Sunday, 16 June 2019 00:00

ዶ/ር አረጋዊ በርሄ - በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 • እኛ ከሌለንበት ሽግግር አይሆንም ከሆነ አግባብነት የለውም
             • በትግራይ የገጠመን አፈና በቀላሉ የሚነገር አይደለም
             • በትግራይ የመብት ጥያቄ ምላሹ - ዱላና እስር ነው

             ትግራይ ቆይተው ተመለሱት የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ሊቀ መንበር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፤ የትግራይ ህዝብ የመብት ጥያቄ እያነሳ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ ጠቁመው፣ የህወኃት ምላሽ ግን ዱላና እስር ነው ይላሉ፡፡ የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ድንገተኛ የአክሱም ጉብኝት በተመለከተም ሲናገሩ፤ ተገቢ የጠ/ሚኒስትርነት ሥራቸውን ነው የሰሩት ብለዋል- ሊቀመንበሩ:: የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ከትዴት ሊቀ መንበር ጋር በአጭሩ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡


             ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ  አክሱምን መጎብኘታቸውን እንዴት አዩት?
እኔ እንደገባኝ ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ነች፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ደግሞ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ናቸው:: ስለዚህ አክሱምን መጐብኘታቸውና ያለውን ሁኔታ መከታተላቸው አዲስ ነገር መሆን የለበትም፡፡ በእርግጥ የቀድሞ ባለስልጣናት መቀሌ መሽገው ብዙ ነገር እያወሩ ነው፤ ህዝብ ለህዝብ ለማፋጀት ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ጠላት በሰሜን መጣብህ፣ በደቡብ መጣብህ እያሉ የሚነዙት ፕሮፓጋንዳ አለ፡፡ ይሄ የብዙ ሰው ጆሮ አደንቁሯል፤ብዙ ሰዎችንም ወደ ፍርሃትና ያለመተማመን ስሜት አስገብቷል፡፡ በተለይ የትግራይን ህዝብ አስጨንቀውት፣ ከጭንቀቱ የተነሳ፣ እነሱን እንዲደግፍ ወይም በእነሱ ዙሪያ እንዲሰባሰብና በእነሱ ቁጥጥር ስር እንዲውል እያደረጉት ቆይተዋል:: ይሄን አደገኛ ሴራቸውን በጣጥሰው ጠ/ሚኒስትሩ መሄዳቸው፣ ህዝቡንና ሀገሩን ለማረጋጋትና የእነሱን የውሸት ፕሮፓጋንዳና ውዥንብር ለማጥራት ጠቃሚ ነው፡፡ በዚያ ላይ የክልሉ አስተዳዳሪ ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል፤ ጠ/ሚኒስትሩን ተቀብለው አነጋግረዋል:: ከህዝቡም ጋር ተወያያተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ተገቢውን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስራ እየሰሩ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሰሞኑን ትግራይ  ነበሩ፤ በክልሉ ያለው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
ወትሮም ቢሆን፣ ህወኃትና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው የሚል ወሬ የሚያስተጋባው የህወኃት አመራር ነው፡፡ ይሄ ስልት ደግሞ በህዝብ ውስጥ ተወሽቆ ለመኖር የተነደፈ ነው፡፡ ህዝቡ ግን ህወኃቶችን የተለያቸው በ1983 ስልጣን እንደያዙ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እነሱም አዲስ አበባ ከትመው ህዝቡን ረስተውታል፡፡ ህዝቡ የት እንዳለ አያውቁም፡፡ እነሱ ሰማይ ሰማይ ነበር የሚያዩት፤ ህዝቡ ደግሞ ምድር ምድር ነበር የሚያየው፡፡ ችግሩን ሲያስታምም ነው የኖረው፡፡ ዛሬም ከችግሩ አልተላቀቀም፡፡ ስለዚህ ህወኃትና የትግራይ ህዝብ ልዩነታቸው ሰፊ ነው:: በተለይ ገጠሩ በአስከፊ ሁኔታ ላይ ነው ያለው፡፡ እርግጥ አንዳንድ ያልገባቸው ጽንፈኞች፣ ህወኃትና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው የሚለውን ፕሮፓጋንዳ ያስተጋባሉ፡፡ ህዝቡ ግን ዛሬም ድምፁን እንኳ እንዳያሰማ በመብት እጦት፣ በኢኮኖሚ  ችግር መከራውን እያየ ነው፡፡ ድርጅትህን መቃወም የለብህም እየተባለ፣ ሌት ተቀን እየተደበደበ ነው፡፡ አሁን ህወኃትንና የትግራይም ህዝብን እያገናኛቸው ያለው ዱላና እስር ነው፡፡ ምክንያቱም እኔ እንዳየሁት፣ ህዝቡ በየአካባቢው እየተቃወመ ነው፡፡ በውቅሮ፣ መቐሌ አዲግራት፣ አቢ አዲና በሌሎች አካባቢዎች የመብት ጥያቄ እያነሳ፣ ሠላማዊ ሰልፍ ያደርጋል፤ ምላሹ ግን ዱላና እስር ነው፡፡
አሁን እኛም በምናደርገው የፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ እንዳልሆነ እንዲሁም የመብትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ እያነሳ መሆኑን አጉልተን ለመታገል እቅድ ነድፈናል:: ነገር ግን ገና ከወዲሁ አባሎቻችን እንዳይንቀሳቀሱ እገዳ እየተደረገባቸው ነው፡፡ አንዳንዶቹም እየታሠሩ ነው፡፡ ከሰሞኑ ለምሣሌ አቢ አዲ ከተማ፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ተባባሪዎች ናችሁ እያሉ በርካቶችን ሲያስሩ ነው የሰነበቱት፡፡ በልዩ ሃይል ድብደባና እስራት እየተፈፀመ ነው፡፡ ይሄ ችግር ትግላችን እንዲጠነክርና ብዙ ብልሃቶች እንድንፈልግ ነው የሚያደርገን እንጂ ትግሉን አያቆመውም፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ በህወኃት አገዛዝ ተማርሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት ያለው የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ለፓርቲ ፖለቲካ ምን ያህል አመቺ ነው?
በእርግጥ ሀገሪቱ ከባድ ችግር ውስጥ ነው የነበረችው፡፡ ሲንከባለል የመጣ የህዝቡ ጥያቄ፣ ለዘመናት ሳይፈታ ነው የኖረው፡፡ ሰፊው ህዝብ ከፊውዳል ስርአቱ ጀምሮ የዲሞክራሲ፣ የእኩልነት፣ የፍትህ --- ጥያቄው እየተንከባለለ ዛሬ ድረስ መጥቷል፡፡ ኢህአዴጎች ደግሞ በማይረባና መላቅጡ በማይታወቅ፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት በሚል ሀገሪቱን በቋንቋ ክልል ከፋፍለው፣ ሀገርና ህዝብን ለያይተው፤ በችግር ላይ ችግር ነው የጨመሩለት:: የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይፈቱ ሲተላለፉ በመጡ አያሌ ችግሮችና ጥያቄዎች የተተበተበ ነው፡፡ አሁን እነዚህ ችግሮች ናቸው መፈተንሻ ቀዳዳ አግኝተው፣ በየቦታው እየተነፈሱ እየወጡ ያለው፡፡ እነዚህ ችግሮች ተንፍሰው ጋብ ሲሉ፣ አሁን እየተደረገ እንዳለው ጥረት፣ ነገሮችን አቅጣጫ ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ በኔ ግምገማ፤ ችግሮች የሚፈቱበት አቅጣጫ ሙሉ ለሙሉ መሬት እስኪቆነጥጥ ድረስ የሚፈጠሩ ችግሮች ሊደንቁን አይገባም፡፡ ትንሽ ጊዜም ይወስዳል፡፡ አሁን ደግሞ በተለይ ህዝባዊ አመለካከት ባለው ወገን፣ ዲሞክራሲያዊነትን ያነገበ ሁሉ በአቋሙ ከገፋበት እንደተጀመረው ውጤታማ ይሆናል፤ ችግሮችም በቶሎ ሊፈቱ ይችላሉ፡፡
አንዳንድ ወገኖች አሁን አገሪቱ ላለችበት ችግር መፍትሔው፡- የሽግግር ጊዜ ማወጅ፣ ህገ መንግስት ማሻሻል፣ ከዚያ በኋላ ወደ ምርጫ መግባት ነው ይላሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ  አስተያየት  ምንድነው?
አሁንም’ኮ በሽግግር ላይ ነው ያለነው፡፡ በኛ ሀገር አንዱ ችግር፣ አንዳንዱ የፖለቲካ ልሂቅ፣ እሱ ራሱ ካልተሳተፈበት ወይም መሪ ካልሆነ ወይም ፖሊሲ ቀራጭ ካልሆነ አይረካም፡፡ እንደ እኔ አመለካከት፤ በአሁኑ ወቅት አዲስ ስርአት የመመስረት ትግል እየተካሄደ ነው፡፡ የህግ ስርዓቱ በአዲስ መልክ እየተዋቀረ ነው ያለው፡፡ የምርጫ ስርአቱም እንዲሁ:: የድንበር ኮሚሽን ተቋቁሟል፡፡ በአጠቃላይ በየፈርጁ ለህዝቡ የሚጠቅሙ ስራዎች ተጀምረው፣ በመካሄድ ላይ ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ በቀድሞ ስርአት የማይታለሙ ነገሮች አሁን እየታለሙ እየተሰሩ ነው፤ ለውጥ ያለ ምንም ጥያቄ እየተካሄደ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሽግግር መንግስት የሚሉ ሰዎች ምን ለማለት እንደፈለጉ ግልጽ አልሆነልኝም፡፡ እኛ ከሌለንበት ሽግግር አይሆንም ከሆነ፣ ይሄ አግባብነት ያለው አይመስለኝም፡፡
የትግራይ ክልል ም/አስተዳዳሪ፣ በቅርቡ፣ ምርጫው በህገ መንግስቱ መሠረት ጊዜውን ጠብቆ ካልተካሄደ፣ ይህቺ ሀገር የመፈራረስ አደጋ ያጋጥማታል ብለዋል፡፡ በዚህ ላይ ምን እርስዎ ምን ይላሉ?-
ህገ መንግስቱን እኮ ሰዎች ናቸው የቀረፁት፤ ስለዚህ የቀረፁት ሰዎች እንደመሆናቸው፣ ካላመቻቸው ደግሞ እነዚያው ሰዎች የማሻሻል መብት አላቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ህገ መንግስቱን ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡ ቁምነገሩ ሃገሪቱን በጠንካራ የዲሞክራሲ አለት ላይ ማቆም ከሆነ፣ የለውጡ ግብ ህገ መንግስቱ ይሄን ይላልና በዚያች ቀን ካልተደረገ ሞቼ እገኛለሁ ማለት ትርጉም የለሽ  ነው፡፡
እርስዎ የሚመሩት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ምን አይነት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው?
እኛ ስደት ላይ ሆነን ነበር የምንታገለው፡፡ እዚህ ከመጣን በኋላ የግድ አላማችንን ለህዝቡ ማስተዋወቅ አለብን፡፡ ደጋፊዎችን መመልመል ይገባናል፡፡ ከህዝቡ ጋር መወያየትም አለብን:: ይሄን ለማድረግ ግን የገጠመን አፈና በቀላሉ የሚነገር አይደለም፡፡ የቀድሞ የኢህአዴግ ስርአት ናፋቂዎች አሁንም መቀሌ መሽገው ነው ያሉት፡፡ አዲስ አበባ የነበራቸውን ወንበር ነቅለው ወስደው ትግራይ ላይ ተቀምጠውበታል፡፡ አሁንም እንደ ድሮው እያስቸገሩን ነው፡፡ ስለዚህ  አሁንም መታገል ይኖርብናል፡፡ ትግላችን ከባድ ነው፡፡

Read 5513 times