Tuesday, 02 July 2019 12:18

ብሩንዲ በመንግስት “አርቆ አሳቢዎች” ዱላ እና በ“ምርጫ ቀረጥ” ተማርራለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)


     ለ13 አመታት የዘለቀውን የብሩንዲ ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ግጭት ለማቆም በሚል እ.ኤ.አ በ2005 የአሩሻው ስምምነት መደረጉን ተከትሎ ስልጣን የያዙት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ፣ በ2010 በተካሄደውና ተቃዋሚዎች ባልተሳተፉበት ምርጫም አሸንፈው ዘመነ ስልጣናቸውን አራዘሙ፡፡
ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ለሁለት የስልጣን ዘመናት አገሪቱን የመሩት ፕሬዚዳንቱ በ2015 ላይ ህገ መንግስቱን በማሻሻል ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን በይፋ ማስታወቃቸውን ተከትሎ፣ በአገሪቱ በተቀሰቀሰው የከፋ ግጭትና ብጥብጥ 1 ሺህ ያህል ሰዎች ለህልፈተ ህይወት ሲሰደዱ ሌሎች 400 ያህል ዜጎችም አገራቸውን ጥለው ተሰድደው ነበር፡፡
ህዝብን ለደም መፋሰስ ዳርገው የያዙትን የስልጣን ዘመናቸውን ሊያጠናቅቁ 2 አመታት ብቻ የቀራቸው የብሩንዲው ፕሬዚደንት ፔሪ ኑኩሩንዚዛ ግን፣ አሁንም ስልጣናቸውን ለማራዘም ፈለጉ፡፡ ይህንን ፍላጎታቸውን እውን ለማድረግና በመንበራቸው ላይ ለመቆየት ግን፣ በአገሪቱ ህገ መንግስት ላይ ማሻሻያዎችን ማድረግ ነበረባቸው:: ኑኩሪንዚዛ የአገሪቱን መሪ የስልጣን ዘመን ገደብ የሚወስነውን የህገ- መንግስት አንቀጽ ለማሻሻል ደፋ ቀና ማለት ጀመሩ፡፡ ባለፈው አመት መጋቢት ወር ላይ ለሁለት ተጨማሪ የስልጣን ዘመናት በመንበራቸው ላይ በሚያቆያቸው የህገ መንግስት ማሻሻያ ላይ ህዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ሁኔታዎችን አመቻቹና ደጋፊዎቻቸው ውሳኔውን እንዲደግፉት መቀስቀስ ጀመሩ፡፡
የአገሪቱ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፕሬዚዳንቱ እድሜ ልካቸውን በስልጣን ላይ የመቆየት ጽኑ ፍላጎት ለማሳካት እስከቻሉ ድረስ አገሪቱ ወደ እልቂትና የእርስ በእርስ ግጭት ብትገባ ግድ የሌላቸው የስልጣን ጥመኛ ናቸው ሲሉ አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን አሰሙ፡፡
ባለፈው አመት ግንቦት ወር ላይ ብሩንዲያውያን የአገሪቱን መሪ አንድ የስልጣን ዘመን ከአምስት አመት ወደ ሰባት አመት ከፍ ለማድረግና ፔሪ ንኩሩንዚዛን ለተጨማሪ 14 አመታት በመንበራቸው ላይ ለማቆየት የታሰበ ነው በሚል ተቃውሞ በቀረበበት የህገ መንግስት ማሻሻያ ላይ ወደውም ተገደውም የህዝበ ውሳኔ ድምጽ ሰጡ፡፡
በተቃውሞ ታጅቦ የህዝበ ውሳኔ ድምጽ የተሰጠበት የህገመንግስት ማሻሻያ፣ ድምጽ ከሰጡት 4.7 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ ከ73 በመቶ በላይ ድጋፍ ማግኘቱ ተነገረ፡፡ የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የድምጽ አሰጣጡ ተጭበርብሯል ሲሉ ውጤቱን በአደባባይ ውድቅ አደረጉት፤ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውም ውጤቱ ይሰረዝላቸው ዘንድ አቤቱታቸውን አሰሙ፡፡
የመንግስት አካላት በድምጽ ሰጪዎች ላይ ማስፈራሪያና ዛቻ ያደረጉበት ስለሆነ ውጤቱ ይሰረዝልን ሲሉ ተቃዋሚዎች ያቀረቡለትን አቤቱታ የመረመረው የአገሪቱ የህገ-መንግስታዊ ጉዳዮች ፍርድ ቤት፣ የተባለው ድርጊት መፈጸሙን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ባለማግኘቴ የድምጽ ውጤቱን ተቀብዬ አጽድቄዋለሁ ሲል ውሳኔውን አሳወቀ፡፡
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የአገሪቱን መሪ አንድ የስልጣን ዘመን ከአምስት አመት ወደ ሰባት አመት ከፍ ያደረገ ሲሆን፣ የስልጣን ዘመናቸው ከሁለት አመታት በኋላ የሚያበቃው የአገሪቱን መሪ ፔሪ ንኩሩንዚዛን ለተጨማሪ ሁለት የስልጣን ዘመናት ወይም 14 አመታት በገዢነታቸው የሚያስቀጥል ነበር፡፡
ለተጨማሪ 14 አመታት በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚስችላቸውን የህገ-መንግስት ማሻሻያ አስጸድቀዋል በሚል ከተቃዋሚዎችና ከአለማቀፍ ተንታኞች ውግዘት ሲወርድባቸውና በስልጣን ጥመኝነት ሲታሙ የከረሙት የብሩንዲው ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ፣ ባለፈው አመት ሰኔ ወር ላይ ደግሞ በ2020 ስልጣን እንደሚለቁ ድንገት ለህዝባቸው በአደባባይ ቃል ገቡ፡፡
በ2020 የስልጣን ዘመናቸውን የሚያጠናቅቁት ፔሪ ንኩሩንዚዛ፣ ብዙዎች እንደሚያሟቸው በስልጣን ላይ የመቆየት ፍላጎት እንደሌላቸውና በቀጣዩ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ እንደማይወዳደሩ በጋዜጣዊ መግለጫ ለህዝባቸው አረጋገጡ፡፡
ህዝቡ ሰውዬው በቀጣዩ ምርጫ አይወዳደርም ብሎ ለማመን ተቸግሮም ቢሆን ጥቂት እንደዘለቀ ግን፣ ከዚሁ ጣጠኛ ምርጫ ጋር በተያያዘ አሳር መከራውን ማየት መጀመሩን ዘ ኢኮኖሚስት ከቀናት በፊት ባወጣው ዘገባ አስታውቋል፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እየፈጸመ ነው በሚል በርካታ የገንዘብ ለጋሾች ፊታቸውን ያዞሩበትና ከፍተኛ የገዘንብ እጥረት የገጠመው የንኩሩንዚዛ መንግስት፣ ቀጣዩን የ2020 ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል በቂ ገንዘብ በማጣቱ ባልተለመደ ሁኔታ በዜጎቹ ላይ የምርጫ ቀረጥ መጣሉንና ይህም ዜጎችን ክፉኛ እያማረረ እንደሚገኝ ነው ዘገባው የሚያትተው፡፡
ዘ ኢኮኖሚስት እንደሚለው የንኩሩንዚዛ መንግስት የምርጫ ቀረጥ በሚል በአገሪቱ ድሃ ህዝብ ላይ የጣለው ቀረጥ እያንዳንዱ ቤተሰብ በአመት 2 ሺህ የብሩንዲ ፍራንክ ለመንግስት እንዲከፍል የሚያስገድድ ነው፡፡ በመላ አገሪቱ ቤት ለቤት እየዞረ የምርጫ ቀረጡን ከዜጎች የመሰብሰቡን ሃላፊነት ከፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ የተረከቡት ደግሞ፣ “አርቆ አሳቢዎች” በሚል የወል ቅጽል ስም የሚጠሩት የገዢው ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ አባላት ናቸው፡፡
ዘገባው አንደሚለው ንኩሩንዚዛ የምርጫ ቀረጥን ከጣሉባት ዕለት አንስቶ “አርቆ አሳቢዎች” ወፈፍራም ዱላቸውን ጨብጠው ነጋ ጠባ በየመንደሩ እየገቡ ቀረጥ ክፈል በሚል ህዝቡን በማማረር ላይ ናቸው፡፡
“የምርጫ ቀረጥ የሚሉት ነገር “አርቆ አሳቢዎች” ለሚባሉት ጎረምሶች ህዝቡን የማስጨነቅና የመበዝበዝ ፍጹም ስልጣን አጎናጽፈዋቿል:: መንግስት ዱላ ስታጥቆ ያሰማራቸው እነዚህ አምባገነኖች በቀረጥ ስም ነጋ ጠባ ህዝቡን እየበዘበዙ ነው የሚገኙት” ይላሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዎች ባልደረባ የሆኑት ሉዊስ ሙጂ፡፡
“አርቆ አሳቢዎች” ከህዝቡ የሚሰበስቡትን የምርጫ ቀረጥ በትክክል ወደ መንግስት ካዘና ማስገባታቸውን የሚቆጣጠራቸው አካል የለም፡፡ መንግስት የሰጣቸውን የቀረጥ ሰብሳቢነት ስልጣን በመጠቀም ድሃ የአገሪቱ ዜጎችን ነጋ ጠባ እያስገደዱ ገንዘብ መዝረፋቸውንና ኪሳቸውን መሙላታቸውን ተያይዘውታል፡፡ እነዚህ ህጋዊ ዘራፊዎች ከመንገድ ዳር ተጎልተው አላፊ አግዳሚውን እያስቆሙ፣ የምርጫ ቀረጥ የከፈለበትን ማስረጃ እንዲያቀርብ ማስገደድና ያላቀረበላቸውንም ክፉኛ መደብደብ ከያዙ አመታት ተቆጥረዋል፡፡
በንኩሩንዚዛ መንግስት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና በ“አርቆ አሳቢዎች” ዝርፊያ የተማረሩ ከ350 ሺህ በላይ የብሩንዲ ዜጎች አገራቸውን ጥለው ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መሰደዳቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በመሰል ሁኔታ አገራቸውን ጥለው ከተሰደዱት ብሩንዲያውያን አንዷ በስደት ላይ ሆነውም በ“አርቆ አሳቢዎች” ይደርስባቸው የነበረውን መከራ በምሬት ነው የሚያስታውሱት፡፡
“በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ “አርቆ አሳቢዎች” ሶስት ጊዜ ወደ ቤቴ ይመጡ ነበር፡፡ በድቅድቅ ጨለማ ድንገት ከተፍ ይሉና፣ የቤቴን በር በርግደው ይገባሉ:: “የምርጫ ቀረጥሽን አሁኑኑ ክፈይ፤ እምቢ ካልሽ እንገድልሻለን!” ብለው ዱላቸውን ጨብጠው ያስፈራሩኛል፡፡” ትላለች ይህቺው ብሩንዲያዊት እናት ይደርስባት የነበረውን መከራ ስታስታውስ፡፡
ሴትዬዋ አገሯን ጥላ ከመሰደዷ በፊት “አርቆ አሳቢዎች” አንድ ምሽት ወደቤቷ መጥተው ያደረጉትን ነገር አሁንም በምሬት ነው የምታስታውሰው፡፡
“በአፋጣኝ የምርጫ ቀረጥ ካልከፈልን እንደሚገድሉን ዛቱብን፡፡ ሽራፊ ሳንቲም እንደሌለንና ልንከፍላቸው እንደማንችል ነገርናቸው፡፡ ባለቤቴን መሬት ላይ ጥለው ገንዘብ እንዲሰጣቸው አስገደዱት:: ምንም ገንዘብ እንደሌለው ቁርጡን ነገራቸው፡፡ ይሄኔ በንዴት ቱግ ብለው ህጻናት ልጆቻችንን ሳይቀር ሁላችንንም በጭካኔ ደበደቡን፡፡ በስተመጨረሻም ባለቤቴን እየጎተቱ ይዘውት ወጡና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ተሰወሩ፡፡ ከዚያ ጊዜ አንስቶ ባለቤቴን አይቼው አላውቅም፤ ይሙት ይዳን የማውቀው ነገር የለም!” ትላለች ሴትዬዋ እንባ እየተናነቃት፡፡


Read 1486 times