Saturday, 09 June 2012 06:45

ቴዲ አፍሮ - ለእኔ “ጥቁር” ነው!

Written by  ታደሰ አ
Rate this item
(1 Vote)

ጥቁር ሰው ጠይም ቢሆንስ? ይሁና!

ይህ ፅሁፍ “ቴዲ አፍሮ የዘመኑ ጥቁር ሰው” በሚል ርእስ ባቀረብኩት ፅሁፍ ላይ ባለፈው ሳምንት አቶ አለሙ “ጥቁር ሰው ጠይም ቢሆን ጀግንነቱ ይጠፋል” ብለው ያቀረቡትን የመልስ አስተያየት መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ፀሀፊው ጥሩ አድማጭ ናቸው፡፡ በአንድ መጣጥፍ ሙሉውን አልበም መዳሰስ በጣም ከጥቂቶች ብቻ የሚገኝ ፀጋ ነው፤ “ከጥቁር ሰው” እስከ “ጨዋታሽ” ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መመርመርና መልስ መስጠት መቻል አቅምን ይጠይቃል፡፡ ምንም እንኳን ግጥም ቁጥብ እና እምቅ በመሆኑ ሁሉም ላይ በጥልቀት መሄድ ባይችሉም፡፡

እኔ ግን አስተያየታቸውን እያነበብኩ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የነበሩት ደበበ ሰይፉ አንድ ቀን ሲያስተምሩ ለተማሪዎቻቸው አንድ ነገር አነሱ፡፡ ከተማሪዎቹ መሀል አንዲት ቀጭን ልጅ አስነሱና ፊት ለፊት አቆሟት፡፡ ከዚያ ሌሎቹን ተማሪዎች እስኪ ይህችን ልጅ አወድሷት ይላሉ፡፡ ተማሪዎቹም ለግላጋ፣ ሀረግ፤ ችቦ ወገብ አሉና አቆሙ፡፡

መምህሩ ቀጥሉ ቢሉም ተማሪዎቹ አልቻሉም፡፡ ቀጥለው ደግሞ እስኪ ስደቧት አሉ፡፡ ጀመሩ ተማሪዎቹ፡- ቋንጣ፣ ወስፌ፣ ክር አንገት፣ ደራቆት፣ ጣውላ፣ ወሰላ እግር… ቀጠለ፡፡ መምህሩ አስቆሟቸው፡፡ ቀጥለው አንዲት ወፈር ያለች ተማሪ አስወጥተው ፊት ለፊት አስቆሙና የመጀመሪያው አይነትን ጥያቄ ጠየቁ፡፡ ለምስጋናው ድንቡሽቡሽ፣ ብርቱካን፣ ሞንዳላ አሉና ከዚያ በላይ ማለፍ ሳይችሉ ቀሩ፡፡

ስድቡን ሲጀምሩ ደግሞ ድብልብል፣ ዱባ፣ አሳማ፣ ዝሆን፣ ወደል፣ ዝርክት… አሁንም አስቆማቸው፡፡ ከዚያም እንዲህ አሉ፤ አያችሁ የተሰራንበት ማህበረሰብ በቂ የስድብ እንጂ የውዳሴ ቃላት የሉትም አሏቸው፡፡ እስኪ እናንተም በውስጣችሁ ስድብና ውዳሴን አስቡ!

 

ጥቁር ሰው ጠይም ቢሆንስ?

ይሁና! በእኛ አገር ሰዎችን ጥቁር ጠይም፣ ቀይ ብለን እንመድባለን፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ጥቁር ነኝ፡፡ ይህ ሁኔታ ከመንግስቱ ለማ “ባሻ አሸብር በአሜሪካ” ግጥም ጋር ይገጥማል፡፡ ገጣሚ፣ ፀሃፌ ተውኔትና መምህር መንግስቱ ለማ ባሻ አሸብርን አሜሪካ አስገብተው ከዚያም እስር ቤት ወርውረው ከአንድ ጥቁር አሜሪካዊ ጋር በማገናኘት ነው የሚያሟግቱት፡፡ እኔ እንዳንተ ጥቁር አይደለሁም በማለት! ይህንን ግጥም ሲያጠቃልሉ፡-

 

ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ

ስልቻ ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ብለው ነው፡፡ ጠይም ሆነ ጥቁር “ስልቻ ቀልቀሎ” እኮ ነው ነገሩ፡፡ ፀሀፊው ከሚመዙት ሃሳብ የሚያሳዝነው ግን “የኔው ዘመን ኢትዮጵያዊያን ከጣሊያን ጋር የተዋጉት ወራሪ መጣብን በሚል እንጂ ነጮች መጡብን በሚል ብቻ አልነበረም፡፡ ከሱዳን ወይም ከሶማሊያ በኩል ጥቁር ቆዳ ያላቸው ወራሪዎች ቢመጡ እጃቸውን አጣጥፈው አይቀመጡማ!” የሚለው ነው፡፡ ይሄ ፍፁም ካለማወቅ የተገኘ ፀጋ ነው (Blessing Ignorance) ካልተባለ በቀር ቅድመ አያቶቻችን ከማን ጋር እንደሚዋጉ ሳያውቁ አልተዋጉም፡፡

“አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል” ማለት እኮ ይኼ ነው፡፡ ከጥቁር ሰው አልበም የግጥም ጭብጥ የምንረዳው (ከምንሊክ ማሪያምን የሚል መሃላ ብቻ እንኳ) ዘመቻው የአድዋ መሆኑን ነው፡፡ የአድዋ ዘመቻ እኮ ብዙ ቅድመ ሁኔታዎች ነበሩት፡፡

ፀሃፊው የውጫሌ ውል አንቀፅ 17 የጦርነቱ መንስኤ መሆኑን እንዴት ዘነጉት፡፡ አዎን ሱዳንና ሱማሌ ሊሆኑ ይችሉ ነበር፤ ግን አልሆኑም፡፡ የአድዋ ጦርነት ድል ደግሞ መለኮታዊ ገፅታ (Divine Image) ተሰጥቷቸው የነበሩት ነጭ ተስፋፊዎች በጥቁሮች ማሸነፍ ቅስማቸው የተሰበረበትና በነጮችና በጥቁሮች መካከል የነበረው ከባድ ግድግዳ የፈረሰበት ነው፡፡

ነጮቹ እኮ አፍሪካን ሲወሩ ሀብት ፈልገን መጣን አላሉም፡፡ እኒህን ያልሰለጠኑ፤ ኋላ ቀርና ከእንስሳት ያልተሻሉ ጥቁሮችን ለማሰልጠን አምላክ በእኛ ጫንቃ ላይ የጣለብን ኃላፊነትና ሸክም “የነጩ ሰው ሸክም” (The white man’s burden) ብለው እኮ ተሳልቀዋል፡፡ አድዋማ የጣሊያኖች ብቻ ሳይሆን የነጭ ተስፋፊነትና የበላይነት የተሰበረበት ትልቅ ድል ነው፡፡ የከበደ ሚካኤል “እሮሮ” የተሰኘ ግጥም የዚሁ የነጭ ሰው ሸክም ሌላ ማሳያ ነው፡፡ በየካቲት 1899 (እ.ኤ.አ) የቀረበውን የደራሲና ገጣሚ ሩደያርድ ኪፕሊንግ “The white man’s burden” ግጥም በጥቂቱ እንመልከት እስቲ፡-

Take up the White Man’s burden---

Send forth the best ye breed---

Go send your sons to exile

To serve your captives’ need

To wait in heavy harness

On fluttered folk and wild---

Your new-caught, sullen peoples,

Half devil and half child

Take up the White Man’s burden

(አፅንኦት የእኔ) እንዲህ የሚል ነበር የዘመኑ መንፈስ (Sprit of the Time) ወይም አመለካከት፡፡

 

ምትና ምጣኔ በሙዚቃ ውስጥ

ምት (rhythm) እና ምጣኔ (Meter) ምንድን ነው? ሁለት የግጥም መስመሮች በእኩል ቀለም ሲቀርቡ የተመጣጠነ ሆነ ማለት ነው፡፡ ምት ደግሞ ከምጣኔ ይወለዳል፡፡ እንዴት ቢሉ በትክክል የተመጠነ ግጥም ምቱ ይስተካከላልና፡፡

ዘፈኑ ሲቀየር እኮ ዳንሱም ይቀየራል፡፡ በአማርኛ ዘፈን ሲያጨበጭብ የነበረ ታዳሚ ትግርኛ ዘፈን ቢቀየርበት በቀደመው ምት አያጨበጭብም፡፡

ፀሃፊው “ፀባየ ሰናይ” ከአረጋኸኝ “ነፋስ ገብቶ በመሃላችን” ከሚለው “ስለፍቅር” ደግሞ ከሚካኤል አልበም ዘጠነኛ ዘፈን ጋር ይመሳሰላሉ ይሉናል፡፡

አያይዘው ግን በእርግጥ “አዎ የቀለም (የድምፅ) ምጣኔያቸው ላይ ልዩነት አለ” ይሉናል፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? የግጥሙ ምጣኔ ከተለያየ እኮ መሰረታዊ የሙዚቃ ልዩነት መጣ ማለት ነው፡፡ ይመሳሰላሉ ከተባለ ምጣኔያቸው ጭምር መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ምጣኔ በመንቶ (በሁለት የግጥም መስመር) መካከል ያለ የጊዜ እርዝመት ስለሆነ ከሁለቱ ሙዚቀኞች ጋር በምጣኔ የተለየ ግጥም ይዞ ከመጣ ዘፈኖቹ አንድ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

“ኦ አፍሪካ“

እዚህ ላይ ከተነሳ አይቀር ዛሬም የጥቁር ሰውን አንድ ዘፈን ከአስተያየት ሰጪው አንፃር በአጭሩ ልመልከት፡፡ “ኦ አፍሪካ” ቀሽም የሚባል ዘፈን ነው? ድህነትን ሽሽት ብዙ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ አገሮች ተሰደው ሲኖሩ ይታያል፡፡ አንዳንዶቹ በአገራቸው ሰርተው ለማግኘት ከመጣር ይልቅ በአጭሩ ለመበልፀግ የሚያደርጉት መቃተት ነው፡፡ አቋራጭ ማለት ይሄ እንጂ አቋራጭ መንገድ አይደለም፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ የተጓዘ ሰው ታዲያ ሺ የዜግነት ወረቀት ቢኖረውም አንድ ቀን ሲባንን ቤቱ አፍሪካ መሆኑን ቢረዳ የግጥም መምታታት ይባላል? በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ሁኔታ ከእኛ አገር ሁኔታ ጋር መመልከት እንችላለን - በሌላው የግጥሙ ስንኞች፡፡

ዮቶር የሙሴ አማት ነው፤ ሙሴ የዮቶርን ሴት ልጅ ኢትዮጵያዊቷን ሲፓራን አግብቷልና፡፡ ስለዚህ ነገሩን አርዝመን ከተመለከትነው ዮቶር ኢትዮጵያዊ ነበር ልንል እንችላለን፡፡ ያ ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን የዮቶር ልጆች መሆናችን ነው፡፡ እርስታችን ደግሞ አባይ - እኛም ያባይ ልጆች! ማንነት አይለወጥም ማለት በአጭሩ ይኼ ነው፡፡ ግጥም እኮ አይዘረዝርም - በጣም ቁጥብ ነው ባህሪው፡፡

ባጠቃላይ ግን የፀሃፊው ሃሳብ ከእኔ ፅሁፍ ጋር የሚያገናኘው ብዙ ነገር የለም፡፡ የእኔ ፅሁፍ ከአልበሙ ሁለት ዘፈኖችን ብቻ ማሳያ በማድረግ የተሰጠ ትንታኔ ነው፡፡ “ፍየልና ቅዝምዝም” ሆኖብኛል፡፡

ደግሞስ እንዴት ቴዲ ነው የሁሉም ግጥም ፀሀፊ ተብሎ በርግጠኝነት ይፃፋል?!

 

 

 

Read 5327 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 06:49