Tuesday, 02 July 2019 11:34

በምዕራብ ወለጋ ከተሞች የታጠቁ ሃይሎች እያደረሱ ያለውን ጥፋት የሚቃወሙ ሰልፎች ተካሄዱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

መንግስት ህግ እንዲያስከብር ተጠይቋል


      በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን የተለያዩ ከተሞች ውስጥ ታጣቂ ሃይሎች እያደረሱ ያለውን ጥፋት በመቃወም ሰሞኑን ነዋሪዎች ሠላማዊ ሠልፍ አድርገዋል፡፡ መንግስት ህግ እንዲያስከብር የጠየቁት ሰልፈኞቹ፤ በአማራ ክልል አመራሮችና በፌደራል መከላከያ ሠራዊት ኢታማዦር ሹም ላይ የተፈፀመውን ጥቃትም አውግዘዋል፡፡ ሠላማዊ ሰልፈኞቹ በዋናነት በኦነግ ስም በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ሃይል ከግድያና ሽፍትነት ተግባሩ እንዲታቀብ ጠይቀዋል፡፡
በምዕራብ ወለጋ ቦነያ ቦሼ፣ ሊሙ፣ ሃይሊሙ፣ ጉምባ፣ ዋዩ ጡቃ፣ ቄለም ወለጋ፣ ኢሉባቡር፣ ነጆን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞችና ወረዳዎች ባለፈው ረቡዕ በተደረጉ ሠላማዊ ሠልፎች “ጦርነት ይብቃን፣ እርስ በእርስ መገዳደል ይቁም” የሚሉ መፈክሮች ተደምጠዋል፡፡
“መንግስት ህግ በማስከበር ኃላፊነቱን ይወጣ” ያሉት ሠልፈኞቹ፤ በኦነግ ስም በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አፈና፣ ግድያና ሴቶችን መድፈር በአካባቢው እየተፈፀመ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
“ለኦሮሞ እንቆማለን የሚሉ የታጠቁ ሃይሎች በአርሶ አደሮች ላይ ከፍተኛ ዝርፊያና ጥቃት እያደረሱ መሆኑን የገለፁት ሠልፈኞቹ፤ “ሴቶች ከቤታቸው እየተወሰዱ ይደፈራሉ፣ ምንጭ ወርደው ውሃ መቅዳትና ቤተሰባቸውን ማስተዳደር አልቻሉም ሲሉ አማረዋል፡፡
ሠልፈኞቹ “ኦሮሞ ከኦሮሞ እርስ በራሱ መገዳደል ማቆም አለባት፤ ለኦሮሞ ህዝብ እኔ የበለጠ አውቅልሃለሁ ማለት ተቀባይነት የለውም” ብለዋል፡፡
ባለመረጋጋትና ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰትን እያስተናገደ ባለው የምዕራብ ወለጋ አካባቢና በመላ ሀገሪቱ መንግስት ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣም ሰልፈኞቹ በመፈክራቸው ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ሠልፈኞቹ በአማራ ክልል አመራሮችና በመከላከያ ኢታማዦር ሹምና ባልደረባቸው ላይ የተፈፀመውን ግድያ በጽኑ አውግዘዋል፡፡


Read 4324 times