Sunday, 23 June 2019 00:00

ያደጉት አገራት ለክትባት ያላቸው አመለካከት ዝቅ ያለ ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የተሻለ እድገት ያላቸው አገራት ክትባትን በተመለከተ ያላቸው በጎ አመለካከት ከድሃ አገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ያለ እንደሆነ ዌልካም የተባለ አንድ የጥናት ተቋም ባለፈው ሰኞ ይፋ ያደረገው አለማቀፍ ጥናት አመልክቷል፡፡
በ144 የአለማችን አገራት ውስጥ በሚገኙ ከ140 ሺህ በላይ ሰዎች ላይ የተሰራውን ጥናት ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ከአለማችን አገራት ለክትባት እጅግ ዝቅተኛ የሆነ አመለካከት ያላቸው ህዝቦች የሚገኙባት አገር ፈረንሳይ ስትሆን 33 በመቶ ያህል የአገሪቱ ዜጎች ክትባት ጥሩ አይደለም ብለው እንደሚያስቡ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡
በአብዛኞቹ ያደጉት አገራት ለክትባት ጥሩ ያልሆነ አመለካከት መኖሩን የጠቆመው ጥናቱ፣ ምላሻቸውን የሰጡት ሰዎች በሙሉ ክትባትን እንደሚደግፉ የገለጹባቸውን ባንግላዴሽንና ሩዋንዳን በመሳሰሉ ያላደጉ አገራት በአንጻሩ ለክትባት በጎ አመለካከት መኖሩን አስረድቷል፡፡
በአለማቀፍ ደረጃ 79 በመቶ ያህል ሰዎች ክትባት ችግር የለውም ብለው እንደሚያስቡ፣ 84 በመቶ ያህሉ ደግሞ ክትባት በሽታዎችን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ነው ብለው እንደሚያስቡ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ለክትባት በጎ አመለካከት አለመኖር አለማቀፍ ክስተት መሆኑንና ከአለማቀፉ የጤናው ዘርፍ 10 ዋነኛ ተግዳሮቶች መካከል ይሄው የተዛባ አመለካከት አንዱ መሆኑን በቅርቡ ይፋ ማድረጉንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 2128 times