Saturday, 06 July 2019 11:01

ቦይንግ፤ አደጋው ተጐጂ ቤተሰቦች የ100 ሚሊዮን ዶላር ካሣ መደበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   “ከተጐጂ ቤተሰቦች ተቃውሞ ገጥሞታል

           ቦይንግ ኩባንያ በኢትዮጵያና በኢንዶኔዥያ የአውሮፕላን አደጋዎች ህይወታቸው ላለፈ የአደጋው ተጐጂ ቤተሰቦች የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ ያስታወቀ ሲሆን የተጐጂ ቤተሰቦችና ጠበቆች ግን ገንዘቡ በቂ አይደለም ሲሉ ተቃውመዋል፡፡
ኩባንያው፤ ቦይንግ 737 ማክስ 8 የተሰኘው የአደጋው መንስኤ የሆነው አውሮፕላን  ስሪት ስህተት የነበረበት መሆኑን በማመን ተጐጂዎችን ይቅርታ ጠይቆ፤ የገንዘብ ድጋፉን ለማድረግ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
በኢንዶኔዥያና በኢትዮጵያ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ በድምሩ 346 ሰዎች ህይወት ማለፉ የሚታወስ ሲሆን 100 ሚሊዮን ዶላሩ ለእነዚህ ተጐጂ ቤተሰቦች ይከፋፈላል ብሏል - ኩባንያው
ገንዘቡ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተሰቦች የሚደርሰው በበርካታ አመታት ክፍያ መሆኑን ያስታወቀው ኩባንያው፤ ከየሀገራቱ የመንግስት ባለስልጣናትና የበጐ አድራጐት ድርጅቶች ጋር በመተባበር እንደሚሰጥ ገልጿል::
የቦይንግ ኩባንያ የመደበውን የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የተጐጂ ቤተሰቦችን ወክለው በፍ/ቤት ክስ ለመመስረት እየተዘጋጁ ያሉ ጠበቆች “በቂ አይደለም” በሚል ተቃውመውታል፡፡
ጠበቆቹ በዋናነት ከአደጋው ጀርባ ያሉ ሃቆች መታወቅ እንዳለባቸው የገለፁ ሲሆን ለአንድ ተጐጂ ቤተሰብ ቢያንስ እስከ 1 ሚሊዮን ዶላር ካሣ እንዲከፈል እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
ከወዲሁም ከ50 በላይ የሚሆኑ የተጐጂ ቤተሰቦች በጋራ ክስ መመስረታቸው የተገለፀ ሲሆን እነዚህ ቤተሰቦች 276 ሚሊዮን ዶላር ካሣ ጠይቀዋል፡፡
በመጋቢት 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ በደረሰው አደጋ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ የ33 ሀገራት ዜጐች የሆኑ 157 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፣ በጥቅምት 2011 በኢንዶኔዢያ ባጋጠመው ተመሳሳይ አደጋ ደግሞ 189 ሰዎች መሞታቸው ይታወቃል፡፡ በዚህም የተነሳ እስካሁን ድረስ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች በሙሉ ከበረራ ታግደው ይገኛሉ፡፡


Read 1071 times