Tuesday, 02 July 2019 12:45

አውግቸው ተረፈ - በወዳጆቹ አንደበት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የሥራውን ያህል ያልተዘመረለት ደራሲና ተርጓሚ አውግቸው ተረፈ በወዳጆቹ ዓይን እንዴት ይታያል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው አራት ወዳጆቹን አነጋግራ አስተያየታቸውን እንደሚከተለው አጠናቅራዋለች፡፡



      “የአውግቸው ስራዎች በጣም የሚገርሙ ናቸው”
ገጣሚ ታገል ሰይፉ
“እያስመዘገብኩ ነው” እና “ወይ አዲስ አበባ” በጣም የሚገርሙ ስራዎቹ ናቸው፡፡ “ወይ አዲስ አበባ” የራሱን ታሪክ የሚያሳይ ነው፡፡ የትግርኛ ቋንቋ ድምፃዊው እያሱ በርሔ፣ በአንድ ወቅት “እያስመዘገብኩ ነው” የተሰኘውን አጭር ልቦለድ፣ በረሃ ሳሉ፣ ወደ ቲያትር ቀይረው ሰርተውት እንደነበር ለእኔና ለአውግቸው ነግሮናል፡፡  የህዝቡን ችግርና ሰቆቃ ያሳያል ብለው ነበር የሰሩት፡፡  ደርግም የህዝቡን በደል ያንጸባርቃል በሚል አሳትሞ በሬዲዮ ተርኮታል፡፡ ይሄ የሥራውን ጥንካሬና ጊዜ ተሻጋሪነት ነው የሚያሳየው፡፡ በኢትዮጵያ የአጭር ልቦለድ ታሪክ ውስጥ ከሚጠቀሱ ጥቂት መጻህፍት አንዱ ነው፡፡
ሌላው ተጠቃሽ ሥራው “እብዱ” የተሰኘው ነው:: የአዕምሮ ህመምተኛ እንዴት ነው የሚያስበው የሚለውን የሚያሳይ ልዩ መጽሐፍ ነው፡፡ ለአዕምሮ ህመም ተመራማሪዎችና ለህክምና ባለሙያዎች ጭምር እንደ ዋቢ መጽሐፍ የሚያገለግላቸው  ነው፡፡ እንደሰማሁት፤ አውግቸው በዚህ መጽሐፍ ምክንያት አማኑኤል ሆስፒታል ቆይቶ ከወጣ በኋላ ዋርድ በስሙ ተሰይሞለታል፡፡ የአዕምሮ ህሙማን የራሳቸው መዝገበ ቃላት እንዳላቸው የአውግቸውን መጽሐፍ ሳነብ ነው የገባኝ፡፡
“ወይ አዲስ አበባ”ን ስንመለከት በረንዳ አዳሪ ሆኖ ሲኖር፣ ድንገት ከበረንዳ አዳሪዎቹ አንዱ ሰው ይገድላል፡፡ በዚህ ምክንያት ፖሊሶች እሱንም ጠቅልለው እስር ቤት ይጨምሩታል:: እሱ ግን እስር ቤቱን ወደደው፡፡ በተፈታም ጊዜ እንዲህ አለ፡- “ፖሊስ እንደ መላዕክ ሆኖ እስር ቤት ጨመረኝ፤ዳኛው ግን እንደ ሰይጣን ሆኖ ንፁህ ነው፤ ወንጀሉ ላይ የለበትም ብሎ አባረረኝ፡፡”  
እኔ እንደ አንድ አንባቢና አድናቂ ነው እየነገርኩሽ ያለሁት፡፡ አውግቸው ብዙ የሚዘመርለት፣ ብዙ የሚነገርለት ሰው ነው፡፡ አውግቸው ምንም ነገር ቢነገረው በቀላል ቁጭ ማድረግ ይችላል፡፡ አንድ ሰው ሰክሮ ጽሑፍ ከፃፈ ደመ-ነፍሱ ንቁ ነው ማለት ነው:: “እያስመዘገብኩ ነው” የሚለውን መጽሐፍ ጥንብዝ ብሎ ሰክሮ እንደፃፈው ነግሮኛል፡፡ ለእኔ ምርጥ የምለው “እያስመዘገብኩ ነው”፡፡ “እብዱ” እና “ወይ አዲስ አበባ”ም  ልዩ ናቸው፡፡
አውግቸው በጣም አንባቢ ነው፤ ጥንቁቅ ነው፤ ከሁሉም ሰው ጋር በፍቅር መኖር እንጂ መጋጨት አይፈልግም፡፡ ዩኒቨርሲቲ አንደኛ አመት ገብቶ ነው ያቆመው፡፡ ምክንያቱን ስጠይቀው፤ ከባሴ ሀብቴ ጋር ፀብ ነበራቸው፤ ባሴ ከተግባረ ዕድ ተመርቋል:: “አንቺ ስላልተማርሽ ነው” እያለ ብዙ ነገሮቹን ያጣጥልበታል፡፡ እልህ ያዘውና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ጨርሶ፣ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ አንድ ዓመት ከተማረ በኋላ ባሴ ጋ ሄዶ እንዲህ አለው፡- “ከፈለግሁ መጨረስ እችላለሁ፤ ስለማይጠቅመኝ አልማርም፡፡”
“አብዮታዊ ዲሞክራሲ”ን ለቆ ከወጣ በኋላ ብሔራዊ ትያትር ሳር ላይ ነበር መጽሐፍ ዘርግቶ  የሚሸጠው፡፡ በተመስጦ እያነበበ ሳለ መጽሐፍ ብትጠይቂው፣ መጽሐፉ የለም ነው የሚልሽ፡፡ አንዴ እያነበበ ሳለ እኔ አጠገቡ ነበርኩ፤በጐች ሳሩን ለመጋጥ ሲሉ መጽሐፉን ገፉበት፤ “እነኚህ መሃይም በጐች!” ብሎ ማጉረምረሙ አይረሳኝም፡፡   

“20 መጽሐፍ በአንድ ሰው
ሲበረክት ብዙ ነው”
ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ
አውግቸው በስነ ጽሑፍ ብቻ ሳይሆን በስነ አዕምሮ ዘርፍም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ለዚህም “እብዱ” የተሰኘው ሥራው ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡ በአማርኛ አጭር ልብወለድ ውስጥ “ወይ አዲስ አበባ” በጣም ትልቅ ቦታ አለው፡፡ “እብዱ” ከሥነ ጽሑፍም ባሻገር ለስነ አዕምሮ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ተብሎ ይታሰባል፡፡ በ1976 ዓ.ም አካባቢ “ወይ አዲስ አበባ” አጭር ልቦለድን ያነቃቃ ስራ ነበር፡፡ አዲስ አበባን ባዕድ አድርጐ በእሱ መንገድ ማቅረቡ የተሻለ ትኩረት እንዲሰጠውና እንዲደነቅ አድርጐታል፡፡
አውግቸው፤ በሥነ ጽሑፍ እንደ ሁለተኛ ትውልድ ከሚቆጠሩ ደራሲያን ተርታ የሚሰለፍ ነው፡፡ እነ ስብሃት እያለመዱ ወደ ሥነ ጽሑፍ እንዲገቡ ካደረጓቸው፤ እነ የሺጥላ ኮከብ፣ ሲሳይ ንጉሱና ሌሎችም ጋር ሊመደብ የሚችል ነው፡፡ ከአጭር ልብወለድ በተጨማሪ በትርጉም ስራዎችም ይታወቃል፡፡ “ሀማቱማ” የሚል መጽሐፍ ጽፏል:: ከኢህአፓ ጋር የተገናኘ መጽሐፍ ተርጓሟል:: ከህመም ጋር የቆየ አይመስልም፤ ትጋት ነበረው:: ሃያ መጽሐፍ በአንድ ሰው ሲበረክት ብዙ ነው፡፡ በአማርኛ ስነ ጽሑፍ፣ ሃያ መጽሐፍ የደረሱ በጣም ጥቂት ናቸው፤ ከእነሱ ጋር አብሮ የሚደመር ነው ማለት ይቻላል፡፡
የአዕምሮ ህመምተኞች እለት ተዕለት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ተከትሎ፣ አንድ ስነ ጽሑፍ ማበርከት ትልቅ ነገር ነው፡፡ በህመም ውስጥ ሆኖ ቤተሰብን በሚረሳበት ሰዓት ስነ ጽሑፍን አስታውሶ መፃፍ  ትልቅ አስተዋጽኦ ነው፡፡ በስነ ልቦና ከተጐዱ በኋላ በህመም ውስጥ ሆኖ እንኳን ስነ ጽሑፉን አለመርሳት ትክክለኛ የሥነ ጽሑፍ ሰው መሆኑን አመላካች  ነው፡፡ ሰው በተመቻቸ ነገር እንኳን አይሞክረውም፡፡
አውግቸው የዋህነት አለበት፤ እራሱን ይጐዳል እንጂ ሰውን አይጐዳም፡፡ በህይወቱ ተቸግሮ እርዳታ እስኪጠየቅለት ደርሷል፡፡ የሚሠራ ሰው መቸገር የለበትም፡፡ እራሱን ቤተሰቡን ማስተዳደር አቅቶት ሚዲያ ላይ እስከሚቀርብ ድረስ መቸገሩ፣ የአገር ጭምር ውርደት ነው፡፡ አውግቸው ሲወድም ሲጠላም ጠበቅ አድርጐ ነው፡፡

“በአደባባይ የተጨበጨበለት ሰው አይደለም”
የአይናለም መጽሐፍት መደብር ባለቤት
አውግቸው በብዙ አደባባይ የተጨበጨበለት ሰው አይደለም፡፡ ነገር ግን ቤቱ ተቀምጦ በርካታ መጽሐፍትን የፃፈ ያነበበ ሰው ነው፡፡ በብዙ ሰዎች ዘንድ በብዕር ስም የሚታወቀው አውግቸው፤ ከሠላሳ አመት በፊት አብሬው ለመኖር እድል አግኝቼ ነበር፡፡ ሙሉ ለሊት የሚያነብ ሰው ነው፤ ደሞዝ ተቀብሎ  ከቤት ወጪው በፊት የሚያደርገው ነገር ቢኖር መጽሐፍ መግዛት ነው፤ በርካታ መጽሐፍትን  ገዝቶ ሙሉ ለሊት ሲያነብ ነበር የሚያድረው፡፡ እኔንም ከእንቅልፌ ይቀሰቅሰኝና ነቅቼ “ምን ሆነህ ነው?” ስለው “አይገርምህም ምን አይነት መሠሪ ናት!” ይለኛል፡፡ ምክንያቱም ውስጥ ገብቶ ነው የሚያነበው፤ ሲያለቅሱ ያለቅሳል፤ ሲስቁም ይስቃል:: አውግቸው በጣም ትልቅ አንባቢ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ያበረከታቸው ሥራዎቹ ይመሰክራሉ፡፡
“ወይ አዲስ አበባ” በአንባቢ ዘንድ የሚታወቅለት መጽሐፍ ነው፡፡ በሩሲያኛም ተተርጉሞ ብዙ ሰዎች አንብበውታል፡፡ “እብዱ” በጣም አስገራሚ፣ ከምንገምተው በላይ ስሜት የሚፈጥር፣ አንዴ ማንበብ ከጀመሩ የማያቆሙት መጽሐፍ ነው፡፡ ለመሆኑ እንዲህ ይሆን ነበር ወይ? ብዬ እንድጠይቅ አድርጐኛል፡፡ እኔ የስጋ ዘመዴ ስለሆነ አይደለም፤ የመጨረሻ ደግ፣ ትሁት፣ ሰው አክባሪ ነው፡፡ የተጐዳ ሰው ሲያገኝ እራሱ ሳይበላ ለሌሎች ያስባል፡፡ ይሄ ከባህሪው የምወድለት ነው፡፡ በህመሙ ምክንያት በርካታ ስራዎቹን አውጥቶ ጥሏል፤ ቀዷል እንጂ በርካታ ድርሰቶች ነበሩት፡፡

“አስቂኝና ቀልድ አዋቂ ነበር”
ምትኩ ይርጋ
አውግቸው ሩሩህ ነው፤ ሰው ሲቸገር ማየት አይፈልግም፡፡ ሰው ተቸግሮ ከሚያይ ይልቅ እራሱን መጉዳት ይቀለው  ነበር፡፡ ለእውቀቱና ለስራው የለፋውና የደከመው ብዙ ነው፡፡ ያለውን ነገር አቻችሎ ይሄን ያህል ከሠራ የተመቻቸ ነገር ቢኖረው ኖሮ፣ ከዚህም የበለጠ ይሰራ ነበር፡፡ በርካታ ትርጉሞችን ሠርቷል፡፡ የራሱንም ጥርት ያሉ ድርሰቶች አበርክቷል፡፡
የተለየ አስተዋጽኦ አበርክቷል የምለው፣ ለስነ ጽሑፍ ያበረከተውን ነገር ሳይ ነው፡፡ እኔ “እያስመዘገብኩ ነው” የሚለውን መጽሐፉን እወድለታለሁ፡፡ የማርክሲዝም ርዕዮት አለም ስላለቀቀው ለሰዎች በጣም ያዝናል፡፡ በወር ቢያንስ አራት ቀን ያመው ነበር፡፡ ለቀቅ ሲያደርገው ይዘፍናል፤ በጣም አስቂኝና ቀልድ አዋቂም ጭምር ነበር፡፡    


Read 1893 times