Saturday, 22 June 2019 11:18

“የገደለው ባልሽ፣ የሞተው ወንድምሽ፣ ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ

Written by  ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(0 votes)


                 “--የትግራይ ህዝብ፣ ኢትዮጵያ ችግር ላይ ስትወድቅ ይጋፈጣል እንጂ “እናንተው ተወጡት” ብሎ ፊቱን የሚያዞር ራስ ወዳድ አይደለም፡፡ የትግራይ ህዝብ ለዚች ሀገር ከማንም በላይ ከፍ ያለ መስዋእትነት የከፈለ ህዝብ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በመመስረቱ ሂደት ቀዳሚ ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር ሳያስደፍር ጠብቆ ኖሯል፡፡ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ የመገንጠል ዓላማ ያላት ህወሓት ናት፡፡ ዶ/ር ደብረጽዮን የነገሩን የህወሓት አባላትን ስሜት ነው፡፡---”
             
          ባለፈው ሰሞን ስሜታችንን ከፍና ዝቅ ሲያደርጉ የሰነበቱ በርካታ ክስተቶች ነበሩ፡፡ በአክሱም ዩንቨርስቲ በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፉንና በሌሎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን የሰማነው ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡ ይህ ክስተት በማህበራዊ ሚዲያውም መነጋገሪያ ነበር፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የሰጡትን መግለጫም ሰምተናል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዩንቨርስቲዎች ግጭት መቀስቀሱም ሆነ ሰው መሞቱ እየተለመደ በመምጣቱ፣ አእምሯችን በመደንዘዙ መደናገጣችን እየቀነሰ መጥቷል:: ይልቁንስ የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ግጭቱን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ “ግጭቱ የብሔር ገጽታ አለው” ማለታቸው ነው ያስደነገጠኝ:: (በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝን አስተያየት ወደ ኋላ እመለስበታለሁ)
በአክሱም ዩንቨርስቲ የደረሰውን ሰምተን እያዘንንና እየተከዝን ሳለ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ በዚያው በአክሱም ከተማ ድንገተኛ ጉብኝት ማድረጋቸውን ሰማን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከቀደምት የሀገሪቱ መሪዎች በተለየ ሁኔታ ያልተጠበቁ ተግባራትን በማከናወን ብዙዎችን እያስደመሙ መሆናቸው በሰፊው እየተወራ ነው፡፡ ባልተጠበቀ ሁኔታ ወደ አክሱም ከተማ ማምራታቸውም የሰውየውን ድንገቴና አይጠበቄ ተግባር ያሳየ ነበር፡፡ ከትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር የተነሱት በሳቅ በፈገግታ የተሞላ ፎቶ ግራፍ ደግሞ የበለጠ አግራሞትን የሚፈጥር ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክልሉን ምክትል ፕሬዝዳንት ከማነጋገር አልፈው፣ የአክሱም ከተማ ህዝብ ጋር ስብሰባ ተቀመጡ፡፡ ስለ መሰረተ ልማት ግንባታ፣ ስለ አክሱም ሀውልት ጥገና፣… ደስ በሚል ሁኔታ ከህዝባቸው ጋር ተነጋገሩ፣ ተወያዩ፣ ተመካከሩ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አክሱም መሄድ ደስ የሚያሰኝ ዜና ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ትግራይ አምርተው የአክሱም ከተማ ህዝብ ጋር ተወያይተው ከተመለሱ በኋላ ዶ/ር ደብረ ጽዮን በሰጡት መግለጫ፤ “ህዝቡ የመገንጠል ስሜት ውስጥ ገብቷል” ማለታቸውን ከመገናኛ ብዙሃን ሰማን፡፡ ይህ አስደንጋጭ መግለጫ ነበር፡፡
በእነዚህ ተከታታይ ክስተቶች ላይ በመመስረት ነው ይህቺን መጣጥፍ ለማዘጋጀት የተነሳሁት፡፡ እናም፤ በቅድሚያ በአክሱም ዩኒቨርስቲ ስለተፈጠረው ግጭት ቀጥሎም ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትግራይ ጉብኝት፣ በመጨረሻም በትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት መግለጫ ላይ ያለኝን ያለኝን ጠቅለል ያለ አስተያየት እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
***
በሀገራችን በተከሰቱ የተለያዩ ግጭቶች ዙሪያ በመንግስት አካላት የተሰጡ መግለጫዎችን ስንሰማ ኖረናል፡፡ ለበርካታ ዓመታት በየመግለጫው በተደጋጋሚ ስንሰማት የኖረች የባለስልጣናት የተለመደች አባባል አለች፡፡ ይኸውም፡- “በግጭቱ የተሳተፉ እነማን እንደሆኑ ፖሊስ እያጣራ ነው” የሚል ነው የብዙ ባለስልጣናት መልስ:: ስለተከሰተው ግጭት መግለጫ የሚሰጡትም ግጭቱ በተከሰተበት አካባቢ ያሉ ኃላፊዎች ወይም የአካባቢው ፖሊስ አሊያም የክልል የማስታወቂያ ቢሮዎች መሆናቸው የተለመደ ነው፡፡ የአክሱሙን የተማሪዎች ግጭት በተመለከተ ግን ባልተለመደ ሁኔታ መግለጫ የሰጡት የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ ያልተለመደው ነገር የፕሬዝዳንቱ መግለጫ መስጠት ብቻ አይደለም፡፡ ምክትል ፕሬዝዳንቱ በሰጡት መግለጫ ላይ “ግጭቱ የብሔር ገጽታ አለው” ማለታቸውም ያልተለመደ ነገር ነው፡፡
የምክትል ፕሬዝዳንቱ መግለጫ በርካታ ጥያቄዎችን እንድናነሳ የሚያስገድድ ነው፡፡ ለመሆኑ ዶ/ር ደብረጽዮን የግጭቱን ምንጭ ከምንጊዜው አጣርተው አውቀው ነው የብሄር ገጽታ ያለው መሆኑን የተናገሩት? እዚያ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ያስቻላቸው መረጃ ቢኖር እንኳ በተጣደፈ ሁኔታ እንደዚያ ዓይነት መግለጫ መስጠት፣ በሌላ አካባቢ ሊፈጥረው የሚችለውን የስሜት መነሳሳት ግምት ውስጥ ማስገባት አልነበረባቸውም?... ዶ/ር ደብረጽዮን፤ “ህዝቡ የመገንጠል ስሜት ውስጥ ገብቷል” ያሉትን በተመለከተም በህዝቡ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ስሜት ቢኖር እንኳ ከጊዜ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እግራቸው ከትግራይ ምድር እንደ ወጣ በተጣደፈ ሁኔታ እንዲህ ያለ አስደንጋጭ መግለጫ መስጠት ነበረባቸው?
ምክትል ፕሬዝደንቱ እንደ ኢህአዴግ ከማእከላዊ መንግስት ጋር በጋራ ሲወስኑ ቆይተው፣ ወደ ትግራይ ተመልሰው የማእከላዊ መንግስትን ውሳኔዎች ማስፈጸምና ህዝቡን ከመንግስት ጎን ማሰለፍ ሲገባቸው፣ ይህንን ባለማድረጋቸው ህዝብ ቢያኮርፍ ተጠያቂው ማን ነውና ነው እንደዚያ ዓይነት መግለጫ የሰጡት? እንዲህ ያለው ትግራይን የመነጠል አካሄድ ትግራይንም ሆነ ሀገሪቱን ይጠቅማል? ከዚህ መግለጫ በስተጀርባ ያለው የፖለቲካ ትርፍ ምንድነው?... የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት የዶ/ር ደብረጽዮንን መግለጫ በተመለከተ ትችት ማቅረብ ይቻላል፡፡ ወደ ትችት መግባት ግን አልፈለግሁም:: ከዚህ ይልቅ ለማንሳት የምፈልገው፤ በትግራይ ልጆች “ኢትዮጵያዊው ፑቲን” እየተባሉ የሚሞካሹት ዶ/ር ደብረ ጽዮን፤ “ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ምን ነክቷቸዋል? በአሁኑ ወቅት በምን ዓይነት የስነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ ነው ያሉት?” የሚሉ ጥያቄዎችን ነው፡፡
ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት መላምት ውስጥ መግባት አስፈላጊ ሆኖ አይታየኝም፡፡ ጊዜ መልስ ይስጥ ብሎ ማለፍን እመርጣለሁ፡፡ በበኩሌ ዶ/ር ደብረጽዮን ሰሞኑን እየተናገሩት ያለውን ነገር ስታዘበው ፈረንጆቹ “Politically incorrect” የሚሉት ዓይነት “የፖለቲካ ስህተት” መስሎ ይታየኛል፡፡ መፍትሄው “ህዝብ ልገንጠል እያለ ነው” ብሎ ማስፈራራትም አይደለም፡፡ (መፍትሄውን ወደ ኋላ እመለስበታለሁ)
አጠቃላይ ሁኔታዎችን እናንሳ… ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ስልጣን ከጨበጡበት እለት ጀምሮ የትግራይ ፖለቲከኞች ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ መቀሌ መሄዳቸው በገሃድ የተስተዋለ ጉዳይ ነው፡፡ ፖለቲከኞቹ ባለፉት ዓመታት “አራት ኪሎ” አካባቢ የሰሩትን ስለሚያውቁ አሁን የምኒልክን ቤተ መንግስት የተቆጣጠሩት ኃይሎች የከፋ “የፖለቲካ ሽመል” ከመምዘዛቸው በፊት ስልታዊ ማፈግፈግ (strategic retreat) በማድረግ ምሽግ ለመያዝ ወደ ሰሜን ያቀኑ ይመስላል፡፡ (በዚህ ረገድ የተሳካላቸው ይመስላል)
ፖለቲከኞቹ የሚያገኙትን የፖለቲካ ትርፍ አስልተው ምንም ዓይነት ውሳኔ ቢወስኑ የሚገርም አይደለም፡፡ የማዕከላዊ መንግስት ትግራይን በተመለከተ የሚያራምደው ፖሊሲ ግን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብዬ ስለማስብ የተወሰኑ ነጥቦችን ማንሳት እወዳለሁ፡፡ በማእከላዊ መንግስት የሚከናወኑ ተግባራትን ስናይ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ መንግስት ትግራይን በተመለከተ የሚያራምደው “ያልተጻፈ ፖሊሲ” ይኖረው ይሆን? የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡ ለዚህ አባባሌ ብዙ ብዙ መገለጫዎችን መጠቃቀስ ይቻላል፡፡ ወደ ትግራይ የሚጓጓዙ ተሽከርካሪዎች የትግራይ ህዝብ ጭምር አዋጥቶ፣ ታክስና ግብር ከፍሎ በተገነቡ በፌዴራል መንግስት የሚተዳደሩ ክልል ዘለል አውራ ጎዳናዎች እንዳይሄዱ በጉልበተኞች መሰናክል ሲፈጠር ፌዴራል መንግስት ምን እርምጃ ወሰደ? ወደ ትግራይ የሚጓጓዙ ንብረቶች በጠራራ ፀሐይ በወሮበሎች ሲዘረፉ ምን እርምጃ ተወሰደ? እነዚህ ሁኔታዎች ህዝብን አያስከፉም? የሚሉ ተጨማሪ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ግድ ይለናል፡፡ በመሆኑም ትግራይን የረሷት የመሰሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሰሞኑን ወደ ትግራይ ማቅናታቸው የተካረሩ ሁኔታዎች እንዲረግቡ የሚያደርግ በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
***
ይህንን ጽሁፍ ለማሰናዳት ሳስብ ለአንዳንድ ተጋሩ የፌስቡክ ወዳጆቼ የዶ/ር ደብረ ጽዮንን መግለጫ በተመለከተ ጥያቄ አቅርቤላቸው ነበር፡፡ የአንዳንዶቹ መልስ እንዲህ ይላል፡- “… ወጣቱ አካባቢ የመገንጠል አዝማሚያ ሊኖር ይችላል። ለዚህም እህልና ሸቀጥ እንዳያልፍ ሲያስቆሙና ሲዘርፉ የከረሙት ፋኖዎችና እጁን አጣጥፎ ያያቸው የክልሉ፣ ብሎም የፌደራል መንግስት ተጠያቂ ናቸው። ቅጣት በሚመስለው በዚህ ድርጊት፣ እንዲሁም በመጠቃት ስሜት ሰዉ መገንጠል ቢያስብ አይገርምም። ይህንን ሁኔታ ሕወሓት ለራሷ ፕሮፓጋንዳ በደንብ መጠቀሟ ግልጥ ነው--”  አንደኛው ደግሞ “ህወሓት የበለጠ ኢትዮጵያዊ በመሆን የትግራይን ህዝብ እያስመታ ያለ ድርጅት ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ልቡ ከሸፈተ ቆይቷል፡፡ የግዜ ጉዳይ ነው እንጂ እውን ይሆናል፡፡ ደብረፅዮን ከመሬት ተነስቶ አይደለም የተናገረው” የሚል አስተያየት ነው የሰጠኝ፡፡
ሌላው ደግሞ “… የመገንጠል ሀሳብ የሌለው ህወሓት ነው… የትግራይ ህዝብ ስንት ጊዜ በኢትዮጵያ ይካድ? ጽሁፍህ ይህንን ጥያቄ ከእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የሚመልስ ይሁን” ብለውኛል፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ “ስለ መለያየት ማንም ያውራ ማንም በፕሬዝዳንቱ ስለተነገረ ሊገርመን አይገባም፡፡ በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ የሚመስል ድርጊት፣ መንገድ መዝጋት፣ ንብረትና ሀብት እየተዘረፈ ዝም ያልን ሰዎች፤ ነገ የታሪክ ተወቃሾች እንደሚያደርገን ማወቅ ይገባል፡፡ በተለይ ከወደ ወሎ አካባቢ እማንጠብቀው ድርጊት ነው የተፈጸመው፡፡ አሁንም ለማስተካከል አልመሸም:: የአካባቢ ተቆርቋሪ ነን እምትሉ ሁሉ አካባቢውን ከዝርፍያ አጽዱ፣ በማናለብኝነት ስሜት የተዘጋውን መንገድ አስከፍቱ፡፡ ህዝብ ለህዝብ ለማቀራረብ ድከሙ፡፡ ነገ ጦሱ ለሁሉም ነው” ብለውኛል፡፡ ተመሳሳይነት ያላቸው በርካታ ምላሾች ደርሰውኛል፡፡
ለእነዚህ አስተያየቶች ምላሽ የሚሆን ሃሳብ ለማመንጨት ወደ ኋላ መለስ ብለን አንዳንድ የታሪክ እውነታዎችን እንቃኝ፡፡ በኔ እምነት ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)፤ የተሰኘቺው የፖለቲካ ድርጅት ገና ካነሳሷ “ህዝባዊ” አልነበረቺም፡፡ ደርግ በትግራይ ህዝብ ላይ በተከተላቸው ተገቢ ያልሆኑ ፖሊሲዎችና እነዚያን ፖሊሲዎች መሰረት አድርጎ በወሰዳቸው የጭቆናና የጭፍጨፋ እርምጃዎች፤ ህዝቡ ከሁለት ጋኔኖች አንዱን የመምረጥ አጣብቂኝ ውስጥ ገባ፡፡ በመጨረሻም ሕወሓትን ደግፎ ደርግን ለማስወገድ ወሰነ፡፡ ይህም አማራጭ የማጣት ውሳኔ ህወሃት “ህዝባዊ ነኝ” የሚል የድርቅና አመለካከት እንዲኖራት እንዳደረገ መገንዘብ ይቻላል፡፡
በዚህም ወቅት ቢሆን ህወሓት “ህዝባዊ” አይደለቺም፡፡ ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ መንግስት፣ በትግራይ ክልል ላይ እየተከተለው ባለው ለዘብተኛ አቋምና ከወደ አማራ ክልል እየተፈጠረ ባለው ጫና ምክንያት ህዝቡ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡ ዛሬም አማራጭ በማጣቱ “ከማላውቀው መልአክ የማውቀው ጋኔን ይሻለኛል” ወደሚል ውሳኔ እየተገፋ መሆኑ ይስተዋላል፡፡ በዚህም ምክንያት በህብረተሰቡ ውስጥ የመነጠል ስሜት መቀንቀኑ የሚጠበቅ ነው፡፡ ህብረተሰቡ ውስጥ እንዲህ ያለ የመነጠል ስሜት መንጸባረቁ ደግሞ ቀድሞም “ህዝባዊ” ላልነበረቺው ህወሓት፤ ሰርግና ምላሽ መሆኑ የሚያስገርም አይሆንም:: የሰሞኑ የዶ/ር ደብረጽዮን መግለጫ አንደምታ፤ ህወሓት የትግራይን ህዝብ ሰብአዊ ጋሻ (Human Shield or Hostage) አድርጋ የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር የተነሳች መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡
በበኩሌ ህወሓት ለትግራይም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ውጋት ከመሆን የዘለለ ህዝባዊ ዓላማ አላት የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይህ ማለት ግን ህወሓት በታሪኳ የሰራቺው ፋይዳ ያለው ነገር የለም ማለት አይደለም፡፡ ደርግን በመጣሉ ሂደት ህወሓት የነበራት አቅምና የተግባር እንቅስቃሴ አክብሮት ሊቸረው የሚገባ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ዴሞክራሲን በማምጣቱ ሂደት ግን ህወሓት ከመገንባቷ ማፍረሷ ይበልጣል፡፡ ሀገሪቱን አሁን ላለቺበት ውጥንቅጡ የወጣ ሁኔታ የዳረጋት በዋናነት ህወሓት ይዛው የመጣቺው የመገንጠል ዓላማና የጎሣ ፖለቲካ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ህወሓት በጎ ነገር አለመስራቷ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን ሊለውጥ የሚችል አዲስ አስተሳሰብና አመለካከት ይዘው የመጡ ኃይሎችን “ባልበላውም ጭሬ ላፍስሰው” በሚል መንፈስ ስራ እንዳይሰሩ የማድረግ መንገድን መከተሏ ነው፡፡
ህወሓት አሁንም አቅም የላትም ተብላ የምትናቅ ድርጅት አይደለቺም፡፡ ህወሓት ትግራይንና ኢትዮጵያን እንደ አሻንጉሊት ልትጫወትባቸው እንደምትፈልግ ከአንዳንድ የተግባር እንቅስቃሴዎቿ መገመት ይቻላል፡፡ ህወሓት ከአፈጣጠሯ ጀምሮ አምባገነን፣ ፀረ ዴሞክራሲ ድርጅት ናት፡፡ ለበጎ ሥራ ያልታደለች ቢሆንም ለክፋት የሚሆን አቅም አታጣም፡፡
በሌላ በኩል፤ በአሁኑ ወቅት በትግራይ አካባቢ ሆድ የባሳቸው ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት ነብይነትን የሚጠይቅ ጉዳይ ሆኖ አይታየኝም፡፡ በዚህ ወቅት በትግራይ “ተገፋን” ብለው ያኮረፉ ሰዎች የሉም ብሎ መደምደምም አይቻልም፡፡ የመነጠል ስሜትም ሊንጸባረቅ ይችላል፡፡
ይሁን እንጂ የትግራይ ህዝብ፣ ኢትዮጵያ ችግር ላይ ስትወድቅ ይጋፈጣል እንጂ “እናንተው ተወጡት” ብሎ ፊቱን የሚያዞር ራስ ወዳድ አይደለም፡፡ የትግራይ ህዝብ ለዚች ሀገር ከማንም በላይ ከፍ ያለ መስዋእትነት የከፈለ ህዝብ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በመመስረቱ ሂደት ቀዳሚ ነበር:: የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር ሳያስደፍር ጠብቆ ኖሯል፡፡ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ የመገንጠል ዓላማ ያላት ህወሓት ናት፡፡ ዶ/ር ደብረጽዮን የነገሩን የህወሓት አባላትን ስሜት ነው፡፡ እነሱንም ቢሆን “ከእብደታቸው” እንዲመለሱ እናስታምማለን እንጂ “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው” ልንላቸው አይገባም፡፡ በአጠቃላይ 6 ሚሊዮን የሚሆነው የትግራይ ህዝብ ቸል ሊባል አይገባውም፡፡
ለማንኛውም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ መንግስት፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ፈንጂ እየተጠመደ መሆኑን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ መፍትሄው ምንድነው? ከተባለ፣ መድኃኒቱ ከህወሓት የተሻለ በማሰብ፣ የላቀ ሥራ በመስራት ለትግራይ ህዝብ አለኝታነትን በተግባር በማረጋገጥ ህወሓትን ራቁቷን ማስቀረት ነው፡፡ ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ጠቃሚ የልማት ፖለሲዎችን በማውጣት በአጭር ጊዜ ተጨባጭ፣ ስር ነቀል፣ በያንዳንዱ ሰው ቤት ደጃፍ የሚደርስ የልማትና ብልጽግና ውጤት ማስመዝገብ ነው፡፡ ይህንን ተጨባጭ ለውጥ ለማስመዝገብ ደግሞ የትግራይን ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ባለሃብቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አክቲቪስቶች፣ ሴቶችና ወጣቶች በማሰባሰብ፣ በማወያየት የጋራ አቋም ይዞ ወደ ሥራ መሰማራት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡
በትግራይ ምሁራን በኩል ደግሞ ብሔርተኝነት ሰዎች የፈጠሩት (constructed) መሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል:: የትግራይ ህዝብና ልሂቃኑ ብሄርተኛነትን በዴሞክራሲ አግባብ በመግራት ለሀገራዊ አንድነቱ ቅድሚያ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የትግራይ ህዝብ ደሙን ሲያፈስ፣ አጥንቱን ሲከሰክስ፣ ልጆቹን ሲገብር፣… የኖረው ትግራይን ለመነጠል ሳይሆን እንደ ሀገር ኢትዮጵያን ለመገንባት መሆኑን ልብ ልትሉት ይገባል፡፡ ገና ብዙ መስዋእትነት ይጠብቃችኋል፤ ይጠብቀናል:: ልንሰለችም ተስፋ ልንቆርጥም አይገባም፡፡ ተስፋ ቆርጦ ማፈግፈግ፤ ቀደምት አያቶቻችን የከፈሉትን መስዋእትነት የትም ጥሎ መፈርጠጥ ነው የሚሆነው::
እንደ መውጫ አንዲት ሃሳብ ልጨምር…
አንዳንድ የትግራይ ወዳጆቼ ደጋግመው የሚያነሱብኝ ነገር “… እህልና ሸቀጣ ሸቀጥ ወደ ትግራይ እንዳያልፍ ተደርጓል… ፋኖዎች ወደ ትግራይ የሚጓጓዝ ተሽከርካሪ አስተጓጉለዋል… ማዕቀብ የሚመስል እርምጃ ተወስዷል… በተለይ ከወደ ወሎ አካባቢ እማንጠብቀው ድርጊት ነው የተፈጸመው… ዘመዶችህ መኪና አስቁመው በግና ፍየል ጭምር ቀምተውናል…” የሚሉ ወቀሳዎችን ያካትታል፡፡
ወቀሳውን የነገርኳቸው በወሎ በኩል ያሉ ወገኖቼ ደግሞ “ብረት ይዘው የመጡ ልጆቻቸውን የምንበላውን አብልተንና አጠጥተን፣ ስንቅና ፍቅር ሰጥተን ነው ወደ መሀል ሀገር የሸኘናቸው፡፡ ለዚህ ውለታችን የመጀመሪያ እርምጃቸው ፋብሪካ መትከል አልነበረም፡፡ ደርግ የተከለልንን ጄኔሬተር ከወልዲያ፣ ከመርሣ፣… ነቅለው ወሰዱ፡፡ ብዙ ነገር በቤታችን ደጃፍ እየተጫነ ሲያልፍ ‘ግድ የለም አንድ ቀን ያስታውሱናል’ እያልን በትዝብት አለፍነው:: በይህ ብዙም አልከፋንም…  ልጆቻቸው በጥጋብ ተነሳስተው ስጋችንን ሰርስሮ፣ አጥንታችንን ሰብሮ የሚገባ ስድብ በአደባባይ ሲሰድቡን እነሱስ ምን አደረጉ?… እዚያው አገራቸው ላይ መሳደባቸው ሳያንስ፣ እዚሁ እቀያችን ድረስ መጥተው ሲሰድቡን የኛስ ልጆች ምን ያድርጉ?... ለማንኛውም ልጅና ልጅ ነው የተጣላው፡፡ አገር አልተጣላም፡፡ ከሦስት ቀን በላይ ኩርፊያ አላህ አይወደውም፡፡ አሁን ሁሉም ነገር አልፏል፡፡ መሀላችን የገባውን ሸይጧን በፈጣሪ ስም እናባረው… እላፊ ነገር ተሰርቶ ይሆናል… የበደለ ይካስ! … በላቸው” ብለውኛል፡፡
እንዲህ ያለው ሁኔታ ለእኔ “የገደለው ባልሽ፣ የሞተው ወንድምሽ፣ ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ” እንዲሉ ነው የሆነብኝ፡፡ እርቅ አማራጭ የሌለው አማራጭ ነው… ሽማግሌ ይዤ፣ ሁለቱም እግር ላይ ወድቄ፣ የእናቴንና የአባቴን ዘመዶች (ወሎንና ትግራይን) ማስታረቅ ቀዳሚ አጀንዳዬ መሆን ይገባዋል፡፡ በሽምግልና የምታግዙኝ ወገኖቼ በአድራሻዬ አግኙኝ!
ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻው: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1726 times