Saturday, 06 July 2019 10:59

መኢአድ መንግስት ቢሆን ኖሮ፣ ምን ያደርግ ነበር?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

በህዝብ ተቃውሞና መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ወደ ስልጣን የመጣው የዶ/ር ዐቢይ አህመድ የአመራር ቡድን ለውጡን እየመራሁ፣ የሀገሪቱን የዲሞክራሲ የሽግግር ሂደት አሳልጣለሁ ብሎ ቃል ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ እነዚህ ውጤታማ ተግባራት በአንፃሩ፤ በተለያዩ ተግዳሮቶች የተፈተኑ፣ የበርካቶችን ክቡር ህይወትም ያሣጡ ናቸው፡፡
የመንጋ ፍርድና ግድያ፣ የዘር ተኮር ጥቃትና መፈናቀሎቹ፣ የፀጥታ መደፍረስና አለመረጋጋት እንዲሁም የኑሮ ውድነትና የኢኮኖሚ አጣብቂኝ፣ የባለስልጣናትና የመንግስት አመራሮች ግድያ የዶ/ር ዐቢይን የለውጥ አመራር የፈተኑ ክስተቶች ሆነዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩና መንግስታቸው በተለያዩ ተግዳሮቶች ሲፈተኑ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በአንፃሩ፤ መንግስት ይሄን ቢያደርግ፣ ያንን ባያደርግ ሲሉ ትችቶችን ይሰነዝራሉ፤ መግለጫዎችን ያወጣሉ:: ለመሆኑ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አገሪቱ በተቃውሞና ነውጥ ተፈትና፣ ከቋፍ በፈረሰችበት ጊዜ መንግስት የመሆን እድል ቢያገኙ ኖሮ ምን ያደርጉ ነበር? መንግስት ሲኮን መሥራት እንጂ መተቸት ብዙም አያዋጣም፡፡ ይህን ጥያቄ ያቀረብንላቸው አንዳንድ ተቃዋሚዎች “መንግስት ስንሆን የምናደርገውን እኛ እናውቃለን” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
መኢአድ በበኩሉ፤ መንግስት ቢሆን ሊያከናውን የሚችላቸውን ተግባራት የፓርቲው ተ/ም ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም ያስረዳሉ፡፡ መኢአድ የመንግስትነት ስልጣን ይዞ ቢሆን ኖሮ ሃገር ማረጋጋት የመጀመሪያ ተግባሩ ይሆን ነበር ያሉት ተ/ም ፕሬዚዳንቱ፤ ከዚያም የሚሠራው የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡ “የመንግስት ተፈጥሮአዊ ባህሪው የዜጐችን መብት ማስከበር ነው፤ ስለዚህ የመጀመሪያ ስራችን ህግን ማስከበር ይሆን ነበር፤ ህግን ማስከበር ሊባል ደግሞ ሀገርን ማረጋጋት ማስቻል ነው፤ ይሄ የሚከወነው መንግስት ህግን የማስከበር ጥንካሬ እንዳለው በሚያስመሰክር መልኩ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ የመኢአድ መሪ፡፡  
በቀድሞ ስርአት ዜጐችን የበደሉ፣ ሃገር የዘረፋ ወንጀለኛችን ለፍርድ በማቅረብ ነው ህግን የምናስከብረው፤ ይሄን አስተማሪ እርምጃ በመውሰድም ሌሎች ከህገወጥ ተግባራት ተገትተው፣ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን እናደርግ ነበር በማለትም መኢአድ የሚመራው መንግስትየ ሚያከናውናቸውን ተግባራት አብራርተዋል፡፡
መፈናቀልና በዩኒቨርሲቲ ያለ የፀጥታ ችግርን በተመለከተ ደግሞ በመጀመሪያ ችግሩ ከምን መጣ የሚለውን ቁጭ ብለን እንመረምራለን እናጠናለን የሚለው ፓርቲው፤ እኛ አሁንም የዚህ ችግር ምንጭ ብሔር፣ ቋንቋና ዘር ተኮር የሆነው የፌደራሊዝም ስርአት ነው፤ የፌደራል ስርአቱ ነው ችግር የፈጠረው ይላል፡፡ ስለዚህ የትኛው የፌደራል ስርአት ነው ተስማሚ የሚሆነው ብለን በማጥናት፤ በፖለቲካ ፕሮግራማችን ላይ ያለውን ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥን፤ ኢኮኖሚውና ባህልን መሠረት ያደረገውን የፌደራል ስርአት ስልት ተግብረን ችግሩን እንወጣው ነበር ይላሉ አቶ አብርሃም::  
“ገደብ ያጣው የዘር ፖለቲካ፣ ገደብ የሚኖረው በዚህ መንገድ ነው፤ መፈናቀል፣ መገዳደል፣ መወነጃጀል፣ መጠላላት፣ እርስ በእርስ መጠራጠር የመጣው ከቋንቋና ብሔር ተኮር ፌደራል ስርአቱ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ መንግስት ብንሆን ለዚህ መፍትሔ የምናደርገው የፌደራል ስርአቱን ስልት መለወጥ ይሆናል፡፡” ብለዋል - መሪው፡፡
ህገመንግስቱም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ህገመንግስቱንም እንቀይራለን እንዲቀየር እናደርግ ነበር ይላሉ - አቶ አብርሃም፡፡
ክልል እንሁን እየተባለ የሚጠየቅ ጥያቄም እንዳሁኑ አይኖርም ነበር፤ የምናደርገው ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ዘርንና ቋንቋን መሠረት ያደረገውን ስርአት መለወጥ ነበር ሲሉ የመኢአድን ስትራቴጂ አስረድተዋል፡፡
“የኑሮ ውድነትንና ኢኮኖሚን በተመለከተ መኢአድ ምን ያደርግ ነበር፤ ከተባለ ደግሞ እውነተኛ የሆነ ነፃ የንግድ ስርአትን በመዘርጋት፣ ገበሬውም በሰፊው እንዲያመርት ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ሙሉ ትኩረት እናደርግ ነበር” የሚሉት የፓርቲው መሪ ይሄን ለማድረግ ግን መጀመሪያ ፖለቲካውን በጠንካራ የህግ የበላይነት እናስተካክለው ነበር - ብለዋል፡፡
“መኢአድ በዚህ ወቅት የመንግስት ስልጣን ላይ ቢሆን ኖሮ አሁን ሀገሪቱ የገጠማትን ፈተና ለመወጣት የምናደርገው የመጀመሪያ ስራችን፤ የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ ጐን ለጐን ድብልቅልቅ ያለውን ፖለቲካ ለማስተካከል ህገመንግስቱን መቀየር ነው፤ በሁለተኛ ደረጃ ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎች ያቀፈ አንድ አካል አቋቁሞ በመግባባት ምርጫ እናካሂድ ነበር” በማለት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ከምሁራን፣ ከሽማግሌዎች፣ ከወጣቶች፣ ከታዋቂ ግለሰቦችና ፖለቲከኞች የተውጣጣ እውነተኛ የአማካሪ ቡድን እናቋቁም ነበር- ያሉት አቶ አብርሃም፤ ጠ/ሚኒስትሩም ይሄን ቢያደርጉ መልካም ይሆን ነበር ሲሉ መክረዋል፡፡


Read 1200 times