Saturday, 22 June 2019 11:06

ሞተረኞች ክልከላው ኑሮአቸውን እንደሚያቃውሰው ተናገሩ

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(2 votes)

ህጋዊነታቸውን ጠብቀውና ተደራጅተው መሥራት ይችላሉ - አ.አ መስተዳድር
                                              

                      በአዲስ አበባ ከሞተር ሳይክሎች ጋር የተያያዙ የሌብነትና ንጥቂያ ወንጀል መበራከትን ተከትሎ ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ላይ የአዲስ አበባ መስተዳድር ከመንግስት መ/ቤቶችና ከኤምባሲዎች ሞተር ሳይክሎች በቀር በግል ሥራ ላይ የተሰማሩ ማናቸውም ሞተር ሳይክሎች ከሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ መንቀሳቀስ አይችሉም ሲል እገዳ ጥሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሄን ተክትሎም በርካታ የኑሮ መተዳደሪያቸውን የሞተር ሳይክል አገልግሎት በመስጠት ላይ ያደረጉ ነዋሪዎች፤የመስተዳደሩ ድንገተኛ እገዳ ኑሮአቸውን እንደሚያቃውሰው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ትላንት ማተሚያ ቤት በመግቢያ የመጨረሻዋ ሰዓት ላይ በደረሰን መረጃ መሰረት፤ የሞተር ሳይክል ባለቤቶች አስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የአዲስ አበባ ታርጋ በማውጣት፣በመደራጀትና ከመንገድ ትራንስፖርት ባጅ በመውሰድ በህጋዊነት መሥራት እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡ ሁሉንም በደፈናው አልከለከልንም ያለው መስተዳድሩ፤በክልል ታርጋና ያለ ታርጋ እንዲሁም ከመንገድ ትራንስፖርት ባጅ  ሳይወስዱና ሳይደራጁ መንቀሳቀስ ግን የተከለከለ ነው ብሏል - ትላንት ምሽት ላይ ባደረሰን መረጃ፡፡ በከተማዋ ውስጥ ከሚፈፀሙ የቅሚያና የዘረፋ ወንጀሎች መካከል ከ72.8 በመቶ በላይ የሚሆነው በሞተር ሳይክል የታገዘ መሆኑን ከኮሚሽኑ ያገኘነው ሪፖርት ያመለክታል:: አዲስ አበባ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት ሞተር ሳይክሎች አብዛኛዎቹ የክልል ታርጋን የለጠፉ ሲሆን ሰሌዳ የሌላቸው ሞተር ሳይክሎችም ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን የጠቆመው የፖሊስ መረጃ፤ ወንጀል ፈፅመው የሚሰወሩትን ሞተር ሳይክሎች ለማግኘት ይህ ሁኔታ እንቅፋት እንደሆነም ያመለክታል፡፡ በከተማዋ ባለፉት 10 ወራት አስራ አራት የሞተር ሳይክል አደጋዎች ደርሰው 15 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውንም መረጃው ያሳያል፡፡
ከኮሚሽኑ እንዳገኘነው መረጃ፤ አብዛኛዎቹ የክልል ሰሌዳ ያላቸው ሞተር ሳይክሎች የተመዘገቡት በገጠር በሚኖሩ እናቶች ስም ሲሆን ከእነዚህ ሞተር ሳይክሎቹ በስማቸው ከተገዛላቸው እናቶች መካከል ሞተሩ በስማቸው መሆኑን እንኳን የማያውቁ በቁጥር በርካታ መሆናቸውንና ይህም ፖሊስ ወንጀል ፈፃሚዎቹን ለማግኘት የሚያደርገውን ጥረት አስቸጋሪ እንዳደረገው ከፖሊስ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡ ሰሌዳ በሌላቸው ሞተር ሳይክሎች ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች ሞተርሳይክሎቹን መንገድ ላይ አቁመዋቸው የሚሄዱ በመሆኑ ወንጀለኞቹን ተከታትሎ ለመያዝ መቸገሩንም ፖሊስ አስታውቋል::
ይህንን ሁኔታ ተከትሎ በከተማዋ በሞተር ሳይክል የሚፈፀሙ ወንጀሎች በመበራከታቸው ሳቢያ የከተማዋ መስተዳድር ህጋዊ ፈቃድ ከተሰጣቸው መስሪያ ቤቶችና ኤምባሲዎች ሞተር ሳይክሎች በስተቀር ከሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ማንኛውም ሞተር ሳይክል በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ መንቀሳቀስ እንደማይችል ገልጿል፡።
የመስተዳድሩ ውሳኔ በሞተር ሳይክል በመታገዝ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ከማስቻሉም በላይ በከተማዋ የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች ይገልፃሉ፡፡ በሌላ በኩል፤ ክልከላው አግባብ እንዳልሆነ በመሞገት መንግስት ሁሉንም የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች በአንድ አይን በማየት የወሰነውን ውሳኔ ደግሞ ሊያጤነው እንደሚገባ የሚገልፁ የከተማዋ ነዋሪዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡
የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ወ/ሮ ሰውነት ፀጋዬ፤ ነዋሪነቷ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ሲሆን ቄራ አካባቢ በሚገኝ አንድ የመኪና መለዋወጫ ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ ትሠራለች፤ የኮንዶሚኒየም ቤት ሃያት ጨፌ በሚባል አካባቢ የደረሳት ቢሆንም ለባለቤቷና ለእሷ ስራ የቦታ እርቀት ያለው በመሆኑ ቄራ አካባቢ ተከራይታ ትኖራለች፡፡
መጋቢት 6 ቀን 2011 ዓ.ም እራሷን ህመም ስለተሰማት ከስራ ቦታዋ አስፈቅዳ ወደ ቤቷ ለመሄድ ትነሳለች፤ ነገር ግን ብዙም ሳትጓዝ በሞተር ሳይክል ላይ የተሳፈረ ግለሰብ በእጇ አንጠልጥላው የነበረውን ቦርሳ ይጐትታል፡፡ እሷም ቦርሳዋን ለማስጣል  ብትታገልም ያደረገችው ነጠላ ጫማ አንሸራቷት፣ የእግረኛ መተላለፊያ መንገድ ጠርዝ ላይ በጐኗ ትወድቃለች፡፡ ከቦርሳዋም ከጤናዋም ያልሆነችው ሰውነት፤ ሁለት የጐን አጥንቷና የግራ እግሯ መገጣጠሚያዋ ላይ ስብራት ደረሰባት፡፡
በወቅቱ ጉዳቱን ያደረሱባትን ሞተረኛና ተሳፋሪ ማንም ሊይዛቸው አልቻለም፤ ምክንያቱ ደግሞ ሞተር ሳይክሉ ታርጋ የሌለው መሆኑ ነው ሰውነት፤ ከህመሟ ለማገገም ያወጣችው ወጪ ለከፋ ችግር እንደዳረጋት ትናገራለች፤ ዛሬም ግን ጉዳት አድራሾቿ አልተገኙም፡፡
ከስምንት ወራት በፊት ጋብቻዋን ፈፅማ፣ ኑሮዋን ጎተራ ኮንዶሚኒየም ውስጥ ያደረገችው ወ/ሮ አየለች መብራቱ፤ በግል ድርጅት ውስጥ በሒሳብ ሠራተኝነት ተቀጥራ ትሠራለች፡፡ በአንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የሚሠራው ባለቤቷ፤ የግል መኪና ቢኖረውም፣ አብዛኛውን ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ ለስራ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ በትራንስፖርት ነው የምትጠቀመው፡፡ “እንዳልነዳ ደግሞ እፈራለሁ” ትላለች ወ/ሮ አየለች፡፡ ሚያዚያ 8 ቀን 2011 ዓ.ም ግን ለአየለች ጥሩ ቀን አልነበረም፤ ጠዋት ከመኖሪያዋ የኮንዶሚኒየም ግቢ ወጥታ ዋናውን አስፋልት ለመሻገር ስትል ከየት መጣ ያላለችውና ከኋላው ሰው የጫነ ሞተር ሳይክል አጠገቧ ደርሶ ቦርሳዋን ይነጥቃታል፡፡ ወ/ሮ አየለች ቦርሳዋን ለማስለቀቅ ታግላ ቦርሳዋን ብታስጥልም በደረሰባት የመውደቅ አደጋ ምክንያት በሆዷ የነበረውን የአራት ወር ጽንስ ግን ማትረፍ አልቻለችም፡፡
በመኪና ሞተሩን ለማስቆም የተባበሯት ወጣቶች፤ ሹፌሩና ከኋላ የተሳፈረው ልጅ ሞተሩን አቁመው በማምለጣቸው ሊይዟቸው አልቻሉም፡፡ ሞተሩም ቢሆን ምንም ታርጋ ስለሌለው እስካሁን አካባቢዋ ላይ ባለ ጣቢያ ውስጥ ቆሞ ይገኛል እንጂ ባለቤቱ ታውቆ ወንጀሉን የፈፀመባትን ለህግ ለማቅረብ አልተቻለም፡፡  ሀይሌ ማሞ ይባላል፡፡ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪ ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ከአዲስ አበባ በ65 ሺህ ብር የገዛው ሞተር ሳይክል፤ እሱን ጨምሮ አምስት ቤተሰቦቹን በቀን በሚያገኘው ሦስት መቶ ብር ያስተዳድራል፡፡ ቄራ አካባቢ በሞተር ሳይክል እቃ በማድረስ ለሰዎች በመላላክ እንደሚተዳደር የገለፀው ሀይሌ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰሞኑን ያስተላለፈው ውሳኔ እንዳሳዘነው ይናገራል፡፡
“የከተማ አስተዳደሩ የሰጠው ውሳኔ በእርግጠኝነት ለፍቶ አዳሪውን የሚጎዳ ውሳኔ ነው:: ከተማ አስተዳደሩ የሚያግደው ህገ ወጦችን ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡ ያለበለዚያ ግን አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ ነው የሚሆነው” ይላል - በሞተር ሳይክል የሚተዳደረው ሀይሌ፡፡ የተላለፈው ውሳኔው ለከፋ ችግር እንደሚዳርገውና ሌላ አማራጭ ስራ እንደሌለውም ይናገራል፡፡
ውሳኔውን መስተዳደሩ ሊያጤነው ይገባል ያለው ሀይሌ፤ ሌቦች የሉም አልልም፤ እነሱ በፈፀሙት እኛ ለፍቶ አዳሪዎችን መጎዳት የለብንም ብሏል፡፡
አበበ አምባቸው፤ ጎፋ መብራት ኃይል አካባቢ የሞተር ሳይክል አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም ከደብረዘይት 80 ሺህ ብር በገዛው ሞተር ሳይክል፤ በቀን ከሰባት መቶ ብር በላይ ገቢ እያገኘ፣ ሶስት ልጆቹና ባለቤቱን ጨምሮ በኪራይ ቤት ውስጥ እንደሚያስተዳድር ይገልፃል፡፡
“የአዲስ አበባ መስተዳደር ያስተላለፈው ውሳኔ ለእኔ ዱብ እዳ ነው” ያለው አበበ፤ ውሳኔው ከመወሰኑ በፊት ተጠቃሚ ህዝብንና እኛን ሊያወያዩን ይገባ ነበር” ሲል ይናገራል፡፡
በቦሌ ሚካኤል አካባቢ ለደንበኞቹ እቃ የማመላለስ ስራ የሚሰራው የሞተር ሳይክል ባለቤቱና ሹፌሩ መሀመድ ሸረፈዲን፤ ሞተር ሳይክሉን ከአንድ ወር በፊት በ91 ሺህ ብር ከደብረዘይት መግዛቱን ይናገራል፡፡ ሁለት ወንድሞቹን አባታቸው ከሞተ በኋላ የማስተማር ኃላፊነት የተጣለበት መሀመድ፤ ከጋራዥ እቃ ማመላለስ፣ ጫት ማድረስና የተለያዩ ፖስታዎችን በመላላክ በቀን ከስድስት መቶ ብር በላይ ገቢ ያገኛል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ ቅር መሰኘቱን የገለፀው መሀመድ፤ “ሌቦች እንዳሉ እናውቃለን፤ መንግስት እነሱን አጋልጠን እንድንሰጥ ከለላ ቢያደርግልንና ተባበሩ ቢለን እናጋልጣለን” ይላል፡፡ ነገር ግን ሁሉንም በአንድ ጨፍልቆ መወሰኑ የቤተሰቦቻችን ህልውና አደጋ ላይ ይጥላል ብሏል፡፡
የተከራየነውን ቤት ካልከፈልንበት መኖር አንችልም ያለው መሀመድ፤ ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ ከሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑ ከተለያዩ ቦታዎች የተውጣጡ ሞተረኞች ከትናንት በስቲያ ቄራ አካባቢ ቢሰባሰቡም በፖሊስ መበተናቸውን  ይገልፃል፡፡
አሁንም መንግስት ጉዳዪን ቁጭ ብሎ ሊያየው ይገባል የሚለው መሀመድ፤ “ዘረፋ ላይ የተሰማሩትን እኛ ማጋለጥ እንችላለን፤ ነገር ግን ሰርቶ የሚበላውን መንግስት ከለላ ሊሰጠው ይገባል” ብሏል፡፡
አቶ ኤፍሬም ዮሴፍ የጀሞ አካባቢ ነዋሪ ናቸው:: ለፍጥነትና አስቸኳይ ነገር ሲገጥማቸው ሞተር ሳይክልን እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ፡፡ የሞተር ሳይክል መከልከል ተገቢ አይደለም የሚሉት አቶ ኤፍሬም፤ በተለይ ለፍጥነት ስራ ሞተር ሳይክል ጠቃሚ መሆኑን ገልፀው፤ ያደጉት አገራትም ይጠቀሙበታል ይላሉ፡፡  አቶ አለማየሁ ግርማ ግን የሞተር ሳይክል ክልከላውን ይደግፋሉ፤ ምክንያታቸው ደግሞ ህገ ወጦች ናቸው የሚል ነው፡፡ አብዛኛው ሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች ስብዕና የሌላቸው ናቸው፤ ለንጥቅያ እንዲመቻቸው በተለይ ሴቶችን በመጠጋትና እንዲደነግጡ በማድረግ፣ ቦርሳቸውን ነጥቀው ሲሄዱ ሶስት ጊዜ ማየታቸውንም ይናገራሉ። አብዛኛው ሞተር አሽከርካሪ እድሜያቸው በጣም ትንሽ በመሆኑ ለመታየትና በሰዎች መደናገጥ ለመሳቅ ከባህሪ ወጣ ያለ ተግባር እንደሚፈፅሙ ጠቁመው፤ ይሔም ከተማዋን አበላሽቷታል ባይ ናቸው - አቶ አለማየሁ፡፡

Read 2088 times