Print this page
Tuesday, 02 July 2019 12:44

ጣዖቷ

Written by  መኮንን ማንደፍሮ
Rate this item
(10 votes)


      ትዝታን ሽሽት   
እኩለ ሌሊት ነው፡፡ ጥቁር ካፖርቱን እንደደረበ በረንዳ ላይ ተቀምጦ ዐይኖቹን ሰማዩ ላይ ተክሏል:: እንደ ወትሮው ሁሉ ከዋክብት፣ ሙሉዋ ጨረቃ ዙሪያ ወዲህና ወዲያ ተበታትነው ይታያሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ሁሌም ተፈጥሮአዊ ሕጉን ተከትሎ ሲከናወን እያስተዋለው የኖረው ሂደት ነው፤ ግን ዘወትር በእዛ ሰዓት ብርድ እየቆጋው ደጅ ላይ መቀመጡን ልማድ አድርጐታል፡፡ ሰፊ ቅጥር ግቢው መሀል ያረፈውን ትልቅ ቪላ ቤቱን የከበቡት ትላልቅ የዝግባና የወይራ ዛፎች፣ ነፋሱ አልፎ አልፎ እየመጣ በኃያል ጉልበቱ ሲወዘውዛቸው የሚፈጥሩት የሌሊቱን ፀጥታ የሚያደፈርስ ድምፅ ይሰማዋል፡፡ ረጅም ዓመት በስደት ከኖረበት ምዕራብ አገር ተመልሶ አገሩ መኖር ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡   
…ተጭሶ ቂጡ ላይ የደረሰ ሮዝማን ሲጋራውን ስቦ መሬት ላይ ጥሎ በእግሩ ረገጠና ከአሮጌ የቀርከሀ ሶፋው ላይ ተነስቶ ወደ ቤት ገባ፡፡
ፊት ለፊቱ ከሚገኘዉ ረጅም ሶፋ ላይ፣ ባለቤቱ በተጋደመችበት እንቅልፍ ወስዷት ታንኮራፋለች:: ተጋብተው አብረው መኖር ከጀመሩ ቅርብ ጊዜአቸው ነው፡፡ እራት በጋራ በልተው አብቅተው ሶፋ ላይ ተጋድማ ቴሌቪዥን እየተመለከተች ሳለ ነበር ትቷት ወደ ደጅ የወጣው፡፡ ሐምራዊ የቀሚስ ቢጃማዋ ላይ የደረበችው ነጭ ፎጣ እግሮቿን ሙሉ በሙሉ ማልበስ ስላልቻለ ተጋልጠው ይታያሉ፤ ሎሚ የመሰሉ ተረከዞቿ፣ በጥቁር የጥፍር ቀለም የተዋቡት የእግሮቿ ጣቶች፡፡ ለጠይም ፊቷ ታላቅ ግርማ የሆነው ሰልካካ አፍንጫዋ ዙሪያ ላቦት ችፍ ብሎ ይታያል፡፡
ከሶፋው ላይ ተነስቶ አጠገቧ ሄደና፡-
“ማርቲ … ማርቲ…” አለ፤ እየቀሰቀሳት፡፡ ከእንቅልፏ ነቃች፡፡
“ተነሽ፣ መኝታ ቤት ገብተሽ ተኚ”  
“እሽ፣ እዚሁ ተኛሁ አይደል? ስንት ሰዓት ነው? ሰባት ሰዓት!” አለች፤ ፊት ለፊት ግድግዳው ላይ የተሰቀለው ሰዓት ላይ አፍጣ፡፡
“አንተስ አልጨረስክም? ብታርፍ ይሻልሃል::” አለች፤ ሶፋዉ ጫፍ ላይ ተቀምጣ ራሷ ላይ ሸብ አድርጋው የነበረውን ሻሿን እያስተካከለች፡፡ ለስላሳ ነው ድምጿ፤ ልክ እንደ አርጋኖን በጆሮ ውስጥ የሚፈስ፡፡
“እሽ፤ ትንሽ ልቆይና እተኛለሁ፡፡” አለ፤ በፈገግታ እየተመለከታት፡፡ ከተቀመጠችበት ተነስታ፣ በግራ እጇ አፏን ጋርዳ እየተንጠራራች አዛጋችና በእንቅልፍ የዛለ ጅስሟን እየጐተተች ወደ መኝታ ቤት ገባች፡፡
ቴሌቪዥኑን ዘጋና መኝታ ቤት ጐን ወደሚገኘው የንባብ ክፍሉ ገብቶ፣ ግድግዳውን ታኮ ከቆመ በመጻሕፍት ከተሞላ ትልቅ የመጽሐፍ መደርደሪያ አጠገብ ወደሚገኘው የመጻፊያ ጠረጴዛው ሄዶ ወንበሩ ላይ ተቀመጠ፡፡ የመጻፊያ ጠረጴዛው በተለያዩ መጻሕፍት፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች ተጣቧል፡፡ ሲጋራ አቀጣጥሎ ወንበሩ ላይ ወደ ኋላ ተለጥጦ ተቀመጠና ሊጽፈው ያቀደውን ሐሳብ ማውጠንጠን ያዘ፡፡ ፊት ለፊቱ  ገና ያልተጠናቀቁ የፈጠራ ሥራዎቹ ተከምረዋል:: ከወራት በፊት ሁለት ምዕራፎችን ብቻ ጽፎ ያቆመውን የልብወለድ ድርሰቱን ረቂቅ አነሳና ቀጣዩን ታሪክ ሊጽፍ ብእሩን ጨበጠ፡፡
* * *
ሕይወት፤ አስመራሪ ስንክሳሯ አታክቶኝ ስልቹነት ቢከበኝም ልጋፈጣት እዳዬ ነው:: በሁሉም ጎዳናዋ አልፌ መራርና ጥዑም ግብስብሷን ተቋድሻለሁ፡፡ አፍቅሬ አብጃለሁ፤ መውደድን ሊለግሱኝ ሽተው ፊቴን ያዩ ብዙዎችን አሳፍሬ ሰድጃቸዋለሁ፤ ያኔ ተወድጄ ተመልኬ ሳለ፡፡ በከባድ ሐዘን ተውጬ በባይተዋርነት የገፋኋቸው ብዙ ጊዜያት ነበሩ፤ ረሀብና እጦትን በደንብ አድርጌ አውቃቸዋለሁ …፡፡
እጅግ ጭምት እንደሆንኩ ነው በዙሪያየ ያሉት ሰዎች የሚያወሩት፡፡ ይህ አብሮኝ ያደገ ባሕሪዬ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር በሆዴ ማሳደርን ነው የምመርጠው፤ ሐዘኔንም ደስታዬንም፣ ፍቅሬንም ጥላቻዬንም፡፡ ስለ ሕይወት ያለኝ ርዕዮት አልተለወጠም፡፡
ያደግኩት፣ በጉዲፈቻ በወሰዱኝ ቤተሰቦቼ እጅ ነው፡፡ የሶስት ዓመት ልጅ ሳለሁ ነበር በእነዚሁ አሳዳጊዎቼ (አቶ ግርማ ኃይሉ እና ወይዘሮ ገነት አሰፋ) ጥያቄ መሠረት፤ የእናቴ ዘመዶች ፈቅደው የተሰጠሁት፤ ወላጅ እናቴ ሒሩት ስትሞት፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ ነበር አሉ የምትኖረው፣ የኪራይ ቤት ውስጥ፡፡
የሆነ ወቅት፣ የአሳደጉኝ ቤተሰቦቼ እውነተኛ ወላጆቼ አለመሆናቸውን ያወኩ ሰሞን ለተወሰኑ ጊዜያት አእምሮዬ ተዘባርቆ ነበር፤ ቸልተኛነቴ ረድቶኝ እየቆየሁ ጉዳዩን ቸል አልኩት እንጂ፡፡ አሁን አሁን ይህ ታሪኬ ትልቅ ጉዳይ ሆኖ አሳስቦኝ አያውቅም፣ ምክንያቱም እጣዬ ነው፡፡
ለቤተሰቦቼ ግርማ እና ገነት ያለኝ ፍቅርና አመለካከት ወደር አይገኝለትም (አሁንም ድረስ):: የማታ ማታ እድሌ ባያምርም ሁሉንም ነገር አሟልተውልኝ በልዩ እንክብካቤ ነው ያደግኩት፤ ከታላቅ እህቴ ቤርሳቤህ (የአሳዳጊዎቼ ብቸኛ ልጅ ነች) ጋር የጣመ በልቼ፣ ያማረ ለብሼ:: ለቤርሳቤህ ያለኝ ፍቅር የተለየ ነው፣ እሳሳላት ነበር፡፡ በባሕሪዋ ሲበዛ የዋህ ነች፡፡  በመካከላችን ጠንካራ መተማመን ስለ ነበር የግል ገመናዎቿን ዘርግፋ ትነግረኝ ነበር፡፡
* * *   
ካለፈው ቅዳሜ ውሎዬ ጀምሮ የራቅሁት የሚመስለኝን፤ ግን ከልቤ ሰሌዳ ላይ ያልተፋቀዉን ትዝታዬን ሳብሰለስል ነው ሳምንቱን የዘለቅኩት:: ይህ የትዝታዬ መዝገብ ከዓመታት በፊት ከመጀመሪያ ፍቅረኛዬ ዳንኤል ጋር ያሳለፍኩትን የፍቅር ሕይወቴን የሚመለከት ነው፡፡ ዳንኤልን የተዋወቅኩት አንድ ምሽት ከእህቴ ቤርሳቤህ ጋር በሄድንበት ቦሌ አካባቢ በሚገኝ የምሽት የሙዚቃ ክለብ ውስጥ ሲዘፍን አግኝቼው ነው፡፡
እጅግ የታወቀ ሱዳናዊ ዘፋኝ ለረጅም ሰዓት በአድናቂዎቹ ዘንድ በሰፊው የሚታወቅባቸው ዘፈኖቹን ተጫውቶ ከመድረኩ እንደ ወረደ አንድ ቀይ ወጣት ድምፃዊ በተራው ሊጫወት ወደ መድረክ ወጣ፤ ይህ ድምፃዊ ዳንኤል ነበር:: ከረፈደ እና ቃል አባይ የተሰኙ ሁለት ዘፈኖችን አከታትሎ ተጫወተ፡፡ የተለየ ተሰጥኦ ነበረው፡፡ የድምፁ ቅላፄ፣ የተጫወታቸው ዘፈኖች… ብቻ ሁሉም ነገር ውብ ነበር፡፡ ታዲያ፣ መድረክ ላይ ቆሞ ሲያዜም ባየሁት ቅፅበት ልቤ ደነገጠለት፡፡
ዳንኤል እየዘፈነ ሳለ የቤርሳቤህን በአጨዋወቱ መመሰጥ አስተውዬ፡-
“ደስ የሚል ዘፈን ነዉ!” አልኳት፤ ወደ ጆሮዋ ተጠግቼ፣ ድምፄን ከፍ አድርጌ፡፡        
“በጣም!” አለች፤ ቤርሳቤህ ጮክ ብላ:: የሙዚቃዉን ምት ተከትላ በተቀመጠችበት በእርጋታ እየተወዛወዘች ነበር፡፡ ከአጠገባችን ተቀምጠው የነበሩት ወጣት ፍቅረኞች ዳንስ ወለሉ ላይ ወጥተዉ በዝግታ እየደነሱ ነው፤ የወንዱ እጆች የፍቅረኛው ወገብና ዳሌ ላይ አርፈዋል፡፡ የዳንሳቸው ኪነት የሰመረ ነው፡፡
ሲጋራዋን ስባ ጭሱን ሽቅብ አትጎለጎለችና፡-  
“ለምን ወጥተሽ አብረሽው አትደንሱም?” አለችኝ፤ ቤርሳቤህ ወደ ጆሮዬ ተጠግታ ወደ ክለቡ እንደገባን መጥቶ ሰላም ብሎን ወደ ሄደው፣ ኮሌጅ ሳለች እንደሚተዋወቁ ወደ ነገረችኝ፣ ጎናችን ወደ ተቀመጠው ቀይ ረጅም ባለ አፍሮ ወጣት እያመላከተችኝ፡፡ አንገቴን ግራ ቀኝ በአሉታ በመነቅነቅ፣ አብሬው ለመደነስ ፈቃደኛ አለመሆኔን ገለፅኩላት፡፡
ዳንኤል ተጫውቶ አብቅቶ ከመድረክ ከወረደ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አንድ ጥቁር ጎልማሳ ድምፃዊ የያዘ የፈረንጆች የሙዚቃ ባንድ ተተካ፡፡
“እዚህ ቤት ስመጣ ማን ትዝ እንደሚለኝ ታዉቂያለሽ?” አለች፤ ቤርሳቤህ ሲጋራዋን መተርኮሻ ላይ ተርኩሳ አተኩራ እያስተዋለችኝ፡፡
“ማን ነዉ? ”
“ካሌብ! ”
“ካሌብ? ዛሬም ታስቢዋለሽ ማለት ነው? ”
“እንዴ! አዎ፡፡ የመጀመሪያዬ እኮ ነዉ፡፡ ”
“ባለጌ ሰው ነው ግን፣ ያደረገሽን ነገር ሁልጊዜ ሳስብ እበሳጫለሁ፡፡”
“ምን ታደርጊዋለሽ፡፡” አለችና ቢራውን ብርጭቆዋ ላይ ማንቆርቆር ጀመረች፡፡
“በስንት ጊዜው ትናንት ደውሎልኝ ነበር፡፡ ”
“ምን አለሽ?”
“ስልኩን አላነሳሁለትም፡፡”
“ከምርሽ ነው? የእሱ ነገር ቆርጦልሻል ማለት ነው?”
“በድሎኛል፣ ግን ሙሉ ለሙሉ ከልቤ ላወጣው አልቻልኩም፡፡”
“ከንቱ ተስፋ የሰነቅሽ ይመስላል፡፡”
“ሰው ምን ይላል ግን አሁን ተመልሼ ወደ እሱ ብሄድ?”
“ግን እኮ እምነትሽን አጉድሏል፡፡ በዚያ ላይ አሁን አብሮሽ ላለው ሰው ማሰብ
አለብሽ”
“ጆንን ማለትሽ ነው?”
“አዎ”
“ተይው እባክሽ! ሁሉም ያው ናቸው” አለችና አንገቷን ሰብቃ ከፊል ፊቷን አልብሶ የነበረውን ረጅም ፀጉሯን ወደ ጆሮዋ ኋላ መለሰች፡፡
“እንዴት እንዲህ ልትይ ቻልሽ? ከዮሐንስ ጋር ሰላም አይደላችሁም እንዴ?”
“ኧረ በጣም ሰላም ነን! እጅግ መልካም ሰው እኮ ነዉ፡፡”
“ካሌብ ቢበድልሽም ኋላ ላይ ጥሩ ሰው ገጠመሽ፡፡”
“አዎ፣ ግን ነገ እሱም መለወጡ አይቀርም፤ በዚያ ላይ የካሌብን ያህል ልወደው አልቻልኩም::”
“በሂደት ትወጅዋለሽ፡፡”
“እስቲ እናያለን” አለችና ብርጭቆዋን አንስታ ቢራዋን ተጎነጨች፡፡                                  

Read 3173 times