Tuesday, 02 July 2019 11:38

የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ድንገተኛ ህልፈት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(6 votes)

ባለፈው ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም  በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማና በአዲስ አበባ በሰዓታት ልዩነት የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ መላው ኢትዮጵያውያን በከባድ ሐዘን ውስጥ ሰንብተዋል:: የክልል አመራሮቹም ሆኑ የወታደራዊ መኮንኖቹ ድንገተኛ ህልፈት ዝርዝር መንስኤ ወደፊት በፖሊስ ምርመራ የሚታወቅ ሲሆን የሟቾቱ የቀብር ስነስርዓት ባለፈው ረቡዕ ሰኔ 19፣ በባህርዳርና በመቀሌ ከተሞች ተፈጽሟል፡፡
ከሟቾቹ መካከል የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም የነበሩት የጀነራል ሰዐረ መኮንን እንዲሁም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት የዶክተር አምባቸው መኮንንና  የክልሉ የሰላምና ህዝብ ደህንነት ሃላፊ የነበሩት ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌን አጭር ታሪክና መሪዎቹ በልጆቻቸው አንደበት እንዴት የተገለጹበትን ሁኔታ ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡  
       

     ጀነራል ሰዐረ መኮንን
በትግራይ ክልል ሽረ እንዳባጉና፣ በ1954 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ አካባቢያቸው ተከታትለዋል፡፡ በ1969 ዓ.ም በ15 ዓመት ዕድሜያቸው ትምህርታቸውን አቋርጠው የትጥቅ ትግሉን ተቀላቀሉ፡፡ በዚህም ከተራ ታጋይነት አንስተው በተለያዩ የወታደራዊ አመራር እርከን ላይ አገልግለዋል፡፡ በቀይ ኮከብ ዘመቻ ወቅት ወደ ኤርትራ ለድጋፍ ከዘመተው የህውሓት ቡድን ጋር በአመራርነት ተጉዘው ለአንድ ዓመት ያህል ቆይተዋል፡፡ በርካታ ታጋዮች በውሃ ጥም ባለቁበት ሰርዶ በተባለው የአፋር ክልል ውስጥ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገው፣ በህይወት ከተረፉ ጥቂት ታጋዮች መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላ በተለይ በምስራቅ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ወታደራዊ የድንበር ጦርነት ወቅት የቡሬ ግንባርን በመምራት የኢትዮጵያ ሰራዊት ከፍተኛ ድል እንዲቀዳጅ ካደረጉ የጦር አዛዦች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በኢትዮ ኤርትራ ድንበር አካባቢ ተሰማርቶ የነበረው የሰሜን ዕዝ፣ ዋና አዛዠ ሆነው አገልግለዋል:: ባለፈው ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የቀድሞውን ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሳሞራ የኑስን ተክተው፣ ህይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ ለአንድ ዓመት የጦር ኃይሉን መርተዋል፡፡ ጀነራል ሰዐረ፤ የሁለት ልጆች አባት ሲሆኑ የመጀመሪያ ልጃቸው የተወለደችው በትግል ላይ እያሉ ነበር፡፡ ሁለተኛ ልጃቸው ደግሞ ከደርግ ውድቀት በኋላ ነው የተወለደው፡፡  
ሜ/ጀነራል ገዛኢ አበራ
ከአባታቸው ከቀኝ አዝማች አበራ ደስታና ከእናታቸው ወ/ሮ ሙሉ አብርሃ በትግራይ ዞን አክሱም ከተማ ጥር 1953 ዓ.ም ተወለዱ፡፡  በአክሱም አብርሃ ወአፅብሃ ት/ቤት ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአክሱም ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እየተማሩ በነበረበት ወቅት  አስከፊውን የደርግ ስርአት በትጥቅ ትግል ለመፋለም በ1969 ጥር ወር ህውሓትን ተቀላቀሉ፡፡
የትምህርት ዝግጅት
የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በ1986 ዓ.ም በሎጀስቲክስ ማኔጅመንት ከአሜሪካ ሀገር ፣  በ1998 ዓ.ም ሁለተኛ ዲግሪ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ከለንደን ኦፕን ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በሎጀስቲክስ ማኔጅመንት ሁለተኛ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በኦፕንፊልድ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡።
የስራ ልምድ
ከ1969 እስከ ግንቦት 1970 ዓ.ም በህውሓት 30ኛ ሻምበል በተዋጊነት ከ1970 እስከ 1971 መጨረሻ በማዕከላዊ ግንባር ማሰልጠኛ ማዕከል ክፍል ኃላፊ በመሆን  ፣ ከ1972 -1975 ዓ.ም የሪጅን ሁለት የስንቅና ንብረት ኃላፊ /ሎጀስቲክ/ በመሆን ግዳጃቸውን ፈፅመዋል፡፡
ከየካቲት 1980 እስከ የካቲት 1981 ዓ.ም ድረስ በተደረጉ ተከታታይ ውጊያዎች በትግራይ የነበረውን የደርግ ሰራዊት ጠራርጎ በማውጣት ፣ ትግራይን ነፃ እንዲወጣ አስችለዋል፡፡ ከ1983 እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በአዲስ መልክ በተደራጀበት ወቅት በሀገረ መከላከያ ሚኒስቴር በሎጀስቲክ ዋና መምሪያ የስንቅና ንብረት መምሪያ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከ1985 እስከ 2005 ዓ.ም የሀገር መከላከያ የሎጀስቲክ መምሪያ ዋና ኃላፊ በመሆን  በመከላከያ ሰራዊት ሎጀስቲክ በማደራጀት፣ ዘመናዊ ሎጀስቲክስ በመከላከያ እንዲገባ ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል፡፡ አንደኛ ደረጃ የወርቅ ሜዳልያን ጨምሮ የአገልግሎት ሜዳልያና ኒሻኖች ከኢፌድሪ መንግስት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ጄኔራል ገዛኢ በ2005 ዓ.ም በመከላከያ የመተካካት ሂደት ፣ በክብር በጡረታ ከተሰናበቱበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዕለተ ህልፈታቸው በፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት የተለያዩ መመሪያዎችን አዘጋጅተው በማደራጀትና በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በልዩ አማካሪነት ሲያገለግሉ የነበረ ሲሆን ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በተተኮሰባቸው ጥይት፣ በተወለዱ በ58 ዓመታቸው ህይወታቸው አልፏል፡፡ ከባለቤታቸው ታጋይ አበባ ዘሚካኤል አራት ወንድ ልጆችና አንድ ሴት ልጅ አፍርተዋል፡፡  
ዶ/ር አምባቸው መኮንን
ከአቶ መኮንን ሲሳይና ከወ/ሮ አማን እንደብልሃቱ በ1962 ዓ.ም በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ታች ጋይንት ወረዳ አቄቶ ቀበሌ ተወለዱ፡፡ ለቤተሰቦቻቸው የበኩር ልጅ ሲሆኑ አንድ ወንድምና ሁለት እህቶች አሏቸው፡፡
የትምህርት ዝግጅት
ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪ፤
ከደቡብ ኮሪያው ኬዲአይ ዩኒቨርሲቲ፣በፐብሊክ ፖሊሲና ኢኮኖሚክስ የማስተርስ ዲግሪያቸው፤
ሁለተኛ የማስተርስ ዲግሪያቸው ደግሞ በእንግሊዝ አገር ከሚገኘው ኬንት ዩኒቨርሲቲ፣ በአለም አቀፍ ሳይንስና ኢኮኖሚ ልማት፤
የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከዚሁ ኬንት ዩኒቨርሲቲ፣ በኢኮኖሚክስ፤ አግኝተዋል፡፡
የሥራ ልምድ
ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ በህዝብና መንግስት ስራዎች ከወረዳ እስከ ፌደራል ባሉ መ/ቤቶች አገልግለዋል፡፡
የአማራ ክልል ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር
የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ የፅህፈት ቤት ኃላፊ
የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አልመድ) ዳይሬክተር
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ  
ከመስከረም 25/2008 እስከ ጥቅምት 21/2009 ዓ.ም ድረስ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር፣  የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር
ከህዳር ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት የመሰረተ ልማት አማካሪ ሚኒስትር
ከመጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ሕይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ አገልግለዋል፡፡
አቶ ምግባሩ ከበደ
ከአባታቸው አቶ ከበደ እውነቱ ፣ ከእናታቸው ወ/ሮ የሺ ውበቱ ሐምሌ 23 ቀን 1966 ዓ.ም በቀድሞው ጎንደር ክፍለ ሃገር በደብረ ታቦር አውራጃ በአሁኑ የደቡብ ጎንደር አስተዳደር ዞን ወረሃ ወረዳ ልዩ ስሙ ወፍ አርግፍ ታምሬ ልደታ ቀበሌ ተወለዱ ፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በባህርዳር ጣና ሃይቅ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትለዋል፡።  
የትምህርት ዝግጅት
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል ፡፡ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዲሁ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተከታትለው በህግ የማስተርስ ድግሪ ተቀብለዋል ፡፡
የስራ ልምድ
በምዕራብ ጎጃም ዞን የደጋ አሞትና ሰከላ ወረዳ ውስጥ በአቃቤ ህግነት አገልግለዋል፡፡ የምስራቅ ጎጃም ዞን ፍትህ መምሪያ የዞን አቃቤ ህግ በመሆን በኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ የብአዴን የምስራቅ ጎጃም ዞን አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ሆነው እንዲሰሩ ተመድበው ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡  
ከ1999 ዓ.ም እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ የምስራቅ ጎጃም ዞን የአቅም ግንባታ መምሪያ ኃላፊ፣ ከ2000 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እንዲሁም ከ2003 እስከ 2008 ዓ.ም የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ በመሆን አገልግለዋል፡።
ከ2008 ዓ.ም አንስቶ የአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከየካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ አቃቤ ህግ በመሆን ህይወታቸው እስካለፈበት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል፡፡ አቶ ምግባሩ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ነበሩ፡፡
አቶ እዘዝ ዋሴ
ከአባታቸው ዋሴ መንግስቱና ከእናታቸው የውብዳር በወጣ በ1957 ዓ.ም በቀድሞ ጎንደር ክ/ሃገር በደብረ ታቦር አውራጃ በአሁኑ ደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ በስኳ በርጉት ቀበሌ ተወለዱ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም በተወለዱበት አካባቢ የቅዳሜ ገበያ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመካነ ኢየሱስ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትለዋል፡፡ በ1987 የደርግ አገዛዝን በመቃወም ከጓደኞቻቸው ጋር ህዝባዊ ትግሉን ተቀላቅለዋል፡፡
የትምህርት ዝግጅት
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ ማኔጅመንት ከባህርዳር ዩንቨርስቲና የማስተርስ ዲግሪያቸውን ከዚሁ ዩንቨርስቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አግኝተዋል፡፡
የስራ ልምድ
ከ1998 እስከ 2002 ዓ.ም የእስቴ ወረዳና ህዝብ ወክለው የኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በአባልነት አገልግለዋል፡፡ ከ2003 ዓ.ም እስከ 2004 ዓ.ም የደቡብ ጎንደር አስተዳደር ዞን የብአዴን ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡
ከ2004-2008 ዓ.ም ድረስ የደቡብ ጎንደር የዞኑን አስተዳደር በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር አጋጥሞ የነበረው አለመረጋጋት ወደ ሰላም ለመመለስ ከአቶ ምግባሩ ከበደ ጋር ወደ አካባቢው በመሄድ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡
ከ2009 እስከ 2011 ዓ.ም የአማራ ክልል ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የአስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው እንዲያገለግሉ የተደረጉ ሲሆን ከጥቅምት 2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊና ርዕሰ መስተዳደሩ አማካሪ በመሆን ሲያገለግሉ ነበር አቶ አዘዝ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ነበሩ፡፡
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌ
በ1970ዎቹ አጋማሽ የትጥቅ ትግሉን ተቀላቀሉ፡፡
በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የሀገርን ዳር ድንበር በማስከበር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡
በ2001 ዓ.ም በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ወንጀል ተከሰው የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው ነበር፡፡
የዛሬ አንድ ዓመት  የተደረገውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ በይቅርታ ከእስር ተፈቱ፡፡  
ከእስር እንደተፈቱም ሙሉ ማዕረጋቸውና ጥቅማቸው ተመልሶላቸው፣ የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የአማራ ክልል የሠላምና ህዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሾሙ፡፡  
ህይወታቸው እስካለፈበት ሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስም የክልሉ የሰላምና ህዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡።
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ነበሩ፡፡
የቀብራቸው ስነ ስርዓት በትውልድ ሥፍራቸው ላሊበላ ተፈፅሟል፡፡
ሌተናል ጀነራል አበባው ታደሰ፤ ስለ ጀነራል ሰዐረ መኮንን የመሰከሩት
“ሰዐረ ሀይማኖት ዘርና ብሔር የማይለይ፣ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር፣ ፍፁም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ይህ ለውጥ ከመጣ በኋላ ሰዐረ እንደ ከሃዲ ተቆጠረ፡፡ ኢትዮጵያዊነቱን አሳልፎ እንዲሰጥ በጥቂት ቡድኖች ተፅኖ ደረሰበት፡፡ ያም ሆኖ ጀነራል ሰዐረ መኮንን “ቤተሰቤ ይበተናል እንጂ ኢትዮጵያ አትፈርስም” ብለው ነበር፡፡ “ማንም ይምጣ ማንም የኔ መሪ ነው፤ እስክሞት ድረስ በኢትዮጵያዊነቴ ሳልደራደር እሰራለሁ” ይል ነበር፡፡
ጀነራል ሰዓረ መኮንን
“እኔ ትግሬ ነኝ፡፡ አገሩን የሚወድና በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ፡፡ በለውጡ ማመን ከሃዲነት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከዘር ግንዴም ከህይወቴም በላይ ነው፡፡ በረሃ የገባሁት ጭቆናን ለማስወገድ እንጂ ሌላ ጨቋኝ ለመሆን አይደለም:: መቃብር እስከምገባ ድረስ የማይለወጥ እምነቴ አገሬን ማስቀደም ነው፡፡ እኔ የአገሬ ወታደር ነኝ፡፡”
መአሾ ሰዐረ (የጀነራል ሰዐረ መኮንን ልጅ)
“አባቴ በመቻቻል አብሮ በመኖር የሚያምን ፍፁም ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ ጀነራል ሰዐረ ስለሞተ አገር ይፈርሳል ማለት አይደለም፡፡ እኛ ጠንክረን ከቆምን ኢትዮጵያን አንድ እናደርጋታለን፡፡”
መአዛ አምባቸው (የዶ/ር አምባቸው መኮንን ልጅ)
“የአምባቸው ልጅ መባሌ ቀረና የሟች ልጅ ተባልኩ፡፡ አባቴን በጀርባ እንጂ በፊት ለፊት ማንም አይነካውም፡፡ አባቴ ጀግና ነው፡፡ አባቴ ተንኮል አያውቅም፡፡  አባቴ የኢትዮጵያ ልጅ ነው፤ እሱ ደም ውስጥ ያለው ኢትዮጵያ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ነው ያፈረሷት፡፡ የአባቴ ደም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ የእኔም ደም ኢትዮጵያዊ ነው፤አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ነው፡፡”

Read 3790 times