Print this page
Tuesday, 02 July 2019 12:33

አዲስ አበባ - የዘውጌ ፖለቲካ ማቅለጫ ጋን

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(2 votes)


      የንደፈ ሐሳብ ቋጠሮ
ታዋቂው የሥነ ማኅበረሰብ ፈላስፋው ቱርካዊው ዱርካይም፣ ከተሜነት የዘውጌ ማንነት ማቅለጫ ጋን (melting pot) እንደሆነ ያብራራል፡፡ እንደ ልሂቁ አባባል፣ የከተማ መስፋፋት ከኢንዱስትሪ አብዮት መፈንዳት ለጥቆ የሚመጣ ኹነት ነው፡፡ ይኽ ነባራዊ ኹኔታ ደግሞ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካውና በኢኮኖሚ ረገድ የፋፋ ዘመናዊ ማኅበረሰብን ለዐይነ ሥጋ በማብቃቱ ረገድ ድርሻው የላቀ ነው፡፡ በዚህ አውድ ውስጥ የተፈጠረ የዳበረ ማኅበረሰብ ለዘውጌ ማንነት ፊት አይሰጥም፡፡ አጠቃላይ የግለሰቦች የእርስ በርስ ግንኙነት በላቀ ኅላዌ (ኦርጋኒክ ሶሊዳተሪ) የሚገለጽ እንደሆነ ከፈላስፋው ሐተታ እንረዳለን፡፡
በአንጻሩ የዘመናዊነት መዳፍ ያልዳበሰው ኋላ ቀር ማኅበረሰብን ያስተሳሰረው የግንኙነት መረብ፣ ከአምክንዮ በተራቆተ የደቦዋዊ ቅኝት፣ ማለትም በወንዝ ልጅነት፣ በእምነት፣ በባህል ወይም በትውፊት የሚገለጽ ይሆናል፡፡ እሴቶቹ በመወለድ ብቻ የምንላበሳቸው ቆሞ ቀር የማንነታችን መገለጫዎች ናቸው፡፡ የእኛን ማውጣት ማውረድ /Rational endeavor/ ወይም የአእምሮ ፍሬ የሚጠይቁ አይደለም፡፡ እነዚህ ኋላ ቀር የትስስር ዘረ-መሎች ዘመናዊነት በሚፈነጥቃቸው እድገቶች ምክንያት በሌላ ውስብስብ መስተጋብር ደብዛቸው ይጠፋል፡፡
በሌላ አነጋገር የዘውጌ ፖለቲካ በጽኑ የሚሻው ባህላዊ ንጣፍ፣ ከተሜነት በሚያመጣው እድገት የተነሳ ጠፍ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ባህላዊውን ማኅበረሰብ እንደ ወጋግራ ያቆመው ከምክንያት ይልቅ፤ ለስሜት ቅርብ የሆነው የጋራ ማንነት፣ ዝመና የሚፈጥረውን ልህቀት መቋቋም ተስኖት ሥፍራውን ለሌላ ገዢ መስተጋብር መልቀቁ ግዴታ ይሆናል፡፡ ከተሜው በሐሳብ የበላይነት እንጂ፤በቋንቋ ማንነት ወይም በወንዜ ልጅነት ልቡ ሊሸፍት አይችልም፡፡
የዘውጌ ብሔርተኝነትና አዲስ አበቤነት
አዲስ አበቤነት በዘውጌ ማንነት ኪሳራ የተቀለሰ የላቀ ሰብእና ነው፡፡ የአዲስ አበባን ውሃ ጠጥቶ ያደገ ኮበሌ እንደው በቀላሉ የቤተሰቡን የዘውጌ ውርስ እንደ ካባ አንስቼ ላጥልቅ ቢል አይቻለውም፡፡ አዲስ አበቤነት የደም ውርስ አይደለም፤ ከግለሰቡ አቅም በላይ በሆነ ማኅበራዊ ስሪት/ሶሻል ኮንስትራክሽን/ በጊዜ ሒደት የሚዳብር ማንነት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፣ ከሐሳብ ይልቅ በዘውግ ፖለቲካ ላይ መሕልቃቸውን ለጣሉ ብሔርተኛ ድርጅቶች መርዶ እንደሚሆን የሚጠበቅ እውነታ ነው፡፡ አዲስ አበባ የዘውግ ፖለቲካ ማቅለጫ ጋን (ሜልቲንግ ፖት) ናት፡፡ በአዲስ አበባ ዜጎች በደቦ በሚቧደኑበት ዝግ ማንነት (ቋንቋ እና ዘረመል) ምትክ ከተሜነት በወለደው ሁሉን አቃፊ በሆነ፣ ሥልጡን መስተጋብር እርስ በርሳቸው ሳይነጣጠሉ የተቆራኙ ናቸው፡፡ አዲሱ የለውጥ አስተዳደር የሥልጣን መንበሩን በተቆናጠጠባቸው ጥቂት ወራት ውስጥ ዋንኛ የክረት ማእከል ሆኖ ብቅ ያለው የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ጫፍና ጫፍ የረገጡ የዘውጌ ብሔርተኞች፤ አዲስ አበባን ያለ አበሳዋ አዲስ ማንነትን ሊያላብሷት ከፍ ዝቅ ከማለት ወደ ኋላ አላሉም፡፡
የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር አምባቸው መኮንን (ነፍሳቸውን ይማረውና) በአንድ መድረክ ላይ የተናገሩት ፍሬ ሐሳብ ከዚሁ ጋር በእጅጉ የሚቆራኝ ነው፡፡
“ለውጡን ለማደናቀፍ ሌት ተቀን የሚተጉት ቡድኖች፣ ያለ የሌለ ኃይላቸውን በመጠቀም ፣አዲስ አበባን እንደ ውዝግብ ማእከል ለማድረግ በብርቱ እየሠሩ ነው፡፡ ፀረ ለውጥ የሆኑት አክራሪ ኃይሎች፣ ማእከሉ ሲረበሽ የሁለቱ ታላላቅ ሕዝቦች አንድነት ይናጋል የሚል ምኞት አላቸው፡፡ ይኽ ምኞታቸው ግን የቁም ቅዠት ሆኖ ይቀራል፤ በፍጹም አይሳካም::” ብለው ነበር፡፡
እርግጥ ነው፣ የአማራና የኦሮሞ አክራሪ የዘውግ ኃይሎች፣ በመዲናይቱ ላይ የይገባኛል ጥያቄ መሰንዘር ከጀመሩ ሰንበተዋል፡፡ “ፊንፊኔ ኬኛ” እና ”በረራ የእኛ” በሚሉ ዋልታ ረገጥ ትርክቶች፣ ማዶ ለማዶ ሆነው እየተጓተቱ ነው፡፡ የአማራ ብሔርተኞች፤ የአዲስ አበባንና የበራራ ታሪክን ለማስተሳሰር፣ ወደ ኋላ ሩቅ ሄደው በ16ኛው ክ/ዘመን የነበረውን ኹነት ያጣቅሳሉ፡፡ ዶ/ር ሐብታሙ ተገኝ ካሰፈረው ረጅም ጽሑፍ ጥቂት ልውሰድ፡-
“በኦሮሞ ብሔርተኞች የሚቀነቀነው የአዲስ አበባ ታሪክ በፈጠራ የታጀለ ነው፡፡ የአዲስ አበባ የጥንት ስም በረራ ነው፡፡በረራም የኢትዮጵያ የነገሥታቱ ዋና መቀመጫ በመሆን ከአጼ ዳዊት ቀዳማዊ (1380-1413) ጀምሮ እስከ አጼ ልብነ ድንግል (1508-1540) ከመቶ ዓመት በላይ አገልግላለች፡፡ በረራ ወረብ በሚባል አውራጃ ትተዳደር እንደ ነበር የታሪክ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ በ16ኛው ክ/ዘመን ይኖሩ የነበሩ ብዙ የውጭ ሀገሮችን የጎበኙት አባ ዳንኤል የተባሉ ኢትዮጵያዊ መነኩሴ ወረብን በኢየሩሳሌም መስለው ጽፈዋል፡፡”
በአንጻሩ የኢምሬት ፕሮፌሰሩ ሙከሪያ ቡልቻ፤ “Greater Addis Ababa in the making: Stop them or Perish” (ታላቂቷ አዲስ አበባ እየመጣች ነው፤አቁሟቸው አሊያም ዝም በሉና ጥፉ) በሚለው ሐተታቸው የተለመደውን የታሪክ ትንታኔ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ የሐተታቸው የጊዜ ምሕዋር የሚሽከረከረው ግን፣ የቅርቡን የ19ኛው ክ/ዘመንን የታሪክ ውጣ ውረድ ታሳቢ አድርጎ  ነው፡፡ በርግጥ ታሪክን ለትንታኔ ከሚመቸን የጊዜ ውቅያኖስ ጨልፎ መውሰድ አመክኖአዊ አይሆንም፡፡ ለማንኛውም ልኂቁ በከተማዋ ዙሪያ ካሰፈሩት በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል እነሆ፡-
“አጼ ምኒልክ ወደ ኦሮሞ መሬት መስፋፋት እንደ ጀመሩ የፊንፊኔን ውብ ሜዳና ሸለቆ ሊያሳይ በሚችለው እንጦጦ ተራራ ላይ ቤተ መንግሥታቸውን መገንባት ነበር፡፡ አንጦጦ በዛን ጊዜ ላልገበረው ፊንፊኔም ሆነ ዙሪያ መለስ ለሚገኙ አካባቢዎች፣ እንደ ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ቦታ የሚያገለግላቸው መሆኑ በንጉሡ ዘንድ ተመራጭ አድርጎታል፡፡ 1880ዎች አጋማሽ ወረራውን በድል ፈጽመው ከእንጦጦ ወደ ፊንፊኔ በመውረድም ቤተመንግሥታቸውን ገነቡ:: የአካባቢውን ስምም ወደ አዲስ አበባ ቀየሩ፡፡ በመቀጠል ምኒልክ በዙሪያቸው ለሰፈሩት መሳፍንት እና ወታደሮች መሬት ሲከፋፍሉና ከተማዋ እየሰፋች ስትሄድ በሺዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ተፈናቅለዋል::”
እነዚህን የኋላ ኹነቶች በዚህ ዘመን ላይ ቆሞ የንትርክ አጀንዳ መፍጠር፣ በታሪክ ፊት የዋኽ የሚያስብል ተግባር ነው፡፡ አዲስ አበባ መመዘን ያለባት አሁን ባለው አጠቃላይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማእቀፍ ብቻ መሆን አለበት:: ሁለቱም ኃይሎች ከተማዋን ያለ ሥሪቷ ባእድ ማንነትን ለመጫን የሚያደርጉት ሩጫ ማሳረጊያው ጥፋት እንደሚሆን ለመገመት ሊቅ መሆንን አይጠይቅም፡፡
ካሊፎርኒያ የካሊፎርኒያዊያን ናት እንደሚባለው ሁሉ፣ የአዲስ አበባም የባለቤትነት ጉዳይ በዚህ አውድ ውስጥ ነው መበየን ያለበት፡፡ በርግጥ አዲስ አበባ፤ የአዲስ አበቤዎች ነች የሚለው ትርክት ከተተከለው የፖለቲካ ሥርዓት ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ ይኽ እውነታ ሕገ መንግሥታዊ እውቅና ተነፍጎታል፡፡ የሉአላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ብሔር ብሔረሰቦች ስለሆኑ፣ ከዚህ ከረጢት ውጭ የሆነ በዜግነት ወይም በአዲስ አበቤነት የተገኘ ማንነት የሚስተናገድበት ምንም ማእቀፍ የለም፡፡ ይኽም ሆኖ ግን የዘውጌ ፖለቲካ አራማጆች፤ የአዲስ አበቤዎችን ልብ የሚያሸፍቱበት ቁመናን  መላበስ እስካሁን አልቻሉም፡፡
“ኬኛ” አንብሮ እና “የእኛ” ተቃርኖ
የ“ኬኛ” እና “የእኛ” ፖለቲካዊ ትርክት አራማጆች የቆሙበት መደላድል ከከተሜ መሠረታዊ ባሕሪያት ጋር ፈጽሞ የሚሄድ አይደለም፡፡ ዳር እና ዳር ሆነው የሚጓተቱት እነዚህ ኃይሎች ድጋፋቸው፣ከተሜነት የወለደው ውስብስብ ነባራዊ ሁኔታ ሳይሆን በሩቁ ዘመናት የተከሰቱ ታሪካዊ ኹነቶች ናቸው፡፡ ሽኩቻቸውን ጤናማ ማድረግ ይቻላል፡፡ ቅራኔያቸው ዲያሌክቲካል (የተሻለ ነባራዊ ሁኔታን የሚወልድ ፍጭት) መሆን ከቻለ ግን ውጤቱ መልካም ይሆናል:: “የኬኛ” ትርክት በአንብሮ (thesis) መልክ ማዶ ላይ ቆሞ በሌላ ጫፍ ቆሞ ከሚገዳደረው “የእኛ” ትርክት /antithesis/ ጋር በሚፈጥሩት ሰላማዊ የስሜት ፍጭት ሁሉን አቃፊና ሰብሳቢ የሆነው አዲሰ አበቤነት በአስተጻምሮ /synthesis/ ደረጃ መወለድ ለሁሉም የሀገራችን ዜጋ ብሥራት ነው የሆነው፡፡ ይህን ገቢራዊ ለማድረግ ስክነት የተሞላበት የሐሳብ ሙግትን የሚያስተናግድ ምህዳርን መፍጠር ግዴታ ይሆናል፡፡
ማሰሪያ
በአዲስ አበባ ላይ ብሔር ተኮር ቁመና ያላቸው ኃይሎች በሰለጠነ መንገድ የሐሳብ ሙግት የሚያደርጉበት አውድ መፍጠሩ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የለውጡ ሒደት ተቋማዊ ቅርጽን እንዲላበስ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የማንነት ፖለቲካ አቀንቃኞች የኋላ ታሪክን መሠረት ያደረገ የበደለኝነት /victimhood mentality/ ትርክትን እንደ ነዳጅ ከመጠቀም የዘለለ ሙያ እንደሌላቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ኃይሎች በሰከነ የውይይት መንፈስ አሸንፈው የሚወጡበት እድላቸው የመነመነ ነው፡፡ ይኽ ደግሞ፣ ለአዲስ አበባ ማኅበረሰብ በጎ ውጤትን ይዞ መምጣቱ የማይቀር ይሆናል፡፡ እውነተኛ የአዲስ አበቤነት መንፈስ ወይም የዜግነት ፖለቲካ ከበባውን ሰብሮ እንዲወጣ ከተፈለገ፣ ተቋማዊ ዋስትና ያለው፣ የሐሳብ ሙግት የሚያስተናግድ የተለቀቀ ምህዳር እውን መሆን አለበት፡፡

Read 1588 times