Sunday, 16 June 2019 00:00

የጥር ቅዳሜ - (ጥበባዊ ወግ)

Written by  አሸናፊ
Rate this item
(1 Vote)


        ታክሲ ውስጥ ከተዋወቅን በኋላ በአካለ ሥጋና በመጠነ ሐሳብ ለመገናኘት ፣ዛሬ የመጀመሪያ ቀጠሯዋችን ነው…ፒያሳ Five town
ቀደም ብዬ እየጠበኩት ነው፡፡ እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ:: ሌላ…ብዙው ምክንያት ቢቀር እንኳ ከእኔ ለመገናኘት ዛሬ…የመጀመሪያው ቀጠሮዋችን ስለሆነ…ይመጣል…የተንቀዠቀዡ ዐይኖች ቢኖሩትም የኔን ውበት ለማክበር እንደማይዘገይ ተስፋ አደርጋለሁ…ስለዚህ እጠብቀዋለሁ…እዚህ ፒያሳ “Five house” (በነገራችን ላይ ይሄን ቤት በጣም እወደዋለሁ…ሌላ…ብዙ …ምርጥ…ቤቶች …ሳላይ ቀርቼ አይደለም…ያየኋቸው…ምርጥ መሸታ ቤቶች፣ ዶሮ ማነቂያ ውስጥ ስላልሆኑ ከዚህ ቤት አይልቁብኝም…) እዚያ…ነኝ…
የተለያዩ የውስኪ ዓይነቶች ለምሳሌ…white horse, Red label, Black label, Jock Daniel…የተለያዩ የቮድካ ዓይነቶች Smirnoff, stochilyta, Absolute vodka, witer palace, የወይን …የምናምን…የመጠጥ ዓይነቶች ለዐይን ማራኪ በሆነ መልኩ ከተደረደሩበት፣ ፊት ለፊት ባልኮኒው አጠገብ ተቀምጬ እየጠበኩት ነው…
በቤቱ ውስጥ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ …ጥንዶች…ነጠላዎች…ተመሳሳይ ነጠላዎች (ሴት ጓደኛማቾች…ወንድ ጓደኛማቾች)…ነጠላ ብቸኞች (ብቻውን የሚጠጣ ወንድ ብቻዋን የምትጠጣ ሴት) እንደየመልካቸው እንደየዐይነታቸው አሉ፡፡ ከዚህ ፒያሳ…በፊት - ለፊት ስትሄዱ ሽቅብ ከላይ (ከጀርባ) ከመጣችሁ ቁልቁል ያለው ቤት…እርሷም እዚህ ነበረች፡፡
“እርሱም ወደዚያው ገባ፡፡ ተደራጅቶ እየተቀመጠ በጣም አስተዋላት “ዓይኖቿ የፈገግታ የበኩር ልጆች ይመስላሉ…ቀኝ ዐይኗ ሰላም፤ ግራዋ ማስተዋል..የሚባሉ መንታዎች … ሁለመናዋ ሳቅ ነበረ (ታክሲ ውስጥ እንዳዋራት እንጂ እንዳላስተዋላት ገባው) የሚገርመኝ ነገር ብዙ ጊዜ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባላውቅም እነዚህ ዓይናቸው ወደ ጐን ረዝሞ የሚታዩ ሴቶች…ሌላ ሦስት ረዣዥም ነገሮች አላቸው፡፡ ከናፍራቸው ረዘም ብሎ ወፈር ያለ፤ የጥርሶቻቸው …ሰልፍ…ብዙ ጥርሶቼ ያላቸው ሲያስመስላቸው …ንጣቱ…የ”ታቦርን ፀዳዳ”.. ቁመታቸው  …ጉንጮቻቸው መጠጥ ያሉ ይሆኑና … ከዐይኖቻቸው ስር ያሉት አጥንቶቻቸው ጉልህ ስጋ ያልከደናቸው … ዓይነት፡፡ ብዙ ጊዜ ብዙዎቹ እንዲህ ናቸው…ከብዙዎቹ አንዷ እርሷ ነች፡፡
“እንደሱ አትመልከተኝ…” አለችው
“ለምን”
“እፈራለሁ…(ሳቅ …እያለች…ዐይኑን እየሸሸች) እፈራለሁ…ዐይን ሲበዛብኝ…እደነግጣለሁ አለ አይደል … የሆነ ምናምን ነገር…(ይሄ ምናምን ነገር የሚሉት አወራር በዚያ ጊዜ የሴቶቹ ሁሉ የወሬ አዝማች፣ የአነጋገር ስልት ምናምን ነገር ነበር)
“እንደዚህ የማይሽ…ሁሉ ነገርሽን ለማወቅ…ስለምፈልግ…ይሆናል”
“ማለት?”
የሆነ የተሰቀለ ስዕል የሚመራመር …ይመስል …ከበስተጀርባዋ በኩል ዐይኖቹን ለአትኩሮት ካዘገያቸው…በኋላ… “የሆነ …የማውቃት ልጅ …ያየሁ…መስሎኝ ነበር…(ውሸቴን ነው ምንም የማውቃት ሴት አላየሁም…ሆነ ብዬ ነው…ትንሽ ቅናትና ፉክክር ቢጤ ለመፍጠር ነው)
ኦ! ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ …ዐይኖቻችን ውስጥ ሁሉም ነገሮች አሉ … ይሄ የፊታችን አጥንት ላይ ማንነታችንና ምንነታችን በጉልህ ተጽፏል…እርሱን ማንበብ ፈልጌ ይሆናል::
የፊታችን ስሙ ፊት ነው፡፡ …ወደ ልብ መውረድ የሚቻለው በፊታችን በኩል ነው፡፡ ፊትን ማስተዋል …የማይችል ልብን አያገኝም…ፊታችን ሁሉንም ነው…ጽድቃችንንና ሐጢአታችንን…ንጽህናችንንና …ውርደታችንን…በጐነታችንና ክፋታችን…የያዘ…የፃፈ “ፊታችን”… እሱን ነው ማየው፡፡
ሲጋራዋን በረዥሙ ስባ …ቮድካዋን እየተጐነጨች “እርሱን ነገር እኔም ትንሽ…ትንሽ…አምንበታለሁ…አንዳንዴ …ዝም ብዬ የማላውቀውን ሰው ሄጄ …አዋሪው…የሚያሰኝ…መልካምነት…የሚታይበት … ጋባዥ የሆነ ፊት…አለ አንዳንዴ …ደግሞ…እንዲህ ዓይነት ፊት ያለበት …ቦታ…ልቀመጥ…አልችልም…ብዬ …ገና …ከርቀት ባየሁት ፊት የምጠላው…የምሸሸው…ሥፍራ አለ…በፊት፡፡  …ግን…አሁን…ሁሉንም…እኔ…ስለምነግርህ...
(የሆነ …የሚያምር ነገር አላት…ሲጋራዋን ወደ ከናፍሯ ስትልክ ራሱን የቻለ …ጥበብና ውበት…መልዕክት ጭምር አለው…ሌላ ዓይነት አምሮት የሚቀሰቅስ…ሁኔታ…ሲጋራዋን ከከናፍሯ…ስታላቀቅ …የሆነ…ከከናፍሯ ወደ ሲጋራው…ጫፍ የሚለቀው የሊፒስቲኳ ቅላት በራሱ አንድ ትርጉም አያጣም)
“ምናልባት አንቺ…የምትነግሪኝ …ሕይወት ውስጥ ….የተፃፈብሽን አልያም ለመኖር የፃፍሽውን የትውስታ ማንነትሽን ይሆናል…እኔ ማወቅ የምፈልገው…የማይታየውን ነው .. ብትኖሪው ደስ የሚልሽን… ያልኖርሽውን የምትመኝውን”
“ታውቃለህ ቃላቶችን ማሽኮርመም ትወዳለህ…የሆነ ስዕል ምናምን ማድረግ”
በመሃል የሆነ …ኮትና ሱሪ የለበሰ…ወይም ረዘም ያለ…የፊት ጥርሱ በትንሹ የተሸረፈ…ሰውዬ ነገር አለባበሱና ነገረ ስራው ወጣትነቱን አስጐልሞሶታል) ይቅርታ እያለ ወደ መሃላቸው ገባ…
ልጅቷን …ሲጨብጣት …አንገቱ ተበጥሶ የሚወድቅ ይመስል ነበር፡፡ “እኔ ምልሽ እንደዚህ ይጠፋል እንዴ? ኧረ…ልክ አይደለሽም ገብሬልን”…እርሷ ሳትፈልግ መዳፏን ለመሃላ አንስቶ እየመታ፡፡
“ጠፋን አይደል… ተዋወቀው ጓደኛዬ ነው” አለች…ወደኔ እየጠቆመችው…እየጨበጠኝ “እንዴት ነው ቤቱ ተመቻችሁ?” አለኝ ተፈጥሮአዊ…ባልሆነ ማን እንዳዋሰው በማላውቀው የድምጽ ልስላሴና የወገብ ስበራ (እንዲህ ዓይነት ሰው ዕጣ ክፍሌ አይደለም … እንዲህ ዓይነት ፊት ራሱ አልወድም … የራስ ያልሆነ…ማስመሰል የተላበሰ ፈገግታ ወደ ላይ ይለኛል…የዚህ ደቃቃ ሰው ዘዴ…እንኳን …ሲያደርገው ሲያስበው የሚያስታውቅ ተራ ዘዴ ነው…”እንዴት ነው …ቤቱ ተመቻችሁ?”…ይገባኛል ባለቤቱ ነኝ…እያለኝ…ነው፡፡ ከቆንጆ ሴት ጋር መሆኔን አትርሱ) ከብትነቱ ስለገባኝ ፈጠን ብዬ፤
“አሪፍ ነው በጣም ተመችቶናል” አልኩት ፊቴን ወደ ቢራዬ እያዞርኩኝ፡፡
አንዳችና ከወገቡ እየተከፈለ “ተጫወቱ” ብሎን ሲሄድ እርሷን በመቅለቅለስ እየተመለከተ ነበር፡፡
“ትንሽ ደደብ ቢጤ ይመስላል”
“ምን መምሰል ብቻ ነው’ንጂ … ከተማ በህይወቱ የሚችለው ነገር ቢኖር፣ ከአንድ እስከፈለግኸው ድረስ መቁጠር ብቻ ነው … ብርር….1,2,3,4,5,6,7 …” እየሳቀች “በፊት ከጓደኞቼ ጋር እንመጣ ነበር፡፡”
“በጣም ትውውቅ አላችሁ እንዴ?” ትንሽ የቅናት ነገር ሳይሰማኝ …አልቀረም…
“ብዙ ጊዜ እኮ ሠውን ለመረዳት በጣም ማወቅ አያስፈልግም…ማወቅን የማይጠይቁ የሚያስታውቁ ብዙ ነገሮች አሉ…ቅድም እንዳወራኸኝ የአጥንትና የፊት ዐይነት ነገር … ይልቅስ … እኔ ምልህ…” በእጁ የያዘውን ግማሽ የደረሰ…ሲጋራ እየተቀበለችው
“አንቺ የምትይኝ?”
“አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ እችላለሁ”
“የፈለግሽውን” አለ…ወደ ጆሮዋ እየተጠጋ፡፡ በቤቱ …ውስጥ…የነበረው…ሙዚቃ…በጣም ጩኸታም … ነበር፡፡ ሙዚቃው…ጩኸታም…ሙዚቀኛው…አድማጩ…ሁሉም…የተሳሳተበት ሙዚቃ፡፡
“ሆ”
“ሆ”
“ሆ” ብቻ የሚሉ…ጩኸቶች…እየዋ…የሁሉም ነገር ጩኸቶች…ሁለቱን የፍቅር መንገደኞች ስለረበሻቸው …አማራጩ ሁለቱም በየተራ ጆሮዋቸውን እየተዋዋሱ ማውራትና መስማማት ነበር…ወደ ጆሮው ተጠግታ፤
“አፍቅረህ…ታውቃለህ?” አለችው፡፡
ሊያልቅ ያለ ሲጋራዋን…እየተቀበላት  (ይህን በጆሮ ተጠግቶ ማውራት ሁለቱም የወደዱት ይመስላል…አንዳች ዓይነት ልዩ…ስሜት …የመቀስቀስ…ሃይል…አለው፡፡ የሆነ ሰውነት የሚወር ምናምን ነገር)…በግራ ጆሮዋ…በኩል…
“እውነቱን ልንርሽ?“
“እንዳትዋሸኝ”
“እሺ…አንድ ጥያቄ እኔም ልጠይቅሽ?”
“ደስ እንዳለህ”…
“አብሬያቸው…የተኛኋቸውን…ማለትሽ ነው?…ወይስ…አብረውኝ…የወደቁትን ጭምር”
ልትጠጣው ያነሳችውን…መልሳ …እያስቀመጠች…የምትጠይቀውን ሳይሆን የሚመልሰውን  ለመስማት…እየተፋጠነች “ቃላቶችህ..ተሳከሩብኝ…ግልጽ አድርጋቸው…”
“አየሽ…እኔ…ብዙ…ሴቶች አውቃለሁ … እጅግ ብዙ (ያጋነንኩት ሆን ብዬ ነው…ቅናት ለማጋባት) እና ግልጽ እንዲሆንልሽ ፈልጌ ነው…አንዳንዴ…እንዲህ በመሆኑ ራሴን የማልረባ አድርጌ እቆጥረዋለሁ…ሁሉንም…ዓይነት ሴቶች አይቻለሁ… ከሀ እስከ ፐ (አሁንም ሆነ ብዬ ነው…ምክንያቱም ይህ የዚህ ዘመን የሀበሻ …ወንዶች…የማጥመጃ …መረብ …ነው…እኔም ከነርሱ አንዱ ነኝ) ለምን …መሰላችሁ…እኔ …ብቻ…ነኝ ያላየሁት ወይም ብዙ ዓይነት…የሴት ዕድል …ስላለው … ይህ ሰው የኔ ዕጣ ፈንታ ነው ብላ እንድታስብ …ፈልጌ፡፡ ስለፈለግኋት፡፡
“ለእኔ አብሬያት የተኛኋት ሴት… እርሷ ያፈቀርኳት የወደድኳት ናት፡፡ ልቤ ላይ የተሰማኝን በዚህ መልክ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ…ሴቶች ጋር…እጅግ …መልካም ጊዜያቶች …ነበሩኝ፡፡ ሙሉ ደቂቃዎች…በተረፈ …ሌሎቹ የወደቅኩባቸው ወይም የወደቁብኝ ናቸው… ምናልባት… ለደቂቃዎች…ለሰአታት…ለወራት…ያልተሰሙኝ፡፡
ፊደል አልባ … መልካም ሰሌዳዎች … ልቤ ላይ…ያልተፃፉ ትዝታዎች “እ…ከአመታት በፊት
ይሄ …ቀን ሲያምር!...ብለሽ…ታውቂያለሽ?”
“እጅግ ብዙ ጊዜ” አለች- ፈጠን ብላ…
“እና ካቻምና የዛሬው ቀን ሲያምር ያልሽበትን ቀን ታስታውሽዋለሽ?”
“እኔ - እንጃ! አይመስለኝም”
“በቃ ለኔም …አብረውኝ የወደቁት - ሴቶች…እንደዛ …ናቸው… ደስ ሲል እንደተባለው ቀን… ከ አሪፍ ነበረች … ከቆንጆ ነበረች ከፍ የማይሉ”
“ቃላቶችን በጣም ነው የምወዳቸው … ታውቃለህ “Your saying is so poetic” (እንደ ሴትነቴ የሆነ ግራ መጋባት ዐይነት ውስጥ ነኝ፡፡ አብሬው መሆን ግን እፈልጋለሁ፡፡ ከርሱ የምልቅ የህይወት ሰው ነኝ…የዚህን ሰው ወሬውን መስማት … ዳሩን ማየት…መሃሉን ማሳየት እፈልጋለሁ፡፡ ግን እኔም ከመውደቅ ያለፈ …ታሪክ እንደሌላቸው ሴቶች መሆን ፈራሁ (እንደዚያ ብዙ ሆኛለሁ)…የሆነች ልጅ…ነበረች…ቆንጆ ነበረች…ተኝቻት…ነበር…ይህን …ማንም …ይለዋል…ከዚህ ከፍ ማለት እፈልጋለሁ…ሴትነቴን ወደ ሰው ከፍ ማድረግ…ደግሞም እኔ ቆንጆ…ሸክላ…ብቻ አይደለሁም…በውስጤ…ህይወት አለ…”ውሃ”…የዚህ ሰው ቃላቶች…በሸክላው ያለውን …ማይ…ሲንጠው ይሰማኛል … የገንቦ …ማዕበል ነገር … ቃላቶቹ!!!) እኔ እንጃ…የሆነ ደስ የሚል ነገር እየተሰማኝ ነው … ማርያምን! ደግሞም ግልጽ ነገር ነው…ክፍት … የተዘጋጉ ነገሮች የሉትም:: (ዛሬ ግን ቮድካ …ሳላበዛ… አልቀረም)… አዲስ የተቀዳውንና ዐዲስ የተከፈተውን መጠጣቸውን አጋጭተው እኩል ተጎነጩ፡፡ በቤቱ ውስጥ የነበረው የቅድሙ ጩኸት ትንሽ ጋብ ብሏል … ምናልባት ከዚያ በኋላ የነበረው የሙዚቃ መንፈስ የተረጋጋ ስለሆነ ይሆናል… አሁን ከ Seal Paul ጋር Rihana እየጮኸች ነው …
“You don’t know how I love you
Now even how to kiss me…
Um still in love with you boy…
ወደ ጆሮው ተጠግታ በተለሳለሰ ድምፅ “እኔ ምልህ?” አለች፡፡ ወሬዋን እንድትቀጥል አንገቱን ከፍ ዝቅ አደረገላት::  “በተኛሃት ሴትና በወደቀላት ሴት መሃል ልዩነቱን ትነግረኛለህ?” (በልቤ በመጠኑም ቢሆን እኔ የትኛዋን ዓይነት ሴት ነኝ የሚል ጥያቄ አለ፡፡ ግን እኔ የትኛዋ ነኝ? ብዬ ልጠይቀው አልፈልግም፡፡ ስለ ራሴ ብጠይቀው የወንዝ ርዝመት ያህል ቁመት ያላት ሞኝ የሆንኩ ይመስለኛል፡፡ ስለ እኔ ከጠየኩት ሊመልስ የሚችለው ግልፅ ነው - ምክንያቱም ቢያንስ ለዛሬ እንኳ ይፈልገኛል፡፡ ስለዚህ መጠየቅ ያለብኝ ምን ዓይነት ልዩነት አላቸው? ብዬ ነው፡፡ በልዩነቱ የራሴን ቀለም መለየት እችላለሁ … ዛሬም ባይሆን ነገ ተነገ ወዲያ)
ሊያወራት ሲጀምር የተጎነጨው ቢራ ትን አለው:: ከቢራው ጠርሙስ አፍ ደግሞ ነጭ የቢራ አረፋ ወጣ… የጠርሙስ ትንታ መስሎ … እንደ ቸኮለ ስሜት ገንፍሎ … የቢራውን አፍ እየጠረገ “በተኛኋትና በወደቅኋት ሴት መሃል ልዩነት ባይኖርማ ቃላቶቹም ባልተለያዩ ነበር፡፡ የምተኛት ሴት የማፈቅራት ናት፤ በመተኛት ዕረፍት አለ እፎይታ:: በምወድቃት ግን ፀፀት፡፡ ከምተኛት ሴት መርፌና ክር ሆኜ ነው የማነጋው፡፡ (ወድጃታለሁና) ከወደቅኋት ሴት ጋር ግን “ኤክስ” (X) እሰራለሁ፡፡ እርሷ ወደ ምዕራብ … እኔ ወደ ምስራቅ እግሮቻችንን አጣጥፈን .. የተንጋደደ መስቀል ሠርተን…
“እሺ እንዲህ ከሆነ ታዲያ ፍቅር ላንተ ምንድነው?” … እያወራች ሲጋራ ልትለኩስ ስትል የመጀመሪያው ክብሪት ብልጭ ብሎ ጠፋ፡፡ ሁለተኛው የክብሪቱ አናት ተሰብሮ ወደቀ፡፡  ሦስተኛውን ልትሞክር ስትል ክብሪቱን ተቀብሏት ሲሞክር የክብሪቱ አናት ነደደ … ሲጋራውን ለኩሶ እያቀበላት የክብሪቱን ቤት አይቶ ተመለከተው … ባዶ ነበር፡፡ ባዶ! …አገጩዋን በእጇ ይዛ ፊቷን ወደ ፊቱ እያዞረች “በላ ንገረኝ… ፍቅር ላንተ ምንድነው?”
ከአዘጋጁ፡- ከላይ የቀረበው ጽሁፍ ለትውስታ ከቀድሞ ዕትሞች ላይ ተቀንጭቦ የወጣ መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን:: (Saturday, 14 April)

Read 718 times