጥ ልትወልድ ትችላለች፡፡ ምናልባት አንዳንድ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ ቢባል እንኩዋን ብዙም የሚያሳስብ አይሆንም፡፡ ካለማቋረጥ ጊዜዋን ጠብቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የምታደርግ ሴት ከልብ ሕመም ፤ከስኩዋር ሕመም እና ከአንዳንድ የካንሰር ሕመሞች ልታመልጥ ትችላለች፡፡ ቢሆንም  ግን በእርግዝና ወቅት የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎቹ አይነት መለየት እንዳለባቸው መዘንጋት የለበትም፡፡
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከእርግዝና በፊት፤
የስሜት መለዋወጥ ወይንም መረበሽ በእርግዝና ጊዜ የተለመደ ሲሆን እንዲያውም እርግዝናው አብቅቶ ልጅ ከተወለደ በሁዋላም ይህ ስሜት ሊቀጥል የሚችል መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ ያረገዘችው ወይንም ወላድዋ ምክንያቱ በግልጽ በማይገባት ሁኔታ ስሜትዋ ሊጎዳ ፤የወለደችውን ልጅ ችላ ልትል፤ በአካባቢዋ ካሉ የቤተሰብ አባላት ጋር መስማማት ሊያቅታት የሚችልበት አጋጣሚ አልፎ አልፎ ይስተዋላል፡፡ የዚህ ገጠመኝ ምክንያት ተደርጎ ከሚወሰዱት መካከል ሴትዋ በተፈጠረው እርግዝና ምክንያት የሰውነት ቅርጽዋ መለዋወጥ ወይንም ከነበረ ችበት ሁኔታ የተለየውን አጋጣሚ መቀበል ሊያቅታት ስለሚችል መሆኑ እንደ አንደ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የአካል መድከም ወይንም በምትፈልገው መልክ መንቀ ሳቀስ አለመቻል ጥሩ ያልሆነ ስሜትን ሊፈጥር እንደሚችል የሚገመት ነው፡፡ ስለዚህ አንዲት ሴት ከእርግዝናዋ በፊት የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ብትሰራ በሁዋላ ላይ ልትደበር የምትችል ባቸውን ሁኔታዎች አስቀድሞ ለመከላከል ያስችላታል፡፡ ከእርግዝና በፊት የሚደረግ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሰውነትን ቅርጽ እንደጠበቁ ለመቆየት የሚያስችል ሲሆን እርግዝናው በራሱ የሚያመጣውን አካላዊ ለውጥ በቀላሉ ተቆጣጥሮ ከወሊድ በሁዋላ የአካል ቅርጽ ቀድሞ ወደነ በረበት ሁኔታ እንዲመለስ ይረዳል፡፡   ጭን ቀት፤ መረበሽ ፤ እና የስነልቡና ችግርን በአካል ብቃት እንቅስቃሴ መከላከል ይቻላል፡፡
በእርግዝና ወቅት እስፖርት መስራት ጠቃሚ መሆኑ ባያጠያይቅም ክትትል በሚያደርጉበት የህክምና ተቋም ሐኪምን ማነጋገር ወይንም ምክር መቀበል ግን ትክክለኛው አካሄድ መሆኑን የሴቶች ጤና ገጽ ይመክራል፡፡ ይህ የሚያስፈልግበትም የተለያዩ ምክንያቶች ተዘርዝረዋል፡፡
ያረገዘችው ሴት፤
የልብ፤የሳንባ ወይንም የጉበት ሕመም ካለባት፤
የስኩዋር ሕመም፤
የአጥንት ወይንም የመገጣጠሚያ አካላት ሕመም፤
መመረዝ ወይንም infectious disease ካለባት፤
ከልክ በላይ ውፍረት ወይንም ከልክ በላይ ቅጥነት ፤
በተፈጠረው እርግዝና ወይንም ቀድሞ በነበረው እርግዝና ምክንያት የጤና ችግር ካለ፤
የደም ማነስ ችግር፤
እርግዝናው መንታ ወይንም ሶስት ከሆነ…ወዘተ፤
ከላይ የተጠቀሱት የጤና ችግሮች ካሉ ማንኛውንም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከማድረግ አስቀድሞ የህክምና ባለሙያን ማማከር ይገባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በእርግዝና ጊዜ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጉ ቢፈቀድም እንኩዋን በእንቅስቃሴው ወቅት የሚከተሉት ስሜቶች የሚከሰቱ ከሆነ አሁንም ድርጊቱን ገታ አድርጎ ወደ ባለሙያ መሄድ ይገባል፡፡
በደረት  ላይ ሐመም የሚሰማ ከሆነ፤
የልብ ምት ከወትሮው ወይም መሆን ከሚገባው በላይ በፍጥነት የሚመታ ከሆነ፤
ከተለመደው ውጭ የትንፋሽ መቆራረጥ (በአጭር በአጭር መተንፈስ) ካጋጠመ፤
በእርግዝና ላይ ያለው  ህጻን እንቅስቃሴው ከቀነሰ፤
በሆድ አካባቢ የሰውነት መኮማተር ወይም መጨምደድ እና ፈታ ማለት ስሜት ካለ፤
የመደበር ስሜት ወይንም ራስን የመሳት ስሜት ካለ…..ወዘተ
ማንኛዋም እርጉዝ ሴት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንድታደርግ በሕክምና ባለሙያ ተነግሮአት ብትጀምረውም እንቅስቃሴውን በምትከውንበት ጊዜ ከላይ የተዘረዘሩት እና ሌሎች መሰል ስሜቶችን የምታስተውል ከሆነ አሁንም በፍጥነት ወደ ሐኪምዋ መሄድ ይጠበቅባታል፡፡
በእርግዝና ወቅት የተጀመረ እስፖርት ከሌለ እና ለመጀመር ገና የታሰበ ከሆነ ቀለል ያለውን አንዱን አይነት በመምረጥ ወደእንቅስቃሴው መግባት ይቻላል፡፡ ማድረግ የሚገባው እንቅስቃሴ ለ30/ደቂቃ ቢሆንም ሰአቱን ለሁለት ከፍሎ በየ 15/ደቂቃው መሞከር ይጠቅማል፡፡ በእርግጥ ሙሉ ጤናማ የሆነች ሴት እርግዝናዋ ምንም ችግር እንደሌለው በሕክምና ባለሙያ ከተረጋገጠ እና እስዋም ጤንነትዋን የምታዳምጥ ከሆነ በእርግዝና ወቅት መወገድ አለባቸው ከሚባሉት እንቅስቃሴዎች በስተቀር እስፖርቱን መስራት ትችላለች፡፡ ስለዚህም እርጉዝዋ ሴት ዘና በማለት ሳትረበሽ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዋን በማድረግ ከእንቅስቃሴው በፊት ሰውነትን ለእስፖርት ዝግጁ በማድረግ እና ከሰራችም በሁዋላ በማፍታታት በእራስዋ ፍጥነትና አቅም መተግበር ትችላለች፡፡ በዚህ ወቅት የሚሰራው እንቅስቃሴ ግዴታ ወይንም ፉክክር የሌለበት ውጤት ለማስመዝገብ የሚጣደፉበት አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡  
አንዲት እርጉዝ ሴት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በምታደርግበት ጊዜ ማስወገድ የሚገባት የእንቅስቃሴ አይነቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
እንቅስቃሴውን ከልክ በላይ በማድረግ ሰውነት ከፍተኛ ሙቀት እንዲሰማው ማድረግ አይመከርም፡፡
በእንቅስቃሴው ወቅት ለመውደቅ ከሚያበቁ ስራዎች መቆጠብ ይገባል፡፡
እንቅስቃሴ በሚደረግ ጊዜ ሆድን በባእድ ነገር በማስመታት ልጁ እንዲጎዳ ማድረግ አይገባም፡፡
ብዙ መዝለል ወይንም ሽቅብ ቁልቁል የሚያሰኝ ስራ መስራት አይገባም፡፡
እንቅስቃሴው በሚደረግበት ወቅት በድንገት አቅጣጫ መቀየር ወይንም ሰውነትን ማጠማዘዝ ፤ፍጥነት በተሞላበት ሁኔታ ቁጭ ብድግ ማለት የመሳሰሉትን አሰራሮች ማስወገድ ይገባል፡፡
ዋና የሚዋኝ ከሆነ እስፖርተኞች አንደሚያደርጉት ውሀ ውስጥ በዝላይ መግባት ወይንም ከከፍታ ቦታ ዘሎ መግባት የመሳሰሉትን ማስወገድ ይገባል፡፡
አንዲት እርግዝና ላይ ያለች ሴት የሚከተሉትን አሰራሮች ብትከተል ይጠቅማል፡፡
ከሰው ጋር ጭርሱንም የማያገናኝ ወይንም ውስን የሆነ ግንኙነት ሊኖረው የሚችል እንቅስቃሴ ማድረግ፤
የሰውነት ክብደትን በማወቅ በሚሰሩት እንቅስቃሴ መደገፍ መቻል፤
በዋና ወቅት የውሀው ሙቀት ከ32/ዲግሪ ሴልሽየስ በላይ ከሆነ ረዘም ላለ ጊዜ አለመቆየት፤
መጠማዘዝ የሌለበትና ቀጥ ባለ መስመር የሚሰራ እንቅስቃሴን መምረጥ፤
መካከለኛ በሆነ ጭንቀት ባልበዛበት ሁኔታ እንቅስቃሴውን ማድረግ፤
የሚሉት በእርግዝና ላይ ላሉ ሴቶች እስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚመከሩ ናቸው ፡፡  

Read 7989 times Last modified on Saturday, 06 July 2019 15:40