Tuesday, 02 July 2019 12:47

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

    “የነፃነት ዋጋ ሲቀንስ ባርነት ከፍ ይላል”
             

      ሮማውያን “ኩፒድ”፣ ግሪካውያን “ኤሮስ” እያሉ የሚጠሩት ግማሽ ሰው፣ ግማሽ አምላክ የሆነው የ “ፍቅር ጌታ” አንድ ምሽት በዘንዶው ጀርባ እየጋለበ ወደ አንድ ከተማ መጣ፡፡ ከቤተ መንግስት ደርሶም ከአገሩ ንጉሥ ጋር ተገናኘ፡፡ ንጉሡ ከዙፋኑ ብድግ ብሎ ከእንግዳው እግር ላይ አጐንብሶ ሰላምታውን አቀረበ፡፡ በዛው ቅጽበት ከብዙ ዓመታት በፊት በሁለቱ መሃከል የተደረገውን “ቃል ኪዳን” በማስታወሱ ዓይኖቹ በዕንባ ተሞሉ፡፡
“በቀጠሮአችን መሠረት መጥቻለሁ” አለ ኤሮስ፡፡
“አውቃለሁ ጌታዬ” በማለት ከመለሰለት በኋላ ንግስቲቱ በፍጥነት ወደ እልፍኛቸው እንድትመጣ ላከላት ንጉሡ፡፡ ባለቤቱ እንደመጣች እጇን እየሳመ፣ በተጋቡበት ጊዜ የሆነውን፣ ከእንግዳው ጋር ያደረጉትን ውለታ እያዘነ ነገራት፡፡ ቃሉን በማክበርም እጇን ስቦ፤
“ይቻትልህ” አለው፡፡ ኤሮስ አምላክ ግን ተቆጣ፡፡
“ልታታልለኝ ይገባሃልን?” ሲል አፈጠጠ፡፡
ንጉሡም በድንጋጤ፤
“ስለምን አታልልሃለሁ? ስለ ምንስ ትቆጣለህ?” ባለው ጊዜ
“ሴቲቱ ይቺ አይደለችም” አለ ኤሮስ
ንጉሡ ግራ ተጋባ፡፡ በዚህን ጊዜ ንግስቲቱ የምትናገረው ነገር እንዳለ በማስፈቀድ ከሰላሳ ዓመታት በፊት ልዕልቲቱን ተክታ እንዴት ንጉሡን እንዳገባች ሚስጢሩን ነገረቻቸው፡፡ የሁለቱንም የፍቅር ታሪኮች መጨረሻ ላይ ታነበዋለህ፡፡
***
ወዳጄ፡- የአንዱን “እውነት” ሌላው ላያውቅ ወይም ላይረዳው ይችላል፡፡ “ስህተት” የተባለው ትክክል፣ “ትክክል” የተባለው ደግሞ ስህተት የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ሁሉም በየራሳቸው “ሃሳብ” ናቸው፡፡ የግል፣ የቤተሰብ፣ የማህበረሰብ፣ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የጥበብ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ማሰብ አይከለከልም፡፡ ጥቅም የሚሰጥ ፍሬ ማፍራት ከቻለ ደግሞ “ፅንሱ” እውነት ነበር ያሰኛል፡፡ ዕውነት አይመክንም፡፡ የጽንሱ ምክንያታዊነት ወይም ሰብስታንሱ ደረጃውን የጠበቀ (Proportional) ካልሆነ ይጨነግፋል፡፡ ቢወለድም አያድግም፡፡ አያፈራም፡፡ በውስጡ ያለው እውነት ዐቅም የለውም፡፡ ያሰቡት ቀርቶ ያላሰቡት ይሆናል:: ከልምድና ከሳይንስ ሳይማሩ “ሴት እንወልዳለን” ብለው ወንድ ልጅ የሚወልዱ ወይም የተገላቢጦሽ የሚያስቡ ብዙ ናቸው፡፡
ወላጆቻችን፤ “ሰው ያስባል አምላክ ይፈጽማል (man propose, God dispose) ማለታቸው ያለ ነገር አይደለም፡፡
ወዳጄ፡- በሰለጠኑና ከሞላ ጐደል ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በገነቡ መንግስታት የሚተዳደሩ ዜጐች የመሰላቸውን ነገር ማሰብም ሆነ መመኘት አይከለከሉም፡፡ እስከቻሉ ድረስ ህልማቸውን ዕውን የማድረግ መብታቸውም እንደ “መርህ” የህግ ጥበቃ አለው፡፡ ነገር ግን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሌሎችን ስሜት የሚጐነትል “ሃሳብ” ከሆነ ገደብ ይደረግበታል፡፡
ለምሳሌ ቅጥ ያጣ ጋጠወጥነት ወይም የሌሎች ሀገራት ዜጐችን መናቅና የበላይነትን ለማሳየት መሞከር (acting out ይሉታል) ሊሆን ይችላል፡፡ ገደቡ ነፃነታቸውን ለማሳነስ ሳይሆን የነፃነትን ዋጋ አውቀው የበለጠ ነፃነት እንዲሰጣቸው ለማስተማር ነው፡፡
“Whoever refuses to obey the general will of the people shall be constrained to do so by the whole society; thins means nothing else than that he shall be forced to be free” ይልሃል ታላቁ ሩሶ፡፡
ወዳጄ፡- አንተን የሚመችህ ሌሎች ሰዎች ሲመቻቸው ነው፡፡ የሌሎች ነፃነት ያንተ ነፃነት ነው:: አለበለዚያ ከማወቅና ከመረዳት የምታተርፈው ደስታ ይቀንሳል፡፡ ነፃነት፤ ሰላምና በራስ መተማመን ነው፡፡ ነፃነት የፈጠራ ጉልበትህ፣ ደግነትና ሰብዓዊነት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ዳግም ፍቅር!! ስልጣኔና ዕድገት ያለ ነፃነት ጭቆና ነው፡፡ የነፃነት ዋጋ ሲቀንስ ባርነት ከፍ ይላል፡፡ “ለነፃነቱ ሞተ” ሲባል “ህይወት ያለ ፃነት ከንቱ ነው” እንደማለት ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ነው “ከዘለዓለም ባርነት ያንድ ቀን ነፃነት ይበልጣል” የሚባለው፡፡
ነፃነት ሃሳብ ነው፡፡ በያንዳንዳችን የማሰብ ዐቅም ልክ የሚበራ የሃሳብ ጮራ፡፡ ሃሳብ ሲጨልም ቂመኛ ያደርጋል፡፡ ቂም የመጥፎ ሃሳብ መታቆር ነው:: በቀል ደግሞ ከስሜት የሚቀዳ መርዝ፡፡ ሁሉም ምክንያታዊነት ይገድላሉ፡፡ ምክንያት ሞተ፤ ነፃነት ሞተ ነው፡፡ ምክንያትህ እንዲፋፋ ነፃነትህ ከዕውነት ይወለድ!!
***
ወደ ትረካችን እንመለስ፡- ከላይ የጠቀስነው ንጉሥ፤ ልዑል በነበረበት ጊዜ ወደተለያዩ ቦታዎች ሲዘዋወር ያያትን ልዕልት አፈቀረ፡፡ ሊያገባትም አማላጅ ላከ፡፡ ልዕልቲቱ ግን ሌላ መስፍን ታፈቅር ነበርና አሻፈረኝ አለችው፡፡ ልዑሉ ቢጨንቀው የፍቅር አማልክት ወዳሉበት ቤተ መቅደስ ሄዶ፣ ታላቁ ኤሮስ መላ እንዲፈልግለት ለመነው፡፡ ኤሮስም መንፈሱን በመላክ የልዕልቷ ቤተሰቦች ልጃቸውን እንዲያስገድዱ አደረገ፡፡ ነገር ግን…
“ከሰላሳ ዓመታት በኋላ መጥቼ እወስዳታለሁ:: በድንግልና ከተገኘች ለምትወደው መስፍን እድራታለሁ፤ ያ ካልሆነ ለዘንዶዬ ግብር ትሆናለች፤ ለዚህ ቃል ግባልኝ” በማለት ንጉሡን አባላበው፡፡ ንጉሡም፡-
“ቃሌን እንደምጠብቅ እምላለሁ፣ ድንግልና ያልከው ግን እንዴት ይሆናል?” ብሎ ሲጠይቀው
ኤሮስ፡-
“ማን ያውቃል? ብሎት ተሰወረ፡፡
ማን ያውቃል?
ተፈቃሪዋ ልዕልት በበኩሏ፤ የማግባቷ ነገር ቁርጥ ሲሆንባት ደንገጡርና ሞግዚት ትሆነኛለች ያለቻትን፣ በመልክና በቁመና ቁርጥ እሷን የምትመስል ልጃገረድ አፈላልጋ ቀጠረች፡፡ ለልጅቱም ንጉሡን ማግባት እንደማትፈልግ በማስረዳት፣ በሷ ምትክ ተሞሽራ እንድታገባ አመቻቸች፡፡ የሞግዚቷን ልብስ ለብሳ፣ ሻሿን ተከናንባ ከአባቷ ቤተ መንግሥት በመጥፋት ወዳፈቀረችው መስፍን ኮበለለች፡፡ አለባበሷን የተጠየፉ የመስፍኑ ዘበኞች ግን “ዕብድ ናት” ብለው አባረሯት፡፡ ወደ አባቷ ቤተ መንግስት ብትመለስም ታሪኳን የሚቀበል ጠፋ፡፡ እንደውም “አምላካችን ሊፈትነን የላከብን ሰይጣን ነች” ብለው ሊገድሏት ዛቱ፡፡ ወደ ደንገጡሯ ተሰደደች፡፡ እዛም መግባት ተከለከለች፡፡ ከአጥሩ ባንደኛው ጥግ እየለመነችና እየተኛች ብዙ ዘመናት ቆየች፡፡ አንድ ቀን ግን ንግስቲቱን በመናፈሻዋ አይታ ድምጿን ከፍ አድርጋ በድሮ ስሟ ጠራቻት፡፡
ንግስቲቱም እንዳወቀቻት አዘነች፡፡ ወደ መኖሪያዋ ወስዳም መልካሙን ሁሉ አደረገችላት:: ከተገናኙ ዛሬ ሰላሳ ዓመት ሞላቸው፡፡ ከኤሮስና ከንጉሡ ቀጠሮ ጋር ተገጣጠመ፡፡
ነፃነትና ሞት ከፊቷ ተደቅነዋል፡፡ “ድንግል ትሆን እንዴ?” … ማን ያውቃል?



Read 1313 times