Tuesday, 02 July 2019 12:12

አንዲት ወፍራም ሴት እንዴት ማርገዝ ትችላለች?

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)


     አንዲት ሴት ጽንስ እንዳትቋጥር ከሚያደርጓት ምክንያቶች መካከል ከመጠን ያለፈ ውፍረት አንዱ ነው፡፡ በሚሺጌን ዩኒቨርሲቲ የተደረገው ጥናት እንደሚያመላክተው የቦዲ ማስ ኢንዴክስ (Body Mass Index)  ልኬታቸው 40 የሆነ ሴቶች መጠነኛ የሰውነት ክብደት ኖሯቸው የቦዲ ማስ ኢንዴክሳቸው ከ18.5 እስከ 24.9 ከሚለካ ሴቶች ጋር ሲነጻጸሩ የመጸነስ እድላቸው 35 በመቶ ያነሰ ነው፡፡ መውለድን በተመለከተ የላቀ አስተዋጽኦ በሚያደርጉ ረቂቅ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ክትትል ሲደረግላቸው የቆዩ 50 ሺህ ሴቶች የጥናቱ ግብአት በመሆን ተሳትፈዋል፡፡ በግኝቱም ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው ሴቶች መጸነስ እንደሚችሉና የእርግዝና ጊዜያቸውም በውፍረታቸው ምክንያት ብቻ እጅግ የከፋ ይሆናል ብሎ መደምደም እንደማይቻል ያሳያል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ የተቀመጠው መጠነኛ የክብደት መጠን ያላቸው ነገር ግን ከእርግዝና ጋር ተያይዞ ለተለያዩ የጤና ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች መኖራቸው ነው፡፡
ቢሆንም ግን አንዲት ሴት በሚኖሯት የእርግዝና ጊዜያት ከመጸነሷ ጋር ተያይዘው የሚመጡና ጥንቃቄ የሚያሻቸው የጤና መስተጓጎሎች ሊኖሯት ይችላሉ፡፡ በመሆኑም እነዚህ ሁኔታዎች ላይ ውፍረት ከታከለበት ሁኔታዎቹ እንዲባባሱ የራሱ የሆነ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ልብ ማለት እንደሚገባ የሕክምና ባለሙያዎች አበክረው ያሳስባሉ፡፡  
አንዲት ሴት መጠነኛ የሰውነት ክብደት ኖሯት ውስብስብ የእርግዝና ሂደት ሊያጋጥትማት እንደሚችል ሁሉ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላትም ሴት ለውስብስብ የእርግዝና ጤና መታወክ ተጋላጭ ትሆናለች፡፡ ቢሆንም ግን ውፍረት ያላቸው ሴቶች በውፍረታቸው አማካይነት ጽንስ መቋጠር አለመቻላቸው፣ መጠነኛ የሰውነት ውፍረት ካላቸው ሴቶች የጎላ በመሆኑ ወፍራም ሴቶች ከመጸነሳቸው በፊት ውፍረታቸውን በመጠኑም ቢሆን መቀነስ እንዳለባቸው አጥብቆ ይመከራል፡፡ ይህ መሆን ያለበት ውፍረቱ ገና ከመጀመሪያው የሴቶቹን የመጸነስ እድል በእጅጉ ስለሚቀንሰው ነው፡፡
ውፍረትን ቀንሶ ለመገኘት ግን ተፈጥሯዊ የሆነ የሰውነትን አሰራር በሚያዛባ መልኩ የአመጋገብ ሥርአትን መቀየር እንደማይገባ ይገለጻል፡፡ ይህ ሆኖ ቢገኝ ግን ሰውነት ላይ ያልነበረ አካላዊ ጉዳት ሊደርስ ስለሚችል፣ ጎጂ በሆነ መልኩ የአመጋገብ ስርአትን መቀየርና መከተል ትክክል እንዳልሆነ ባለሙያዎች ያሳስባሉ፡፡ እ.አ.አ. በ2017 የሮተርዳም የህክምና ማእከል ዩኒቨርሲቲ ኔዘርላንድ ውስጥ ባደረገው ጥናት ላይ እንደሚያሳው፣ የቦዲ ማስ ኢንዴክሳቸው ከ29 በላይ የሆነ ሴቶች የመጸነስ እድላቸው በአምስት በመቶ የቀነሰ ነው፡፡ በመሆኑም ቦዲ ማስ ኢንዴክሳቸው ከዚያ በላይ ሆኑ ሴቶች ከመጸነሳቸው በፊት እስከ አምስት ኪሎ ድረስ እንኳን ቢቀንሱ ለማርገዛቸው አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ሂደት ግን ፍጹም ጤናማ ሊሆን እንደሚገባውም ተገልጿል፡፡
ከመጠን በላይ የወፈሩ ሴቶች ለማርገዝ እንዲችሉ ሌላው ጠቃሚ መንገድ ደግሞ የወር አበባ ኡደታቸውን በመከታተል እንዲያረግዙ መንገዱን ማመቻችት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ቢጠቀሙ ይበልጥ ውጤታማ የሆኑት ሴቶች እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆነና፣ ያልተዛባ የወር አበባ ኡደት ያላቸው ሴቶች እንደሆኑ የአሜሪካ የእርግዝና ማህበር (American Pregnancy Association) ያብራራል፡፡ አንዲት ሴት ማህጸኗ ለእርግዝና እንደተዘጋጀ ለማወቅ ከሚረዱ ዘዴዎች መካከል ከማህጸን የሚወጡ ፈሳሾችን መለየት ነው፡፡ ይህ ዘዴ የሚሠራው ግን ያልተዛባ የወር አበባ ኡደት ላላቸው ሴቶች ብቻ በመሆኑ በተቃራኒው የወር አበባቸው ተዛብቶ የሚመጣባቸው ሴቶች ግን ለማርገዝ የህክምና ባለሙያ እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ማህበሩ ያስረዳል፡፡         
አንዲት ሴት የወር አበባ ኡደቷን እየተከታተለች ለማርገዝ የምታደርገው ጥረት በተከታታይ ስድስት ወራት ውስጥ ውጤታማ መሆን ካልቻለ፣ ተጨማሪ ምርመራና የህክምና እርዳታ ስለሚያስፈልጋት የህክምና ባለሙያ ማነጋገር ይኖርባታል፡፡ የደምና ሌሎች ምርመራዎች ከተደረጉላት በኋላ መጸነስ ያልቻለችባቸውን ምክንያቶች በማወቅና መፍትሔ በመስጠት፣ በቀጣይ በምን አይነት መልኩ ማርገዝ ትችላለች ለሚለው ጥያቄ ባለሙያዎቹ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡   
ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው ሴቶች ለማርገዝ እንዳይችሉ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ የሆነው አንዱ ጉዳይ፣ በሳይንሳዊው አጠራር ፖሊሲስቲክ ኦቫሪያን ሲንድረም (Polycystic Ovarian Syndrome) ተብሎ የሚጠራው በሽታ ነው፡፡ የዚህ በሽታ መገለጫዎች ከፍተኛ የሆነ የወንድ ሆርሞን በሴቷ ውስጥ መኖር፣ የወር አበባ አለመኖርና ትክክል ያለሆነ/ያልተለመደ የኢንሱሊን ምላሽ በሰውነቷ ውስጥ መኖር ናቸው፡፡ የዚህ በሽታ ተጠቂ የሆኑ ሴቶች አካላቸው ላይ ከሌሎች ሴቶች በተለየ ሁኔታ ጸጉር/ጺም የሚኖራቸው ሲሆን፣ የሰውነታቸው የክብደት መጠንም ከፍተኛ የሆነ ነው፡፡ በማህጸናቸውም የሚገኙት እንቁላሎች ጊዜያቸውን ጠብቀው እንደማይኳርቱ በሳይንስ የተደገፉ ማስረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይሁንና ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት የህክምና ባለሙያዎች እንዲህ ያሉ ሴቶች እነዲጸንሱ የህክምና ዘዴዎችን በመጠቀም መርዳት የሚችሉ ሲሆን፣ ሰውነታቸው ተገቢ ባልሆነ መልኩ አዛብቶ የሚጠቀመውንም የኢንሱሊን መጠን በመድሃኒት እንዲስተካካል ማድረግ ይችላሉ፡፡   
በተጨማሪም ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላት ሴት እንድታረግዝ ከህክምና ባለሙያች የታዘዙላትን መድሀኒቶች በተገቢው መንገድ የምትወስድ ከሆነ የማርገዘ እድሏ ከፍ ያለ እንደሚሆን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የወር አበባ ኡደት የተስተካከለ እንዲሆን የሚታዘዙትን መድሃኒቶች ባግባቡ የምትወስድ ሴት የማርገዝ እድሏ በሰፊው የጨመረ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ የቺካጎው አድቫንስድ ፈርቲሊቲ ሴንተር (Advanced Fertility Center of Chicago) ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ የአላስፈላጊ ውፍረት መኖር በሴቷ ሰውነት ውስጥ ያለውን የኤስትሮጂንን መጠን ይበልጥ እንዲጨምር የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ይህ በመሆኑ ደግሞ የሴቷ ሰውነት በውስጡ የያዘው የኤስትሮጂን መጠን ከመደበኛው መጠን ከፍ ያለ እንደሆነ እንዲያስብ ስለሚያደርገው የሴቷ ማህጸን እንቁላሎቹን በተገቢው መንገድ እንዳያዘጋጅ ያግደዋል፡፡ በመሆኑም የህክምና ባለሙያዎች አንዲት ሴት ከእርግዝና ሊያግዳት የሚችለውን አላስፈላጊ የኤስትሮጂን መጠንን በመድሀኒት ኃይል እንዲቀንስ ማድረግ የሚችሉ በመሆኑ ችግሩ መፍትሔ እንዳለው ማወቅ ጠቃሚ ይሆናል፡፡  
ከመጠን ያለፈ ክብደት ያላቸው ሴቶች ጸንሰውና የእርግዝና ጊዜያቸውን አጠናቀው መውለድ የሚችሉባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ቢሆንም ግን ባካባቢያቸው ያሉ ሰዎች የሚሰጧቸው አስተያየቶች የስነ-ልቦና ተጽእኖ እንደሚያሳድርባቸው በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ወፍራም ሴቶች እርግዝናቸው የአንድ ልጅ ብቻ ሆኖ ‹‹ያረገዝሽው መንታ ነው?›› ተብሎ መጠየቃቸው እንደማያስደስታቸው በጥናቶቹ ላይ ተጠቁሟል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች የሚነሱት በተደጋጋሚና እርግዝናው ገፍቶ መታየት ከጀመረበት ወር አንስቶ እስከመውለጃቸው ድረስ በመሆኑ ጥያቄው ስነልቦናቸውን እንደሚጎዳው ይናገራሉ፡፡  
በአጠቃላይም በተገቢው ጊዜ የማይቋረጥ የቅድመ ወሊድ ክትትል ማድረግ የእርግዝናን ጤናማነትን አሊያም ተያያዥ ችግሮችን ለማወቅና ለመከታተል የሚረዳ ቁልፍ መንገድ ነው፡፡ ተከታታይ የሆነ የቅድመ ወሊድ ክትትል ማድረግ የእናትየዋንም ሆነ የጽንሱን ጤንነት ለመከታተል ይረዳል፡፡ በእነዚህ የክትትል ጊዜያቶች ውስጥ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላትም ሆነ ተመጣጣኝ የሰውነት ክብደት ያላት ነፍሰጡር የሚሰማትን ማንኛውንም ያልተመቸ ስሜት ለሐኪሟ መንገር አለባት፡፡ ይህን ማድረጓ ያለችበት ሁኔታ ወደተባባሰ የጤና ችግር እንዳይቀየር ታላቅ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ነው፡፡
ጤናማ የሆነ የአመጋገብ ስርአትን መከተል፣ አካላዊ እንቅስቃሴን ማድረግ፣ ጤና ላይ ችግር ከሚፈጥሩ ጎጂ ንጥረ ነገሮች (ሲጋር፣ አልኮል መጠጥ፣ አደንዛዥና አነቃቂ ዕጾች) እራስን ማቀብ ጤናማ የሆነ እርግዝና እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ኖሮ እርግዝና ቢጨመርና ከላይ የተዘረዘሩትን አለማድረግና ለጎጂ ንጥረ ነገሮች እራስን ማጋለጥ፣ ከባድ  የጤና መቃወስ ችግር ውስጥ ይከታል፡፡            

Read 9583 times