Print this page
Sunday, 16 June 2019 00:00

የተስፋ ጭላንጭል ለችግሮች ክምር

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

    ጊዜ ከማይሰጡ አጣዳፊ ችግሮች … ከስንዴና ከዳቦ እጥረት ጀምሮ፣ … በተዳከመ ኢኮኖሚ ላይ ኤሌክትሪክ እየጠፋ ስራ መፍታትና የፋብሪካ ኪሳራ፤ … የተጎሳቆለውን ኑሮ የሚያናጋ የዋጋ ንረት፣ … ባለፉት አስር ዓመት እየተቆለለ የመጣው የውጭ እዳ አላንስ ብሎ፣ ኤክስፖርት እያሽቆለቆለ፣ አንድ ዶላር በመንግስት ተመን 30 ብር በጥቁር ገበያ 40 ብር የሚመነዘርበት ምስቅልቅል … ኢትዮጵያ ላይ ተደራረቡት ችግሮችና ፈተናዎች ተዘርዝረው አያልቁም፡፡
የአዲስ አበባ ባቡር የእለት ተእለት ወጪዎቹን እንኳ መሸፈን አቅቶት፣ የ400 ሚሊዮን ዶላር ባለዕዳ ሆኖ መቅረቱ፣ በቀላሉና በአጭር ጊዜ የማንገላገለው መከራ ነው፡፡ ግን የባሰ አለ፡፡ 6 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጁት የጅቡቲ መስመር የባቡር ፕሮጀክቶች መሰናክል፣ በአገራችን ላይ የሚያስከትሉት ኪሳራ ምንኛ ከባድ እንደሆነ አስቡት፡፡ ስንዴ ለእለት ዳቦ፣ እና ማዳበሪያ ለክረምቱ እርሻ፣ ማጓጓዝና ማድረስ ለአገሪቱ ፈተና ሆኗል፡፡
ከጅቡቲ ወደ አገር ለማስገባትና ወደየአካባቢው ለማድረስ፣ ማጓጓዣ ጠፍቶ፣ … በሌሎች ጭነቶች ላይ ገደብ እስከመጣል ተደርሷል፡፡ መኪኖች ስንዴና ማዳበሪያ ብቻ ነው መጫን የሚችሉት:: ይሄም አልተሳካም:: “ቅድሚያ ለማዳበሪያ ብቻ” በሚል ትዕዛዝ፣ ሌላ ነገር መጫን አይቻልም የሚል ክልከላ ማወጅ የግድ ሆኗል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ አገር ውስጥ የሚሰሩ ሌሎች የጭነት መኪኖች፣ ወደ ጅቡቲ መስመር እንዲሰማሩ ታዘዋል:: ለዚያውም መንግስት በተመነው ዋጋ ነው ማዳበሪያ እንዲያጓጉዙ የተደረጉት፡፡
ቢሊዮን ዶላሮች የፈሰሰባቸው የባቡር ፕሮጀክቶች፣ ለዚህ ለዚህ መጥቀም ነበረባቸው:: በአነስተኛ ወጪ በነዳጅ የሚሰራ አስተማማኝ፣ መደበኛና ዘመናዊ የባቡር አገልግሎት ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ “በኤሌክትሪክ የሚሰራ የባቡር ፕሮጀክት” ተብሎ፣ አገሪቱ ተጨማሪ ወጪና እዳ አተረፈች፡፡ እንዲያም ሆኖ በወጉ መስራት ቢችልኮ አንድ ቁም ነገር ይሆን ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ድርብ ኪሳራ ነው፡፡
“የኤሌክትሪክ ባቡር” እያሉ መቀናጣት፤… የድሃ አገርን ሃብት ማባከንና እዳ ውስጥ መግባት፣ … ከዚያም የስንዴና የማዳበሪያ ማጓጓዣ እስከማጣት አደረሰን፡፡ ይህም ብቻ አይደለም:: በድንገት ሳይታሰብ ያጋጠመ ሳይሆን፣ ይሁነኝ ተብሎ የተፈፀመ ጥፋት ነው፡፡ የሰሜን ዋልታ በረዶ እንዳይቀልጥ፣ ከመቶ አመት በኋላ የዓለም የሙቀት መጠን በ2 ሴንቲግሬድ እንዳይጨምር ታስቦና ታቅዶበት የተከፈለ ከንቱ መስዋዕትነት፣ አገርን የሚጎዳ አሳፋሪ ጥፋት ነው - አረንጓዴ ልማት ተብሎ እየተዘመረለት፡፡
በመላ ኢትዮጵያ፣ በእያንዳንዱ ከተማም፣ “የካርቦን ልቅት” ቅንጣት እንዳይጨምር ይደረጋል የሚል የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ታውጆለታልም እንጂ፡፡ (የዓለም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ተብሎ!)፡፡ ኢትዮጵያውያን፣ ከፋብሪካ፣ ከመኪና፣ ከኤሌክትሪክ … ከሁሉም ነገር፣ አየር ከመተንፈስም ጭምር ለ500 ዓመታት ቢቆጠቡ፤ የቻይና የአንድ ዓመት የካርቦን ልቀትን ማካካስ አይችሉም:: የሚያመጡት ቅንጣት ለውጥ የለም፡፡ የቻይና ኢኮኖሚ የማደጉና የቻይናዊያን ኑሮ የመበልፀጉ ያህል፣ ኢትዮጵያውያን “አረንጓዴ ልማት” በሚለው የዩኤን መዝሙር ከተመሩ፣ ከስራ አጥነትና ከድህነት በታች ተርበውና ተሰቃይተው፣ በፍጥነት ለመጥፋት ካልመረጡ በቀር! ይሄ ደግሞ አስፀያፊና ዘግናኝ ለውጥ ነው::
የኑሮ ዋስትና የሆኑ ነገሮችን በሙሉ፣ ከትልቅ እስከ ትንሽ ሁሉንም የሚሸረሽር ፈሊጥ፣ በየመስኩ በቢሊዮን ዶላሮች ኪሳራ አገርን ሲያብረከረክ፤ ወይም “ሚኒባስ ታክሲዎችን በአውቶብስ መተካት” የሚል የአዲስ አበባ አስተዳደር ዘመቻም የከተማዋን ትራንስፖርት ሲያናጋ እያየን ነው፡፡
“የኤሌክትሪክ ባቡር” ብሎ የባቡር ትራንስፖርትን የሚያደናቅፍ ብቻ ሳይሆን፤ ለፋይዳ ቢስ “የነፋስ ተርባይን”፤ እንዲሁም ኪራሳ እንጂ ትርፍ እንደማይገኝበት በግልጽ እየታወቀ “የእንፋሎት ኃይል” ፕሮጀክት እያሉ ብዙ ቢሊዮን ብር ሃብት በከንቱ ማባከንና በኤሌክትሪክ ላይ መቀለድ … የኢኮኖሚ ዋነኛ ቁልፍ በሆነው የኤሌክትሪክ ጉዳይ ላይ ማላገጥ የበረከተውም፤ በሌላ ምክንያት ሳይሆን “አረንጓዴ ኢኮኖሚ” በሚለው የነዩኤን ፈሊጥ ነው (የአውሮፓ ህብረት አዳማቂነት፣ በዚያ ላይ የዓለም ባንክ ብድርና ምክር ተጨምሮበት):: የከተሞች ዋና አላማ፣ በግል ኢንቨስትመንት የስራ እድል እንዲበራከት፣ ለኢንዱስትሪ እድገት፣ ለፋብሪካዎች ስኬት፣ ለአስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የሚመች ሳይሆን እዚህን በሙሉ የሚያሰናክል መሆን ነበረበት? “የካርቦን ልቀት ቅንጣት እንዳይጨምር ወስነናል”! ብለው ሲናገሩ፣ አንዳች ቅዱስ ነገር የተናገሩ ይመስላቸዋል፡፡
የዓለም ባንክ ይሁንታ፣ የአውሮፓ እርዳታ፣ የዩኤን ሽልማት ወይም ምክር እንዳገኙ በመግለፅም ይኩራራሉ፡፡ እስቲ የነ ዩኤን ምክር ለአፍታ ይብቃና ሌሎች አዋቂዎችንና ተመራማሪዎችንም እንስማ፡፡ የጆሴፍ ስቲግሊትዝ እና የጀፍሪ ሳችስ ምክሮችን ለበርካታ አመታት ተግተናል፡፡
ሰሞኑን ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ እንዳደረጉት፤ እስቲ ደግሞ እነ ፉክያማ የሚናገሩትን ሰምተን ለመዳኘት እንፍቀድ፡፡ “አገርና መንግስት፣ ህግና ስርዓት” ከሌለ፤ የሚሻሻል አገርና ህግ፣ የሚመረጥ ፓርቲና የሚመርጥ ዜጋ እንደማይኖር ነው ፉክያማ በመፅሃፋቸው የሚያስረዱት (ስህተትን ባረሙበት መጽሐፋቸው)፡፡
በህግ የበላይነት ስር,፣ በህግ የበላይነት አማካኝነት ስርዓት ካልተበጀለት በስተቀር፤ “ዲሞክራሲ” በሌጣው ከቀውስና ከትርምስ የተለየ ትርጉምና ውጤት እንደሌለውም ይገልፃሉ፡፡
አገር ያለ ኢንዱስትሪ፣ ከተሞች ያለ ፋብሪካ በአንዳች መንገድ የማደግ እድል ቢያገኙ እንኳ፣ ውለው አድረው ከቀውስና ከድቀት እንደማያመልጡም፣ ምሁሩ ታሪክን በማጣቀስ ይተነትናሉ፡፡
እንዲህ አይነት ሃሳቦችንም ሰምቶ፣ አገናዝቦና አመዛዝኖ ለመዳኘት መጣር፣ ችግሮችን ለመፍታትና ለመቀነስ፣ ተስፋዎችን ለማጉላትና ስኬትን ለመቃመስ አስፈላጊ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፈተናዎች፣ … የኢኮኖሚው ችግሮችን ብቻ እንኳ ስናይ በክብደታቸውና በብዛታቸው አስፈሪ ቢሆኑም፤ የተስፋ ጭላንጭሎች የሉም ማለት አይደለም፡፡
ቢያንስ ቢያንስ፣ “አገር፣ መንግስት፣ ህግና ስርዓት” የሚባሉ ነገሮች አሁንም አሉ፡፡ እነዚህን ሳናናንቅና የማፍረስ እሽቅድድምን ትተን፣ ለማሻሻልና ለመሻሻል መጣር እንችላለን፡፡
በኢኮኖሚም፣ የማሰናከል ዘመቻዎችን ትተን፣ … ኑሮን ለማሻሻልና ኢኮኖሚን ለማሳደግ የሚበጁ መንገዶችን መከተል እንችላለን፡፡
አዎ፣ የተስፋ ጭላንጭሎች ጥቂት፣ የችግሮች ቁጥርና የፈተና አይነቶች ደግሞ ብዙ ናቸው - ተዘርዝረው አያልቁም፡፡ ግን ደግሞ፣ “የባሰም እንዳለ” መዘንጋት አይገባም፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሻሻል፣ የሚረጋጋ፣ የሚያንሰራራ አገር፣ … ዛሬ ዛሬ ጥቂት ነው፡፡ በተቃራኒው እየተበላሸና፣ እየተቃወሰ፣ እየተተራመሰ ወይም እየተፍረከረከ ቁልቁል የሚወርድ አገር በዝቷል፡፡ እናም፣ የአገራችን ችግሮች ቢበዙም ቢከብዱም፣ “የባሰም አለ” ቢባል እውነት አለው፡፡ የአቅመቢስነት ከንቱ የማፅናኛ አባባል ይመስላል፡፡ ግን ከምር ትንሽ ትንሽ ያፅናናል፡፡ የማስጠንቀቂያ አባባልም እንደሆነ ካልተረዳን ነው ከንቱ ማፅናኛ የሚሆነው፡፡ ለመፅናናት ብቻ ሳይሆን፣ ለመፅናት፣ ለመጠንቀቅና መንገዳችንንም ለማስተካከል ካልተጠቀምንበት ነው፣ ከንቱ አቅመቢስነት የሚሆነው፡፡  

Read 567 times