Print this page
Tuesday, 02 July 2019 11:51

መንግሥታችን ተዝረክርኳል!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)


    “--መንግሥት የሚያምርበት እንደ እግዚአብሔር ሲሆን ነው፡፡ በአንድ ፊቱ እየሳቀ፣ በሌላው ይቀጣል፡፡ ባንድ ገፁ በርህራሄ እያለቀሰ፣ በሌላው
ኮስተር ይላል፡፡ ባንድ እጁ አበባ ይዞ፣ በሌላው ጅራፍ ይይዛል፡፡ ለመልካም ሥራ ሽልማት፣ ለጥፋት ደግሞ ቅጣት ያስፈልጋል፡፡”--
 
      ሀገሬ ልጆቿን ለጅብ አስጥታ፣ በሮችዋን በርግዳ፣ የተኛች፤ አባወራ የሌላት ሰነፍ ሴት እየመሰለችኝ መጣች፡፡ ያለፈ ያገደመ ሁሉ እየቀማት የሚሄድ፣ ጫጩቶችዋን ሆነ አውራ ዶሮዎችዋን ለሸለምጥማጥ የምትገብር ቀሽም እናት ሆነችብኝ፡፡ የዛሬ ዐመት በለውጡ ድንኳን ውስጥ የነሰነስነው አበባ፣ እሾህ እስኪሆን፣ አሸወይና ያልነው፣ ሙሾና ደረት መድቃት እየሆነ ድንኳናችንን የእንባ ጤዛ አሸከመው፡፡
ለውጡ ክፉ አልነበረም፤ ከአውሬ መንጋጋ ነጥቆናል፣ ከጨካኞች ክንድ አውጥቶናል፣ ይሉኝታ ከሌላቸው ዘራፊዎች ገላግሎናል፡፡ በምንም ተዓምር “ምነው በቀረብን!” ብለን እንደ ሙሴ ዘመን፣ የእሥራኤል ህዝብ፣ የግብጽን ሽንኩርት የሚያስመኝ ቅንጣት ትዝታ የለንም፡፡ መታሰር አይናፍቅም! መገደል አያጓጓም! ግን ደግሞ ከአውሬ አፍ ያወጣን ለውጥ ልስላሴ፣ መልሶ ለአውሬ እየሰጠን ነው፡፡ ከጅብ አፍ ነጥቆ መልሶ ለተኩላ መስጠት ልዩነቱ እምብዛም ነው፡፡ ልዩነቱ የሞቱ ዐይነትና የአበላሉ ስልት ነው፡፡
“መግደል መሸነፍ ነው!...”የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግርና ፍልስፍና በፍፁም ክፉ አልነበረም፡፡ መግደል አውሬነት፣ መግደል ኋላቀርነት ነው!...ይሁንና ለአንዳንዶች መግደል ጀግንነት ነው፡፡ በሰለጠነ ምድር፣ ለሰለጠነና ልዩነቱ ለገባው ህዝብ ቢሆን ውጤቱ የትየለሌ ነበር፡፡ እንደኛ ላለው ዴሞክራሲን በጆሮው እንጂ በጣዕሙ ለማያውቅ ኋላቀርና ደሀ ሕዝብ ግን ቅንጦት ነው፡፡ ወይም የቂል መዝሙር ነው፡፡ ቢያንስ ለጊዜው!
እኛ ዘንድ መግደል የአመፀኛን አፍ መዝጊያ፣ የጥጋበኛን ጥጋብ ማብረጃ፣ ባለጋራን ማስወገጃ ነው:: ልምምዳችን ይሄ ነው፡፡ የዚህ ዐይነቱ መሠሪነት የፖለቲካውን አደባባይ ብቻ ሳይሆን የእምነት ተቋማትንም ካጣበበ ቆይቷል፡፡
ታዲያ ከዚህ ኋላቀር ልምምድ፣ ዛሬውኑ “ጠመንጃና ፍርድ ቤትን ለህግ ማስከበሪያነት አላውልም” ብሎ በፈንታው ዘንባባ እያሳለሙ ብቻ መኖር ከቶ የሚቻል አይደለም፡፡ ጠበቅ ያለ ህግ ወይም አቶ ቡልቻ ደመቅሳ አንዴ ለአንድ መጽሔት እንደተናገሩት፤ ቁንጥጫ ቢጤ ከሌለ ያልለመድነውን ነገር ባንድ ዓመት ልንዋሀደው አንችልም፡፡ ሁሉም ነገር ልምምድና ጊዜ ይጠይቃል፡፡ አስተሳሰብ ደግሞ ከሁሉም የበለጠ  ጊዜ ይወስዳል፡፡ እናትና አባቴ፣ ጐረቤቴና ዕቁብተኞቼ አለዚያም ዕድርተኞቼ “በለው የታባቱ!” እያሉ ያሳደጉኝ ሰውዬ፤ እንዴት ብዬ ነው ባንድ ጊዜ  “መነጋገር ብቻ ይበቃል” የምልበትን ሰብዕና የምላበሰው!?  ደረጃ ሳይረግጡ ባንድ ጊዜ እላይ የሚያወጣው አሳንሰር ብቻ ነው! ባይሆን በመጠኑ እየተጠነቀቅን ሀይል እየቀነስን፣ በሃሳብ ማሸነፍን በትምህርት ቤት እያስተማርን ለቀጣዩ ትውልድ ሀብቱ እንዲሆን ካላደረግን በስተቀር ለዚህ ትውልድ ባልተቃኘበት ቅኝት መዘመር የሚሆን ይመስለኛል፡፡
ሌላው አስገራሚ ነገር፣ የአንዲት ሀገር የህዝብ ደህንነት መሥሪያ ቤት፣ በሩ ሲንኳኳ እንኳን ጆሮው መደንቆሩ ነው፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያለ እጅግ አደገኛና ሴረኛ መንግሥት ሥልጣን ለቅቆ፣ ግን አድብቶ ዛሬም ተንኮል በሚጠመጥባት ሀገር፤ ደህንነቱ እንቅልፍ አጥቶ መሥራትና መትጋት ሲገባው፣ ለጥ ብሎ መተኛቱ የሚገርም ነው፡፡ ብዙ ነገር ተዝረክርኳል፡፡ ስለዚህም ያለ ልክ ተጠቅተናል:: መክፈል የማይገባንን ዋጋም እየከፈልን ነው፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ የተፈጠረው መፈናቀልና ሞት እንኳን ቢሰላ ኪሣራው የትየለሌ ነው፡፡ መፈናቀል ለምን ተከሰተ? ለምን ሰዎች ሞቱ አይባልም? የዚህ ሁሉ ክፉ ውጤት መንስዔው፤ ኢህአዴግ ለሃያ ሰባት ዓመታት የዘራው ክፉ ዘር ነው፡፡ ከዚህም በላይ አለመፍረሳችን ይገርማል፡፡  
ነገር ግን ውጤቱን መቀየር፣ ሁኔታውን ማስተካከል ይቻል ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ጥፋት በተፈፀመበት ቦታ ሁሉ ያሉ ጥፋተኞችን ይዞ ተገቢውን ፍርድ መስጠት ቢቻል፣ ተቀጪው ብቻ ሳይሆን ተመልካቹም ያንን መሰል ወንጀል ለመፈፀም አይደፋፈርም ነበር፡፡ ግና እንደዚያ አልተደረገም!  በፍቅር ላላደገ ሰው፤ ፍቅር ፍቅር እያሉ መጮህ ትርፉ ላንቃን ማድረቅ ነው፡፡ ቅጣቱን ከሰጡ በኋላ ማስተማር ነው የሚሻለው፡፡ እንኳን የኛ ዐይነቱ ኋላቀር አገር ቀርቶ የቱም ስልጡን የሰው ልጅ፣ በጐኑ ሻጥ ያደረጋት አውሬያዊ ተፈጥሮ አለችው፡፡ ያቺ ደግሞ የምትነቀለው በዕውቀት ነው፡፡ ዕውቀት ደግሞ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ባህል፣ እምነት ሥነልቡና ማህበረሰባዊ ውቅር በራሱ ብዙ ጣጣ አለው፡፡
ቶማስ ጀፈርሰን በርሱ ዘመን ለአንድ ወዳጁ በፃፈው ደብዳቤ፡- “The law of our general nature inspite of individual exceptions; and experience declare that man is the only animal which devours his own kind.” ብሏል፡፡
ይህ በእንግዲህ አጠቃላይ ተፈጥሮ ነው፡፡ እንደ ሁኔታው እንደ አስተዳደጋቸው ከአውሬነት ወጥመድ ያመለጡ ጥቂት ግለሰቦች ቢኖሩ እንጂ ሰው የራሱን ወገን የሚያጠፋ እንስሳ ነው፡፡ ምናልባት ዛሬ ቢሆን ጀፈርሰን አሜሪካ ውስጥ ሆነው ይህንን ሃሳብ ላይደግሙት ይችላሉ፤ ምክንያቱም ሥልጣኔ የሚገርዘው የዚህን ዓይነቱን ሸለፈት ነውና! በተለይ በኛ ሀገር ደግሞ አውሬነቱ ሊበዛ እንደሚችል መጠርጠር አይከብድም፤ በየዘመናቱ ከተለያዩ ጠላቶች ጋር ውጊያ የገጠመ ህዝብ፣ ጠላት እየመጣ “ልግዛህ” ሲለው “እምቢ!” ለማለት ሲፋለምና ሲሰድ - ሲያሳድድ የኖረ ሕዝብ፣ በምንም ዐይነት “ፍቅር ብቻ” በሚል ሳይንስ ልንመራው አንችልም፡፡ ስለዚህ በፍየል ዘመን፣ በግ ሆኖ መበላት አስፈላጊ አይደለም::
በዋናነት መንግሥት የሕዝቡን ደህንነት መጠበቅ እንጂ ግብረገብነት ማስተማር የለበትም፡፡ ይህ የቤተ-እምነቶች ሃላፊነት መሆን አለበት፡፡ በሠላም ወጥቶ መግባት፣ ከውጭና ከውስጥ ጠላት መጠበቅ ያለብን በመንግሥታችን ነው፡፡ መንግሥትና ሠራዊት እያለን፣ በተዝረከረከ አሠራር ማለቅ የለብንም፡፡
ከዚህ በፊት ቡራዩ ሰው ሲታረድ፣ ቤኒሻንጉል ሰው ሲፈናቀል፣ ጉጂና ሃዋሳ በጠራራ ፀሐይ ያገር ልጅ ሲገደል  ተገቢ የሆነ የአፀፌታ እርምጃ  ቢወሰድ ኖሮ፣ ዛሬ ችግሩ አናታችን ላይ ወጥቶ ለከፋ ውርደት ባልተዳረግን ነበር፡፡ መንግሥት የሚያምርበት እንደ እግዚአብሔር ሲሆን ነው፡፡ በአንድ ፊቱ እየሳቀ፣ በሌላው ይቀጣል፡፡ ባንድ ገፁ በርህራሄ እያለቀሰ፣ በሌላው ኮስተር ይላል፡፡ ባንድ እጁ አበባ ይዞ፣ በሌላው ጅራፍ ይይዛል፡፡ ለመልካም ሥራ ሽልማት፣ ለጥፋት ደግሞ ቅጣት ያስፈልጋል፡፡
እውነት ነው፤ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ አሁኑ ዝብርቅርቅ ያሉ ሰዎች ያዘለ መንግሥት ኖሯት አያውቅም፡፡ በብሔር ተደራጅቶ የተቋቋመ መንግሥት፣ ለሀገሪቱ አንድ ዐይነት ህልም ከማለም ይልቅ ለየሠፈሩ መሬት ሊቆርስና ሀብት ሊሻማ የሚዋትት የሰነፎች ቅርጫት ውስጥ የተሰበሰበ መንጋ ያለበት ነው፡፡ ሀገር አጣብቂኝ ውስጥ ሆና እንኳ ታሪክ ማዛባት፣ ከተማ መናጠቅ፣ ለመሬት መቧቀስ … የሚቃጣቸው ማፈሪያዎች ያሉበት አገር ነው፡፡ ይህ ትንሽነት ደግሞ የቀደመው ወያኔ/ኢህአዴግ፤ ቀጥ ለጥ ብለው የሚገዙ እንጂ የማይጠይቁ፣ ከሆዳቸው በቀር ህልም የሌላቸውን ሰብስቦ ስላስረከበን ነው፡፡ ብዙዎቹ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች፤ በዕውቀት ተመርጠው፣ በታማኝነት ተለክተው ሳይሆን፣ ከህዝብ ይልቅ ስልጣናቸውን በመውደዳቸው የተሰገሰጉና የራሳቸው ህልም የሌላቸው መሆናቸው ነው፡፡
የዚህ ዓይነቱ ስብስብ ደግሞ ባለህልሞቹን የለውጥ ሰዎች አላፈናፍን ብሏቸዋል፡፡ እነዚህ ሀገርን ሲያዩ፣ እነዚያ መንደርን፤ እነዚህ ላለመፍረስ ሲታገሉ፣ ብብታቸው ሥር ያሉት የሌላውን መንጠቅ ይመኛሉ፡፡ ስለዚህ ፖለቲካችን ተሳክሯል፡፡ ለውጡ ጠላተ ብዙ ሆኗል፡፡ ብቻ ወጣም ወረደ ያለንበት ወቅት በእጅጉ ፈታኝ ነው፡፡ ፈተናዎቹም ብዙ ናቸው፡፡ ይሁንና አንዱ ፈተና ግን መንግሥት ራሱ ያመጣው  ነው፡፡
ህግ ሳያስከብሩ ሀገር ማቆም ይቻላል ብሎ ያመነ መንግሥት፤ በኢትዮጵያ ዐውድ የትም ሊደርስ እንደማይችል ለማወቅ ነቢይ መሆን አያስፈልግም፤ ሀቁ ብቻ ሳይሆን አሁን እየተፈጠረ ያለው ሁኔታ ራሱ ቁልጭ አድርጐ ያሳያል፡፡ ለምሳሌ፣ በየአካባቢው የሚነሱ ግጭቶች ቀስቃሾች በአብዛኛው ይታወቃሉ፡፡ ወይም ሊደረስባቸው ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ተደርሶባቸው እርምጃ አልተወሰደባቸውም፤ ስለዚህ በለመዱት መንገድ ይቀጥላሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሚነሱ ብጥብጦች እነማን የችግሩ መነሻ እንደሆኑ ታውቆ እርምጃ ካልተወሰደ፣ ያ ችግር ነገም መቀጠሉ አይቀርም፡፡ አመጽ ያስነሳ ተማሪ ወይም ኃላፊ ኮስተር ያለ ቅጣት ቢቀጣ፣ ያንኑ ወንጀል የሚደግም አይኖርም፤ ነገሮች እየሰከኑ ይሄዳሉ:: ሰው ገድሎ በሰላም መኖር ከተቻለ፤ “መግደል ጀግንነት” በሆነበት ሀገር፤ ችግሩን ማን ያቆመዋል?
ዋናው ችግር መንግሥት፣ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሕዝቡን ሥነልቡና ያለማጤናቸው  ይመስለኛል፡፡ ሕዝባችንን ቢያውቁት ኖሮ፣ እንደዚህ ያለ አመራር ወደሚያስከትለው አበሳ አይከቱንም ነበር፡፡ በገቢር እንደምናየው፤ ኢትዮጵያ ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ አያሌ ችግሮችን ያለፈችው በነፃ አይደለም፤ የበርካቶች ደም ፈስሷል፡፡ ብዙ ሀብት ወድሟል፡፡ ብዙዎች ያለመጠለያ ቀርተዋል፡፡
አሁን ሰሞኑን የተከሰተው ግን በእጅጉ አሳዛኝና መንግሥትን ትዝብት ላይ የሚጥል ስንፍናና ዝርክርክነት የታየበት ነው፡፡ የሀገሪቱ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በመኖሪያ ቤታቸው ሲገደሉ ማየት፤ ሀገሪቱ ያለ ደህንነት ተቋም የቆመች፣ ቅጥር አልባ ድንኳን እንደሆነች ያሳየ ይመስለኛል፡፡ የሀገሪቱ ጠባቂ ሠራዊት ቁንጮ የሆኑ ሰው፤ እንዴት በቀላሉ ሊገደሉ ይችላሉ? የሀገሪቱ የደህንነት ተቋምስ ጠባቂዎቻቸውን ማጥናትና መከታተል አልነበረበትም? ከምደባው ጀምሮ ጀርባቸውን ማጥናት፤ ከዚያም በኋላ ከማን ጋርና የት እንደሚውሉ፣ ከማን ጋር እንደሚደዋወሉ ክትትል መኖር አልነበረበትም? ምናልባት ክትትል እንደሚደረግባቸው ቢያውቁ፣ ገዳዩም አስገዳዩም ይህንን ለማድረግ ባልደፈሩ ነበር፡፡ ግን ምን ያደርጋል … የተበረገደ በር አግኝተው ሠተት ብለው ለጥፋት ገቡ፡፡
ከቀደመው ጥፋት  ትምህርት ቢወሰድ ኖሮ፣ የዛሬው ጥፋት ባልደተገመም ነበር! ቤተ መንግሥት ድረስ ወታደሮች ተልከው ጠቅላይ ሚኒስትሩን እስከ መግደል ከደፈሩ በኋላ በጣም ብዙ ሁለንተናዊ ጥንቃቄና ክትትል ሊደረግ ይገባ ነበር፡፡ የባህር ዳሩም ሁነት በተመሳሳይ ሁኔታ “ለጥ ብሎ የተኛ ደህንነት” እንዳለን ነው የሚጠቁመው፡፡ በሌላ በኩል ብርጋዲየር ጀነራሉ ብዙዎች እንደሚሉት፤ ”ችግሮችን በመነጋገር መፍታት ነበረባቸው” የሚለው ሃሳብ ትክክል የሚሆነው ሰውየው ከማረሚያ ቤት ከወጡ በኋላ ተገቢውን ህክምና አግኝተው ቢሆን ነበር:: ያለበለዚያ ግን የተጠራቀመ ቁጣቸውን በሆነ የሃይል መንገድ  መግለጣቸው አይቀርም፡፡ ሰውየው ፍትህ ተነፍገዋል፤ ራቁታቸውን ተደብድበዋል፤ በጨለማ ክፍል ውስጥ ታጉረዋል፡፡ ያንን ቁጣና ያንን የበደል ክምር ሳያራግፉ ወደ መሪነት ከመጡ ያልተስማማቸውን ነገር ሁሉ ለማስወገድ የሚሞክሩት በሀይል እንጂ በፍቅር ሊሆን አይችልም:: አሁን እኛ የምንለውን ከየት ሊያመጡት ይችላሉ?
የአማራ ክልላዊ መንግሥት፤ ከኦሮሚያው ከማል ገልቹ መሾም ጋር በተመሳሰለ ሁኔታ ሰውየው የሥነ ልቦና አገልግሎት ሳይሰጣቸው፣ፈተና ወደተሞላው ሥልጣን ማምጣቱ፣ ያየነውን መሪር ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ በሌሎች የሰለጠኑ ሀገራት፣ እሥር ቤት ውስጥ የቆዩ ሰዎች እንኳን ወደ ሥልጣን ቀርቶ ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚደባለቁት ሥነልቡናዊ ህክምና “Psychotherapy” ተደርጐላቸው ነው፡፡ ይሄን አለማድረጋችን የመዝረክረካችን ውጤት ነው::  
በአጠቃላይ የሰሞኑ አደጋ የደረሠብን ቀድመን ልንሰራ የሚገባንን ሥራዎች ባለመሥራታችን ነው:: አሁንም ጉዳታችንንና ስብራታችንን ወደ በረከት ልንቀይረው የምንችለው ወደፊት እንዳይደገም ጠንክረን ስንሰራ ነው፡፡ በግሌ ሀገሬ ባጣቻቸው ታላላቅ መሪዎች እጅግ አዝኛለሁ፡፡
ሀገሬ ፅናቱን ይስጥሽ!!
ከአዘጋጁ፡- በዚህ ፅሑፍ ውስጥ የተንፀባረቀው ሃሳብ የሚወክለው የፀሐፊውን ብቻ እንደሆነ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

Read 1712 times