Print this page
Sunday, 16 June 2019 00:00

ቃለ ምልልስ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ይናገራሉ---

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  የምርጫ ሥርዓት መዋቅራዊ ለውጥ፣
                   የቀጣዩ ምርጫ ጉዳይ፣ የአንድነት መንግስት?---

              የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላትን ለመምረጥ ጠ/ሚኒስትሩ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ከሰሞኑ ውይይት አድርገዋል፡፡ ውይይቱ ምን መልክ ነበረው? መድረክ ስለ ቀጣዩ ምርጫ ምን ያስባል በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በውይይቱ ላይ የተሳተፉትን የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀ መንበር እና የመድረክ ም/ሊቀ መንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ተከታዩን አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡


               በምርጫ ቦርድ አባላት ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ማድረጋችሁ ይታወቃል፡፡ ስለ ውይይቱ በዝርዝር ሊነግሩን ይችላሉ?  
የምርጫ ቦርድ ማሻሻያን በሚመለከት ለመደራደር ለረዥም ጊዜ ሙከራ ስናደርግ ነበር፡፡ አሁን ጠ/ሚኒስትሩ ለማድረግ የሞከሩት በመጠኑም ቢሆን የድርድሩን መንገድ ለመከተል ነው፡፡ መቶ በመቶ ሃሳባችን ተቀባይነት አግኝቷል ባንልም፣ ቢያንስ ለድርድር ስናቀርባቸው የነበሩ ጉዳዮችን ለመተግበር ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን ለቦርድ አባልነት በእጩነት የቀረቡትን ስምንት ግለሰቦች የመረጠው ኮሚቴ፣ አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለብቻቸው ያቋቋሙት ኮሚቴ ነው፡፡ በእርግጥ ጥቆማ አድርጉ ተብሎ በሚዲያ ተነግሯል፡፡ ለኛም በደብዳቤ ጥቆሟ አቅርቡ ተብለን ነበር፡፡ በዚህ መሰረት ነው እኛም ሌላውም ከጠቆማቸው መካከል ስምንት ሰዎች ተመርጠው የቀረቡት፡፡
የኛ ቅሬታ ያለው መልማይ ኮሚቴው ላይ ነው፡፡ የኛ ፍላጎት፣ መልማይ ኮሚቴ፣ ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲውጣጣ ነበር፡፡ አሁን ግን ራሳቸው ጠ/ሚኒስትሩ ናቸው መልማይ ኮሚቴውን የመረጡት፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ መልማይ ኮሚቴውን  መምረጣቸው ለምን ቅሬታ ፈጠረባችሁ?
መልማይ ኮሚቴ፤ ለሚመለመሉት ሰዎች ማንነት ወሳኝ መሆኑን ማንም የሚስተው ጉዳይ አይደለም:: በዚያ ላይ በዚህ መልማይ ኮሚቴ ውስጥ ኢህአዴግ … ኢህአዴግ የሚሸቱ ሰዎች ነበሩበት:: ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ኮንፈደሬሽን ፕሬዚዳንት አንዱ ናቸው፡፡ እሳቸው ደግሞ ኢህአዴግ ያደራጀው ነው ተብሎ የሚታማውን ማህበር ነው የሚመሩት:: እውነተኛ የሰራተኛ ማህበር እዚህ ሃገር የለም:: የኢህአዴግን አይን እያዩ፣ ላለማስቀየም ፈራ ተባ እያሉ የሚሄዱ ሰዎች ናቸው በአባልነት የተካተቱት:: መልማይ ኮሚቴው ላይ መቶ በመቶ እምነት ለማሳደር ያስቸግራል፡፡ በዚህ መልማይ ኮሚቴ የቀረቡ ስምንት ሰዎች ላይ አስተያየት ካላችሁ ብለውን ነው፣ ጠ/ሚኒስትሩ በፅ/ቤታቸው ጠርተው ያወያዩን፡፡ በውይይታችን ወቅትም ይሄን ቅሬታችንን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀንላቸዋል፡፡
በተመረጡት ስምንት ሰዎች ላይ አልተስማማችሁም?
ያለመስማማት ጉዳይ ሳይሆን ለምሳሌ እኔ የማውቀው አንድ ሰው ብቻ ነው፡፡ በእኛ ፓርቲ በኩል የጠቆምናቸው ሰውም በዝርዝሩ ውስጥ የሉም፡፡ ትኩረታቸውን ያደረጉት፤ የፖለቲካ ሳይንስና የህግ ባለሙያ በሚለው መስፈርት ላይ ነው፡፡ አጥበው ነው የመለመሉ:: የተመለመሉትን ሰዎች ደግሞ አብዛኞቻችን አናውቃቸውም ነበር:: ለዚህ ጊዜ ተሰጥቶን ሰዎቹን እናጥና ብለን ነበር:: ነገር ግን  አስቸኳይ ስለሆነ አይቻልም ነው የተባልነው:: ይሄ አንዱ ትንሽ ቅሬታ ያሳደረብን ነገር ነው፡፡ ሌላው  አብዛኞቹ በግል የተለያዩ የአማካሪነት ስራ ላይ የተሰማሩ ናቸው ተብለናል፡፡
በምርጫ ቦርድ ተሿሚዎች ጉዳይ ጠ/ሚኒስትሩ ከእናንተ ጋር መወያየታቸው ለቦርዱ ተአማኒነት ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል?
የተአማኒነቱ ጉዳይ መቼም ቢሆን ፍፁም ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ነገር ግን በዚህ ደረጃ ግልጽ ሆኖ፣ ሰዎቹ እነማን ናቸው ብለን ተወያይተንበት መሾማቸው ጥሩ ነው፡፡ እኔ ሰዎቹን ስለማላውቃቸው ሙሉ መተማመን ባይኖረኝም፣ ቦርዱ ተአማኒ ይሆናል አይሆንም የሚለው በተግባሩ የሚታወቅ ነው የሚሆነው፡፡ ብዙ ቅሬታዎች ቢኖሩንም እንግዲህ ዜጎችን በተወሰነ ደረጃ ማመን የግድ ይሆናል፡፡ አሁን ያለውን የህዝቡን ፍላጎትና መንፈስ ስለሚያውቁትም፣ ገለልተኛ ሆነው ይሰራሉ ብዬ ነው የምገምተው፡፡
በአጠቃላይ በምርጫ ቦርድ ውስጥ በሚካሄደው መዋቅራዊ ለውጥ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
የቦርድ ሊቀ መንበርና ቦርዱን ከመሾም ባሻገር፣ ታች የደረሰ የመዋቅር ለውጥ እስካሁን የለም:: የመዋቅር ለውጥ በዋናነት መደረግ  ያለበት፣ ቀጥተኛ አስፈፃሚ በሆነው የታችኛው መዋቅር ላይ ነው:: አሁንም በታችኛው መዋቅር ያሉት የኢህአዴግ ተሿሚዎች  ናቸው፡፡ ይሄን ወደ ማጥራት ገና አልተገባም፡፡ ይሄ ለምን አልጠራም ብለን ስንጠይቅ፣ ቦርዱ ስላልተሟላ ነው ይባላል፡፡ አሁን እንግዲህ ቦርዱ ተሟልቷል:: እንዴት ይጠራል የሚለውን በቀጣይ የምናየው ይሆናል፡፡ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አስፈፃሚዎች ናቸው በታችኛው መዋቅር ያሉት፡፡ እነዚህ እንዴት ይዋቀራሉ የሚለውን እኛም በጥንቃቄ የምንከታተለው ነው፡፡  ያልተነካው ትልቁ ጉዳይ የታችኛው መዋቅር ነው፡፡  
አሁን ወደ ምርጫ ሂደት እየገባችሁ ያላችሁ ይመስላል፡፡ ቀደም ሲል እናንተ የብሔራዊ አንድነት መንግስት መቋቋም አለበት የሚል አቋም ይዛችሁ ነበር ----  
እኛ የብሔራዊ አንድነት መንግስት ይቋቋም የሚል ጥያቄ ስናነሳ የነበረው ከአቶ ኃይለማርያም ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ነው ጥያቄውን ስናቀርብ የነበረው፡፡ አቋማችንን አሁንም አልቀየርንም:: ነገር ግን አሁን የዚህ ዓይነት ነገር እንሞክር ቢባል ሁኔታው አመቺ አይደለም፡፡ ዝም ብላችሁ እኛ የምናደርገውን ጥረት ደግፉ ነው የተባልነው:: ስለዚህ አሁን እኛ እያደረግን ያለነው መልካም መልካሙን እየደገፍን፣ የሚተች ሲገጥመን መተቸት ነው፡፡ የብሔራዊ አንድነት መንግስት የሚለውን አቋም ይዘን ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር አቅሙ አንሶናል፡፡ ህዝቡም ጠ/ሚኒስትሩ ህዝባዊ ቋንቋ መናገር ሲጀምሩ ግማሹ እንደ ነብይ፣ ግማሹ እንደ አሻጋሪ አድርጎ ተቀበላቸው፡፡ ታዲያ ከዚህ ጋር የብሔራዊ አንድነት መንግስት ሃሳብን ይዞ እንዴት መጋፋት ይቻላል? መርሁን ትተን ሳይሆን የህዝብ ድጋፍ ማግኘቱ አስቸጋሪ ስለሆነብን ነው ወደፊት መግፋት ያልቻልነው:: የሃገሪቱን ፖለቲካ ያውቃሉ፣ ይተነትናሉ የሚባሉ ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮች ሁሉ ይሄን ሃሳብ አልወደዱትም:: ዳያስፖራውም ጨርሶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሉትን ብቻ የሚከተል ሆነ:: ይሄ አቅም አሳጣን፡፡ ፖለቲካ ደግሞ ህዝባዊ ነው መሆን ያለበት፡፡ ህዝቡ ከተከተለህ ነው በሃሳብህ የምትገፋው፡፡  ስለዚህ ዶ/ር ዐቢይ ያሸጋግሩናል በሚል ተስፋ ውስጥ የተቀመጠውን ህዝብ፤ምን ብለን ነው ተነስ ብሄራዊ የአንድነት መንግስት አቋቁም የምንለው? የህዝብ ድጋፍ ሳይኖር፣ ዝም ብሎ  መጋፋት ጠቃሚ አይሆንም፡፡
ስለ ቀጣዩ ምርጫ ምን ታስባላችሁ ?
እኛ አሁንም ምህዳሩ ይስተካከል ነው የምንለው፡፡ የምርጫ አስተዳደር መዋቅሩ፣ ታች የህዝብ ድምፅ መስጫ ድረስ ጠርቶ ማየት እንፈልጋለን፡፡ የፍትህ ድጋፍ የሚሰጠውም አካል ጠርቶ ለዚሁ ለምርጫ ጉዳይ ተቋቁሞ ማየት እንሻለን፡፡ ይሄን መደላደል እስከ ምርጫው ባለው ጊዜ ውስጥ መፈጠር ከተቻለ፤ እሰየው! በምርጫው ለመሳተፍ ምንም የሚያስፈራ ነገር የለም፡፡ ህዝቡ በሚገባ ያውቀናል፤ እንደ አዲስ ራሳችንን ማስተዋወቅ ብዙም አያስፈልገንም፡፡ መራጩ ልብ ውስጥ ለመግባት ሰፊ ጊዜ ያስፈልገናል  አንልም:: መንግስት ሰላምና መረጋጋት ፈጥሮ፣ የምርጫ አስተዳደሩን ተአማኒ አድርጎ ማሳየት ከቻለ ወደ ምርጫው መግባት አያስቸግረንም፡፡ ነገር ግን ይሄ ሳይሆን ወደ ምርጫ ለመግባት አንሞክርም፡፡
መድረክ በሂደት አንድ ውህድ ፓርቲ ይሆናል የሚል እቅድ ነበራችሁ፡፡ ይህ እቅዳችሁ ምን ላይ ደረሰ?
የውህደት ነገር አልተሳካልንም፡፡ ሁሉም አባል ድርጅቶች ለውህደቱ በእኩል ደረጃ ዝግጁ መሆን አልቻሉም፡፡ ነገር ግን ግንባር ሆኖም ተወዳድሮ ስልጣን መያዝ ይቻላል፡፡ ለዚህ ኢህአዴግ ምሳሌ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ አሁንም ጥረት እያደረግን ያለነው ግንባሩን በማጠናከር ላይ ነው፡፡ አባል መሆን ለሚሹ ድርጅቶች ጥሪ እያቀረብን ነው፡፡ ያመለከቱም አሉ፡፡ ጉዳያቸው በመታየት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በውህደት ጉዳይ ግን እኩል እየተጓዝን አይደለም፡፡ እኔ የምመራው ኢሶዴፓ፣ ውህደት ይደረግ ነው የሚለው፤ ሌሎቹ ደግሞ ለዚህ አልተዘጋጁም፡፡ ስለዚህ በግንባር ለመንቀሳቀስ ነው የወሰነው፡፡ ከመድረክ ለመውጣት መሞከር መድረክን ማፍረስ ሊሆን ስለሚችል መቆየቱን መርጠናል፡፡

Read 1777 times