Saturday, 22 June 2019 11:12

“ሳድግ አነስኩ” አለች ውሻ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንዲት ሙሽራ ከባሏ ቤት ወደ እናቷ ቤት፣ እናቷን ልታይ ትመጣለች፡፡
እናት ጥጥ እየፈተሉ ነው፡፡ ልጅ እንዝርቷን እያሾረች በማዳወር እያገዘች ነው፡። በመካከል እናት ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡
“አንቺ ልጅ”
“አቤት እማዬ”
“ወደፊት የሚሆነው አይታወቅም”
“ምኑን እማዬ?”
“አይ፣ ድንገት ልጅ ፀንሰሽ ሊሆን ይችላልኮ፡፡ የገንፎ እህልም…ምኑም ሳይዘጋጅ፣ መውለጃሽ ከተፍ እንዳይልና እንዳታዋርጂን!”
“አይ አስቤበታለሁ እማዬ”
“እና መቼ ነው ቀንሽ?”
“አይ እማዬ፤ በየቀኑ ይጨምርበታልኮ፡፡ እኔ እቅጩን ቀን በየት አውቄው ብለሽ ነው?”
“አዬ የኔ ልጅ፣ እኔም የፈራሁት ይሄንኑ ነበር!”
*   *   *
በሀገራችን ዛሬም ለውጥ ይጠበቃል፡፡ ከስንትና ስንት ዓመታት በኋላ፤
“ሞኙን ላኩትና ሞኞች ሞኞች አገር
ሞኙም አልጠየቃት፣ ሞኟም አትናገር”
የሚለውን ተረት ለመቃኘት መገደድ የለብንም፡፡
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ጥበብ ይጠይቃል፡፡ የውስጡ ዲፕሎማሲ አንድ ሥራ ነው:: የደጁ ዲፕሎማሲ ሌላ ሥራ ነው፡፡ ሁለቱ ካልተቀናጁ ደግሞ የራሱ ፈተና አለበት፡፡
አንዳንድ የአገራችን ዘፈን ግጥሞች የበሰለ ቁም ነገር አላቸው፡፡ ግን በዜማና በቅላፄ ሲታጀቡ የግጥሞቹ ፍሬ-ጉዳይ ይመነምንባቸዋል፡፡ ጉዟችን ደግሞ በጣም ውስብስብ ነው፡፡ በየቀኑ ይጨመርበታል፡፡ ከስንት ዘመን በኋላ ዛሬም ማለት ያለብን፣ “የአዝማሪና ውሃ ሙላትን” ጉዳይ ነው፡፡ ቢያንስ ላልደረሰበት ትውልድ አንዳች መቅሰስ እንደሚሆን ጥርጥር የለንም፡፡
የቆየ ተረታችንን ልብ እንበል፡-
“ሴትየዋ ከውሽማዋ ጋር እንደተዘናጋች ባል ይደርሳል፡፡ ውሽሜ አልጋ ሥር ይገባል፡፡ ግን ክፉኛ ይንቀጠቀጣል! ይርገፈገፋል!
የፈረደባት ውሽሚት (የተቸገረች ሚስት) ጥጧን እያባዘተች፣ በዜማ እንዲህ ትላለች፡-
“የወንፈሌ፣ የወንፈሌ ጥጥ፣
ተው አትንቀጥቀጥ፣
እርጋ - ይወጣሉ ደጋ፣
እርጋ - ይወጣሉ ደጋ!”
አሁን ወደ ከበደ ሚካኤል ግጥም ወደ “አዝማሪና ውሃ ሙላት” እንጓዝ፡-
አንድ ቀን አንድ ሰው ሲሄድ በመንገድ፣
የወንዝ ውሃ ሞልቶ ደፍርሶ ሲወርድ፣
እዚያው እወንዙ ዳር እያለ ጎርደድ፣
አንድ አዝማሪ አገኘ ሲዘፍን አምርሮ፣
በሚያሳዝን ዜማ ድምፁን አሳምሮ፣
ምነው አቶ አዝማሪ ምን ትሰራለህ፣
ብሎ ቢጠይቀው ምን ሁን ትላለህ፣
* * *
አላሻግር ብሎኝ የውሃ ሙላት፣
እያሞጋገስኩት በግጥም ብዛት፣
ሆዱን አራርቶልኝ ቢያሻግረኝ ብዬ፣
አሁን ገና ሞኝ ሆንክ ምነዋ ሰውዬ፣
ነገሩስ ባልከፋ ውሃውን ማወደስ፣
ግን እንደዚህ ፈጥኖ በችኮላ ሲፈስ፣
ምን የሰማኝ ብለህ ትደክማለህ ከቶ፣
ድምፁን እያሽካካ መገስገሱን ትቶ፣
እስኪ ተመልከተው ይህ አወራረድ፣
ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ፣
ተግሳፅም ለፀባይ ካልሆነው አራሚ፣
መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ!
ዛሬም ሰሚ እንዳይጠፋ እንፀልይ ጎበዝ!

Read 14438 times