Tuesday, 02 July 2019 11:56

የሰሞኑ ዱብ ዕዳ!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(2 votes)


     “--ጀነራሉ የተወሰኑትን አግተው በሌሎች ላይ በህይወታቸው ፈርደው፣ ያሰቡት ተሳክቶ፣ የክልሉን መስተዳደር መያዝ ቢችሉ ኖሮ፣ ክልሉን ምን ያደርጉት ነበር? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው፡፡ መልሱ ግን “ምንም” ከሚለው ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡--”

     ሕወሓት ኢሕአዴግ ግንቦት 1983 ዓ.ም አዲስ አበባ ገባ፡፡ ሰኔ ሃያ የሽግግር መንግሥት መሠረተ፡፡ ሰማኒያ ሰባት አባላት ያሉት የተወካዮች ምክር ቤት ተቋቋመ፡፡ አርባውን ድምፅ ሕወሓት፣ ብአዴን፣ ኦሕዴድና ኢዲመን (የኢትዮጵያ ዲሞክራት መኮንኖች ንቅናቄ) በሚላቸው ድርጅቶች ስም ወሰደው፡፡ ኦነግ አስራ ሁለት መቀመጫ አገኘ፡፡ ሁለት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለት ለኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር ሰጥቶ ሌላውን ለሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች አከፋፈለው፡፡ በዚህ የሽግግር ወቅት የአማራው ብሔረሰብ ምንም ውክልና ሳያገኝ ቀረ፡፡
በ1984 ዓ.ም የመላ አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ተመሰረተ፡፡ ሕወሓት ኦነግን ለመፈታተን ኦሕዴድን እንደመሰረተ ሁሉ፣ አማራን ለማዳከም ኅብረብሔራዊ ድርጅት የነበረውን ኢሕዲንን በአንድ ለሊት የአማራ ተጠሪ አድርጎት አረፈ፡፡ በዚሁ ዓመት መጀመሪያ ላይ በባሕር ዳር “የጭቁን አማራ ጉባኤ” ተካሄደ፡፡ አማራው አንድ እንዳይሆንና በአንድነት ቆሞ የሚመጣበትን ጥቃት እንዳይከላከል፣ በጨቋኝና ተጨቋኝ ተከፋፈለ:: ከአማራ ክልል ውጪ ያለው አማራ በጨቋኝነት ተፈረጀ፡፡ ሕወሓት ኢህአዴግ በትጥቅ ትግል አሸንፎ መንግሥት የያዘ ኃይል ቢሆንም፣ በትግሬ፣ በኦሮሞ፣ በወላይታ፣ በሲዳማ ወዘተ በቀደመው ጊዜ በየአካባቢው የራሳቸው ጦር የነበራቸው ባላባቶች ቢኖሩም፣ “ነፍጠኛ” የሚለው ቃል ለአማራው ብቻ እንዲሰጥም ተደረገ:: ነፍጠኛ ማለት አማራ፣ አማራ ማለት ነፍጠኛ ሆነ፡፡
አማራን ነፍጠኛና ትምክህተኛ በማድረግ በመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በራዲዮና በቴሌቪዥን ሰፊ ቅስቀሳ ተካሄደ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም የሁሉም ብሔረሰቦች ጠላት አማራ፣ ሁሉም ብሔረሰቦች የአማራ ጠላቶች ሆኑ፡፡ አንዱ የአማራ ብሔረሰብ ከሰማኒያ በላይ ከሚሆኑት ብሔረሰቦች መሀል ኢላማ ሆኖ ቆመ፡፡ መገፋት፣ መገረፍ መደብደብ፣ ንብረት መቀማትና መገደል እጣ ፈንታው ሆነ፡፡ ለመገረፍና ለፍዳ የሚዘጋጀው አማራ በሙሉ የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት አባል ወይም ደጋፊ የሚል የክስ ሰሌዳ ይለጠፍለታል፡፡ የመላ አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) የደሴ ኮሚቴ ለማደራጀት ወደ ቦታው በሄዱበት ወቅት ከስሙ በስተቀር መአሕድ የሚባል ድርጅት የማያውቁ፣ በመአሕድ ስም ግን ሶስት ጊዜ ተይዘው ተደብድበው የተፈቱ ሰው ማግኘቴን አስታውሳለሁ፡፡
ሕወሓት ኢሕአዴግ፤ ሕገ መንግሥት አርቅቆና አፅድቆ የሽግግር መንግሥቱን ተክቶ ሥልጣን በእጁ ሲያስገባ፣ አማራው አንዳችም ሚና እንዳልነበረው ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ አማራ ባልሆኑ፣ ለአማራ ሕዝብ የሚቆረቆር መንፈስ በሌላቸው፣ እንዲያውም አማራን ለማዳከምና ለማጥፋት ታጥቀው በሚሰሩ ሰዎች አመራሩ የተያዘው ብአዴን፤ በክልሉና ከክልሉ ውጪ በሚኖረው አማራ ላይ የግፍ ግፍ ሲፈፀምበት የዳር ተመልካች ሆኖ መቆየቱም ድብቅ አይደለም፡፡
ትንሽ ሥጋ እንደ መርፌ ትወጋ ይባላል፡፡ በአማራው ላይ በልዩ ልዩ መንገድ የሚፈፀመው ጥቃት ያብሰለሰላቸው የአማራ ልጆች፤ በድርጅቱ ውስጣዊ ትግል በማድረግ ተጠምደው እንደቆዩ፣ በከፍተኛ መገለል ውስጥ ሆነው በሰሩት ሥራም ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ አቶ መለስ፤ ኦሕዴድ ሲፋቅ ኦነግ ይሆናል አሉ እንደተባለው ሁሉ፣ ብአዴን ሲፋቅ መአሕድ ይሆናል ሳይሉ በመሞታቸው አዝናለሁ፡፡ እሱ ብቻ አይደለም፤ ማግለል ከፖለቲካ የትግል መንገዶች አንዱ ቢሆንም እኔና መሰሎቼ የብአዴንን ሰዎች ለረዥም ጊዜ ስናገል መቆየታችን፣ ትግላቸው ፈጥኖ ዛሬ ከደረሰበት ደረጃ እንዳይደርስ በማድረጋችን ይፀፅተኛል፡፡
ከብዙ ትግል በኋላ ኢሕዲን ለአማራ ጉዳዮች ጀርባውን መስጠቱን ማቆም ጀመረ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም በኦሮሚያ ክልል በበደሌ አካባቢ በአማራዎች ላይ የተፈፀመው ግድያ አሳስቦት እቦታው ድረስ እነ አቶ ንጉሡ ጥላሁንን ልኮ ነገሩን ተከታተለ፡፡
አምጦ አምጦ ቢሆንም ሚያዚያ 2010 ዓ.ም ላይ የአማራ ምሁራን ጉባኤ ተጠራ፡፡ እዚህ ጉባኤ ላይ ድርጅቱ የአማራን ኢኮኖሚ በማዳከምም የተጫወተው ሚና ተዘረዘረ፡፡ በጣና በለስ ኃይል ማመንጫ አጠገብ የምትገኘው ባሕር ዳር፤ በአካባቢዋ ለሚገኙ ፋብሪካዎች የሚበቃ ኃይል እንኳ እንደማታገኝ ተገለጠ፡፡ ከሰም አካባቢና ደጀን ላይ ለሃይል ማሟያ ይሰራል የተባለው የመብራት ኃይል መለስተኛ ማስተላለፊያ ጣቢያ ወደ ተግባር አለመሻገሩ ይጠቀሳል፡፡ በዋግ ህምራ ዞን ብቻ በመቶ የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች በዳስ ውስጥ እንደሚካሄድ ታወቀ:: አማራን መልሶ ማቋቋም ያስፈልጋል የሚል ጥያቄ ተነስቶ ተመከረ፡፡ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ይህን ለመግፋት ቢያስቡም፣ ለውጡ የመጣባቸው ወገኖች ክልሉን የሁከት መናኸሪያ በማድረጋቸው ወደፊት ለመሄድ ሳይችሉ ቀሩ፡፡ ዶክተር አምባቸው መኮንን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ሥልጣን በያዙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ድንገት ቱግ ያለው፣ ከአጣዬ እስከ አንፆኪያ አድማሱን ያሰፋው ሁከት በአካባቢው ስላለው ችግር ጥሩ ማሳያነት ይጠቀሳል፡፡
“ንፁህ ልብ ይዘን መጥተናል፤ በንፁህ ህሊና እንድንሰራ እድል ስጡን” ያሉት ዶ/ር አምባቸው መኮንን፤ የበአዴንን ግድፈቶች ለማረም የፈለጉትን ጊዜ ሳያገኙ ቀሩ፡፡ ያልታሰበው ያልተጠበቀው ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌ እጅ አረፈባቸው፡፡
በ1951 ዓ.ም በላስታ አውራጃ ቡግና ወረዳ ቆቤ ተክለ ሃይማኖት የተወለዱት አሳምነው ፅጌ፤ እንደ ማንኛውም የካህን ልጅ የቤተ ክህነት ትምህርት አግኝተዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በላሊበላ ከጨረሱ በኋላ ወደ ማስተማር ስራ ገብተው፣ በስሪንቃና በይሆና ትምህርት ቤቶች አገልግለዋል፡፡ በ1981 ላይ ከኢሕዴን ጦር ጋር በመቀላቀል የህክምና ስልጠና ወስደው ሰርተውበታል፡፡ ከ1983 የሕወሓት ኢሕአዴግ አሸናፊነት በኋላ የላስታ ወረዳ አስተዳዳሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ ጦርነት ጊዜም በባድመ ግምባር የ22ኛ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ ሆነው ግዳጃቸውን ተወጥተዋል፡፡ መከላከያ ኢንጂነሪንግ፣ አየር ኃይል፣ የጦር ኃይሎች ሆስፒታል የሠሩባቸው መ/ቤቶች ናቸው፡፡ ለሁለት ዓመት ወደ አሜሪካ ተልከው ወታደራዊ ትምህርት ገብይተዋል፡፡
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፤ ግልፅና ደፋር፣ የሚያምኑበትን ሀሳብ በአደባባይ ከመናገር ወደ ኋላ የማይሉ ሰው በመሆናቸው በሕወሓት ኢሕአዴግ ሰዎች ዘንድ የማይወደዱና በጥርጣሬ የሚታዩ ሰው መሆናቸው ይገለጻል፡፡ በ2001 ዓ.ም ምልክቱ እንኳ ባልታየ መንግሥትን የመገልበጥ ሙከራ ተከስሰው ወደ እስር የተወረወሩት በዚሁ ባህርያቸው እንደሆነ ጎልቶ ይነገራል፡፡ የክልሉ መንግሥት በተፋቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአማራ ክልል የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አድርጎ ሾማቸው:: መገፋታቸውን አይቶ እንደሆነ ይታመናል እሳቸውን ግን በታሰሩበት ጊዜ፣ ብአዴን ምንም ባለማለቱ ቅሬታ እንደነበራቸው ይነገራል፡፡
“እኔን ያስፈታኝ ህዝብ ነው፤ የማገለግለውም የአማራን ህዝብ ነው” በማለት የተነሱት ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ፅጌ፤ የክልሉን ሚሊሽያ በማሰልጠን ረገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ ከክልሉ ውጪ ያሉ ወገኖች እንደ ስጋት ያዩዋቸው እንደነበርም ድብቅ አይደለም፡። “አማራ በዘሩ ሲደራጅ ለምን የሌላው አይን ይቀላል” እየተባለም ነበር፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ላቀ አያሌውና ሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸው በአማራ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ፣ በብርጋዴር ጀነራል አሳምነውና በአመራሩ መካከል ምንም ዓይነት ችግር እንዳልነበር፣ እሳቸውንም ከቦታቸው ለማንሳት እንዳልታሰበ ደጋግመው ገልጠዋል፡፡ እሳቸው ደግሞ አመራሩ ሊያነሳቸው እንደተዘጋጀ፣ ቦታውን ለአቶ አዘዝ ዋሴ ለመስጠት እንደታሰበ ሰምተዋል የሚሉም አሉ፡፡ ይህ እውነትም ካልሆነ  ይሁነኝ ተብሎ በተፈጠረ ወሬ፣ ሰውየው አሳዛኝ ወደሆነ እርምጃ ተገፍተዋል ብሎ መላምት ማስቀመጥ  ይቻላል፡፡
እባብ ያየ በልጥ ይበረግጋል ይባላል፡፡ የአማራ ሕዝብ የሚፈልገውን የሕግ የበላይነት ለማግኘት አልቻለም በሚለው መገምገማቸው ይታወቃል::  ከሥልጣን ከተነሱ በኋላ የሚቀጥለው እርምጃ መከሰስ መወቀስና መታሰር ሊሆን ይችላል ብለው  ሊፈሩ አይችሉም ብሎ ማሰብ ትክክል አይሆንም:: ቁስለኛው አሳምነው የወሰዱት እርምጃ ግን የእሳቸውንም ሆነ የሌሎቹን ሕይወት ያሳጣ፣ የአማራን ሕዝብ ስሜት ያቆሰለ፣ መረጋጋት እየቸገራት ላለችው ድሃዋ  ኢትዮጵያ፤ የባሰ የምታሰጋ አገር ሆና እንድትቆጠር ያደረገ ነው፡፡
ያሰቡት ተሳክቶ፣ የክልሉን መስተዳደር መያዝ ቢችሉ ኖሮ፣ ጀነራሉ ክልሉን ምን ያደርጉት ነበር? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው፡፡ መልሱ ግን “ምንም” ከሚለው ውጪ ሊሆን አይችልም:: ይህ ማለት ደግሞ በእኔ እምነት፣ ያሰለፉት ኃይል ቢበዛም የወሰዷቸው እርምጃዎች የመፈንቅለ መንግሥት ናቸው ብሎ ለመደምደም እጅግ የሚያስቸግር ያደርገዋል፡፡ ምናልባት በግንፍልነት የተወሰደ እርምጃ ሊሆን ይችላል፡፡   
ከጊዜ በኋላ የሚወጡ መረጃዎች በጉዳዩ ላይ የሚያስከትሉት ለውጥ እንደተጠበቀ ሆኖ “መፈንቅለ መንግሥቱ”ን መፈንቅለ መንግሥት ለማለት ለሚከብዳቸው የእኔ ቢጤ ሰዎች፤ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የጀነራል ሰዐረ መኮንንን አሟሟት፣ ከባሕርዳሩ ግድያ ጋር ለማያያዝ ይከብዳል፡፡ ሚዛን የሚደፋ ምክንያት ለማግኘት ይቸግራል፡፡ ጊዜና ምርመራ ይፍታው፡፡
በግሌ በሆነው ነገር ሁሉ ክፉኛ አዝኛለሁ፡፡ በአጠቃላይ ጉዳዩ  ቅስም ሰባሪ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ በክልሉ  ያለው የመከላከያ ኃይል፣ የብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌን አስከሬን በክብር ወደ ትውልድ ቀዬው በመሸኘት ላሳየው መልካም ተግባር፣ የላሊበላ አካባቢ ሕዝብም፣ ቀብራቸውን አክብሮ በመፈፀሙ፣ ሁለቱም ምስጋና ይገባቸዋል፡፡  
ለሞቱት ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን፤ ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን እመኛለሁ፡፡ ፈጣሪ ለኢትዮጵያ ሰላምን ያውርድ!     Read 4615 times