Monday, 24 June 2019 00:00

ቃለ ምልልስ “ዓይናችንን ቀጣዩ ምርጫ ላይ አድርገናል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀ መንበር ፕ/ር መረራ ጉዲና፣ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ፣ ስለ አዲሱ የምርጫ ቦርድ፣ ስለ ቀጣዩ ምርጫና ስለ ፓርቲያቸው ዝግጅት--- እንደሚከተለው አውግተዋል፡፡


              አዲሱን የምርጫ ቦርድ  እንዴት አገኙት?
ከድሮ የተሻለ ነው፡፡ ይሄ ምንም ጥያቄ የለውም፤ ቢያንስ ቢያንስ እኛንም አነጋግረውናል:: ወደ መጨረሻ ዙር ባለፉ 8 ሰዎች ላይ ሁላችንም መክረናል፡፡ ስለምናውቃቸው ሰዎች የየራሳችንን አስተያየት ሰጥተናል፡፡ በዚህ ረገድ ከዚህ በፊት ከነበረው አካሄድ የተሻለ ሆኖ አግኝቸዋለሁ:: እንደሚታወቀው፣ ከዚህ ቀደም ምርጫ ቦርድ፣ የሀገሪቱን ፖለቲካ ባልተገባ መልክ ሲወስን የኖረ፣ ለብዙዎች ህይወት መመሠቃቀል ምክንያት የሆነ፣ ለበርካቶች ህይወት ማለፍ ምክንያት የሆነ ተቋም ነው፡፡ የኢህአዴግ ሽፋን ሆኖ አንድን ቡድን ሲያገለግል የነበረ ተቋም ነው፡፡ አንድ ጊዜ ከእነ በረከት ስምኦን ጋር ስንነጋገር፣ ሁለት ምርኩዝ አላችሁ ብያቸው ነበር፡፡ አንዱ ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ሌላኛው ጠመንጃችሁ ነው፤ እነሱን አስቀምጡና ተወዳደሩ ብያቸዋለሁ፡፡ በእነሱ ጊዜ ያንን ማድረግ አልቻሉም ነበር፡፡ ይሄኛው ግን አሁን ቢያንስ አንዱን ምርኩዝ ለማስቀመጥ እየሞከረ ይመስለኛል፡፡ ዋናው ፈተና፤ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ ምን ያህል ይዋቀራል የሚለው ነው፡፡ በሀቀኝነትና በገለልተኝነት ምን ያህል ያደራጃሉ የሚለው ከፊታቸው ያለ የታሪክ ፈተና ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ይሄን የአመታት ፈተና ለማለፍ መዘጋጀትም እንዳለበት ይሰማኛል:: አሁን በደፈናው ግን ከበፊቱ  ይሻላል፡፡ ቢያንስ ተወያይተናል፡፡ መንግስት ለእነዚህ የቦርድ አባላት ምን ያህል የፖለቲካ ምህዳሩን እንደሚከፈትም ከፊት ለፊቱ የተደቀነ ሌላኛው የታሪክ ፈተና ነው፡፡
ይህ አዲስ የምርጫ ቦርድ በቅድሚያ ሊያከናውን ይገባል የሚሉት ተግባር ምንድን  ነው?
የቅድሚያ ስራው መዋቅር መዘርጋት ነው:: በፍጥነት ከላይ ወደ ታች ገለልተኛ መዋቅር መዘርጋት አለበት፡፡ በህዝብ የሚታመኑና በሃቅ ምርጫውን ያስፈጽማሉ የሚባሉ ሰዎችን ወደ ታች ወርደው መመልመል መቻል አለባቸው፡፡ እንደ ከዚህ በፊቱ የኢህአዴግ ጉዳይ አስፈፃሚዎች በቦታው ላይ  ፈጽሞ መቀመጥ የለባቸውም፡፡ ከዚህ ባህል ወጥተን፣ በሃቀኛና ገለልተኛ ሰዎች የተዋቀረ፣ ገለልተኛና ሃቀኛ ባህል ያለውን ምርጫ ቦርድ መፍጠር አለባቸው:: አለበለዚያ ምርጫ ቦርድ ተመልሶ የፖለቲካችን የውዝግብ ማዕከል ሊሆን ይችላል፡፡
አሁን በሀገሪቱ የምርጫ ሂደት ውስጥ ለመግባት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ማለት ይቻላል?
ምቹ ሁኔታ እንኳ በኢትዮጵያ ለመፍጠር ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን አሁንም ከህዝብ ጋር ሆኖ በፍጥነት መዋቅር የመዘርጋት ሥራ ይቀራል፡፡ ይሄ መሠራት አለበት፡፡ የምርጫ ቦርዱም ትልቁ ፈተና፣ ይሄን መዋቅር መዘርጋት እንጂ ድምጽ ቆጥሮ ማስረከቡ አይደለም፡፡ አሁንም ቢሆን ከዚህ ቀደም እንዳልኩት የምርጫ ሂደት ውስጥ መግባት ጠቃሚ ነው፡፡ የህዝብን ቀልብ ወደ ምርጫ ለመሳብ፣ የምርጫ ሂደት ውስጥ መግባት አንዱ መፍትሔ ነው፡፡ ሀገሪቷን ለማረጋጋት በእጅጉ ጠቃሚ ነው:: ለምሣሌ እኛ በምንዘዋወርባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች፣ ህዝቡ የሚያነሳው ጉዳይ ለውጡ እዚህ አልደረሰም የሚል ነው፡፡ ትናንት ሲዘርፉ ሲያዘርፉን የነበሩ ናቸው አሁንም እየዘረፉን ያሉት ነው ህዝቡ የሚለው፡፡ ታዲያ ይሄን ህዝብ በምን ዘዴ ነው ማረጋጋት የሚቻለው፡፡ በጠመንጃ ነው? በምንድን ነው? ለኔ የሚታየኝ ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ መስራት የሚያስችለን የምርጫ ሂደት መጀመር ነው፡፡ አሁን ለምሣሌ የቀበሌና የማሟያ ምርጫ ጊዜው አልፏል፤ ያንን ለምን ማካሄድ አይቻልም፡፡ ቢያንስ የታችኛው መዋቅር ለውጡ ደርሷል የሚለውን ለመፍጠር ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄ እንዳይሆን የሚፈልገው ካድሬ ደግሞ ችግር ፈጣሪነቱ ከበፊቱ ብሶበታል:: ለምሣሌ ሰሞኑን ገጆ ላይ ገላና የሚባል አካባቢ የኛ ቢሮ ተሰብሮ፣ ንብረታችን ተዘርፎ፣ አባሎቻችን ተደብድበው ነበር፡፡ አዲአ በርጋ አካባቢም እንዲሁ የመንግስት ባለስልጣናት፣ በአርሶ አደሮች ላይ የተለያየ ግፍ እየፈፀሙ መሆኑን መረጃዎች እየደረሱን ነው፡፡ አሁን የቀድሞ በላተኛ ካድሬም በዚህ መልኩ ለዚህ መንግስት መታዘዝ እየቻለም አይመስለኝም:: ስለዚህ እነዚህን ነገሮች በሙሉ መልክ ማስያዝ የሚቻለው ህዝቡን የምትፈልገውን ሰው መርጠህ፣ መብትህን አስከብር በማለት ነው፡፡ መንግስት ይሄን በማድረግ ብቻ ነው ችግሩን መወጣት የሚችለው፡፡
የተረጋጋ ሁኔታ እስኪፈጠር ምርጫው ይራዘም የሚሉ ሰዎች የበለጠ አለመረጋጋት እየተፈጠረ እንደሚሄድ የተገነዘቡ አልመሰለኝም፡፡ እስኪረጋጋ ምርጫው ይቆየን የሚሉ ሰዎች፤ ማን ነው የሚያረጋጋላቸው? ሠራዊቱ ነው? ካድሬው ነው? ማን ነው? የሚለውን አይመልሱልህም፡፡ ዝም ብሎ ይረጋጋ ነው የሚሉት፡፡ ባለፉት 27 አመታት የኢትዮጵያን ህዝብ ሲያምስ የነበረ ሃይል ነው በስልጣን ላይ ያለው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩን ጨምሮ የተወሰኑ ሰዎች የተሻሉ ናቸው፤ ነገር ግን የተቀረው ወይም መሬት ላይ የሚመርመሰመሰው ካድሬ አመለካከቱን የቀየረ አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከላይ የመጣለትን ትዕዛዝ የሚቀበልም አይደለም:: በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ያለን ነገር፣ ማን ነው የሚያረጋጋው የሚለውን ጥያቄ መመለስ አለባቸው:: በሌላ በኩል አራቱም የኢህአዴግ ድርጅቶች፣ ገመድ ጉተታ ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ የሀገሪቱን ችግር መፍታት የሚቻለው ከህዝቡ ጋር ተባብሮ፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ በማካሄድ ነው:: መንግስት ማድረግ ያለበት፤ ህዝቡ ተረጋግቶ የፈለገውን እንዲመርጥ ማመቻቸት ነው፡፡ ምርጫ በዋናነት የህዝብ ነው እንጂ የፖለቲካ ድርጅቶች ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ ለውጥ ፈላጊው የመንግስት ሃይል፣ በቁርጠኝነት ለዚህ መስራት አለበት፡፡ በሌላ በኩል ተቃዋሚዎች በፍጥነት ብሔራዊ መግባባትና ድርድር  ውስጥ መግባት፣ ምርጫ ቦርድም በፍጥነት መዋቅሩን መዘርጋት አለበት፡፡ ዝም ብሎ ምርጫ ይተላለፍ ማለት ለችግሮች መፍትሄ  አይሆንም፡፡
ይሄ ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ ካልተካሄደ ህገ መንግስት ይጣሳል፤ ሀገርም ይፈርሳል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት  ምንድን ነው?
ይፈርሳል የሚሉት እንኳን ዝም ብለው ነው፡፡ ብዙ አመታት አብሮ የኖረ ህዝብ ዝም ብሎ አይፈርስም:: ነገር ግን ፈታኝ የሆኑ አደጋዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ፡፡ ለዚያም የሚያዘጋጁን ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ እዚያ ላይ እኔም ስጋት አለኝ፡፡ በጥንቃቄ ካልሠራንና በሚሆን መንገድ ካልተባበርን፣ ህዝቡን ወዳልተረጋጋ ህይወት እንዲገባ ልናደርግ እንችላለን:: ዝም ብለን የስልጣን ድጋፍ ለመሰብሰብ፣ ለስልጣን ፍርፋሪ ህዝቡን ወደ ማጋጨቱ፣ ወደ ማባላቱ ከሄድን ብዙ ችግር ይገጥመናል፤ አደጋው እኔም ይታየኛል፡፡
ለእርስዎ  የሚታይዎት አደጋዎች ምንድን ናቸው?
የበለጠ ግጭት ሊመጣ ይችላል፡፡ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ልንገባ እንችላለን፡፡ ለውጡ ተቀልብሶም ድሮ ወደነበርንበት ልንመለስ እንችላለን:: ሌሎች እንደሚሉትም ወደ መበታተኑም ልንሄድ እንችላለን፡፡
ምርጫው በተቀመጠለት ጊዜ ካልተካሄደ መከላከያ ህገ መንግስት ማስከበር አለበት፤ ስልጣን መያዝ አለበት የሚሉ ሃሳቦችም ይራመዳሉ፡፡ ይሄን እንዴት ይመለከቱታል?
ወታደሩ ስልጣን ይያዝ የሚሉት እንኳ ፖለቲካ ያልገባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ወታደሩ እኮ አይተነዋል፡፡ 17 አመታት በደርግ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ መከራውን ያየው በወታደራዊ መንግስት ነው፡፡ ህዝብ የተፈጀው በወታደራዊ መንግስት ነው፡፡ ኢህአዴግም ቢሆን 27 አመታት የቆየው በወታደራዊ መንግስት ነው:: ወታደር ነው በኢህአዴግ ዘመን ሲገድል፣ ሲያስር የኖረው፡፡ ወታደሩ ስልጣን መያዝ አለበት የሚሉት ፖለቲካና ታሪክን ጠንቅቀው ያልተረዱ አካላት ናቸው፡፡ በዚህ መጠን ለስልጣን ብለው ሲቀብጡ ሃገሪቷን ፍሬ ቢስ እንዳያደርጓት፣ ባይመኙት ጥሩ ነው፡፡ ወታደራዊ አገዛዝ እንደ መፍትሔ ይታይ የነበረበት ዘመን አልፏል፡፡ አሁን ጥይት ለህዝቦች ጥያቄ ምላሽ አይሆንም፡፡ ይሄን ባያስቡት፣ የማይረባ ምክርና ሃሳብ ባያቀርቡም ይሻላል፡፡
የእርቅና ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሮ፣ ህገ መንግስቱ ተሻሽሎ ነው ምርጫ መካሄድ አለበት የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ ይህን ሃሳብስ እንዴት ያዩታል?
ነገሮችን በፍጥነት ማካሄድ ከተቻለ እርቅና ብሔራዊ መግባባቱንም ምርጫውንም ማካሄድ ይቻላል፡፡ ዋናው በፍጥነት ስራዎቹን ለመስራት ያለ ፍላጐት ነው፡፡ ብሔራዊ መግባባትና እርቅ መከናወን እንዳለበትማ አጠያያቂ አይደለም፡፡ እኔ ፖለቲካ እስከሚገባኝ ድረስ ቀጣዩ ምርጫ ውጤታማ እንዲሆን እስከተባበርን ድረስ አንድ ውጤት ማምጣት እንችላለን የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ፡፡ ስልጣን ወይም ሞት የሚሉ ወገኖችም ለሚመጣው ሁሉ ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ ህዝብ መቼም በመረጠው መንግስት ላይ ድንጋይ አይወረውርም፡፡ በ2008 ድንጋይ መወርወር የጀመረው እኮ ያልመረጠው መንግስት ስለሆነበት ነው፡፡ ምርጫው ይራዘም እያልን ጊዜውን ስናባክን፣ በየቦታው የተቀበሩ ቦንቦች እጃችን ላይ እንዳይፈነዱ ነው የኔ ስጋት፡፡
ኦፌኮ ለምርጫው ምን አይነት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው?
እኛ የምንችለውን ያህል ዝግጅት ጀምረናል፡፡ አይናችንን ቀጣዩ ምርጫ ላይ አድርገናል፡፡ ለዚህም እናወዳድራቸዋለን ብለን ያሰብናቸውን እጩዎቻችን ከወዲሁ መርጠን እያሰለጠንን ነው፡፡ እስካሁን አዲስ አበባና አዳማ ላይ አሰልጥነናል፡፡ በቀጣይ ጅማና ነቀምት ላይ እናሰለጥናለን፡፡ እኛ በሙሉ ሃይላችን ስልጠናዎችን እየሰጠን፣ ስብሰባዎችን እያካሄድን ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከምናቀርበው የበለጠ የሰው ሃይል ይዘን ወደ ውድድሩ ለመግባት እየጣርን ነው፡፡
ከኦነግ ጋር ውህደት ልትፈጽሙ ነው ተብሎ ነበር--- ?
ከኦነግ ጋር የመናበብና የመተባበር ስምምነት ነው ያለን እንጂ ውህደትን በተመለከተ እስካሁን ውይይት አላደረግንም፡፡ ለውህደት የተያዘ አጀንዳም የለም፡፡ ነገር ግን በትብብር ለመስራት ተነጋግረናል፡፡
ቀጣዩ ምርጫና የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
 ሁሉም የየራሱን የቤት ስራ በጐ በሆነ መንገድ ከተወጣ፣ የተሳካ ዲሞክራሲያዊ መንግስት መመስረት ይቻል ይሆናል፡፡ ሁለተኛው  ደግሞ  ባለፉት 27 ዓመታት ስንጋጭ ስንባላ፣ ስንተላለቅ የነበረው ሂደት ሊቀጥል ይችላል፡፡
ሦስተኛው፤ አሁን ያለውም ለውጥ ሳይሳካ ይቀርና ወደ ኋላ ተመልሶ ወደ ቀድሞ ትርምስ ልንገባ እንችላለን፡፡ አራተኛው፤ አንዳንድ ሰዎች የሚሰጉበት የመበታተን አደጋ ውስጥም ሊገባ ይችላል፡፡ እኔ የሚታዩኝ ሁኔታዎች እነዚህ ናቸው፡፡    


Read 1886 times