Tuesday, 02 July 2019 12:21

ቃለ ምልልስ መንግስት በቀጣይ ምን ያድርግ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 የአማራ ክልል አመራሮች እና የመከላከያ ኢታማዦር ሹም ላይ የተፈፀመው አሳዛኝ ድርጊት እና በቀጣይ መንግስት ሊያከናውናቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች የፖለቲካ ተንታኞቹና ፖለቲከኞቹ ዶ/ር አለማየሁ አረዳ እና አቶ ሙሼ ሰሙ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ባደረጉት ቆይታ ምልከታቸውን እንደሚከተለው አጋርተውናል፡፡

           “የመንግሥትን አቅጣጫ በጉልበት የሚያስለውጡ በርክተዋል”
               አቶ ሙሼ ሰሙ


      ከሰሞኑ በአማራ ክልል አመራሮችና በፌደራል የመከላከያ ሰራዊት አዛዦች ላይ የደረሰው ጥቃት እንዴት ሊከሰት የቻለ  ይመስልዎታል? መንግስት ለዚህ ችግር የተጋለጠው በምን ምክንያት ነው  ብለው ያስባሉ?
ኢህአዴግ እንደ ድርጅት አንድ መስሎ ቢታይም ውስጣዊ መከፋፈሉ ቆይቷል፡፡ ውስጣዊ መከፋፈሉን  የፈጠረው ደግሞ የስልጣን ሽኩቻ መልክና ቅርፁን እየለዋወጠ፣ በተለያየ መልክ ሲገለፅ ነው የቆየው፡፡ መንግስት እንደ መንግስት፣ መሳሪያ ወይም ሃይል ሊኖረው የሚገባው ማን እንደሆነ በህግ ማረጋገጥ አልቻለም፡፡ እንደሚታወቀው በተለያየ ብሔረሰብ ስም በተለያየ ቡድን የተደራጁ ኃይሎች አሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች በጉልበት መንግስት ላይ ተፅዕኖ እያደረጉ፣ የሚፈልጉትን ነገር ማግኘትን ተለማምደዋል፡፡ የፈለጉትን አጀንዳ ይዘው እየመጡ መንግስትን እጁን ጠምዝዘው፣ እነሱ የፈለጉትን ማስደረግን በሚገባ ሲለማመዱ ቆይተዋል፡፡ ይሄ ልምድ ደግሞ ቀስ እየተባለ በኃይል ወደ መንግስትነት እንደሚመጣ ያመላከታቸው  ይመስላል፡፡ መንግስት ራሱም እነዚህን ቡድኖችና ኃይሎች በፍርሃት ነው የሚያየው፡፡ እነዚህን ቡድኖች የሚመሩ  ኃይሎች፣ የመንግስት ያህል ነው  እየተንቀሳቀሱ ያሉት፡፡ ይሄ የአንድ ክልል ችግር ብቻ አይደለም፡፡ በየክልሉ ያለ ችግር ነው፡፡ የመንግስትን ፖሊሲ የሚያስለውጡ፤ የፈለጉትን ጥያቄ በጉልበት የሚያስመልሱ በርክተዋል፡፡ ይሄን ባደረጉ ቁጥር “መንግስት ደካማ ነው፤ የተደራጀ ኃይል ከያዝክ መንግስት ለመሆን አይቸግርህም” ወደሚል ዝንባሌ በርካቶችን የከተተ ይመስላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የህግ የበላይነት በሚገባ አለመረጋገጡ ነው፡፡ ቡድኖች፤ የየብሔረሰባቸውን መብት ማስከበር ከፈለጉ እንደ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ተመዝግበው፣ ሰርተፍኬት ወስደው መታገል ነው ያለባቸው፤ አሁን እኮ ህጋዊነት የላቸውም፡፡ የሚጠየቁበት አግባብም የለም፡፡ የሚፈልጉትን ነገር በማስፈራራት፣ በጫና ነው የሚያስፈጽሙት፡፡
መንግስት ዋነኛ ተግባሩ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ነው፡፡ የመንግስትነት የመጀመሪያ ማረጋገጫው፤ የህግ የበላይነትን በማያወላዳ መልኩ ማስከበር ነው፡፡ የህግ የበላይነት ሲጠፋ ነው ሰላም የሚደፈርሰው፡፡ በእርግጥ ሽግግር በአንድ ጊዜ የተሟላ አይሆንም፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮችንም ይፈጥራል፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ የህግ የበላይነት በማያሻማ መልኩ እየተሰራበት ቢመጣ ኖሮ፣ አሁን እንደምናየው ከኋላቸው ቡድኖችን ወይም የተደራጁ ኃይሎችን አስቀምጠው መንግስት ላይ የሚፎክሩ ግለሰቦች አይፈጠሩም ነበር፡፡ በዚህ መጠንም ጉልበተኛ ሊሆኑ አይችሉም ነበር፡፡ በሌላ በኩል፤ በየክልሉ ሚሊሻዎችና ልዩ ኃይሎች አሉ:: እነዚህ ልዩ ኃይሎች ምን ያህል በመንግስት መዋቅር ስር ናቸው? ይሄም ሌላው አጠያያቂ ጉዳይ ነው:: በአጠቃላይ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና የተደራጁ ሃይሎች ይዘን መንግስትን በጉልበት ማንበርከክ እንችላለን የሚል አመለካከት እየሰፈነ መምጣቱ ለዚህ ችግር ዳርጎናል፡፡ አንዳንድ ክልሎች ላይ እኮ አንድ ጥያቄ ይዘው መጥተው፣ ህዝቡን ሰላማዊ ሰልፍ አስወጥተው፣ መንግስትን በጉልበት የሚፈልጉትን ነገር እንዲያደርግ እያስገደዱት ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት መንገድ ነው እየተጓዝን ያለነው፡፡ አንዳንዶቹ ለለውጡም ምክንያት ናቸው ተብለው ስለሚታመኑ ጉልበት ለመጠቀም የሚያደርጉት ጥረት ችላ ተብሏል፡፡ ይሄ በሂደት 85ቱም ብሔረሰቦች ቡድን እየሰየሙ፣ የየራሳቸውን ፍላጎት በመንግስት ላይ የማይጭኑበት ምክንያት አይኖርም፡፡ የቡድን አደረጃጀቶችን እኮ በስም እናውቃቸዋለን፡፡ ድንገት ብድግ ብለው፤ “ይሄን ቦታ እንፈልገዋለን፣ እገሌ ከዚህ ውጣ፣ እገሌ ስልጣን መያዝ አለበት” ሲሉ ይሰማል፡፡ ይሄን ስንታዘብ ነው የከረምነው፡፡ መንግስትን በግልፅ እኮ “እኔ የምልህን እምቢ ካልክ እገሌን እለቅብሃለሁ” የሚሉ ግለሰቦች ተፈጥረዋል፡፡ መንግስት ለእያንዳንዱ ጉዳይ ሰላማዊ ሰልፍ እየተወጣ፣ እየተፎከረ መፍትሄ እንደማይሰጠው በህግ የበላይነት ማረጋገጥ ነበረበት:: ይሄን ስል በሰላም ላይ አልተሰራም ማለቴ አይደለም፡፡ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ነገር ግን ሰላም እንዲሰፍን መስራትና ሰላም እንዲሰፍን ሁኔታዎችን ማመቻቸት የተለያዩ ስራዎች ናቸው፡፡ ሰላም እንዲመጣ ማህበረሰቡን መስበክና ማነቃቃት ይቻላል፤ ነገር ግን መሬት ላይ በህግ መስራት የራሱን ጥረት ይጠይቃል፡፡
እርስዎ የጠቀሷቸው ችግሮች ወይም ክፍተቶች ለአሁኑ ክስተት መደላድል ፈጥሯል ማለት ይቻላል?
አዎ! በእርግጥ ሰዎቹ ለምን ይሄን እንዳደረጉ በቀጣይ በምርመራ ሊናገሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን ይሄን አይነቱን ድርጊት ለመፈፀም ነገሮች ተመቻችተው ነበር፡፡ ነገ ምናልባት ሌሎች ክልሎች ላይም ህግ ካልተከበረ ተመሳሳዩን ልናይ እንችላለን፡፡ ሌሎች ቡድኖችም ነገ ከነገ ወዲያ የክልሎችን አስተዳደር በመቆጣጠር፣ ክልሉን ከማዕከላዊ መንግስት ቁጥጥር ውጪ ለማድረግ ሊሞክሩ  ይችላሉ፡፡ አሁንም ይህ እንዳይፈጠር መሰረታዊ ስራዎች መሰራት አለባቸው:: ሀገሪቷ ውስጥ ለስርአት አልበኝነትና ለጉልበተኝነት መደላድል ተፈጥሯል፡፡ ይሄ ሁኔታ መለወጥ አለበት:: አሁን መንግስት ችግሩን ወደ ህዝብ መውሰድ የለበትም፡፡ ችግሩ ያለው ኢህአዴግ ውስጥ ነው፡፡ ይሄ የህዝቡ ችግር አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ኃይሎች ናቸው ችግሩን የፈጠሩት፡፡
እነዚህ ኃይሎች ያሰቡት መፈንቅለ መንግስት ቢሳካ ኖሮ፣ ምን ዓይነት ሁኔታ ነበር ሊፈጠር የሚችለው?
ይሄ ነገር በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ ጊዜ ተወስዶበት የተሰራበት ነው አይደለም የሚለው ጉዳይ በመጀመሪያ መታወቅ አለበት፡፡ በግልፍተኝነት የተከሰተ ነገር ነው ወይ? የሚለው መጥራት አለበት፡፡ እርግጥ አመላካች ነገሮች አሉ፤ ነገር ግን ጉዳዩ ምንድን ነው? እንዴት ተፈጠረ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል:: ለምሳሌ የፌደራል መንግስት፤ የተሞከረው መፈንቅለ መንግስት ነው ይላል፤ ከሁኔታው የተረፉት ደግሞ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ ይሄ ነገር ጥቃት ነው፣ መፈንቅለ መንግስት የሚለው መጥራት አለበት፡፡ መፈንቅለ መንግስት ከሆነ ግን ምናልባት እኛ ክልላችንን ተቆጣጥረን፣ ከፌደራል መንግስት ጋር መደራደር እንችላለን የሚል እሳቤ ተይዞ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ትግራይን ስንመለከት አካባቢውን ዘግቶ ተቀምጧል፡፡ የማዕከላዊ መንግስት በዚያ አካባቢ የለም የሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሷል:: ያ እንደ ምሳሌ ተወስዶ ሊሆን ይችላል፡፡ በአማራ ክልልም የዚያ አይነት ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ ሊሆን ይችላል፡፡ ትግራይ፤ የማዕከላዊ መንግስት እንኳ በህግ የሚፈልጋቸውን ግለሰቦች እየተከላከለ ነው፤ይሄ ለኛም ይሰራል የሚል አመለካከት ተፈጥሮ፣ በተግባር ለመሞከር ተፈልጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄ ነገር ቢሳካና ጠቅላላ የአማራ ህዝብ በተፈፀመው ነገር ቢስማማ ኖሮ፣ እንዴት ይሆናል የሚለው ደግሞ ራሱን የቻለ ፈታኝ ነገር ነው፡፡ ያ ክልል የሸዋ፣ የወሎ፣ የጎንደር፣ የጎጃም አማራ አለበት፡፡
ስልጣን እንግዲህ በሁለት መንገድ ይያዛል:: አንዱ በሰላማዊ መንገድ በምርጫ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ህዝብን በነቂስ ለድጋፍ አስወጥቶ ድጋፍ አለኝ በሚል መንግስት መሆን ነው፡። አሁን ትግራይ ላይ የምናየው፣ የዚህ ዓይነቱን ሁኔታ  ነው፡፡ ያለው አስተዳደር ሰፊ ህዝባዊ ድጋፍ አለኝ በሚል ክልሉ ውስጥ የፌደራል መንግስት ገብቶ በህግ የተሰጠውን ጉዳይ ማስፈፀም እንኳ አልቻለም፡፡ የህዝብ ድጋፍ ካለው ኃይል ጋር የማዕከላዊ መንግስት መደራደር የግድ ይሆንበታል፡፡ በአማራ ክልል ተሞክሮ የነበረው ነገርም በህዝቡ ቢደገፍና ቢሳካ ኖሮ፣ በትግራይ ያለውን አይነት ሁኔታ ፈጥሮ፣ ከማዕከላዊ መንግስት ጋር ለመደራደር ይሞክር ነበር፡፡ በደንብ የተጠናና ቅድመ ዝግጅት የነበረው ነገር ቢሆን፣ ለማዕከላዊ መንግስትም ፈታኝ ይሆን ነበር፡፡
በቀጣይ ተመሳሳይ ችግሮች ሊያጋጥሙ የሚችሉበት ዕድል ይኖራል ብለው ይሰጋሉ?
ተወደደም ተጠላም፣ በህገ መንግስቱ ላይ የሀሳብ ልዩነት ቢኖረንም፣ አስሮ ያስቀመጠን ይህ ህገ መንግስት ነው፡፡ ይሄን ህገ መንግስት፣ በህገ መንግስታዊ መንገድ የመለወጥ አጀንዳ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ አጀንዳ መሆን አለበት፡፡ ሁላችንም ስራ ውለን ወደ ቤታችን የምንመለሰው ህገ መንግስትና ህግ አለ ብለን ተማምነን ነው፡፡ ህገ መንግስት በጉልበት ከተጣሰ ግን መተማመን ይጠፋል፡፡ ይሄ እንዳይሆን ትልቅ ስራ መሰራት አለበት፡፡ ሁለተኛ፤ በኢህአዴግ ውስጥ በራሱ ከዚህ ከለውጡ በኋላ ቅርፅና ይዘቱን በአግባቡ መርምሮ አንድነቱን ማምጣት ችሏል ወይ? ሁሉም ድርጅቶች እኮ በየራሳቸው አፈንግጠዋል:: ደቡብ፣ ትግራይ፣ አማራ፣ ሌላውም አፈንግጧል:: እርስ በእርሳቸው ምን ያህል እንደ አንድ ድርጅት ተማምነው እየሰሩ ነው? ውስጣቸው ያለን ችግር ተቀምጠው ተወያይተው እየፈቱ ነው ወይ? የኃይል አሰላለፋቸውን ጥርት አድርገው ተገንዝበዋል ወይ? ምክንያቱም ወደድንም ጠላንም አሁንም እያስተዳደረን ያለው ኢህአዴግ ነው፡፡ ኢህአዴግ ውስጥ ያለው ችግር ደግሞ ቀዳዳ እያበጀ ወደ ህዝቡ እየፈሰሰ ነው፡፡ ችግሮቹ የሚመነጩት ከዚያው ከግንባሩ ውስጥ ነው፡፡ ኢህአዴግ ራሱን አጥርቷል ወይ? ወዴት እንደሚሄድ ያውቃል ወይ? ተወያይቶ ወጥ በሆነ መልክ ራሱን ገምግሞ ተግባብቷል ወይ? ሁሉም ከየአቅጣጫው ሲጎትት አይደለም እንዴ የሚታየው? ክልሌን ህዝቤን የሚል አስተሳሰብ  አልዳበረም ወይ? በተለይ የተለየ ጥቅም ለማግኘት የሚደረግ ግብግብ ይታያል፡፡ ይሄ ሁሉ ነገር ተደማምሮ ስጋት መፍጠሩ አይቀርም:: ስለዚህ ድርጅቱ በዋናነት ራሱን መፈተሽ፣ ማስተካከል፣ በህግ መገዛት አለበት፡፡ ይሄ ካልሆነ ግን ስጋቱ አይቀርም፡፡ የከፋም ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል:: የአመራር ክፍተት ባለበት የደፈረ ሁሉ በቀዳዳው ይገባል፡፡ እየተከሰተ ያለውም ይሄው ነው፡፡ ግለሰቦች ኃይለኛ ተፅዕኖ የሚፈጥሩበት ሃገር እየሆነ እኮ ነው:: ነገሩ ከመስመር ወጥቷል፡፡ አሁን ያን ከመስመር የወጣ ነገር ወደ መስመሩ መመለስ ያስፈልጋል፡፡
የደረሰው ጥቃት የመንግስትን ባህሪ ይቀይረው ይሆን? አንዳንዶች መንግስት ወደ አምባገነንነት እንዳይቀየር  የሚል ስጋት አላቸው---
እኔም እንዲህ ያሉ ነገሮችን እሰማለሁ፡፡ ነገር ግን በአምባገነንነትም፣ ልል በሆነ ሁኔታም በሁለቱም ሃገር ይፈርሳል፡፡ መንግስት ከሚገባው በላይ ኃይል እየተጠቀመ የሚሄድ ከሆነ ሃገር ሊፈርስ ይችላል፡፡ በዚያው ልክ እስካሁን የታዩ ዓይነት ልልነትና ክፍተቶችም ሃገር ሊያፈርሱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ማዕከላዊውን ሚዛን መፈለግ ያስፈልጋል:: መንግስት ህግ ያስከብር ሲባል፣ ህግ ያስከብር እንጂ ዲሞክራሲያዊ መብትን ይጨፍልቅ ማለት አይደለም፡፡ ከህግና ከስርአት የወጡ ኃይሎችን የማረም ግዴታ አለበት፡፡ እስከ ዛሬ ችላ ብሏቸው የመጡ ነገሮች በሂደት ጉልበት እያገኙ መጥተው ነው ለዚህ ችግር የተዳረግነው፡፡ ከዚህ በፊት አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ሲያጠነጥኑ የነበሩ ኃይሎች አሁን ወደ ክልል መጥተዋል፤ ነገ ደግሞ ማዕከላዊ መንግስቱ ጋ  ይመጣሉ፡፡ መንግስት ህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩትን ለማስፈፀም ቃለ መሃላ ፈፅሞ ነው የመጣው፡፡ ስለዚህ ቃለ መሃላውን ማስከበር አለበት፡፡ ወንጀለኛን ለህግ ማቅረብ፣ ከመስመር የወጣን ወደ መስመር ማስገባት ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ዜጎች የደህንነታቸውን ነገር  የሰጡት ለመንግስት ነው፤ መንግስት ደግሞ ይሄን ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡
ሌላው የመንግስት የጥበቃና ደህንነት ጉዳይ ነው፡፡ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንዴት ነው የሚጠበቁት? ምክንያቱም ህይወታቸው ሁልጊዜ ከስጋት ጋር ነው፤ አግባብ ያለው ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ እንዴት ነው እስከ ክልል መሪ ቢሮ ድረስ መሳሪያ ይዞ መግባት የሚቻለው? እንዴት ነው የሚጠበቁት? ይሄ  ለመንግስት ማንቂያ  ሆኖ በርካታ ስራ መሰራት አለበት፡፡
መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ መንግስት ምን ዓይነት እርምጃና ጥንቅቃቄ መውሰድ ይገባዋል?
አንደኛ፤እንደዚህ ዓይነት ቅራኔዎችን የሚያመጡ ችግሮችን በአግባቡ መርምሮና ተወያይቶ መፍትሄ መስጠት ይገባል፡፡ የማያዳግም መልስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ማህበረሰቡንም በዚህ ጉዳይ ማንቃት ይገባል፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ መንግስት የመንግስትነት ኃላፊነቱን ይወጣ፡፡ በህግ የተሰጠውን ስልጣን ይጠቀም፤ ግዴታውን ጠንቅቆ ይወጣ:: ሶስተኛው፤ አሁን ድርጅቱ ውስጥ ያለው ባህሪ ምንድን ነው? የሚለውን በአግባቡ ይመርምር፤ ከለውጡ በኋላ ድርጅቱ ያላግበሰበሰው ነገር የለም:: ከተለያየ አቅጣጫ የተለያየ ፍላጎት ይዞ የመጣ ሰው አግበስብሷል፡፡ እነዚህን ሰዎች በእርግጥስ ያውቃቸዋል ወይ? ለዚህ ነው ብዙ ጊዜ ከራሱ ከድርጅቱ ውስጥ የሚፈነዳ ነገር የሚፈጠረው፡፡ ስለዚህ ሃገር እየመራ እስከሆነ ድረስ ለሃገር ደህንነት ሲባል ራሱን በአግባቡ ይፈትሽ:: አራተኛ፤ አሁንም በተለያየ አካባቢ የየራሳቸውን አጀንዳ ይዘው መንግስትን ከህግ ውጪ ለማስገደድ የተዘጋጁ ኃይሎች አሉ፡፡ እናውቃቸዋለን፡፡ አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር መንግስትን “ዋ! እገሌን ነው የምጠራብህ” እያሉ የሚያስፈራሩ አሉ፡፡ በዚያ ላይ ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውሩ አለ፡፡ የታጠቁ ኃይሎችም አሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን ኃይሎች መስመር ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ ነገሩ ችላ ከተባለ፣ ነገ ከነገ ወዲያ መሳሪያ ታጥቆ መንግስትን የሚገዳደር የማፍያ ቡድን ሊፈጠር ይችላል፡፡ ይሄ የስርአት አልበኝነት ምልክት ነው፤ መታረም አለበት፡፡
አምስተኛ፤ በማህበራዊ ሚዲያ ሰዎችን ነጥለው እያወጡ የማንቋሸሽ፣ የማሳጣት ጉዳይ አለ፡፡ ይሄ በግልፅ ግለሰቦችን ለጥቃት ማጋለጥ ነው፡፡ አንድ ሰው ስራውን መስራት በማይችልበት ሁኔታ በጥላቻ ለጥቃት እንዲጋለጥ ማድረግ አደገኛ አካሄድ ነው:: ይሄን በስፋት እያየነው ነው፤ ይሄንንም መንግስት ስርአት ማስያዝ አለበት፡፡ ስድስተኛ፤ በህዝብና በመንግስት መካከል ጠንካራ ግንኙነት መፈጠር አለበት፡፡ አሁን ብዙ ጊዜ የቴሌቪዥን ውይይቶችን እንኳ ስንመለከት የመንግስትን ውክልና አናይም:: ሁሉም አንድን ወገን አጥቅቶ የሚመለስባቸው ናቸው፡፡ የመንግስት ሚና የታለ? ለሚል ሰው መልስ አይሰጡም፡፡ ስለዚህ በመንግስት በኩል የሚታየው አቅጣጫ፣ በውይይት መድረኮች ብዙም የለም:: ሚኒስትሮች፣ አመራሮች እየወጡ ማብራሪያ መስጠት፣ ጥያቄዎችን አቅጣጫ ማሳየትና ህዝቡ ሚዛናዊ መረጃ እንዲያገኝ ማድረግ አለባቸው:: አሁን እየሆነ ያለው በድንገት ከእንቅልፍ የመነሳትና የመደናበር ነገር ነው፡፡ ዜጎች በዚህ መሃል ደህንነታቸው እንዲጠበቅ  ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

____________

           “አሁንም ኢትዮጵያን ተስፋ ቢስ ሃገር አድርጌ አልቆጥርም”
               ዶ/ር አለማየሁ አረዳ


      ከሰሞኑ በአማራ ክልል አመራሮችና በፌደራል የመከላከያ ሰራዊት አዛዦች ላይ የደረሰው ጥቃት እንዴት ሊከሰት የቻለ  ይመስልዎታል? መንግስት ለዚህ ችግር የተጋለጠው በምን ምክንያት ነው  ብለው ያስባሉ?
በመጀመሪያ ይሄ ችግር ፈፅሞ ያልጠበቅሁት ነገር ነው፡፡ ለህዝብ ፍላጎትና ለውጥ መሳካት በየራሳቸው መንገድ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎች ናቸው የሞቱት:: ይሄ ክስተት በእጅጉ ያሳዝናል:: ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እመኛለሁ፡፡ እኔም በጣም አዝኛለሁ:: እንግዲህ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደርጓል ነው የተባለው፡፡ በእርግጥ መፈንቅለ መንግስት ነው? ሽብርተኝነት ነው? የሚለውን ማጥራት ያስፈልጋል፡፡ በክልሉ ባለስልጣናት ላይ የተፈጸመው፣ በጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ላይ ከተፈፀመው ጥቃት ጋር ተያያዥነት ያለው ከሆነ፣ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ላይ ቀውስ ለመፍጠር  የተቃጣ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ሁኔታው ግን ይከሰታል ተብሎ የሚጠበቅ አልነበረም፡፡ ማንኛውም ጉዳይ  ወደ ጠረጴዛ ይምጣ፤ እንወያያለን በሚባልበት ሰአት መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ መሞከር በራሱ እብደት ነው፡፡
ለአንድ አላማ፣ በአንድ አስተዳደር የሚሰሩ ሰዎች እንዴት እዚህ ደረጃ ደረሱ? ይሄ ለኔም ጥያቄ ነው፡፡ እንደሰማነው 178 ሰዎች በተጠርጣሪነት ተይዘዋል ተብሏል፡፡ ይሄ ማለት ኃይሉ በሚገባ የተደራጀ ነበር ማለት ነው፡፡ ይሄ ኃይል ሲደራጅ እንዴት አልታወቀም? በፀጥታ ክፍል ውስጥ አድመው መሪ ይዘው እዚህ ደረጃ እንዴት ደረሱ? አዴፓን በሚመሩትም ሆነ በሌሎች አመራሮች መካከል በአማራ ህዝብ ጥያቄ ጉዳይ ምንም ልዩነት የለንም ሲሉ ሰምተናቸዋል፡፡ ታዲያ ችግሩን ምን ፈጠረው? ድርጊቱ ታስቦ የተደረገ ነው፡፡ በጥንቃቄ ለማድረግ የተሞከረ ነገር ነው፡፡ ይሄ አንዴት ሊፈጠር ቻለ? መሰረታዊ ምክንያቱ ምንድን ነው? የሚለውን እንድንጠይቅ ግድ ይለናል፡፡ ያሉን መረጃዎች ብዙ ለመተንተን በቂ አይደሉም:: ነገር ግን ከምናስተውላቸው ተነስተን ለምን ይህ ችግር አጋጠመ? የሚለውን ከተመለከትን የሽግግር ጊዜውን ለመምራት ከህዝብ አደራ ተቀብያለሁ ያለው ኢህአዴግ ውስጥ ከብዙ ነገሮች አንፃር የውስጥ ልዩነት አለ፡፡ ለምሳሌ ህውሓት እና መሪዎቹ የሚሰጧቸው መግለጫዎችና ምግባሮች ስንመለከት በግንባሩ ውስጥ ጤናማ ግንኙነት የለም እንዴ? ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድደን ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ የአማራ ህዝብን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝና ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች መፈናቀልን፣ የቅማንት ችግርን፣ ከትግራይ ክልል ጋር ያለውን የቦታ ይገባኛል ጉዳይን፣ በአጠቃላይ አዴፓ የአማራን ህዝብ ጥቅም እያስከበረ ነው ወይስ እያስከበረ አይደለም የሚለውን በተመለከተ በአመራሩ ውስጥ ክርክር እንዳለ ይሰማል፡፡ እነዚህ ክርክሮች የፀጥታውን አካል ወደ አድማ ለውጦ፣ ክልሉን የሚመራውን ድርጅት አደጋ ላይ ጥሎት ይሆናል የሚል ግምት ነው ያለኝ:: በአጠቃላይ በኢህአዴግ ውስጥ ያለው ድርጅታዊ አለመግባባት፣ ድርጅቱ ወዴት ነው የሚሄደው? መድረሻው የት ነው? ለሚለው ጉዳይ በድርጅቱ ውስጥ ልዩነት እንዳለና እስካሁን ያልተፈታ ችግር መሆኑን ያሳየናል፡፡ ከሰሞኑ የተፈፀመው መገዳደልም ይህ ልዩነት መካረርን እየፈጠረ መሆኑን ነው የሚጠቁመው፡፡ በቀጣይ ምናልባት ከዚህ ተምረው የትግራይና የኦሮሚያ እንዲሁም  የደቡብ ክልል ፓርቲዎች በውስጣቸው ያሉትን ችግሮች በውይይት ሊፈቱት ይችላሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ አሁን ግን ኢህአዴግ በውስጡ ጤናማ የሆነ ድርጅት አይደለም፡፡ ይሄ ነው ለችግር እያጋለጠው ያለው፡፡
በክልል ደረጃ መፈንቅለ መንግስት ማድረግ ማለት ትርጉሙ ምንድን ነው? ይሄ ሙከራ ቢሳካ ኖሮስ ምን ሊፈጠር ይችል ነበር?
በአማራ ክልል የተሞከረውን ሁኔታ ካየነው፣ በመጀመሪያ ርዕሰ መስተዳደሩን የማስወገድ እርምጃ ነው የተወሰደው፡፡ ይሄ ተሳክቶ እርምጃ ወሳጆቹ የፈለጉትን ቢያገኙ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለው ለመገመትም አስቸጋሪ ነው፡፡ ምናልባት ሃገሪቱ በአለም ላይ ከሚከሰቱ ቀውሶች ራሷን በአንደኛው ውስጥ ልታገኘው ትችል ነበር፡፡ በሌላ በኩል፤ የእነ ጀነራል ሳዕረ መገደል እቅድ ሁለት ይመስለኛል:: እቅድ ሁለት ማለት ሙከራው በክልል ደረጃ እንደሚከሽፍ ሲያውቁ፣ በፌደራል ደረጃ ቢያንስ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙን በማስወገድ አጠቃላይ ሽብር ለመፍጠር አስበው ሊሆን ይችላል፡፡ አጠቃላይ ነውጥ የመፍጠር እቅድ አካል ይመስለኛል፡፡ ዋና ኢታማዦር ሹሙን መግደል ምናልባት ሰራዊቱን በብሔር ለመከፋፈል ቀላል ይሆናል ተብሎ የታሰበ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ የአማራ ክልል ሙከራ ሲከሽፍባቸው፣ በሁለተኛው እቅድ አጠቃላይ ሃገሪቱን ወደ ነውጥና ግርግር በማስገባት፣ በግርግሩ የሚፈልጉትን ለማግኘት የወጠኑ ይመስላል፡፡ ማወቅ ያለብን ምናልባት እንደተባለው መፈንቅለ መንግስቱን የመሩት ጀነራል በክልል ብቻ መፈንቅለ መንግስቱን አድርገው፣ በፌደራል ደረጃ  ዝም ይላሉ ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለሱም የራሱ እቅድ የነበረው ሊሆን ይችላል፡፡ እንግዲህ በፌደራል ደረጃ ያቀዱት ምን ነበር? ሰውየው ይሄን ሲያደርጉ ከእነማን ጋር ነበሩ? የሚለው ሁሉ ወደፊት በዝርዝር የምንሰማው  ይሆናል፡፡ ምናልባት አብሯቸው የነበረ ነገር ግን ያደፈጠና ያጎነበሰ ቡድን ሊኖርም ይችላል፡፡ አሁንስ አስተማማኝ ሁኔታ ላይ ነው ወይ ያለነው? የሚለውን መንግስት በጥልቀት ሊመረምር ይገባል፡፡
ይህ ክስተት ምናልባት መንግስትን ወደ አምባገነንነት ይቀይረው ይሆን የሚል ስጋት ያላቸው ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎስ?
አይመስለኝም፡፡ ያ ሁሉ የዲሞክራሲ ጅማሮ ተቀልብሶ ወደ አምባገነንነት፣ ዲሞክራሲን ወደ ማፈን ይሄዳል ለማለት ያስቸግራል፡፡ እነዚህ ሰዎችም ዋጋ የከፈሉት ለህዝብ ዲሞክራሲ ነው ካልን፣ አምባገነንነትን ምን ያመጣዋል? ነገር ግን መንግስትን ወደ ከፍተኛ ጥንቃቄና ህግን የማስከበር እንቅስቃሴ የሚገፋው ይሆናል፡፡ አሁንም የኔ ጥያቄ ግን የፌደራል ደህንነት፣ ይሄ ሲፈፀም ምን ሲሰራ ነበር? የክልሎች ጉዳይ አይመለከተውም? 178 ሰዎች ይህን ሁሉ እቅድ ሲያወጡ ምን እየሰራ ነበር? ይሄ ራሱን የቻለ ግምገማ ያስፈልገዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ይህ አይነቱ ሙከራ የመሳካት እድሉ የመነመነ መሆኑም የታየበት አጋጣሚ ነው፡፡ መንግስት ግን ምንም የህግ እርምጃ ሳይወስድ በስብከት ብቻ ሃገር ይመራል ማለት አይደለም፡፡ መልካም ማሰብ ጥሩ ነው፤ ነገር ግን አፈንጋጮችንም መቅጣት ያስፈልጋል፡፡ ንፁሃን አገልጋዮች፤ ያውም ስለ ህዝብ እየመከሩ ባሉበት የሚረሸኑ ከሆነ፣ ይሄን ሽግግር የሚመሩ አካላት፣ እንዴት ነው እየመራን ያለነው ብለው ራሳቸውን  መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡  
አሁን የተፈጠረው ክስተት በመንግስት ላይ ምን ዓይነት እክል ሊፈጥር ይችላል?
መተማመንን ይቀንሳል፡፡ ከጓዳቸው ጋር ሃሳባቸውን የሚያንሸራሽሩ ልባቸውን ቆጠብ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ከውስጡ ይሄን ጥርጣሬ የሚያጠፋ እርምጃ መውሰድ አለበት:: አንዳንዶች እንደሚያስቡት፤ አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያን ልዩ ችግር ውስጥ የገባች ተስፋ ቢስ ሃገር አድርጌ አልቆጥራትም፡፡ አሁንም ቢሆን የተጀመረው ሂደት ይሳካል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም ረጋ ብለው ድርጅቱ እኔ በምፈልገው መጠን እየሄደ ነው ወይስ ወደ ኋላ ቀርቷል የሚለውን መመርመር አለባቸው፡፡  
መንግስት ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?
ኢህአዴግ ሃገር እየመራ ከሆነ መጀመርያ አንድነቱን ያጠናክር፡፡ በፀጥታ ኃይሉና በመንግስት መካከል ያለው ተግባቦት ይፈተሽ፡፡ ኢህአዴግ ሃገሪቱን ወዴት ነው የሚወስዳት የሚለው ላይ ግልፅ ነገር ያስቀምጥ፡፡ ዶ/ር ዐቢይ በአሁኑ ሰዓት በየአካባቢው እሳት የማጥፋት ስራ እየሰሩ ነው ያሉት፡፡ የእሳቸው ሚና እንዳለ ሆኖ፣ እኛ አሁን ይሄን ጥረት የምንፈልገው ከኢህአዴግ ከራሱ ነው፡፡ በተቋም ደረጃ ነው ችግሮች እንዲፈቱ የምንፈልገው:: ህዝቡ በዚህ ጉዳይ እርግጠኛ መሆን ይሻል፡፡ ሌላው ኢህአዴግ ሽግግሩ ባይሳካለት እንኳ ህዝቡን፣ ኢትዮጵያን መጠበቅ የሚችል መከላከያ ሰራዊት ገንብተናል ወይ? መከላከያ ሰራዊቱ የኢትዮጵያን ህዝብና ኢትዮጵያን የመጠበቅ ልዩ ኃላፊነት አለበት:: የአንድ ፓርቲ ሰዎች የሚገዳደሉ ከሆነ ማን ነው ኢትዮጵያን የሚጠብቃት? የመከላከያው ሚና በዚህ በኩል ግልፅ ሆኖ መታየት አለበት፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ በብሔር ወይም በቡድን እንደማይከፋፈል፣ ቁም ነገሩ ኢትዮጵያ እንደሆነች ደግሞ ደጋግሞ ሊያረጋግጥልን ይገባል፡፡
ትናንት ለአንድ ህዝብ ጥቅም በአንድ አዳራሽ ሲመክሩ የነበሩ ሰዎች፣ ከመካከላቸው አንዱ ተነስቶ፣ ጭፍራዎቹን ሰብስቦ፣ እነዚያኑ ጓዶቹን የሚገድል ከሆነ፣ ነገርየው የልጆች እቃ እቃ ጨዋታ ነው የሚሆነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ጠላት አይደሉም፣ አልታጠቁም፣ ቢሮአቸው ተቀምጠው እየተወያዩ ነው የተገደሉት፤ ይሄ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ይሄ ዓይነቱ እኩይ ተግባር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መገታት አለበት፡፡ ሃገራችን እንደምትኖር እርግጠኛ መሆን አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ በቀጣይ እንደ ህዝብ ዋስትና የሚሰጡን ተግባራት መሰራት አለባቸው፡፡  

Read 1489 times