Tuesday, 02 July 2019 11:43

በአገራችን በተከሰተው አስደንጋጭ ክስተት

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(4 votes)


     ታዋቂ ሰዎች ፣ ፖለቲከኞች እና የኪነጥበብ ሰዎች ምን ተሰማቸው መፍትሄውስ ምን መሆን አለበት አሉ በጉዳዩ ላይ አስተያየቶችን እንደሚከተለው ሰብስበናል፡፡
        

          መንግስት መምራት ካልቻለ ይቅርታ ብሎ ማስረከብ አለበት
                አቶ ጌታቸው ረዳ


    ክስተቱ በዚህ መንገድ ይገለጣል ባልልም የምጠብቀው ነገር ነበር፤ ምክንያቱም ስርዓት አልበኝነት በይፋ ሲታወጅ ነው ችግሩ የተጀመረው፤ ሲያጠፉ የነበሩ ሽፍቶች አርበኞች ተብለው አቀባበል ሲደረግላቸው፣ ወንጀል ፈፅመው የታሰሩ ሰዎች አንበሶች ተብለው በየቦታው መወድስ ሲቀርብላቸው ምንም መሰረት የሌለው እርቅና መሰል ነገሮች ሲበዛ  እንደዚህ አይነት ነገር መፈጠሩ የማይቀር ነው፡፡ ጉዳዩ በቅርበት የማውቃቸው  ጓደኞቼ የተገደሉበት በመሆኑ በጣም አዝኛለሁ፡፡ ነገር ግን ሀፍረትም ይሰማኛል፡፡ እንደዚህ አይነት ሞራላዊ ፅድቅና መሰረት የሌለው ይቅርታ ሲሰጥ በሚገባው ደረጃ መታገል አለመቻሌ ያሳፍረኛል፡፡
ህዝብ ግን መጠየቅ መቻል አለበት፡፡ በየቀኑ በየደቂቃው ቃር ቃር እስኪለን ድረስ መጠየቅ መቻል አለበት፡፡ ማንችል ከሆነ “አልቻልንም ይቅርታ አድርጉልን አቅቶናል” ብለን እንድንኖር ሊፈቅዱልን ይገባል፡፡ የአገር ህልውና ነው፡፡ ማንም ሽፍታ እየተነሳ የመሰለውን ሰው የሚገድልበትን ሁኔታ ከፈጠርን እንለምደዋለን፡፡ መከራን ብልግናንና መጥፎነትን ህዝብ እንዳይለምድ ጥያቄ መቅረብ አለበት፡፡ ላለመልመድ ደግሞ በየቀኑ መቃወም ያስፈልጋል፡፡
እንደ ክልል እኛ ክልል ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ነውረኛ ነገር እንዳይፈጠር እናደርጋለን:: ትንሿ ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ ማሳየት አለብን፡፡ ዲሞክራሲን ማስፋት ምህዳሩን ማስፋት ጨዋታ መሆን የለበትም፤ የምር ማስፋት መቻል አለበት:: ሰው ደህንነቱ ተጠብቆ በሰላም የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ሰላማችንን ለመረበሽ የሚንቀሳቀስ ካለ ዋጋውን እንሰጠዋለን፡፡ ማንም ኃይል እኛን አይነካም፡፡ ከድሮም ለመንካት ብዙ ፍላጎት እንዳለ እናውቃለን፡፡ የሰላምን ዋጋ ስለምናቅ ነው ዝም የምንለው፡፡
በእኛ ክልል ህግን ማክበር፣ ዲሞክራሲን ማስፋት የሚለው የቃላት ኳኳታ ሳይሆን የምር የሚደረግ ነው ፌደራል መንግስትም ይህንን ማድረግ አለበት፡፡

__________


        “ዘረኝነትና ፅንፈኝነት መጥፋት አለበት”
           አቶ ክቡር ገና


     ለሁሉም ሀዘን ነው፡፡ ማንም ሰው ያልጠበቀው አደጋ ነው የተከሰተው ፤ነገር ግን ለምንድነው ይሄ አደጋ  የተከሰተው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል:: በቅድሚያ እሱ ጥያቄ ሲመለስ ነው እንደዚህ አይነት ችግር እንዳይደገም ወይም ደግሞ በፍፁም እንዳይታሰብ ማድረግ የሚቻለው፤ በደንብ መጠየቅ አለበት፤ ወደኋላ ሳይባል ሳይፈራ ሁሉም በትክክል ችግሩን ለማግኘት መጣር ይገባዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የነበሩትን ፅንፈኝነት ወይም ደግሞ ዘረኝነት መቀነስና ብሎም ማጥፋት መቻል  አለበት፤ ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡ እንደነዚህ አይነት ሃሳቦችን ፈጽሞ የማንቀበል መሆን አለብን:: መንግስት ህዝብን እንደገና ማስተማር ማስተባበር፤ እንደነዚህ ዓይነት ፅንፈኞችን ማቆም የሚቻልበት ሁኔታ ከበፊቱ የበለጠ ሊሰራበት ይገባል፡፡


___________


           “ይህቺ አገር ከእጃችን ካመለጠች የነገዋ ሊቢያ ነው የምትሆነው”
               አያልነህ ሙላት (ገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት)


      በተፈጠረው ችግር በጣም አዝኛለሁ ያሳዘነኝ ኢትዮጵያውያን እንዲህ አይነት መስዋዕትነት መክፈል አዲስ ነገር ሆኖብን አይደለም፡፡ እቺ አገር እዚህ የደረሰችው እጅግ በርካታ ደሞች ፈሰው፣ በርካታ የሆኑ አጥንቶች ተከስክሰው ነው፤ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያን ያደረጓት፤ የእነዚህም ከእነሱ ጋር የሚደመር እንጂ ተለይቶ የሚታይ አይደለም:: አንደኛ ዛሬ የሃሳብ ጦርነቶች በሚደረጉበት ዘመን ላይ ይሄን የጠመንጃ ትግል ማካሄዱ አሳዛኝ ነው:: ሁለተኛ ይህቺ አገር በተለይም ያ አካባቢ በአንፃራዊነት የመንግስትነት ታሪክን የሚያውቅ ፣በአገር በቀል ዕውቀት አካባቢውንና እራሱን ያዳበረ በብዙ መልኩ ሲታይ ደግሞ በተለያየ ዕውቀት እና ታሪክ ያለፈ ህዝብ ነው፡፡ እዚያ አካባቢ እንዲህ አይነት ደካማና ውርደትን ያስከተለ ነገር መፈፀሙ በጣም ነው ያሳዘነኝ፡፡
እኔ በበኩሌ ምንድነው ይሄ ነገር ብዬ ሳስበው አንድ ነገር ይታየኛል፡፡ ይሄ መፈንቅለ መንግስት ሳይሆን መፈንቅለ መስተዳደር ነው፤ ሰዎች መፈንቅለ መንግስት ነው የሚሉት እሚያሳዝነው እዛ ላይ ነው:: ኢትዮጵያ በአንድ መንግስት ፀንታ የኖረች አገር ዛሬ እንደነዚህ አይነት መፈንቅለ መስተዳደሮችን ገንብታ ገና ዘጠኝ መስተዳደሮች ይጠብቀናል፡፡ የዚህ ሁሉ ችግሩ የሚመስለኝ ኢትዮጵያዊነትን ችላ ብለን፣ መስተዳደራዊ ብሄራዊ ማንነትን አግንነን ብሄራዊ ማንነትን ደግሞ ለፖለቲካ ጥቅም አውለን መገኘታችን ነው፡፡ ነገም ከነገም ወዲያ ኢትዮጵያዊነት የሚለውን መንፈስ ይዘን ካልተራመድን ከችግር አንወጣም፡፡ የምንድንበት ደግሞ በብዝሃነት የበለፀገች ኢትዮጵያ፣ በእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርኣት የታነፀች፣ በቋንቋ ሳይሆን በህጋዊው የፌደራሊዝም ስርዓት ውስጥ የተገነባች አገር ፈጥረን ስናሳይ ብቻ ነው፡፡ ካልሆንን  በየጊዜው ከየመንደሩ የሚወጡ ትናንሽ ዘውድ የደፉ መንግስታት ይባሉ ንጉሶች ይህቺን አገር መበጥበጣቸው አይቀሬ ነው ብዬ ነው ማስበው፡፡
ህዝቡ ዛሬ የተፈጠረውን ችግር መማሪያ አድርጎ ምንም ውዥንብር ውስጥ ሳይገባ፣ ወደ መፍትሄው እንዲሄድ ነው የምጠይቀው፡፡ ዛሬ እንደሚታወቀው አለም በጠቅላላ በጣም የሚያሳዝን ትልቅ እየተዋጋን ያለ፣ ልንቆጣጠረው የማንችለው እርኩስ መንፈስ - ፌስ ቡክ የተባለ (ማህበራዊ ሚዲያ) ከጦርነት በላይ አስጊ የሆነ ጦርነትን የሚያስከትል ኃይል አለው፡፡ ይሄንን ኃይል ወጣቱ በሚገባ በትዕግስት እያየ፣ ኢትዮጵያን ብቻ ሊያድን የሚችልን  እያነበበ እንዲቀጥል እጠይቃለሁ፡፡ ይህቺ አገር አንዴ ከእጃችን ካመለጠች የነገዋ ሊቢያ ነው የምትሆነው:: በጣም አደገኛ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው:: ይሄንን ደግሞ የሚጋብዘው፣ በሌሎች አገሮችም የጋበዘው ይሄ እርኩስ መንፈስ ፣ዘመን ያፈራው፣  ልንቆጣጠረው የማንችለው፣ የወጣቱን ቀልብና ልብ የገዛው ማህበራዊ ሚዲያ የሚባለው ነው፡፡
ህብረተሰቡም ወጣቱን ባለው አቅሙ ልጁን ከነባሩ ዕውቀት ጋር ትንሽ እንዲዛመድ፣ በሽምግልናው እንዲሸመግለው፤ (አገር መሸምገል እንኳን ባይችል) ቤተሰቡን እንዲሸመግል፤ አባት እናት ቤተሰቦቻቸውን እንዲሸመግሉና ተው እንዲሉ፤ በተለይ ይህቺን የቀውጢ ጊዜ በምክክር እንዲያሳልፉ ምኞቴ ነው፡፡
መንግስትን በተመለከተ እነዚህ ሰዎች እውን መስዋዕትነት ሆነውልናል ብሎ የሚያስብ ከሆነ፣አስጊ ሁኔታ ላይ ነን ያለነው ብሎ የሚያስብ ከሆነ፣ ከዚህ ተምሮ አንድ ወደፊት የሚያራምድ ሁኔታ መፍጠር መቻል አለበት፡፡ ከእነዚህ ሰዎች መስዋዕትነት መንግስት ካልተማረ፣ አደጋው በጣም እየበዛ ነው የሚመጣው፡፡
እኔ መንግስትን ሁኔታዎች በጠመንጃ ፍታው የሚል አቋም የለኝም፡፡ ይሄንን መንግስት ከማከብርበት ነገር አንዱ፤ ጥያቄዎች ሁሉ በጠመንጃ፣ በጦርና በጉልበት ይፈታሉ ብሎ አለማመኑ ነው:: እስኪ በዚህ እንሞክረው፣ ጠላቶቻችንን ሞተን እንግደላቸው ብሎ በመነሳቱ እኔ በጣም ክብር አለኝ፤ ነገር ግን እየሞቱም መማር አለ፤ እየገደሉም መማር አለ፡፡ አሁን እየሞትን ነው ያለነው፤ ሞታችን የማያስተምር፤ ከሆነ ሞቱ ዋጋቢስ ነው፡፡ ሞታችን የሚያስተምር አንድ እርምጃ ወደ ፊት የሚያራምድ ከሆነ፣ ነው፤ ጋንዲ እየተደበደበ፣ እየሞተ አራት መቶ አመት የተገዛን ህንድ ነፃ አውጥቷል፡፡ እኛ እንደ ጋንዲ የምንሆን ከሆነ፣ እንደብደብ፣ እንሙት ግዴለም፡፡ ነገር ግን ፊታችን ያለውን ተስፋ ማየት መቻል አለብን፡፡ እልቂትና አገር መበተን ህዝብ መበተን፣ ከሆነ ደማችን ደመከልብ ነው የሚሆነው:: ስለዚህ የወደፊት ተስፋችንን በተግባር ሊያሳየን ይገባል፡፡ ይሄን እያሳየን ብንሞት ችግር የለብንም:: አሁን ጭፍን ያለ ነገር ነው፡፡ በይሉንታ የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ ህዝብ ያመጣውን ለውጥ ለውስን ሰዎች “እናንተ ያመጣችሁት ለውጥ ነው” ብለን ሰጠናቸው:: አሁን እነሱን ነው እያየን ያለነው:: ወደድንም ጠላንም ለውጡን ያመጣው ህዝቡ ነው፤ ወጣቱ ነው ያመጣው፡፡ ወጣቱ ያመጣውን ለውጥ ሰጥተናቸዋል:: ይህንን ለውጥ እንዲያራምዱ ከጀርባቸው ሆነን ልንገፋቸው ይገባል እንጂ ሙሉ በሙሉ ሰጥተናቸዋል ብለን ብቻ መቀመጥ አይገባም፡፡ ንጉሱ፤ ስዩመ እግዚያብሄር ናቸው (እግዚያብሄር ያመጣቸው) ብለን ስላመንን፡፡ መነጋገር አልቻልንም ነበር፡፡ ደርግ በጉልበት የመጣ ነው ብለን ስላሰብን፣ ምንም ማድረግ አልቻልንም፤ በጉልበቱ እስከፈለገበት ድረስ ይግዛን አልን፡፡ እነዚህን እኛ ገፍተን አወጣናቸው፤ከአረንቋ ውስጥ ከበሰበሰ እንቁላል ውስጥ የተወሰኑትን መርጠን፣ ንፁህ እንቁላሎች አወጣን፡፡ እነዚህ እንቁላሎች ተፈልፍለው አውራ እስኪሆኑ፣ ሙሉ እስኪሆኑ ድረስ ለምንድነው ቁጭ ብለን “እናንተ ብቻ ናችሁ የምትሰሩት” ብለን የምንተዋቸው፡፡ አብረን እንስራ እና ይህቺን አገር ከችግር አረንቋ እናውጣት፡፡

______________


              “አልሞትኩም ደህና ነኝ የሚል የሚንፈራገጥ ሃይል ይታየኛል”
                 አርቲስት እሸቱ ጥሩነህ


      የተገዳደልነው ወንድም ለወንድም ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለቱም ቤተሰብ አላቸው - ገዳይም ሟችም፡፡ አንድ ውሳኔ ሲወሰን በእኔ ስር ያሉት ምን ይሆናሉ? ምን ይደርስባቸዋል? ብሎ የደቂቃ ሃሳብ ቢያስብ፣ እንዲህ አይነት ውሳኔ ከመወሰን ያድነዋል:: በየትኛውም መንገድ ብትሄጂ  የኢትዮጵያ ታሪክ በአፄ ዮሃንስ ጊዜ የተደረገው ነው  “የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ሃዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ” የሚለው ነው፡፡ እኛው በእኛው አንዱን ክፉ አንዱን ደግ፣አንዱን አብዮተኛ አንዱን ፀረ አብዮተኛ፣ አንዱን የልማት ሰው፤ አንዱን ፀረ ልማት እያልን ስያሜ እየሰጠነው እስከ ብሄር አድርሰነው፤ መጨረሻችን እርስ በእርስ መተላለቅ ነው፡፡
ከመግደል ምንም ነገር አይገኝም፤ የሞተ ሞተ:: የገደለ ሰው እንኳን ባያየው ህሊናው ሲያሰቃየው ይከርማል፡፡ “primer punishment” የሚል የዶስቶቭስኪ መፅሀፍ ውስጥ የሰው ልጅ ምን ያህል እንደሚፀፀት፣ ምን ያህል እንደሚጎዳ ይገልፃል:: በመግደል አሸንፋለው የሚል ሰው የመጀመሪያ ስህተተኛ ነው፤ ሚፈልገውንም አገኘዋለሁ ካለ ከፍተኛ ስህተት ውስጥ ገብቷል ብዬ ነው የማስበው::
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ፤ ለመግደል የሚያስችል ምን ምክንያት አለ? የሚለውን አስባለሁ፤ አጥጋቢ ምክንያት ምንድነው? ሌላ ጥያቄ እራሴን የምጠይቀው፤ ነፃነትን ማግኘት ለካ አናውቅበትም፤አንድ ሰው ነፃነትን ሲያገኝ መጠቀም የሚችልበትን መንገድ አያውቅበትም፤ ያንን ለበጎ ማዋል ትቶ ለክፉ ነው የሚያውለው፡፡
የእኛ የነፃነት ፍላጎት የት ድረስ ነው? ምህዳሩን ማስፋት ቃሉን እናጣፍጠዋለን፤ ግን የት ድረስ ነው ማስፋት? የሚሰጠው ነፃነት ሌላውን ለማጥፋት፣ ያልተዘጋጀን ለመግደል ከሆነ ከበፊቱ በምን ይለያል? እስር ቤትም ገብተን የወጣን ይሄንን የምንፈፅም ከሆነ ለገዳዩ የተሰጠው ነፃነት እስከ ምን ድረስ ነው የሚለው መታየት አለበት፡፡ በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት የሚለው አይደለም፤ ለብቻ እራስን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ እኔ ማነኝ? ምን ባደርግ ነው የምፈልገውን ነገር ልሰራ የምችለው… ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
አንድ የቻይናዎች ተረት አለ፡፡ “ልጅ ሆኜ አባቴ የሚለኝ ትክክል አይደለም፤ አባት ሆኜ ዛሬ ልጄ የሚለኝ ትክክል አይደለም፤ የትኛው ነው ትክክል?” የሚል ተረት ነው፡፡ ስልጣን ሳይኖረን በፊት “ሌሎች የሚሰሩት ትክክል አይደለም” ስልጣን ካገኘን በኋላ “ያንን የሚቃወሙ ሰዎች ትክክል አይደሉም፡፡” እኛ ገና ነን ክፉዎች ነን፤ የአፍ ሰዎች ነን፤ የተግባር ሰዎች አይደለንም፡፡
የግድ የሚያስማማን የውጪ ጠላት መምጣት አለበት? ታሪካችን እንግዲህ ይሄ ነው:: የውጪ ጠላት ሲመጣ አንድ ነን እንላለን:: የአንድ ሰፈር ውሾች እርስ በእርሳቸው ይጣላሉ የውጪ ውሻ ሲመጣ አብረው ይወጣሉ ይጣላሉ:: እኛ እንደዛ ነን እንዴ? አይደለንም፡፡
ህሊና የት ጋ ነው ያለው? ይሄንን መቋቋም ይህንን መብት ምን ያህል ጊዜ እናስኬደዋለን? ከልጅነት ጀምረን በየሃይማኖታችን እንፀልያለን፡፡ ውሸት ነበር እንዴ? የሰው ምርመራ አይደለም፡፡ በእግዚያአብሄር መመርመር ያስፈልገናል፡፡ የማሰቢያ ብሎናችን አንድ ቦታ ላይ የወለቀ ይመስለኛል፡፡
“ተው ምረር ተው ምረር ምረር እንደ ቅል አልመርም ብሎ ነው ዱባ ሚቀቀል”
የሚል የድሮ አባባል ነው፡፡ መንግስት በጣም ልል ሲሆን የሚመጣው ይሄ ነው፡፡ ይግደል ይፍለጥ አላልኩም፡፡ የመቆጣጠር  አቅም ግን ያስፈልጋል:: የሰኔ 16 በዓልን በዚህ አይነት ድርጊት ማሳለፍ የሚፈልጉ እኩይ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች አሉ ብዬ ነው የማስበው፡፡ ምናልባት ዝም ከተባሉ፣ የሚቀጥለው ዓመትም እንዲሁ ሊያደርጉ ይችላሉ፤ አመታቸውን ለማክበር፡፡ ሌላው “አልሞትኩም ደህና ነኝ” የሚል የሚፈራገጥ ሃይል ይታየኛል፤ ይህም አንዱ ነው፡፡ ይቅርታ የምናደርገው የት ድረስ ነው? የሚለውን ጠ/ሚኒስትሩን መጠየቅ እፈልጋለሁ፤ የአገር ኢታማዦር ሹም በአንድ ግለሰብ ተገደለ ማለት አፍነውት ሊወስዱትም ይችላሉ ማለት እኮ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ክፍተት አለ፡፡ ይህንን ክፍተት መሙላት የሚቻለው መረር ሲባል ነው፡፡ ሙሼ ባያ የሚባል ደራሲ ድሮ “ ሰላም ያልገዛውን ነፃነት ኃይል ይገዛዋል” ይላል፤ሰላም የሚፈልግ ሰው የሚቋቋመው አቅም ከሌለው መጫወቻ ነው የሚሆነው፡፡
ህዝቡ ወይ ከዚህ መከራ አውጣን ብሎ፤ ይፀልይ እንጂ “ይዋደድ፣ ይስማማ ፣ፍቅር ያሸንፋል”  ተብሎ ተብሎ አልቋል፡፡ ህዝቡ አትግደሉን ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ ይውጣ? የሚገለው እኮ አይታይም፡፡ መንግስት አልገደለው፤ ማን ላይ ነው ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጣው? አጠገብሽ ያለ ሰው ላይ እንዴት ሰላማዊ ሰልፍ ይወጣል? እምነት የት ድረስ ነው አጠገባቸው ያለ ጠባቂ ሲገል እየታየ ቅጥር ጠባቂ ከሌላ አገር አናመጣ መቼም፡፡ ድሮ ለማህተቡ የሚሞተው ሰው ዛሬ የት ሄደ?


______________


            “አሁን የተፈጠረው የማንቂያ ደውል ነው፤ በትኩረት ሊታይ ይገባል”
                አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ


       እኔ ባገኘሁት አጋጣሚ ለራሳቸው ለመንግስት አካላት በፅሁፍም ጭምር ነግሬያቸዋለሁ፡፡ ይሄ ሃገር እጅግ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ሁኔታው እንዲሁ ዝም ብሎ በዋዛ በፈዛዛ የሚቃለል አይደለም፡፡ በውይይት ነው፡፡ ኤክስትራ ኦርድነሪ ችግር የተሸከመ አገር ነው፡፡ ችግሩ ደግሞ መዋቅራዊ ነው፡፡ የፖለቲካ ብቻ አይደለም፡፡ ስትራክቸራል የሆነ የኢኮኖሚ ፕሮብሌም አለው፡፡ የፖለቲካውን አቃልላለሁ ብሎ ሙከራ ቢያደርግም፤ ቢጀመርም በኢኮኖሚ ባለው ችግር የተነሳ አገር ሊናጋ ይችላል፡፡ ሰባ ሰማንያ በመቶው ወጣት ሥራ አጥ በሆነበት አገር ላይ የፖለቲካ ማሻሻያ እየሰራሁ ችግር አቃልላለሁ ማለት አይቻልም፡፡ በየቀኑ የህዝብ ህይወት፣ ግሽበት እያሻቀበ እየደቀቀ ባለበት አገር ላይ ፖለቲካውን ብቻ አቃልላለሁ ማለት አይቻልም፡፡ ፖለቲካውም ግን ከፍተኛ መዋቅራዊ ችግር አለው፡፡ ያንን መዋቅራዊ ችግር ከምር ወስዶ ለመመርመር፣ ችግሩን ለመፍታት የሚችል የፖለቲካ አመራር ስልጣንን ከያዘ፣ ይሄንን ተረድቶ የፖለቲካ ተቃዋሚው በዚህ መንገድ እንዲመረመር ጥያቄ የሚያቀርብ ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ ያለዚያ ማንም የሚተርፍ የለም፡፡ ሁሌም እንደምናገረው ተያይዞ ወደ ሲኦል የሚሄድበት መንገድ ክፍት ነው፡፡ አሁንም ክፍት ነው ይሄ ሰሞኑን የምናየው የሲኦል ደረጃዎች ነው፡፡ አንድ ሁለት ደረጃዎች ነው የተመለከትነው፡፡ ወደ ቁልቁል የሚወስደን ደረጃ ነገር ግን ይሄ አገር ያለበትን ጠንካራ ችግር ከምር ወስዶ በአንድ ላይ እንደ አንድ ሰው ቆሞ ለመፍታት የሚደረግ አገራዊ ሁኔታ ሳይፈጠር፣ በተፎካካሪ ፖለቲካ የሚፈታ ችግር አይደለም፤ እስከማለት ደርሻለሁ፡፡ አጠቃላይ የአገሪቷን ዜጎች የፖለቲካ ድርጅቶች ሙሉ ትብብር የሚጠይቅ ነው አንዱ ድርጅት ከስሮ ሌላው የሚያተርፍበት፣ አንዱ ህዝብ ጠፍቶ ሌላው የሚድንበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ጨርሶ የለም፡፡ ሁሉንም ይዞ መቀመቅ ነው የሚያወርደው፡፡ ከዳንም በአንድ ላይ ነው የምንድነው፡፡
ይሄንን የሚያስረዳ አይነት ውይይት አላይም፡፡ በየመድረኩ ይሄንን የሚያስረዳ ኮንሰርን በየፖለቲካ ድርጅት አላይም ስልጣን በያዘውም ቢሆን ነገሮች እንዲህ በቀላሉ በሂደት የሚቃለል ነገር ችግር አይደልም እዚህ አገር ላይ ያለው፡፡ ይሄ የማንቂያ ደውል ነው፡፡ አሁን የሆነው በትኩረት ሊታይ ይገባል:: ደወሉ ለመንግስት ብቻ አይደለም፤ ተቃዋሚውም ህዝቡንም ይጨምራል፡፡ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡


______________



            “እግዚአብሄር እንኳን ከቅኖች ጋር ቅን ነው፤ ከጠማሞች ጋር ጠማማ ነው”
               ነብይ ዮናታን አክሊሉ


     የመጀመሪያው ነገር ክፋት በክፋት አይሸነፍም፤ ጥላቻም በጥላቻ አይገደብም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አገራችን በሚቀጥለው ዘመን ማድረግ ያለባት ነገር፣ እስካሁን ድረስ ለዕድገቷ ሳይሆን ለድህነቷ፣ ለብልጽግናዋ ሳይሆን ለኋላ ቀርነቷ ስትጓዝ የነበረውን፣ ተስፋ አልባ ጉዞ ማቆም አለባት:: በመገዳደል ፣በመጠፋፋት የሚያምኑ ሰዎች በራሳቸው ዘመን የፖለቲካ ቁማር የተበሉና የወጣቱን ነብስ አስይዘው ማስመለስ የሚፈልጉ የተሸነፉ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሃገር ከምንም ነገር ትበልጣለች፤ ኢትዮጵያ ብዙ ሃገሮች እንደ ሃገር ሳይቆጠሩ ስም ያላት ሃገር ነበረች፡፡ ይሄ ሰዓት ከቂም ውርስ ወጥተን ለስልጣኔ ለአዳዲስ እድገት አዕምሯችን፣ ልባችንን የመክፈቻ ጊዜ ነው:: አሁን፤ ቂሙ ምንም አይጠቅምም፤ የቴክሎኖጂ ውርስ ነው የሚጠቅመን፣ አሁን የስልጣኔ ውርስ ነው  የሚጠቅመን፡፡ አሁን ግን በተለያየ አቅጣጫ እየተነገረ ያለው ቂም ነው፡፡ አባቶቻችን አያቶቻችን ከጥንት ጀምሮ ሲናገሩ የነበሩት፣ ቂም ለማንም እንደማይጠቅም ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ስናስባት፡ በጄኔራሉ ፊት ሰላምታ እየሰጠ እንደሚያልፍ ሰራዊት ከትንሽ እስከ ትልቅ፣ ከልጅ እስከ ደቂቅ ፣ ከህፃን እስከ ባለስልጣን ያልፍ ይሆናል እንጂ አገራችን ኢትዮጵያ አታልፍም፡፡ ኢትዮጵያ የተሰራችበት ድርና ማግ እንዲሁ በቀላሉ በሰነፎች ምክር የሚበተን አይደለም፡፡ አገራችን ስትገነባ የተገነባችበት ማህበራዊ እሴት አላት፡፡ የሃይል ክብር አላት ያንን እሴታችንን ጠብቀን ሃይማኖታችንን አክብረን መቀጠል ነው ያለብን፡፡ ጥላቻ ለማንም አይጠቅምም ፣ቂም ለማንም አይጠቅምም፣ ክፋት ለማንም አይጠቅምም፡፡ አባወራ አጠፋ ተብሎ ቤተሰብ ይበተን አይባልም ቤት ይፍረስ አይባልም  ክፉም ደግም የሚያደርገው ቤት ውስጥ ነዋሪው እንጂ ቤቱ አያጠፋም፡፡ ቤት እራሱ አይወቀስም፡፡ አገርም እንዲሁ፤ አንድ ከብት ባጠፋው በረት ይነቀል አይባልም፡፡ በመግደል ወይም በማጥፋት ወደ ስልጣን ለመምጣት መፈለግ ማለት ካፒቴኑን እንደ መግደል መርከቡን እንደ ማስጠም ያለውን ስትራቴጂ የሚከተሉ ሰዎች አካሄድ ነው፡፡ መወያየት በሃሳብ ማሸነፍ የተሻለ አመለካከት ይዞ መቅረብ… ይሄንን ዘመን የሚመጥን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
እግዚያአብሄር እንኳን ከቅኖች ጋር ቅን ነው፤ ከጠማሞች ጋር ጠማማ ነው፡፡ ለሌሎች ሰዎች  መኖር ስጋት የሆነውን፣ ህገወጥነት… መንግስት መከላከል አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን በተፈጠረው ነገር ሳይደናገጡ የመንግስት አካላት ያመናቸውን ህዝብ እምነት ማስጠበቅ፤ እና ማስቀጠል መቻል አለባቸው፤ በያዙት መቀጠል አለባቸው፡፡ ይሄ ለውጥ እንዲደናቀፍ የሚሰሩ ብዙ ሰዎች እንዳሉ የታወቀ ነው ይሄንን ለውጥ እኔ የማስቀምጥበት ምሳሌ፤ ልጅ ሲወለድ ከቆሻሻ ጋር ነው የሚወለደው፣ ከደም ጋር ነው የሚወለደው፤ የወደደው ያጥበዋል፤ የጠላው ያንቀዋል፡፡ ይሄንን ለውጥ የወደዱት ያጥቡታል፤ ያሳድጉታል ለተሻለ ነገር ያደርሱታል:: እኛም ማድረግ ያለብን  አንዳንድ ካለበት ውስን እንከኖች የተነሳ ለማናናቅ መሯሯጥ አይደለም፡፡ አጥበን አሳድገን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ትልቅ እመርታ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል፡፡ ለውጡ ለአገራችን በጣም አስፈላጊና ፋና ወጊ ነው ብዬ አምናለሁ፤ ስለዚህ ማህበረሰቡ ማሰብ ያለበት ለውጥ ሲመጣ ከችግሮች ጋር ነው፤ ልክ ልጅ ሲወለድ ከደም ጋር እንደሚወለድ፤ ህፃን ልጅን ማንም አቅፎ የሚስመው ነርሷ አጥባ ጠርጋ ስላመጣችው ነው፡፡ እኛ የሳምነው ሌሎች ሰዎች ዋጋ ከፍለው ያሳደጉትን ልጅ ነው፡፡ ለውጥም እንደዚሁ ነው፤ ከነገሮች ጋር ከአንዳንድ ውስንነቶች ጋር ይወለዳል፤ የጠላው ያንቀዋል፤ የወደደው ያጥበዋል ያሳድገዋል፡፡ ማህበረሰቡ ተንከባክቦ ማሳደግ ይጠበቅበታል፡፡ መታገስ መቻል አለበት፡፡ መንግስት ደግሞ ህዝብ በሰጠው አደራና በተሰጠው እምነት ላይ ቆሞ የህግን የበላይነት እያስከበረ ያለምንም ማመንታትና ወደ ኋላ ባለማለት መቀጠል መቻል አለበት፡፡



______________



            “የማይጠፋ መብራት ማምጣት እምንችለው አንድ ስንሆን ነው”
                የክብር ዶ/ር ተስፋዬ አበበ(ፋዘር)


     እድሜ መስታወት ነው፡፡ እኔ ብዙ አሳልፌያለሁ:: በደርግም በኃ/ስላሴም፡፡ የአሁኑ ግን ፈር የለቀቀ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ለምን? ለማን? ለአገር ነው? ለማነው? …የሚለው አጠያያቂና አነጋጋሪ ነው፡፡ አንድ ብሄር ብሄረሰብ ላይ መናቆር፣ የአንድ ማህፀን ልጆች የአንዳቸው ደም ከአንዳቸው ደም ጋር አብሮ ያለ፣ በታሪክ የተቆራኘ በትውልድ የተሳሰረ፤ የአንደኛው ሚስት ከኦሮሞ ነች፤ የአንዷ ባል ከአማራ ነው፤ ከትግራይ ነው፤ እውነቱ እየሆነ… ይሄ በዘር መባላት በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ ከየኢትዮጵያን ታሪክ አለመማር ይመስለኛል፡፡ ሺ አመት ስትኖር ኢትዮጵያ አንድም ቀን ያለታሪክ ያለወርቃማ ገድል አላለፈችም፡፡ የምናውቀው ይሄንን ነው፡፡  አሁን ያለውን ህገወጥነት ይሄንን ፈር ማስያዝ ያስፈልጋል:: አንደኛ ህገ መንግስታችን አለ፤በአፍሪካ አንደኛ የተባለ መሪያችን አለ፡፡ ለምንም ለማንም የማይበገር በሚሊተሪ የዳበረ ወታደር አለን፡፡ በሳይንስ የካበተ በወንጀል መከላከል እራሱን ያካበተ የፖሊስ ሃይል አለን፡፡ ምሁራን አሉን፡፡ ከዩንቨርስቲ የሚመረቱ፡፡
ይሄ ሁሉ እያለን የተጋረጠብንን ችግር እንዴት ማቆም ያቅተናል? ከጨከንን ይቻላል፡፡ እኔ ሁሉም በአንድነት ወደ ስራ አልገቡም ነው የምለው፡፡ ዳር ዳር የሚሮጠው ሁሉ ወደ ስራ ይግባ እናም የትላንቷን ኢትዮጵያ በትብብር እንደገና ይመስርቷት፤ ለውጤት ለፍሬ ያብቋት፡፡
በአዲስ አበባም በክልልም ያለው ህዝብ፤ እራሱን ለሰላም መሰዋት አለበት፡፡ የሰላምን ጣዕም ለአዲሱ ትውልድ ማስተማር አለበት፡፡ ከሰል ማራገብ አይደለም፤ በተለይ  በየሃይማኖት አባቶች፣ ወላጅ አባቶች፣መምህራን፣ዕድሮች፣ ሽማግሌዎች እነዚህ ሁሉ ወጣቱን በደንብ ማስተማር አለባቸው:: በወጣቱ ላይ ትልቅ ችግር እየተፈጠረ ያለው፡፡ ወጣቱን ሰላም ማስታጠቅ ያስፈልጋል፤ ጠመንጃና ጩቤ አይደለም የሚያስፈልገው፡፡
ይህቺ አገር ገና ደረቷ እየሳቀ፣ ጀርባዋን እያከከች ያለች ሃገር ነች፡፡ ይህችን አገር ወርቅ እናልብሳት እያልን እየጮህን፣ ወጣቱ ትውልድ ገደል ውስጥ እንዳይገባ ከገደል አፋፍ መመለስ ያስፈልጋል፡፡
መንግስት ሁኔታዎችን መስመር ማስያዝ ይገባዋል፡፡ መስመር ያልያዙ ነገሮች አሉ፡፡ እነሱን መስመር ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ያሉ አመራሮችን ፈር ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ ዶ/ር ዐቢይን የመሰለ መሪ እያለን ሁላችንም ለጥፋት ሳይሆን ለልማት መቆም ነው ያለብን፡፡ እሳቸው የአገሪቱን አቅጣጫ መቀየስና ለህዘቡም ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የማትጠፋ መብራት ለዚህቺ አገር ማምጣት እምንችለው ሁላችንም አንድ ስንሆን ነው::


Read 5257 times