Tuesday, 02 July 2019 11:32

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ም/ቤት ከ3 ዓመት በኋላ ህጋዊ እውቅና አገኘ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ከ3 አመት በፊት የተመሠረተው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ከሰሞኑ ከበጐ አድራጐትና ማህበራት ኤጀንሲ እውቅና አግኝቷል፡፡
በጥር 2008 ዓ.ም የግልና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ተቋማትን ጨምሮ የጋዜጠኝነት ሙያ ማህበራትን አካቶ በአዲስ አበባ የተመሠረተው ምክር ቤቱ ላለፉት 3 ዓመታት አስፈላጊውን እውቅና ሳያገኝ ቆይቷል፡፡
ዋነኛ አላማውን የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርን በኢትዮጵያ ውስጥ ማስጠበቅ አድርጐ የተቋቋመው የሚዲያ ምክር ቤቱ፤ በህዝብ ተአማኒ የሆኑ መገናኛ ብዙሃንን በማጐልበት ላይ ይሠራል ተብሏል፡፡
የመገናኛ ብዙሃን ም/ቤቱን የማቋቋም ሃሳቡ የተጠነሰሰው በ1996 ዓ.ም መሆኑን ለአዲስ አድማስ የጠቆሙት የካውንስሉ ስራ አስፈፃሚ አባል ጋዜጠኛ ታምራት ሃይሉ በጉዳዩ ላይ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይቶ በ2008 ጥር ወር ላይ እውን ቢሆንም በወቅቱ የነበረው እውቅና ሰጪ አካል ለመመዝገብ ፍቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን አስረድተዋል፡፡
አሁን በተሻሻለው የበጐ አድራጐትና ማህበራት ምዝገባ አዋጅ፤ ሊመዘገብ መቻሉንም ጋዜጠኛ ታምራት አስታውቀዋል፡፡
የመገናኛ ብዙሃን ም/ቤቱ 29 የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶችና ማህበራት በአባልነት መመዝገቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በቀጣይ የም/ቤቱ አባል ለመሆን የሚፈልጉ የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች እና የሙያው ማህበራት ህጋዊነታቸውን የሚያረጋግጥ ሰርተፊኬት በማቅረብና የመተዳደሪያ ደንቡን በመፈረም አባል መሆን እንደሚችሉ ጋዜጠኛ ታምራት አስረድተዋል፡፡
ም/ቤቱ በቀጣይ የጋዜጠኝነት ስነ ምግባርን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማስጠበቅ በዋናነነት የጋዜጠኞች የሙያ ብቃትን የሚያጐለብቱ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥም ለማወቅ ተችሏል፡፡ መንግስትም ህግን በማስከበር ሰበብ በሆነ ባልሆነው በፕሬሱ ነፃነት ላይ የሚያሳርፈውን ጫና እንዲያነሳም እታገላለሁ ብሏል ም/ቤቱ፡፡
የመገናኛ ብዙሃን ም/ቤቱን የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አቶ አማረ አረጋዊ እንዲሁም የሸገር ሬዲዮ ባለቤት ወ/ሮ መዓዛ ብሩ በፕሬዚዳንትነት በም/ፕሬዚዳንትነት የሚመሩት ሲሆን ም/ቤቱ 5 የሥራ አስፈፃሚ አባላትም አሉት፡፡


Read 3791 times