Tuesday, 02 July 2019 11:37

በመፈንቅለ መንግስትና በባለሥልጣናት ግድያ ተጠርጥረው የተያዙት ከ250 በላይ ደርሰዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

 የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ነው ከተባለውና የአማራ ክልል አመራሮችንና የመከላከያ ኢታማዦር ሹምና ባልደረባቸውን ህይወት ካሣጣው ክስተት ጋር በተገናኘ በባህርዳርና በአዲስ አበባ ከ250 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡
ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት በባህርዳር ከተማ በስብሰባ ላይ ነበሩ በተባሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ በክልሉ የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴና በክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደ ላይ ከተፈፀመው ግድያ በተጨማሪ በተኩስ ልውውጡ 16 የፀጥታ ሀይሎች መገደላቸውም ታውቋል፡፡
ባህርዳር ላይ ከተፈጠረ ክስተት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ሊኖረው ይችላል በተባለውና ባህርዳር ላይ የክልሉ አመራሮች ከተገደሉ ከሰዓታት በኋላ አዲስ አበባ ላይ የተገደሉትን የኢፌድሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰአረ መኮንን እንዲሁም ጡረተኛው ሜ/ጀነራል ገዛኢ አበራን ጨምሮ ከዚህ ክስተት ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ 13 አመራሮችና የፀጥታ ሃይሎች ህይወት ሊያልፍ መቻሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከዚህ ድርጊት ጋር በተያያዘም በአዲስ አበባ 45 ያህል እንዲሁም በባህር ዳር የክልሉን የልዩ ሃይል አዛዥ ብ/ጀነራል ተፈራ ማሞና የክልሉ የፀጥታና ሠላም ቢሮ ም/ኃላፊ ኮ/ል አለበል አማረን ጨምሮ 178 ያህል ተጠርጣሪዎች መታሠራቸውን ተጠቁሟል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፤ በአዲስ አበባ 56 አባላት እንደታሰሩበት አስታውቋል:: በአዲስ አበባ ከታሰሩት ሁለቱ የአዲስ አበባ ባለአደራ ም/ቤት አባላት እንዲሁም ሁለቱ ጋዜጠኞች መሆናቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹን ፍ/ቤት አቅርቦ የ28 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የተፈቀደለት ፖሊስ፤ ተጠርጣሪዎቹ ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለመናድ በሽብር ተግባር ተሳትፈዋል፣ በመፈንቅለ መንግስት ሙከራውና በአዲስ አበባ ወታደራዊ መኮንኖች ግድያ ላይ ተሳትፈዋል በሚል ጠርጥሮ እንዳሠራቸው አስረድቷል፡፡
በአዲስ አበባ ታስረው ፍ/ቤት ከቀረቡት መካከል የ“በረራ” ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ፣ በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የሚመራው የአዲስ አበባ ባለአደራ ም/ቤት አባል የሆኑት ስንታየሁ ቸኮልና አቶ መርከቡ ሃይሌ የሚገኙ ሲሆን የኮሌጅ መምህር የሆኑት አቶ ጌድዮን ወንድወሰንም ፍ/ቤት ከቀረቡት ተጠርጣሪዎች መካከል ይገኙበታል፡፡
ሌላው የ28 ቀን የምርመራ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው የጀነራል ሰአረ መኮንንና የሜ/ጀነራል ገዛኢ አበራ አስከሬን ሽኝት ሲከናወን የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ባሉበት ሥፍራ ጥቃት ለማድረስ መሣሪያ ይዘው ተገኝተዋል ተብለው የታሠሩት አቶ ሃየሎም ብርሃኔ ናቸው:: በባህርዳር የታሠሩ በርካታ ተጠርጣሪዎች ፍ/ቤት ቀርበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደተጠየቀባቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በስብሰባ ላይ ሳሉ ተኩስ ተከፍቶባቸው እንደተገደሉ የተገለፀው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ የርዕሰ መስተዳድሩ የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴና የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደ የቀብር ስነስርዓት በባህርዳር ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ረቡዕ ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን ጥቃቱን አስተባብረዋል፤ መርተዋል የተባሉት የክልሉ የሰላም የፀጥታና ደህንነት ሠላም ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ብ/ጀነራል አሳምነው ጽጌ የቀብር ስነስርአትም በእለቱ በላሊበላ ቤተ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡
ራሱን አቁስሎ በህክምና ላይ በሚገኘው ጠባቂያቸው የተገደሉት የመከላከያ ሠራዊት ኤታማዣር ሹም ጀነራል ሠአረ መኮንንና በጡረታ ላይ ይገኙ የነበሩት ሜ/ጀነራል ገዛኢ አበራ የቀብር ስነስርዓትም በመቐሌ ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ.ም ተፈፅሟል::


Read 6972 times