Print this page
Tuesday, 25 June 2019 00:00

“ኢህአዴግ” - አሮጌው አቁማዳ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

ለውጥ በተለይም አብዮት በሁለት ነገሮች ምክንያት ይመጣል፤ ይህም የቀደመው ወይም ያረጀው ሥርዓት ሊያበቃ ሲል ህሊናዊ (Subjective) እና ነባራዊ ሁኔታዎች የበቁና የደረጁ (matured) ሲሆኑ ነው፡፡ ህብረተሰቡ ጭቆናን የሚሸከምበት ጫንቃ ቆስሎ፤ አዲሱ የምርት ሀይሎችና አሮጌው የምርት ግንኙነት አልጣጣም ሲል፤ ኢኮኖሚውና ፖለቲካው ሲንገታገት፣ ምናልባትም ባፍጢሙ ተደፍቶ ሲንፈራገጥ፣ ህዝቡ ቋቅ ሲለው መሆን አለበት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እዚህ አሮጌ ሥርዓት ላይ ያጐነቆለው ለውጥ እንዴት እንደሚያድግ የሚያመቻችና እየገረዘ፣ ሳይጣመም እንዲያድግ የሚያደርግ፣ የተደራጀ ቡድን ወይም ፓርቲ መኖር ለውጡን /አብዮቱን/ በተቃና መሥመር እንዲሄድና ሕዝቦችን በማሳተፍና በማሰለፍ ተጠቃሚ እንዲያደርግ ይረዳዋል፡፡
ይሁንና ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው ለውጦች /አብዮት/፤ በዚህ ዐይነት ዕድል፣ በተሳካ ሁኔታ ልታስተናግድ አልታደለችም፡፡ በንጉሱ ዘመን፣ የመሬት ከበርቴው ጭቆና በሰፊው ሕዝብ አናት ላይ በወጣበትና ገና በማቆጥቆጥ ላይ የነበረው ኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ የሠራተኛውን መብት በሚጋፉበት ዘመን፣ የተማረው አመጽ ከማነሳሳቱና ብልጭ ድርግም የሚል ተቃውሞ ከማሰማት ያለፈ፣ ለዚሁ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ  የተዘጋጀ ፓርቲ አልነበረም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የመሬት ላራሹ ጥያቄ ጫፍ የወጣበት፣ ሀገሪቱ በተለያዩ ማዕዘናት በረሃብ የተጠቃችበት ጊዜ ነበር፡፡ በዚያ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከስቶ የነበረው የነዳጅ ዋጋ መናር ነባራዊውን ሁኔታ አጡዞት ነበር፡፡
ከላይ እንዳየነው ነባራዊው ሁኔታ የለውጡን ጀንበር ለመለኮስ የደረሰውን ያህል ያንን ለውጥ ሊመራ የሚችል የተደራጀ ቡድን ባለመኖሩ፣ ክፍተቱን የተጠቀመው ወታደራዊ ቡድን ዕድሉን ነጥቆ ለውጡን አጨናገፈው፡፡ በተለያዩ ሀገራት የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ጨምሮ በአብዮቱ ዋዜማ አካባቢ የተደራጁ ፓርቲዎች ቢኖሩም ጨቅላ የሀገሪቱን ሁኔታ በውል ያልተገነዘቡ ስለሆኑ፣ ቀድሞ ቡድን የፈጠረው ወታደር ሀገሪቱን  ወደማይጠቅም አቅጣጫ ወረወራት፡፡
ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ አሳዛኙ ክስተት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የመጣው ወያኔያዊ ለውጥ በሁለንተናው የተደራጀ፣ ከቀድሞው የተሻለና የተመቻቸ ነበር:: ሀገሪቱን ለመምራት ወደ ሥልጣን የወጣው ፓርቲ፤ ለበርካታ ዐመታት የተደራጀና ራሱን እየጠረበና እያስተካከለ የመጣ በመሆኑ በቀላሉ የሚፈርስ አልነበረም፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው፤ የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታም ሙክክ ብሎ የበሰለ ነበር፡፡ ታዲያ ምን ይደረግ? በወያኔ ፊታውራሪነት የመጣው መንግሥት፣ ሀገሪቱን በሰለጠነ መንገድ ዓለም ወይም ትገሰግስበት የዕድገት ጐዳና ከመጓዝ ይልቅ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ መጓዝ ጀመረ:: ዜጐች ለሀገራቸው ብልጽግናና ዕድገት ከማለም ይልቅ፣ የቀድሞውን ቂምና ቁርሾ እየቆሰቆሱ፣ ምድጃ ታቅፈው እዬዬ ማለት ቀጠሉ፤  ሲጀመርም ህልማቸው ኢትዮጵያዊነት ስላልነበር ህዝቡን እያባሉ፣ ሀብትና ንብረቱን ወደ ኪሣቸው መክተት ሥራዬ ብለው ተያያዙት፡፡ ያመጡትን “ዴሞክራሲ” የሚል ቃል፣ ከመፈክር ባለፈ ሳይጠቀሙበት በእጃቸው ላይ ጠውልጐ በአደባባይ ላይ ሞተ፡፡ ስለዚህ መግረፍ፣ ማሠር፣ ማዋረድ የተንሠራፋበት ብዙ ሰቆቃና ጭለማም አሳለፍን፡፡ ሃያ ሰባት ዓመታት ሙሉ የብዙ ሰዎች ድንኳን በልቅሶ ተሞልቶ፣ ሀገሪቱ ነጠላዋን ያዘቀዘቀች ሀዘንተኛ ሆና ኖረች፡፡
በሚያሳዝን ሁኔታ በዚህ ሁሉ ጊዜ ለመደራጀት የሞከሩ ፓርቲዎች፤ በጨካኞች በትር እየተመቱ ወደቁ፡፡ እምቢ ብለው የተጋፈጡትም በየወህኒ ቤቱ መከራቸውን ተቀበሉ፡፡ ስለዚህ የሀገሪቱ ችግሮች ተባብሰው፣ ልቅሶዎች ድንኳን ሞልተው፣ ኑሮ የሞትን አፍንጫ ቢያሸትትም፣ ለውጡን ለመምራት የተዘጋጀ ቡድን ግን አልነበረም፡፡ ይሁንና ግን ከልክ አልፎ መደራጀት የተከለከለው ሕዝብ፤ በነፍስ ወከፍ እየወጣ፣ “ያገር ያለህ!” ቢልም ከጐኑ ቆሞ የሚያበረታው፣ ከፊት አልፎ የሚመራው  በማጣቱ የተበታተነ ጩኸቱ ቀጠለ፡፡ ነውጡ በየቦታው ሲፈነዳ ወያኔያዊው መንግሥት፣ በጥይት አጨዳ፣ ጉዳዩን ለማቃናት ሞክሮ አቃተው፡፡
ይሁንና በዚህ ቀውጢ ሰዓት መሪ የሌለውን የህዝቡን ጩኸት/በተለይም በኦሮሚያ ክልል ገንኖ የወጣውን ሃይል ከሩቅ ሆኖ በኢንተርኔት ለመምራት ብቅ ያለው አቶ ጃዋር መሐመድ ነበር፡፡ ጃዋር መሐመድ፤ ሄነሪ ጄቪድ ቶሮው ባፈለቀውና፣ ማህተመ ጋንዲና ሉተር ኪንግ በተጠቀሙበት ሠላማዊ ዐመፅ፣ የአምባገነኑን መንግሥት መንጋጋ አንገጫገጨው፡፡ ይህም ለየትኛውም ጥያቄ በዕብሪት የተሞላ መልስ ይሰጥ የነበረው መንግሥት፤ የመለሳለስ አዝማሚያ እንዲያሳይ ተገደዱ፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ ሌላ ፍንጭ ብቅ አለ፤ ይኸውም የኢህአዴግ አካል የሆነው ኦህዴድ፤ አንዳንድ የማፈንገጥ ምልክቶች አሳየ፤ ከነዚህም ውስጥ አንዱ ስልት የክልሉ ልዩ ሃይል ለአመጽ የሚወጡት ወጣቶች ላይ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ተቃውሟቸውን በድብቅ ማገዣ መጀመሩ ነው፡፡
እንግዲህ ይህ የአሁኑ ለውጥ መሠል ተሀድሶ መነሻ ነበር፡፡ ታዲያ የመጨረሻው ጊዜ ደርሶ ወያኔያዊው መንግሥት፣ በኦህዴዳዊው መሪነት ብቅ ባለው መንግሥት እጅ ሲገባ፣ ሥልጣኑን ሊጋራው የሚችል አንዳች ሀይል አልነበረም፡፡ ይህም ማለት በሀገሪቱ ውስጥ ከራሱ ከኢህአዴግ ውጭ ሀገሪቱን ሊመራ የሚችል አንድም የተደራጀ ቡድን አልነበረም:: (ሕሊናዊ ሁኔታዎች አልተመቻቹም)
ቢሆንም ከወያኔ መንጋጋ ማምለጡ ህልም የመሰለው ህዝብ፤ ለውጡን እየዘመረ ተቀበለው:: ትልቁ ጥያቄ ግን ለውጡ የሚመራው በማን ነው የሚለው? ነው፡፡ ለውጡ ውስጥ ያሉ ሰዎች፤ ራሳቸው ለለውጥ ተዘጋጅተው ነበር ወይ?” ይህ እስካሁን ድረስ የብዙዎቻችን ጥያቄና እንቆቅልሽ ነው፡፡ “አይደለም” እንዳንል “ለውጡን ለማምጣት በህቡዕ የተደራጁ ጥቂት ሰዎች ነበሩ፡፡ “ነው” እንዳንል ደግሞ በዚያ ክፉ ዘመን ከወያኔ ጋር አብረው እየፈተፈቱ፤ የወገኖቻቸውን ሰቆቃ እንደ ሙዚቃ እያዳመጡ ለህዝቡ ዋይታ ጆሮዋቸውን የደፈኑ እልፍ አረመኔዎች በቀድሞው የግፍ መንበራቸው ላይ እንደተንጠለጠሉ ናቸው፡፡ ይሁንና ውሎ ሲያድር ለውጡን ለማካሄድ የተዘጋጀ አእምሮ እንዳልነበራቸው እየተገለጠ መጣ:: ቀድሞስ ቢሆን አዲሱን የወይን ጠጅ አሮጌ አቁማዳ ሊይዘው ይችላልን?” የማይመስል ነገር ነው:: እነዚህ ለሆዳቸው ያደሩ ሹማምንት፤ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ለስቃይ የዳረገው መንግሥት ለሚያወጣቸው ህጐችና መመሪያዎች እልል እያሉ ሲያጨበጭቡ እንደኖሩ ሁሉ፣ ለውጡም ሲመጣ በዚያው እጃቸው ማጨብጨብ፣ በዚያው አንደበታቸው እልል ማለት አልተውም፡፡
ይልቁንም ቀድሞ በተተለመላቸው የብሔር ጎዳና እየተሰለፉ፣ የጎጣቸውን ስም ለጥፈው፣ በሌላ ለምድ ተኩላነታቸውን መደበቅ ሲሞከሩ እያየን ነው፡፡ ያኔ በየወሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ወገናቸው እንደ በግ ሲታረድ የፓርማ ወንበር ላይ ፊጥ ያሉ ሆድ አደሮች፤ ዛሬ የህዝብ ተቆርቋሪ ለመምሰል በየመገናኛ ብዙሃኑ መለፈፍ ያዙ፡፡ ሀቁ ይኸው ነው፡፡ በቃ!
ዛሬ በለውጡ ዘመን በየክልሉ፣ በየወረዳውና ቀበሌው ያሉት ባለስልጣናት በሙሉ በሚባል ደረጃ፣ የወያኔን የሪፖርት ፖለቲካ በጡጦ ጠብተው ያደጉ፣ ምላሳቸው በአራት ማዕዘን የተሞረደ ዋሾዎችና ሴረኞች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም ትናንት ለለውጥ የታገለውን ወጣት፣ በጥይት ያጨዱ፣ የገረፉና ያጎሣቆሉ ናቸው፡፡  ታዲያ ዛሬም በዚያው ወንበር ተቀምጠው፣ ያንኑ የትናንት ጭቁን፣ በአርጩሜ  እየገረፉት ነው፡፡ እንግዲህ ለውጡ የስምና የዶክተር ዐቢይ አህመድ ሩጫና ዴሞክራትነት ብቻ ነው:: እኒህ ሰው ባይኖሩ ዕጣ ፈንታችን ምን ይሆን እንደነበር ማሰብ ይዘገንናል፡፡ አቶ ለማ መገርሳን፣ ምናልባትም አዲሱን የኦሮሚያ ፕሬዚዳንትና ጥቂት የአዴፓን አመራሮች ይጨምር ይሆናል፡። ከዚህ በቀር አዲስ ነገርም፣ አዲስ ሰውም የለም፡፡
በየቴሌቪዥኑ እየመጡ አዲስ መዝሙር የሚዘምሩልን ሚኒስትሮች፣.ትናንት ከወያኔ ጋር ሆነው እኛ በእንባ ዋንጫ ስንጋት፣ እነርሱ በአሮጌ ዋንጫ የወይን ጠጅ ጠጥተው የሰከሩ ሕሡሞች ናቸው፡፡
ሌላው ቀርቶ በየሚዲያው ተቀምጠው “ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት!” ሲጠራ የሚመራቸውና የሚያስቆጣቸው ኃላፊዎች፤ዛሬም ዘውዳቸውን ጭነው ትናንት ለህዝቦች ነፃነት በወህኒ የተጣሉና የተደበደቡት ላይ ምላሳቸውን እያወጡ ያላግጣሉ፡፡ በብዙዎቻችን ከለውጡ ብዙ ተጠብቋል፡፡ በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልባዊ የለውጥና ሀገር የማዳን እረፍት የለሽነት፣የብዙዎችን ነፍስ በፍቅር አንበርክኳል፡፡ ምንም እንኳ “በተለያዩ ጥያቄዎች ቁርጠኝነት ይጎድላቸዋል!” በሚል ደጋፊዎቸው ቢሳሱም፤ አንዳንዶቻችን “የተከበቡት አርቀው በማያስቡ፣ ሆዳሞችና ብሔርተኞች ነው” በሚል ዛሬም ደጋፊያቸው እንሆን ዘንድ እጅ ሰጥተናል፡፡ እጅ የሰጠነውም የምንወዳትን ኢትዮጵያ የሚወድዱ፣ ሥልጡን መሪ ናቸው ብለን ስላመንን ነው፡፡ ይሁን እንጂ “አዲሱ የወይን ጠጅ በአሮጌው አቁማዳ” ሆኖ በከንቱ የሚፈስሰው እስከ መቼ ነው? የሚለው ጥያቄያችን ውሎ ሲያድር እየጨመረ ነው፡፡
ምክንያቱም ትናንት ከወያኔ እግር ሥር የተቀመጡ ሰዎች፣ ሙሰኝነታቸውን አልተዉም፡፡ አንዳንዶቹም ብሔርተኝነታቸው ጨምሮ “ያለ እኛ ማን አለ?” ወደሚል አስቀያሚ ቆጥ ላይ ተፈናጥጠዋል:: ለዚህ ማሳያ የሚሆኑን ብዙ ነገሮች ቢኖሩም፣ አሁን በቅርቡ የምናየው የፕሬስ ነፃነት አፈና እጅግ ልቆ መጥቷል:: ትናንት ወያኔ ያደረገው ነገር ዛሬም እብሪት ተጨምሮበት፣ ጋዜጠኞችን ማሸማቀቅ ስራዬ ተብሎ ተይዟል፡፡ ሌላው ቀርቶ ቀደም ሲል ሆን ተብለው ለሴራ የተዘጋጁ መመሪያና ደንቦች፣ ዛሬም ለጨቋኞች በሚመች ሁኔታ እየተሰራበት ነው፡፡ ታዲያ ለውጡ የምን ለውጥ ነው እንበል? … የብሔር ወይስ የፍትህና ዴሞክራሲ?
ብዙዎቻችን እንደምናየው፤በርካታ አሳሳቢ ችግሮች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰዎች ያለ አግባብ እየታሰሩ፣ እየተነጠቁ፣ በየቦታው እየሞቱና ደማቸው ከንቱ እየቀረ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የዚሁ የኢህአዴግ የነተበ አካል ውጤቶች ናቸው፡፡ አስተሳሰባቸው፣ ያረጀና ያፈጀ፣ አምባገነናዊ ነው፡፡
አንዳንድ ቦታማ ለውጡ በጭራሽ ስላልደረሰ ሕዝቡ የጭቆና ቀንበሩን እንደተሸከመ ነው፡፡ ለምሳሌ የትግራይ ህዝብ ዛሬም በወያኔ አፈ-ሙዝ ሥር ሆኖ እየማቀቀ፣ እየተደበደበና እየተገደለም ነው፡፡ ለዚህም የራያ ህዝብ ምጥና ዋይታ አድማሳትን ያለፈ ጩኸት ማሳያ ነው፡፡
ሰሞኑን የተሰራጨ በምስል የተደገፈ መረጃ እንደሚያሳየን፤ ተንቤን አካባቢ በርካታ ወጣቶች እየተገረፉና እስር ቤት እየማቀቁ ነው፡፡ (ይሁንና ለውጡ፤ የትግራይን ጉዳይ በትዕግስትና በጥበብ መያዙን እደግፋለሁ) ምክንያቱም ቤንዚን የያዙት የቀድሞ ገዢዎች፤ የትኛውንም አጋጣሚ ለጥፋት መለኮሻ እንደሚጠብቁት ይታወቃል፡፡  
ይህን እንደማሳያ አየን እንጂ ደቡብ ክልልም ብንሄድ፣ ከተወሰኑ ቦታዎች በስተቀር ዛሬም ወንበር ላይ ተቀምጠው ሕዝቡን የሚንጡት የትናንትናውን የወያኔ ልብ የያዙ ጨካኞች ናቸው፡፡ እነዚህን ሰዎች ማስወገድና ለፍርድ የሚቀርቡትን ማቅረብ አይቻልም ወይ? የሚል የከረረ ጥያቄ አለኝ፡፡ ለዘላለም የተቀቡ ነገሥታት የሆኑ ይመስል፣ በግፍ ሥራቸው የሚቆዩት እስከ መቼ ነው?
ለውጡስ የአስተሳሰብ ለውጥ ያላቸውን ሰዎች ካልተካ ፋይዳው ምንድነው? እኛስ በለውጡ ዙሪያ ተደርድረን ጠቅላዩ “እገሌን ሲያደንቅ እኔን ዝም አለኝ” በሚል የግል ምኞት፣ የሀገር ተቆርቋሪ በመምሰል በተቃዋሚነት ቆመን ነገር የምናቀጣጥለው   ነው? … ጋዜጠኛው በጋዜጠኛው፣ ሴቷ በሴት፣ እየተቀናናን በሀገር ስምና ጭንብል ህዝቡን የምናዋክበው እስከ መቼ  ነው? ለውጥ ሲባል የህዝብንም መለወጥ ይጨምራል፡፡ “እኔ የማልነግሥበትና ማማ ላይ የማልወጣበት መንግሥት መፍረስ አለበት!” ብሎ መዝመትም፤ የእኛ ወገን አሣፋሪ አካሄድ ነው፡፡
ወደ ማጠቃለያዬ ስመጣ፣ ለውጡ እስከ ምርጫው ድረስ በእንብርክኩም ቢሆን ሄዶ፣ ከዚያ በኋላ በሀገራዊ ፓርቲዎች ህብረት፤ ሀገራችንን ፍትህ የሰፈነባት፣ ነፃነትና እኩልነት የፈካባት እናደርጋታለን፣ ቢያንስ አንገታቸውን መዝዘው፣ ህዝቡን የሚወጉ እሾሆች ከየወንበሩ ላይ መነቀል አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለውጡ፣ ለእንባና ለስቃይ ከሆነ ግን ፋይዳ የለውም፡፡ ነገሩ ይህ ግጥም እንደሚለው ነው፡፡
እንደምነህ መንግስት፣
እኔ አለሁ በደህና
በተመቻቸልኝ የልማት ጎዳና፣
ታክሲ ለመጠበቅ፣ ሰልፍ ተሰልፌ
አለሁኝ በተድላ¡
በቀን ሶስት ጊዜ
ቁርስ፣ ምሳ፣ ራቴን መከራ ስበላ፡፡
ያንተ ደህንነት ነው፣ እኔን ሚያስጨንቀኝ
ኑረህ እንደሌለህ የምትናፍቀኝ፣
ቀልድህ ቁምነገርህ - ዐመት የሚያስቀኝ…
(በላይ በቀለ ወያ)


Read 704 times