Sunday, 16 June 2019 00:00

ቃለ ምልልስ ለሰላም ዘብ የቆሙ ወጣቶች!

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 • ሁሉም በየአካባቢው ለሰላም ዘብ ቢቆም፣ ሙሉ ኢትዮጵያ ሰላም ትሆናለች
      • በከተማው ላይ በአመራሮችም ጭምር ትልቅ ተቀባይነት አግኝተናል
      • የኢትዮጵያ ወጣት፤ ስራ መስራትና ስራን ባህል ማድረግ አለበት

          አራተኛው የደቡብ የባህል ፌስቲቫል ላይ ለመታደም ወላይታ ሶዶ በተገኘንበት ወቅት በእጅጉ ካስደመሙን ጉዳዮች አንዱ የወላይታ ወጣቶች፣ ሰላምን ለማስከበር ያላቸው ጽናትና ቁርጠኝነት ነው፡፡ ወጣቶቹ ሰላማዊ ሰልፍ ሲደረግ፣ ፌስቲቫሎች ሲካሄዱ -- የማስተባበሩንና ሰላም የማስከበሩን ሃላፊነት በብቃት ይወጣሉ፡፡
በዚህም ሥራቸው ከሚኒስትሮችና ከወረዳ አመራሮች ምስጋናና አድናቆት አግኝተዋል፡፡ እነዚህ ወጣቶች ሰውነታቸው የፈረጠመ ቢሆንም፣ በጣም የተረጋጉና ትሁት ናቸው፡፡ ህብረታቸውና እርስ በርስ መናበባቸው ያስደምማል፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ወጣቶች እንዴት ተሰባሰቡ? ከዚህ ቀደም ምን ይሰሩ ነበር? የወደፊት ዓላማቸው ምንድን ነው? ለአገልግሎታቸው ክፍያ ይጠይቃሉ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከወጣቶቹ ተወካይ  ወጣት ቴዎድሮስ ወልዱ ጋር አውግታለች፡፡  

         እስኪ በጥቂቱ ስለ ራስህ ንገረኝ---
ተወልጄ ያደግሁት ሻሸመኔ ከተማ ነው፡፡ እዚህ ወላይታ የመጣሁት  በጊዜው ፖለቲካ በተፈጠረ የዘረኝነት ችግር የተነሳ ነው፡፡ እትብቴ የተቀበረው ግን በሻሸመኔ ነው፡፡ በዚህ በወቅቱ ውዥንብር ነው ወደዚህ የተሰደድኩት፡፡ ወላጆቼ የወላይታ ሰዎች ናቸው፤ አሁንም የሚኖሩት እዚያው  ሻሸመኔ ውስጥ ነው፡፡ እኔ ግን ብዙ ነገር ደርሶብኝ፣ ወደ ወላይታ ከመጣሁ አንድ ዓመት ሆኖኛል፡፡
በሻሸመኔ ምን ትሰራ ነበር?
በሻሸመኔ “ክለብ ዳይመንድ” የተባለ የምሽት መዝናኛ ቤት ነበረኝ፡፡ አቦስቶ አካባቢ ነው የሚገኘው፡፡ ከዚያ በፊት ለ15 ዓመታት ያህል ቦክሰኛ ነበርኩ፤ ብዙ ሰው የሚያውቀኝ በቦክሰኛነቴ ነው:: የምታወቀው በቦክስ ቢሆንም በመዝናኛው ኢንዱስትሪ ተሰማርቼ፣ ክለብ ከፍቼ፣ በዚያ ገቢ ነበር የምተዳደረው፡፡ እዚያው ሻሸመኔ ውስጥ “ደሴ ባላገሩ” የሚባል የባህል ምሽትም ነበረኝ፡፡ እዚያ በጣም እሰራ ነበር፡፡ ስሰራና ስለወጥ ያዩ ግለሰቦች ናቸው፣ “እኛ እያለን አገራችን ላይ መጥቶ ከበረ” በማለት ብዙ ነገር ደርሶብኝ፣ ተወልጄ ባደግኩበት አገር ተገፍቼ፣ እዚህ ወላይታ የመጣሁት፡፡ ይህን ሁሉ የፈፀሙብኝ በሥልጣን ላይ ያሉ ቢሆኑም እነዚህ የሻሸመኔን ህዝብና ባህል ስለማይወክሉና ስለማይመጥኑ ትቼዋለሁ፡፡ አካባቢውን ህዝቡንና ጓደኞቼን አሁንም እወዳቸዋለሁ፤ እናፍቃቸዋለሁ:: ጥቂት ዘረኞችንና ፅንፈኞችን ግን እፀየፋቸዋለሁ፡፡  
እዚህ  ወላይታ  ምን እየሰራህ ነው የምትኖረው?
ክለብ ከፍቻለሁ፡፡ “ክለብ ፊፍቲ” ይባላል፡፡ ያው የኖርኩበት ስራ ስለሆነ በዚሁ ነው የቀጠልኩት:: የሚገርምሽ ጓደኛዬ ከፍቶኝ ተገፍቼ ከሻሸመኔ ስመጣ ሲያይ፣ የራሱን ክለብ ለቅቆልኝ፣ ስራበት ብሎ ሰጠኝ:: አሁን ክለቡ በጥሩ ሁኔታ እየሰራ ነው ያለው፡፡ ክለቡ የሚገኝበት ህንፃም የራሱ ነው፡፡ አምሳሉ ይባላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ላመሰግነው እወዳለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ሻሸመኔ የነበሩትን ሁለቱን፣ ሃዋሳ የነበረኝንም “ተረት የባህል ምሽት ቤት” አንድ ላይ ዘግቼ፣ ከፍቶኝ ነበር የመጣሁት፡፡ አሁን ፈጣሪ ይመስገን ደስተኛ ነኝ፡፡ የሻሸመኔውን ዘጋሁት ከማለት ተዘርፎ፣ ግማሹ ተቃጥሎ ነው የወጣሁት፡፡ ባለቤቴንና ልጆቼን ብቻ ነው ይዤ የመጣሁት፡፡
የወላይታ ወጣት የሰላም አምባሳደሮች ማህበር  አመሰራረትን ንገረኝ?
የማህበሩ አመሰራረት እንግዲህ እዚህ ከተማ ውስጥ አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን ስንመለከት፣ ሰብሰብ አልንና ይህን ችግር ለምን አናጠፋም፣ በአንዳንድ ህገ ወጦች የሚፈፀሙ ችግሮች ለከተማዋና ለአካባቢው ገፅታ ጥሩ አይደለም፣ ይህን ነገር ካሰብንበት መቆጣጠር እንችላለን በሚል ሃሳብ ነው፡፡ ከዚያም የከተማዋ አመራሮች ጠሩንና ተወያየን፡፡ ግንቦት መጀመሪያ አካባቢ ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡ የክልል እንሁን ጥያቄ ሰልፍ ነበር:: አንዳንድ ሌላ አጀንዳ የያዙ ግለሰቦች ሰልፉን ምክንያት በማድረግ ችግር እንዳይፈጥሩና አላማውን እንዳያበላሹ፣ የዚህን ሰላማዊ ሰልፍ ፀጥታ አስከብሩ ተባልንና፣ ቲ-ሸርት ተሰጠን፤ ሰልፉ ያለ አንዳች ኮሽታ ተጠናቀቀ፡፡ ከዚያ በኋላ በደንብ ተጠናከርን፡፡ የወላይታ ወጣት የሰላም አምባሳደሮች የሚል ስያሜ ነው ማህበራችን ያለው፡፡
ምን ያህል ናችሁ?
መጀመሪያ 60 ነበርን፤ አሁን እየተጣራ እየተጣራ ሲሄድ 50 ደርሰናል፡፡
በጣም ግዙፍ የሰውነት አቋም ነው ያላችሁ፤ ከተለያየ ቦታ እንደተሰባሰባችሁም ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ ስለ ስብስባችሁ  አጫውተኝ?
እንደነገርኩሽ እኔ ቦክሰኛ ነበርኩኝ፡፡ አጋዕዚ ወታደሮች የነበሩም አሉ፣ ቴኳንዶ አሰልጣኞች የሆኑ አሉ፡፡ ብቻ ሁሉም በየዘርፋቸው የበቁና የነቁ ናቸው፡፡ ከአካላዊ ብቃት በተጨማሪ ማለቴ ነው፡፡ እናም የአካባቢያችንን ፀጥታ በማስከበር የአካባቢው ነዋሪ ሆነ ሌሎች ለስራ የሚመጡ ኢንቨስተሮችና ጎብኚዎች፣ ከስጋት ተላቅቀው፣ ልማት ለምን አይፋጠንም የሚል ነው፤ ዋናው አላማ፡፡ ከዚያ ባለፈ እኛ ወጣቶች እጅ ለእጅ ተያይዘን ሰላም ስናስከብርና ፅናት ስናሳይ፣ አንድም የአካባቢው ሰው እርስ በእርሱ ተያይዞ ሰላሙን ያጠናክራል፤ ቀልቡን ሰብስቦ በመስራት ምርታማ ይሆናል፡፡ እኛ ይሄ ጉዳይ ከጅምሩ ተሳክቶልናል፤ ህዝቡም ተቀብሎናል:: ሁላችንም የተለያየ ህይወትና ልምድን ስላሳለፍን፣ የዓይን ብሌን በማየት ወንጀለኛን እንለያለን፡፡
አባባሉ ትንሽ አልተጋነነም?
የምሬን ነው የምልሽ፡፡ አንድ ሊዘርፍ ወይም ወንጀል ሊሰራ ያሰበን ሰው፤ እንዲህ ፊት ለፊት አይተን እንለያለን፡፡ እንዳልኩሽ በውትድርናውም፣ በቦክሱም፣ በቴኳንዶውም ውስጥ ስትኖሪ የየራሳቸው ሳይንስና ጥበብ አላቸው፡፡ የምትማሪውና ብዙ ከመስራት የምታዳብሪው  ልምድ አለ፡፡ እኛም በዚህ መልኩ እየሰራን ነው፡፡ እኛ እያለን ስልክም አይሰረቅ፤ ሌላም ንብረት አይዘረፍም፡፡ ምንም ኮሽ የሚል ነገር አይኖርም፡፡ ይሄ ጉራም አይደለም፤ የተጋነነም አይደለም፤ በተግባር የምናሳየው ነው፡፡
ከሆነ አካባቢ የመኪና ስፖኪዮን ጨምሮ ማንኛውም እቃ ቢሰረቅ፣ ሌባውን የገባበት ገብታችሁ በመያዝ  እቃውን ተረክባችሁ፣ ለተሰረቀበት ሰው እንደምታስረክቡ ሰምቻለሁ፡፡  እውነት ነው?…
በየአካባቢው ያለውን ሁኔታ፣ በየቀበሌው ያለው ወጣት ምን እንደሚሰራ፣ እንቅስቃሴው እንዴት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ እቃ ሲሰረቅ ያዩ ጥቆማ እንዲሰጡን፣ በየአካባቢው የምንቀርባቸው ልጆች አሉን፡፡ በዛ መሰረት ሌባው ሰርቆ የትም አይገባም:: የሰረቀበትም አካባቢ ሆነ ሰርቆ የሚያስረክብበት ለኛ አይሰወርም፡፡ አሁን እየፈሩ ነው ሌቦቹ፡፡ ፖሊስ ያስረናል እንጂ ምንም አያመጣም፤ እነሱ ከሆኑ ግን ይጣሉናል ወደ ማለት አስተሳሰብ እየመጡ ነው፡፡ አንጎዳለን ይላሉ፡፡ አሁን ላይ ፖሊስን እየፈሩ አይደለም፡፡ በተለይ የእኛ ዋናው አላማ፤ ብሔርተኞችና ፅንፈኞች፣ ምንም የማያውቁ ሰዎችን መሳሪያ አድርገው እንዳይጠቀሙባቸው፣ ችግር እንዳይፈጠር፣ ወላይታ ሶዶ ከተማና አካባቢዋ ላይ እግሩ የረገጠ ሁሉ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባና ደህንነት እንዲሰማው፣ ብሎም ዘረኝነት ከአገራችን ጠፍቶ፣ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንና ወንድማማችነታችን እንዲቀጥል የበኩላችን እያደረግን፣ ለሌላው አካባቢ ወጣት ምሳሌና ሞዴል መሆን እንፈልጋለን፡፡ ሁሉም በየአካባቢው ለሰላም ዘብ ቢቆም ሙሉ ኢትዮጵያ ሰላም ትሆናለች፡፡ ሰላምና ፀጥታ ከሰፈነ ሰው እንደ ልቡ ተንቀሳቅሶ ይሰራል፤ ልማት ይፋጠናል፡፡ ይህ እንዲሆን ምሳሌ መሆን እንፈልጋለን፡፡
የከተማውን ሰላምና ፀጥታ ከመጠበቅ ባሻገር፣ ለመስራት ያቀዳችሁት ነገር እንዳለ ሰምቼአለሁ፡፡ እስኪ ከአንተ ልስማው?
እውነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ለማጠናከር፣ የአንዱ አካባቢ ችግር የእኛም ችግር እንደሆነ ለማሳየት፣ የአንዱ አካባቢ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብት የእኛም እንደሆነ እንደምናስብ ለመግለጽና ድጋፋችንን ለማሳየት  ጎጃም ሄደን፣ ጣና ላይ የበቀለውን መጤውን አረም፣ እምቦጭን ለመንቀል አስበናል፡፡ የምንሄድበትን ቀን ለመወሰን ገና በመመካከር ላይ ነን፡፡ ነገር ግን ዋነኛ አጀንዳ አድርገን ተነጋግረንበታል፡፡ ሌላው ሀሳባችን፣ ሁሉም አካባቢ ወጣት አለ፡፡ አካባቢውን አገሩን የሚወድ በርካታ ወጣት አለ፡፡ አንደኛ፤ ለአካባቢው ሰላም ዘብ እንዲቆም፣ በተለያዩ አካባቢዎችና ከተሞች እየተዘዋወርን፣ የእኛን ልምድ ለማካፈልና ሁሉም አካባቢና ከተማ፣ የእኛ ዓይነት የሰላም አምባሳደር ወጣቶች ማህበር እንዲቋቋም ለማድረግ አስበናል:: አገራችንን ለፖለቲካ ነጋዴዎች፣ ለሴረኞች፣ ከብጥብጥና ከግጭት በሚያገኙት ጉቦና መደለያ ሆዳቸውን ለሚሞሉ ባንዳዎች ጥለን፣ እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ የለብንም፡፡ ወጣትነት ሀብት ነው፤ ኃይል ነው፡፡ ይህንን ሀብት፣ ይህንን ሀይል ሁሉም ከተሞች ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ ለዚህ እኛ ምሳሌ ነን፡፡ ይህንን ልምድ ለማካፈል ሀሳብ አለን:: በአቅም ውስንነት እኛ የማንደርስበት አካባቢ ካለ፣ ይኸው እንደ እናንተ አይነት ሚዲያዎች እየመጡ፣ እየጎበኙን ሲዘግቡ፣ ለሁሉም ይዳረሳል ማለት ነው፡፡
አንድ ሰው ወይም ቡድን ጥፋት ሲያጠፋ ብታገኙ የመጀመሪያ እርምጃችሁ ምንድን ነው የሚሆነው?
እንግዲህ በከተማው ላይ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ በአመራሮችም ጭምር ትልቅ ተቀባይነት አግኝተናል:: ሁሉም ለእኛ ትልቅ ግምት አለው፡፡ ስለዚህ ተቀባይነት ያለው ሰው ቀጪ አይሆንም፡፡ ጥፋት የሚያጠፉትን እንመክራለን፡፡ እናስተምራለን፣ ወንጀልና ስርቆት አሳፋሪ እንደሆነ እንናገራለን፡፡ የተጣሉም ካገኘን መሃል ገብተን፣ አንተም ተው፣ አንተም ተው ብለን ወንድማማች እንደሆኑ፣ መተባበር እንጂ መጣላት መጋጨት እንደሌለባቸው መክረን፣ አስታርቀን ነው የምንሸኛቸው፡፡ ጉልበት አለን፣ ጡንቻ አለን ብለን ወደ ቅጣትና ወደ ሀይል እርምጃ አንሄድም፡፡ እስካሁን ትዕግስት የሚፈታተን ቢመጣም እስከ መጨረሻው እንታገሳለን፡፡ በምክክርና በሰላም እንዲፈታ ነው የምናደርገው፡፡ ይሄ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ የኖርንበት ህይወት፣ የመጣንበት መንገድ ያስተማረን ነው፡፡ ገና ጅማሬ ላይ ነን፤ ብዙ ይጠበቅብናል ፤እኛም ለመስራት ብዙ ፍላጎትና ዝግጅት አለን፡፡
በከተማዋ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ፣ ፌስቲቫል፣ እግር ኳስ ጨዋታና ሌሎች ሁነቶች ሲኖሩ ለምታስተባብሩበት፣ ለምታስከብሩት  ሰላም ምን ያህል ይከፈላችኋል?
በፍፁም! ምንም አይነት ክፍያ አይከፈለንም:: በበጎ ፈቃደኝነት ብቻ ነው የምንሰራው፡፡ ግዴታችንም ነው፡፡ ስለዚህ አምስት ሳንቲም የሚከፈለን ክፍያ የለም፡፡ ሁላችንም ባንሆንም፣ አብዛኞቻችን የየራሳችን ስራ አለን፡፡ እኔ ትልቅ ክለብ አለኝ፡፡ ሌሎችም የየራሳቸው ስራ አላቸው፡፡ ከመካከላችን ትልልቅ የሚባል ንብረት ያላቸውም ልጆች አሉ:: ጥቂቶቹ ደግሞ ምንም ነገር የላቸውም፡፡ እነሱን ተነጋግረንና ተመካክረን ለማቋቋም፣ የራሳቸው ስራና ገቢ እንዲኖራቸው ለማድረግ እያሰብን ነው፡፡
በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይ በከተሞችና በዩኒቨርሲቲዎች ግጭትና ረብሻ ተፈጥረዋል፡፡ በየጊዜውም እየተፈጠሩ ነው፡፡ በዚህ ደግሞ ህይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል:: በአጠቃላይ ብዙ ኪሳራ ደርሷል፡፡ በየአካባቢው ለሚገኙ  እንደናንተ አይነት ወጣቶች ምን መልዕክት ታስተላልፋለህ?
የሚገርምሽ በየከተማው በየዩኒቨርሲቲው አሉባልታ እየነዙና ነገር እየጫሩ፣ ችግር የሚፈጥሩት ስራ መስራት የማይችሉ ፍፁም ቦዘኔዎች ናቸው:: እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ወጣት፣ ወጣት ተብለው ሊጠሩም አይገባም፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ወጣት፣ በኢትዮጵያዊነት ሥነ ምግባር ተቃኝቶና ተቀርፆ ያደገ፣ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለው ነው፡፡ እነዚህ ግን ሰርተው ገንዘብ የማያገኙ፣ በሰላም የሚሰሩ ወጣቶች ላይ ቅናትና ምቀኝነት የሚያድርባቸው፣ የበታችነት ስሜት የተጠናወታቸውና ለገንዘብ ሲሉ ማንኛውንም አይነት ወንጀል ለመፈጸም የሚላላኩ፣ ጥቂት ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ናቸው፡፡ አዕምሮ ያለው፣ የሚሰራ ወጣት፣ አገር ያለማል ይገነባል፡፡ ስለዚህ መላው የኢትዮጵያ ወጣት፤ ስራ መስራትና ስራን ባህል ማድረግ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ያኔ አዕምሮ ተንኮልና ሴራ አያስብም፡፡ ያኔ ግጭት አይኖርም፡፡
መንግስትም ወጣቶችን አደራጅቶ ብር ከመስጠቱ በፊት ማስተማር አለበት፡፡ እኔ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ በፊቱ ፈሪሀ እግዚአብሔር አለ ብዬ ለማለት እቸገራለሁ፡፡ መፅሐፍ ቅዱስ ያነባል፤ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳል ይባላል፤ ለእኔ ውሸት ነው፡፡ ምክንያቱም ወንድም ወንድሙን ያረደበት፣ያቃጠለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ አሁን እኔ 20 እና 30 ሰው ተሰብስቦ ሳይ ይጨንቀኛል፡፡ ሰው ተሰብስቦ ዘግናኝ ስራ ሲፈፀም በአይኔ ስላየሁ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ወጣቱ መማር አለበት፡፡ ሁላችንም ዝም ብለን ተወልዶ አድጎ ሞተ ከምንባል ቁም ነገር ሰርተን፣ አሻራ አስቀምጠን  ማለፍ አለብን:: እኛም ለዚህ ምሳሌ ለመሆን እየሰራን ነው ብዬሻለሁ:: በቀጣይ ከሲዳማ ወንድም ወጣቶች ጋር ትክክለኛውን እርቅ ለማድረግ፣ እኛም እዛ ሄደን የሲዳማ ወጣቶችም እዚህ መጥተው መገናኘት አለብን፡፡ ከባለስልጣንና ከካቢኔ እርቅ ባለፈ በወጣቱ መካከል የቀድሞ ግንኙነት እንዲፈጠር ለማድረግ እየሰራን ነው፡፡ ወጣቱ የሀገሩን እጣ ፈንታ ለመወሰን ዕድሉ በእጁ ስለሆነ፣ ወጣትነትን ለመልካም ስራ፣ ለሰላም፣ ለአገር ልማት ግንባታ እንጠቀምበት የሚል መልዕክት አለኝ፡፡

Read 878 times