Print this page
Tuesday, 02 July 2019 11:35

ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በመቀሌ ጥቃት ተፈፀመባቸው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  በጦር ሃይሎች ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዐረ መኮንን እና በብ/ጀነራል ገዛኢ አበራ የቀብር ስነሥርዓት ላይ ለመካፈል ወደ መቀሌ ተጉዘው የነበሩት አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በወጣቶች ጥቃት ተፈፀመባቸው::
የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ሊቀመንበር የሆኑትና ከ48 አመታት የስደት ህይወት በኋላ በለውጡ ማግስት ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፤ በ“ወጣቶች የመንጋ” ጥቃት እንደተሞከረባቸው ተናግረዋል፡፡
የቀብር ሥነሥርዓቱ ላይ ለመገኘት በመቀሌ ሰማዕታት ሃውልት ደጃፍ ላይ ስደርስ በአካባቢው የነበሩ ወጣቶች “መግባት የለበትም” የሚል ሁከት ፈጠሩ የሚሉት ዶ/ር አረጋዊ፤ በዚህ ሳያበቁ ጥቃት ሊያደርሱባቸው እንደሞከሩ ጠቁመው፤ የጐላ አካላዊ ጉዳት ሳይደርስባቸው የክልሉ ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ ሊታደጋቸው እንደቻለ ገልፀዋል፡፡
ሁከቱን ተከትሎ በተፈጠረ ግርግር መሃል ከወጣቶቹ ድንጋይ መወርወሩንና በድንጋይ ውርጅብኝ የፖሊስ አባላትና ተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም ተናግረዋል፡፡
ይህን ግርግር ለማስቆምም ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ እስከመጠቀም መድረሱንና ከግርግሩ በኋላ ዶ/ር አረጋዊ በርሄን ፖሊስ ወደ ጽ/ቤቱ በመወሰድ በእንግዳ ማረፊያ ክፍል እንዲቆዩ ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
“ችግር ካጋጠመኝ በኋላ ፖሊሶች ሁኔታውን ለማረጋጋት እኛን ወደ ኩጆ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን” የሚሉት ዶ/ር አረጋዊ ኋላም እዚያው ፖሊስ ጣቢያ አሳድረዋቸው ጠዋት መቀሌ አሉላ አባነጋ አውሮፕላን ድረስ በራሣቸው አጀብ እንዳደረሷቸው ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
እኛ የቀብር ስነስርዓት ላይ ለመሳተፍ ነው ወደ መቐሌ የተጓዝነው የሚሉት ዶ/ር አረጋዊ የጠበቅነው የቀብር ስነስርዓት ቢሆንም በቦታው ስንደርስ የገጠመኝ የፖለቲካ ቅስቀሳ እና ስድብ ነው ብለዋል፡፡
በባህላችን ለቀብር የተሰባሰበ ሰው በእርጋታ እና በጥሞና ሃዘኑን ሲገልጽ ነው” ያሉት ዶ/ር አረጋዊ በቦታው አስከሬን ተቀምጦ ከሃዲ፣ ባንዳ የሚሉ ስድቦች ናቸው የገጠሙን ብለዋል፡፡
የተደረገው ድርጊት ከባህል ያፈነገጠ፣ የብልግና እና የወራዳነት ተግባር ነው ብለዋል - ዶ/ር አረጋዊ:: ድርጊቱም ጨዋውን የትግራይ ህዝብ እና ወጣት የማይወክል የጥቂት ቡድኖች ፀያፍ ድርጊት ነው ያሉት ዶ/ር አረጋዊ እኛ በዚህ ሳንደናገጥ እየሞትንም ቢሆን ድንጋይ እየተወረወረብን ትግላችንን ስርአቱ እስኪቀየር ድረስ እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
ዶ/ር አረጋዊ ባለው ሐሙስ ሰኔ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ በአውሮፕላን ተመልሰዋል፡፡

Read 5492 times