Saturday, 06 July 2019 11:27

ምሁራን ቀጣዩ ምርጫ መራዘም አለበት አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 “አገሪቱም ሆነ ፓርቲዎች ለምርጫው አልተዘጋጁም”

           በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ የለውጥ እርምጃዎችና መጪ ሁኔታዎች ላይ አተኩሮ በፎረም ፎር ስተዲስ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡ ምሁራን መጪው አገራዊ ምርጫ መራዘም እንዳለበት ገለፁ፡፡
“ዲሞክራሲያዊ የለውጥ ጉዞ በኢትዮጵያ፤ የለውጥ እርምጃዎች አንድምታዎቻቸው እና አማራጮቻቸው” በሚል ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ በተካሄደው ውይይት ላይ ምሁራን፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና የማህበረሰብ አንቂዎች የተሳተፉ ሲሆን በዋናነት የመጪው ምርጫ እጣ ፈንታ ምን ይሁን በሚለው ላይ ውይይት ተደርጐበታል፡፡
በመድረኩ የመወያያ መነሻ ጥናታዊ ጽሑፉ ያቀረቡት ሁለት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስ ምሁራን፤ በሀገሪቱ ለፖለቲካ ብቁ የሆነ ፓርቲ አለመፈጠሩን የጠቆሙ ሲሆን ቀጣዩ ምርጫም ቢራዘም የተሻለ እንደሚሆን ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል- የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስና አለማቀፍ ግንኙነት መምህር ፕ/ር ካሣሁን ብርሃኑ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጥናት፤ ከ1953 ጀምሮ በሀገሪቱ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ አለመፈጠሩ እስካሁን ለዘለቀው ፖለቲካዊ አለመብሰል ሀገሪቱን ዳርጓታል ብለዋል፡፡ የእርስ በእርስ መወነጃጀልና መጠራጠርም ሀገሪቱን ዋጋ እንዳስከፈላት ምሁሩ አስረድተዋል፡፡
በሀገሪቱ የበሰለ የፖለቲካ ስርአት ለመፍጠርም መጀመሪያ ጠንካራና ትክክለኛ የፓርቲ መሠረት ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች መፈጠር ወሳኝ ነው ብለዋል - ፕ/ር ካሣሁን፡፡
አሁን ሀገሪቱ ባልተረጋጋችበት፣ በርካታ የህግ ማስከበር ችግሮችና መፈናቀሎች ባሉበት ሁኔታ በ2012 ምርጫ ማካሄድ የማይቻልና ሀገሪቱን ለበለጠ ምስቅልቅሎሽ መዳረግ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ምርጫው ቢያንስ በአንድ አመት ሊራዘም እንደሚገባው ገልፀዋል፡፡
ሌላኛው የመወያያ ጽሑፍ አቅራቢ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስ መምህሩ ዶ/ር ገነነ አሽኔ በበኩላቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባለፉት ዘመናት ብቁ መሪ መፍጠር እንዳልቻሉ ጠቁመው፤ ብቁ መሪ ያለመፈጠሩ ደግሞ በሀገሪቱ የሰከነና ውጤታማ ፖለቲካ እንዳይኖር አድርጓል ብለዋል፡፡ ሀገሪቱ የበሰሉ መሪዎች በማጣቷ ከሃይማኖት ተቋማት ሳይቀር ሰዎች ወደ አመራርነት እየመጡ መሆኑን የጠቀሱት ምሁሩ፤ ሂደቱ ግን ተገቢ አለመሆኑን አስምረውበታል፡፡ መጪውን ሀገር አቀፍ ምርጫም ለማከናወን የምርጫው ተዋናዮች በብቃት የተዘጋጁ ባለመሆኑ ብዙም ትርጉም አይኖረውም ብለዋል - ምሁሩ፡፡
ምርጫው የፖለቲካ ተዋናዮች በብቃት ባልተዘጋጁበት ሁኔታ ባይካሄድ እንደሚመረጥም ነው ምሁሩ የተናገሩት፡፡ ሌሎች የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ በቂ ዝግጅት ባልተደረገበትና ሰላም ባልሰፈነበት ሁኔታ ምርጫውን ማካሄድ አገሪቱን ከድህረ - ምርጫ በኋላ ለሚከሰቱ ቀውሶችና ምስቅልቅሎች ይዳርጋታል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡

Read 1686 times