Sunday, 23 June 2019 00:00

የሕወሓት ኩርባዎች

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(0 votes)

   ጥቂት ወደ ኋላ
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፤ ገና የሥልጣን መንበራቸውን እንዳሟሹ፣ በጊዜው የቀዝቃዛው ጦርነትን ማክተም ተከትሎ፣ የተፈጠረውን የኃይል አሰላለፍ ከግምት ወስጥ ያስገባ ቁመናን ለመላበስ ብዙ ማውጠንጠን ነበረባቸው፡፡ ኢትዮጵያን የመሰለ ግዙፍ ሀገር ለመምራት በለስ የቀናው ጠባብ ማኅበራዊ መሠረት ያለው ድርጅታቸው፤ከፊት ለፊቱ የሚገጥሙትን ተቀናቃኞች ጭዳ እያደረገ፣ መጪዎችን ዐሥርተ ዓመታት በበላይነት የሚዝልቅበት መላ ቢያሳስባቸው የሚደንቅ አይሆንም፡፡
ይህንን እኩይ አላማ ገቢራዊ ለማድረግ በአማካሪነት ወደ ሀገር ቤት ካስመጧቸው ልሂቃን መካከል ሳሙኤል ሀንቲግተን አንዱ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልሂቁን ለመሞገት የደፈሩት ዴሞክራሲ በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ላይ በመሳለቅ ነበር፤
“Professor Huntington, I have read your book, The Third Wave. According to your analysis, countries become democratic after they have become wealthy. Ethiopia is an extremely poor country, very far from a high level of economic development. Does that mean that democray is impossible in this country?” (ፕሮፌሰር ሀንቲግተን፤ ሶስተኛ ሞገድ የተባለውን መጽሐፍህን አንብቤው ነበር:: በአንተ ትንታኔ መሠረት፤ ሀገራት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ለመግባት በቅድሚያ ሃብታም መሆን አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ እጅግ የደቀቀ ምጣኔ ሀብት ያላት ሀገር ናት፡፡ ስለዚህ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ተምኔታዊ  ነው ማለት ይቻላል?)
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ፤ ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ነች ይሏታል እንደሚለው ብሔል ነው፡፡ መለስ ዜናዊ ገና በጠዋት ግድ ያላቸው፣ ከሕዝብ የመነጨና ለሕዝብ የሚተጋ ፍትሓዊ ሥርዓትን በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ማስፈን ሳይሆን፣ ጠባብ አጀንዳን አንግቦ መሀሉን ድንገት የተቆጣጠረው ድርጅታቸው እንዴት በልእልና ይሰነብታል የሚለው አጀንዳ እንደነበረ ከልሂቁ ጋር ያደረጉትን ሙግት ዋቢ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይኼ ውጥን ፍሬ አፍርቶ ሕወሓት ሀገሪቱን በከፋፍለህ ግዛ የአስተዳደር ዘይቤ፣ ሲያሸብር ከረመ፡፡ ድርጅቱ ሀገሪቱን፣ ከሁለት ዓሥርተ ዓመታት በላይ ያለ ተቀናቃኝ ሲገዛ መኖሩ ለብዙዎች ትንግርት ነው፡፡ ለመሆኑ ድርጅቱ የሥልጣን ልእልናውን ለማስጠበቅ የታጠፈባቸው ወሳኝ ፖለቲካዊ ኩርባዎች ምንድን ናቸው?
ዴሞክራሲን በመዋጮ /ኮንሶሴሽናል ዴሞክራሲ/
ሕወሓት በፖለቲካ ምህዳር ላይ ብቅ ብቅ የሚሉት ተቀናቃኞችን እየጠራረገ፣ የሥልጣን መደላድሉን ለማጽናት በቅድሚያ ዴሞክራሲዊ ቅኝት ላይ ማውጣት ማውረድ ነበረበት፡፡ ድርጅቱ የመረጠው ኮንሶሴሽናል ዴሞክራሲ /የተመጣጣኝ መዋጮ ሥርዓት/ ማእከሉን በእኩል የዘውጌ ውክልና ቀመር አማካኝነት ሀገር የማስተዳደር መንገድን ይከተላል፡፡ ለአብነት ኢሕአዴግን የመሠረቱት የዘውግ ተኮር ድርጅቶች /ethinocenteric political organizations/ እያንዳንዳቸው ዘጠኝ ተወካይን ለሥራ አስፈጻሚው ያበረክታሉ፡፡ ይህ የፓርቲው የላእላይ ምክር ቤት፣ እስከ ታች የቀበሌ አመራር ድረስ ተፈጻሚ የሚሆን ማንኛውንም ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል፡፡ ኢሕአዴግን ያዋቀሩት አራቱ ድርጅቶች ለሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ የሚያበረክቱት የተወካይ ቁጥር፣ የሕዝብ ብዛትን ወይም የሐብት ምጣኔን ታሳቢ አያደርግም፡፡
ይህ የዴሞክራሲ መርህ ሕወሓትን በብዙኃኑ እንዳይዋጥና በሕዳጣን ቁመናው ያሻውን ሲተገብር እንዲኖር አስችሎታል፡፡ በአምሳሉ የቀረጻቸውን የየክልሉ ምስለኔዎችን በብሔር ውክልና ስም ለመዘወር እንዳልተቸገረ በገሀድ ታዝበናል፡፡ ደኢህዴን፣ ኦህዴድ እና ብአዴን የድርጅቱ ፈረስ ሆነው አገልግለዋል፡፡         
ሌላው የዚህ አይነት ዴሞክራሲ  መገለጫ፤ በኮንፌዴራል የግዛት አወቃቀር ውስጥ የተለመደውን ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣን /ቬቶ ፓወር/ ገቢራዊ ማድረጉ ነው፡፡ ለአብነት ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል የሁሉም ክልሎች ይሁንታን ማግኘት አለበት ተብሎ የተደነገገው ምንጩ ኮንሶሴሽናል ዴሞክራሲያዊ መርህ ነው፡፡ ይኽ አናሳ ድርጅት በግድ የጫነውን ሰነድ እንደ ቅዱስ ቃል አይነኬ አድርጎት ኖሯል፡፡ ድርጅቱ በኮንሶሴሽናል ዴሞክራሲ ፈንታ የአብላጫ ዴሞክራሲን /Majoritarian Democracy/ ገቢራዊ አድርጎ ቢሆን ኖሮ፣ ይህን ሁሉ ዘመን ያለ አግባብ በበላይነት ባልዘለቀ ነበር፡፡
በባህል ብዝኃነት ስም የሐሳብ ብዝኃነትን መደፍጠጥ
ሌላው ኩርባ፤ በባህል ብዝኃነት ስም የሐሳብ ብሕዝኃነትን የሚጠየፍ አውድን ማፋፋት ነበር:: ብዝኃነት/ Pluralism/ የዴሞክራሲዊ ሥርዓት ዘረ-መል ነው፡፡ ግሪግስባይ “አናላይዚንግ ፖለቲክስ” በሚለው ድርሳኗ ላይ የመርሁን  አስፈላጊነት እንዲህ አስፍራለች፤ “Pluralism relationship to democracy is crucial: Democracy requires that all the people-with all their differing  ideologies, opinions, values, and so forth-be free to connect to government”.ብዝኃነት የዴሞክራሲ አከርካሪ ነው፤ በመርሁ አማካኝነት ዜጎች ጉራማይሌ የሆነው አመለካከታቸውን፣ የርዕዮተ ዓለም ቅኝታቸውንና ያላቸውን እሴት እንደያዙ፣ ያለ ምንም አድልዎ ከመንግሥት ጋር በእኩል ደረጃ ይስተናገዳሉ፡፡
ባለፉት ሁለተ ዓሥርተ ዓመታት፣ ፍትሓዊ አገዛዝ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ያለ ቅጥ ሲራከስ እንደኖረ ዋቢ የሚሆነን ለዴሞክራሲው ሥርዓት እንደ የማእዘን ድንጋይ የሚቆጠረው የሐሳብ ብዝኅነትን በቅጡ መመርመር ስንጀምር ነው፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ አምጦ የወለደው ሕገ መንግሥት፤ ለባህል ብዝኃነት የሰጠው ትኩረት ከግምት ባላይ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ተከትለው ገቢራዊ የሆኑት አደረጃጀቶች፣ ከሐሳብ ብዝኅነት ጋር ጠበኛ ናቸው:: ልዩነቱን ለማባባስ በተመቸ  ቆሞ ቀር የአጥንት ቆጠራ መለኪያ ገቢራዊ የሆነው የፖለቲካ ሥርዓት፣ የሐሳብ ወጥነትን ሲሰብክ እንደኖረ ይታወቃል፡፡
የሐሳብ ብዝሃነት ከማንነት ፖለቲካ ጋር አይንና ናጫ ነው፡፡ ሁለቱ በአንድነት አይጓዙም፡፡ አንዱ ደመ-ነፍሳዊ፣ ሌላው አመክኖዋዊ መርህን ይከተላሉ:: የአምክንዮ የግብር ልጅ የሐሳብ ብዝሃነት ነው፡፡ በኃይል ወይም በደመ-ነፍሳዊ ስልት የሚደፈጠጥ ምንም አይነት የፖለቲካ አቋም አይኖርም፡፡ ሕወሓት በኢትዮጵያ ፖለቲካ የታጠፈበት ኩርባ ፀጉረ ልውጥ ነው፡፡ ድርጅቱ የዜጎችን እርስ በርስ ትስስርን በመበጣጠስ፣  ለሐሳብ ብዝሓነት ምቹ የሆነው የዜግነት ፖለቲካ እንዲቀበር ጥልቅ ጉድጓድ ሲምስ ነበር፡፡ ደመ-ነፍሳዊ ትስስርን ታሳቢ ያደረገ ሕገ-መንግሥትና የፖለቲካ አደረጃጀትን በማፋፋት ማዕከሉን ያለ ምንም ተቀናቃኝ መዘወር ችሏል፡፡
ደርግ የሐሳብ ብዝኃነትን ሲደመስስ የኖረው አድሃሪያን፣ የአብዮቱ ጠላቶች በሚል ነበር:: ሕወሓት/ ኢሕአዴግ ይህንን እንዳለ በመቅዳት በሐሳብ የሚሞግቱን ኃይሎች፣ ፀረ ሰላም፣ ፀረ ልማት፣ ፀረ ብሔር የሚል ታፔላ ለጥፎባቸው፣ ያሻውን ግፍ ሲፈጽም ኖሯል፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ዜጎች ወደ እስር ቤት ተግዘዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እስራኤልን እንደ አብነት ወስደው ለሐሳብ ብዝኃነት ያላቸውን ቁርጠኛ አቋም ማሳወቃቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ጽንፈኛውም፣ ለዘብተኛውም፣ መሀል ሰፋሪውም ያለ ገደብ ሐሳቡን የሚገልጽበት አውድ፣ ዴሞክራሲዊው ሥርዓት ሲገነባ የመጀመሪያው ጡብ ነው፡፡
ምንም አይነት ብዝኅነትን የሚያስተናግድ ሥርዓት አልተቀለሰም፡፡ ከላይ በዴሞክራሲያዊ ማእከልነት ተቀንብቦ የተያዘ አቋም ወደ ታች ያለ ምንም ማከላከል በቀጭን ትዕዛዝ ይወርዳል፡፡ ይህንን እንደ ወረደ የማጥለቅ ግዴታ የሰፊው ሕዝብ ዕጣ ነበር፡፡
እንደ ገደል ማሚቶ የማያስተጋባ ተሟጋች ዜጋ ድንገት ለአመል ዘለግ ብሎ ከተገኘ፣ ዕጣው ጨለማ ወህኒ ቤት ነው የሚሆነው፡፡ ንጹሐን ዜጎች በያዙት የተለየ አቋም ብቻ እንደወጡ ቀርተዋል፡፡ ከአውዱ አፈንግጠዋል ተብለው የሚቆጠሩ ግለሰቦች፤ ትምህክተኛና ጠባብ በሚሉ ማሸማቀቂያ ፍረጃዎች አንገታቸውን እንዲደፉ ተፈርዶባቸዋል፡፡
የቅስቀሳ ተሳትፎ/mobilization/
ሕወሓታዊያን ዴሞክራሲን በጥቂት የፖለቲካ “ኢሊቶቻቸው” ቀንብበው በመያዝ፣ ሰፊውን ማኅበረሰብ የበይ ተመልካች አድርገውት ኖረዋል:: ይህ የአገዛዝ ጀምበራቸው እስኪያዘቀዝቅ ድረስ ጸንተው የቆሙበት የሴራ ምሶሷቸው ነበር፡፡ አለቆቻቸው ያመነጩት ሐሳብ ቅቡል እንዲሆን የሚጠቀሙበት ሥልት በካድሬዎች ቀስቃሽነት የሚዘጋጅ ስብሰባና ሰልፍ ነበር፡፡ ይህ አይነት ስልት የሐሳብ ብዝኃነት በሚጠየፉ በየትኛውም አምባገነን መንግሥታት ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ ግርግሲባይን እዚህ ጋ እማኝ ላድርጋት፤ Non democratic governments may actually mobilize the people by decreeing that the people act in certain way (for example, attend political rallies),but may remove from the mobilized participation any opportunities for the expression of popular will. አምባገነናዊ አስተዳደር ሰፊውን ሕዝብ በመቀስቀስ ድጋፍ እንዳለው የታይታ ግብሩን ለአውደ ርዕይ ያቀርባል:: ይኽም ሆኖ የሕዝብ ፍላጎት የሚንጸባረቅበትን ተሳትፎ ማድረግ የማይሞከር ነው፡፡    
ሕዳግ
የሕወሓት ኩርባዎች በሕዝብ እምቢተኝነት አፈር ለብሰዋል፡፡ ድርጅቱ ወደ ጠርዝ ቢገፋም መሀሉን ዳር ለማድረግ ላይ ታች ከሚሉ ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር ግንባር መፍጠሩ የማይቀር እንደሆነ አንዳንድ ምልክቶችን ማስተዋል ከጀመርን ሰንብተናል፡፡ ለአብነት ያህል፤ በፌዴራል ፓርላማ የጸደቀውን አዲሱን የወሰንና የማንነት ኮሚሽን የማቋቋሚያ አዋጅን እንደማይቀበለው በክልሉ ምክር ቤት አማካኝነት ውሳኔውን ይፋ ማድረጉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ሕወሓት፤ የዐቢይ አሕመድ የለውጥ አስተዳደርን በሙሉ ልቡ እንዳልተቀበለው አስረጂ የሚሆነን በዘረፋና በሰብኣዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ወንጀለኞችን በጉያው ሸሽጎ  ማንገራገሩን ስንመለከት ነው፡፡ በዚህ የፀረ ለውጥ አቋሙ፣ የፌደራል መንግሥቱ ተገዳዳሪ ኃይል ሆኖ ሊቀጥል ስለሚችል፣ መንግስት የማታ ማታ፣ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ መገደዱ አይቀርም፡፡ እንዲህ መቀጠል የሚቻል አይመስልም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሁፉ የሚያንጸባርቀው የጸሃፊውን ሃሳብ ብቻ መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡  


Read 2673 times