Sunday, 16 June 2019 00:00

ከፍተኛ ገቢ ያገኙ የምንጊዜም ምርጥ ፊልሞች ዝርዝር ይፋ ተደረገ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


               “ጎን ዊዝ ዘ ዊንድ” በ1 ነጥብ 82 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ቀዳሚነቱን ይዟል

               በአለማችን የፊልም ኢንዱስትሪ ታሪክ በአገር ውስጥ ገበያ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ የምንጊዜም ምርጥ 26 ፊልሞች ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ “ጎን ዊዝ ዘ ዊንድ” የተሰኘው ተወዳጅ ፊልም እጅግ ከፍተኛውን ገቢ በማግኘት ቀዳሚነቱን መያዙ ተዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ በ1939 ለእይታ የበቃው “ጎን ዊዝ ዘ ዊንድ” በወቅቱ በአገር ውስጥ ገበያ 200.9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱንና በቦክስ ኦፊስ የምንጊዜም ባለከፍተኛ ገቢ ፊልሞች ዝርዝር ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን የዘገበው ሲኤንቢሲ ኒውስ፣ ይህ ገቢ በዛሬው የአሜሪካ የዋጋ ግሽበት ሲተመን 1.82 ቢሊዮን ዶላር ያህል እንደሚደርስ አስታውቋል::
እ.ኤ.አ በ1977 ለእይታ የበቃውና በወቅቱ 461 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ያገኘው የመጀመሪያው “ስታር ዎርስ” ፊልም በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፣ ፊልሙ ያገኘው ገቢ በአሁኑ የአሜሪካ የዋጋ ግሽበት ሲተመን 1.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስም ዘገባው አመልክቷል፡፡
“ዘ ሳውንድ ኦፍ ሚዩዚክ” የተሰኘው ሙዚቃዊ ፊልም ለእይታ በበቃበት እ.ኤ.አ በ1965 ያገኘው አጠቃላይ ገቢ 159.3 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ በወቅቱ የአሜሪካ የዋጋ ግሽበት ሲተመን 1.28 ቢሊዮን ዶላር የሚደርሰው ይህ ገቢ ፊልሙን በምንጊዜም ባለከፍተኛ ገቢ ፊልሞች ዝርዝር ውስጥ የሶስተኛነት ደረጃ ላይ እንዳስቀመጠው አመልክቷል፡፡
የሳይንሳዊ ልቦለድ ዘውግ ያለውና እ.ኤ.አ በ1982 ለእይታ የበቃው ለእይታ የበቃው “ኢ.ቲ ዘ ኤክስትራ ቴሪስቴሪያል” በወቅቱ የዋጋ ግሽበት ሲተመን 1.27 ቢሊዮን ዶላር በማስገኘት የአራተኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን፣ ዘመን አይሽሬው ታይታኒክ በበኩሉ በ1.22 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
“ዘ ቴን ኮማንድመንትስ” በ1.18 ቢሊዮን ዶላር፣ “ጃውስ” በ1.15 ቢሊዮን ዶላር፣ “ዶክተር ዚያጎ” በ1.12 ቢሊዮን ዶላር፣ “ዘ ኤክሶርዚስት” በ996.5 ሚሊዮን ዶላር፣ “ስኖው ዋይት ኤንድ ዘ ሰቭን ድዋርፍስ” በ982.1 ሚሊዮን ዶላር እንደ ቅደም ተከተላቸው ከስድስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የምንጊዜም ባለከፍተኛ ገቢ ፊልሞች መሆናቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
በአለማችን የፊልም ታሪክ ከፍተኛ ገቢ ካስገቡ የምንጊዜም ምርጥ 26 ፊልሞች ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ሌሎች ፊልሞች መካከልም “ቤንሁር”፣ “አቫታር”፣ “ዡራሲክ ፓርክ”፣ “አቬንጀርስ - ኢንድጌም”፣ “ዘ ላየን ኪንግ”፣ “ዘ ስቲንግ”፣ “ዘ ግራጁዌት”፣ “ፋንታሲያ” እና “ዘ ጋድ ፋዘር” እንደሚገኙበትም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1412 times