Print this page
Tuesday, 02 July 2019 11:36

ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ አንድነት በጋራ እንዲቆሙ የአሜሪካ መንግስት ጥሪ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 በአማራ ክልል አመራሮችና በመከላከያ ኢታማዦር ሹም ላይ የተፈፀሙ ግድያዎችን በጥብቅ እንደሚያወግዝ የገለፀው የአሜሪካ መንግሥት፤ ኢትዮጵያውያን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለሀገራዊ አንድነታቸው በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ አቀረበ፡፡
በአመራሮቹና በወታደራዊ መኮንኖቹ ላይ የተፈፀመው ግድያ ጉዳቱ ለቤተሰቦቻቸው ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱም ትልቅ ጉዳትና ኪሣራ ነው ያለው የአሜሪካ መንግሥት፤ ጥቃቱም የአመራሮቹን ህይወት ከመቅጠፉም ባሻገር በመንግስት ተቋማትና አመራሮቹ ባገለገሏት ሀገር ላይ የተፈፀመ መሆኑን በመግለፅ በክስተቱ ተሰማውን ሃዘን ገልጿል፡፡
መሰል ጥቃቶችን በመፈፀም በብጥብጥና ሁከት የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈታተኑ ወገኖች በቀጥታ የሚፃረሩት የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም ነው ያለው የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያውያን ይህን ተገንዝበው እንደሚደግፉ አስታውቋል፡፡ ከምንም በላይ ለሀገራዊ አንድነታቸውና ለፖለቲካዊ መሻሻሎች በጋራ እንዲቆሙ ጠይቋል፡፡
ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት እያካሄደች ያለችው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች ብልጽግናና ፖለቲካዊ አካታችነትን ለማምጣት አስተማማኝ መንገድ መሆኑን የገለፀው የአሜሪካ መንግስት መግለጫ፤ ለዚህ እውን መሆንና የበለፀገች ሃገር ለመፍጠር ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉትን ጥረት በብርቱ እንደሚደግፉ አስታውቋል፡፡

Read 4890 times