Sunday, 16 June 2019 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)


                “--ማወቅ በኑሮ እየተቃኘ ዓለማዊ ትርጉም ሊኖረውና የስልጣኔ ግብዓት መሆን የሚችለው ግን በሳይንስና በጥበብ እየተገለፀ፣ ሳይንስና ጥበብን መልሶ የማሳደግ ብቃት ወይም ዓቅም ሲያፈራ ነው፡፡ የነበረውን ሲያሻሽል፣ የተደበቀውን ፈልፍሎ ሲያወጣ ወይም ሲያገኝና አዲስ ነገር ሲፈጥር፡፡--”
                
           የዛሬ ሰውየአችን አርቲስት ነው፡፡ አቻ የሌለው ተዋናይ፡፡  ቅርፃ ቅርፅ መስራትና … ሌሎች ብዙ የዕውቀት ፀጋዎችንም የታደለ፡፡ … እንደ ፒተር ኡስተኖቭ፡፡ ለችሎታው ዕውቅና መስጠት የሚተናነቃቸው አንዳንድ ሰዎች “አፈንጋጭ!” ይሉታል፡፡ እሱ ‹ከፍ› ማለት ፈልጎ አይደለም:: እነሱ ወደ ታች እየወረዱ ሚዛኑን አዛቡት እንጂ:: ሰዎቹ ከእሱ ጋር በሚሆኑበት ጊዜ አእምሮው የሚያመነጨውን ‹Positive energy›  መቋቋም ስለሚያቅታቸው ነፃነት አይሰማቸውም፡፡ …
አርቲስቱ ከአንድም ሁለትና ሶስት ጊዜ፣ የአገሩ ብሔራዊ የሽልማት ድርጅት ላዘጋጀው ክብር በእጩነት ቢቀርብም፣ ከሽልማት ኮሚቴው አምስት አባላት ሶስቱ ይኸ ስም “አለርጂካችን” ነው በማለት ተከራክረው አስቀርተውታል፡፡ በዘንድሮውም ውድድር ተመሳሳይ ነገር ለመፈፀም ከወዲሁ የወሰኑ ሲሆን የምርጫው ስነ ስርዓት ሊከናወን ደግሞ የቀረው አንድ ሳምንት ያህል ነው፡፡
በተከታታይ ዓመታት የተሰነዘረበትን ጥቃት አንድ ቀን ጓደኛው ለአርቲስቱ አጫወተው፡፡ አርቲስቱ ተበሳጨ፡፡፡ “እንደውም ‹መኖር› ሰልችቶኛል፣ ለውጥ እፈልጋለሁ” በማለት በራሱ ላይ ዛተ፡፡ በዚያው ሰሞን ሶስት ቀን ሙሉ ቤቱ ከውስጥ በኩል ተቆልፎ ከረመ፡፡ ይህንን ያስተዋሉ ጎረቤቶቹ ደጋግመው ቢያንኳኩም መልስ አላገኙም፡፡ መስኮቱን ሰብረው ወደ ውስጥ ሲመለከቱ ወለሉ ላይ በግንባሩ ተደፍቷል፡፡ ወዲያው ጉዳዩን ለፖሊስ አመለከቱ:: ፖሊሶች ከቦታው እንደደረሱ ከዋናው ኮሚሽነር በተሰጣቸው ጥብቅ ትዕዛዝ መሰረት፤ ያካባቢውን ማስረጃ ከሰበሰቡ፣ ፎቶግራፍና አሻራ ካነሱ በኋላ አስክሬኑን በፍጥነት አፋፍሰው ወደ ‹ሆስፒታል› ወሰዱ፡፡
የአርቲስቱ ሞት የከተማው ወሬ ሆነ፡፡ የትዕግስቱን ልክ የሚያውቁ የቅርብ ወዳጆቹና አድናቂዎቹ፤ ሰውየው በትንሽ ነገር ተበሳጭቶ ራሱን የሚያጠፋ አይደለም ብለው ቢከራከሩም፣ ከሃሜት በስተቀር ምንም ማድረግ አልተቻለም፡፡ የከተማዋን ህዝብ ልባዊ ሃዘን የተመለከቱ የብሔራዊ ሽልማት ኮሚቴ አባላት፤ ስነ ስርዓቱ ከመካሄዱ ሁለት ቀናት ቀደም ብለው ተሰበሰቡና፣ ሃሳባቸውን ቀይረው፣ የበፊት ውሳኔያቸውን ሽረው፣ የዘንድሮው ሽልማት ለሟቹ አርቲስት እንዲሰጥ ተስማሙ፡፡ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ዕለት ደርሶ በዓሉ በድምቀት መከናወን ጀመረ፡፡ በተዋናይነት ዘርፍ የመጀመሪያው ተሸላሚ ተነግሮ ስሙ ተጠራ፡፡ ታዳሚው ከመቀመጫው ተነስቶ በማጨብጨብ፣ አክብሮቱን ማሳየት ሲጀምር፣ የመድረክ መሪው፤ አሸናፊው አርቲስት በህይወት የሌለ በመሆኑ፣ ሽልማቱን ወደፊት ለሚቀርበው ህጋዊ ተወካይ እንደሚያስረክቡ ለመግለፅ ጭብጨባውን አስቆመ፡፡ በዚያው ቅጽበት ከተመልካቹ መሃከል ኮፍያውን ዓይኑ ድረስ የደፋ አንድ ሰው ብድግ ብሎ ወደ መድረኩ አመራ:: ደረጃውን እንደወጣም ኮፍያውን ከፍ አድርጎ … “አለሁ፣ አልሞትኩም!” በማለት ድምፁን ከፍ አድርጎ ማንነቱን አሳወቀ፡፡ ሞቷል የተባለው ተዋናይ ነበር፡፡ አዳራሹ ተነቃነቀ፡፡ ታዳሚው በተፈጠረው ተዓምር ሰክሮ፤ የአርቲስቱን ስም እየተጣራ ሲጮህ፣ ባይሞት እንደማይሸለም ለሚያውቁት ሶስቱ የኮሚቴ አባላት “አለርጂኩ” የምር ሆነ፡፡ ….  ሰውየው ግን ከየት መጣ?... ዓይናችን ላይ ተደገመ’ እንዴ?
***
ወዳጄ፡- ማንኛውም ግዑዝም ሆነ ህይወት ያለው ነገር፤ “አለ” ከተባለ ወይም በተለያየ መንገድ መኖሩ ከተረጋገጠ፣ “የተፈጥሮ አካል” ሆኗል ማለት ነው፡፡ ሰው “ሰው” ከመሆኑ በፊት፣ በመጀመሪያው የፅንስ ቀናት በሳይንሳዊ ምርመራ (ለምሳሌ በላቦራቶሪ) ካልሆነ በስተቀር ምንነቱ አይታወቅም፡፡ በስሜት እንኳ ጭምር፡፡ … ልክ እንደ በሽታ፡፡ ከተወለደ በኋላ ግን በስሜት ህዋሳቶቻችን በኩል በቀላሉ እንለየዋለን:: (ከተወለደ በኋላ ስንል አንዳንዴ የተረገዘ ሁሉ ሰው ላይሆን እንደሚችል በማሰብ ነው::) በስሜት ህዋሳት በኩል ነገሮችን መገንዘብ መቻል ማለት “ማወቅ” ማለት ነው፡፡ ማወቅና መኖር ዕኩል ናቸው… አይነጣጠሉም፡፡ “እያወቁም፣ እየተሳሳቱም “መኖር” አለ፡፡ … ተቃራኒ የሌለው ነገር ባለመኖሩ:: ተቃራኒ የሌለው ነገር ቢኖር “ምንም” ነው እንዳንል እንኳ “ምንም” የሚለው ቃል ራሱ የሚኖረው “አለ” የሚባለው ቃል ሲኖር ነው፡፡… ወይም ሌላ ነገር:: ማቴሪያሊስት ሊቃውንት እንደሚሉት፤ አፒራንስ ከሌለ ኮንሴፕት፣ ኤግዚስተንስ ከሌለ ኤሰንስ አይታሰብም፡፡
ማወቅ ተፈጥሯዊ ህላዌ፣ ፀጋና ደመ ነፍስን (Basic instinct, intuition etc) ይጨምራል፡፡ ማወቅ በኑሮ እየተቃኘ ዓለማዊ ትርጉም ሊኖረውና የስልጣኔ ግብዓት መሆን የሚችለው ግን በሳይንስና በጥበብ እየተገለፀ፣ ሳይንስና ጥበብን መልሶ የማሳደግ ብቃት ወይም ዓቅም ሲያፈራ ነው፡፡ የነበረውን ሲያሻሽል፣ የተደበቀውን ፈልፍሎ ሲያወጣ ወይም ሲያገኝና አዲስ ነገር ሲፈጥር፡፡
ወዳጄ፡- የሰው ልጅ በዕውቀት እየታገዘ ለአዳዲስ ግኝትም ሆነ ፈጠራ እንዲተጋ የሆነበት ዋናው ምክንያት፤ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ … ፍላጎት ወይም ነሰሲቲ!! መኖር መፈለግ ነው፡፡ ፍላጎት ተፈጥሯዊ ነው፡፡ የማይፈልግ ሞቷል፡፡ ፍላጎት እስካለ ፈጠራ አለ፡፡ የፈጠራ እናት መፈለግ ነው፡፡
“የሁሉም ሰዎች ኑሮ የሚንቀሳቀሰው በሰዎች ፍላጎት አስገዳጅነት ነው… ፈጠራም ጭምር” በማለት የፃፈልን ሊሲፐስ (Leucipus) ሲሆን ታላቋ አያን ራንድም፤ በገፀ ባህሪዋ ኤልዝ ዎርዝ ቱሂ በኩል፤ “if one fails in everything else, he develops brain” ስትል ይህንኑ ሃቅ በወርቅ ብዕሯ አስምራበታለች:: … አንድ የድሮ “ቀልድ” ላስታውስህ፡- አንድ የውጭ አገር ዜጋ፤ የትራፊክ መብራት አስቁሞት፣ ወደ ግራ ለመታጠፍ ፍሬቻውን ብልጭ፣ ድርግም ሲያደርግ፣ የአገራችን ባላገር የጎዳና ተዳዳሪ ወደ መኪናው ተጠግቶ ቁራጭ ሲጋራውን በፍሬቻው መብራት ለመለኮስ “እፍ” እያለ ወደ ውስጥ ሲስብ የተመለከተው ቱሪስት፤ በኋላ ቀርነታችን እየተገረመ ሳቀ፡፡ መብራቱ ለቀቀውና መንገዱን ቀጠለ፡፡ ከልቡ መሳቅ የቻለው ግን ከደቂቃዎች በኋላ ነበር:: በራሱ ጅልነት፡፡ በቀኝ ጋቢናው በኩል ወንበር ላይ አስቀምጦት የነበረው ውድ ካሜራ ተሰርቋል:: የሲጋራዋና የፍሬቻዋ ነገር ለካስ ቀልብ መሳቢያ ነበረች፡፡ … እዚህ ጋ ወዳጄ፤ ችግርና ፍላጎት የፈጠራ እናት ስለመሆናቸው ትጠራጠራለህ?
በነገራችን ላይ ፈረንጁ ወደ ጣቢያ ሄዶ ጉዳዩን ካስረዳቸው በኋላ፣ ሌቦቹን ቢያመጡለት፣ ስለ ፈጠራቸው ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶ ነበር አሉ፡፡
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- ፖሊሶቹ ወደ ጣቢያ የወሰዱት ‹አስከሬን›፤ አርቲስቱ ከእንጨትና ከፕላስቲክ የሰራው የራሱ ቅርጽ ነበር፡፡ ራሱን የገደለ ለማስመሰል ልብሱን አልብሶ፤ በግንባሩ በማስተኛት፣ ደም የሚመስል ቀለም ደፍቶበት በመስኮት ወጥቶ ተሰወረ፡፡ ይህንን ድራማ የተጫወተውም “አርቲስት በህይወት እያለ ነው... ወይስ ከሞተ በኋላ ተገቢው ክብር የሚሰጠው?” ለሚለው ጥናት ግብዓት እንዲሆን ነው፡፡ ፖሊሶቹና ኮሚሽነሩም እንደ ሰውየው ገፀ ባህሪያት ነበሩ፡፡ … የሽልማት ኮሚቴው “ተሸወደ”!!
ወዳጄ፡- “The way you live determines the way you think” በማለት የፃፈልን ማን ነበር? .. ተወው --- ተወው አስታወስኩት…ብዙ ናቸው፡፡
ሠላም!!!

Read 616 times