Sunday, 16 June 2019 00:00

መንግስት በሚመድበው በጀት ላይ ቁጥጥር ማድረግ ይገባዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

· በየዓመቱ 3 ቢሊዮን ብር ይባክና
         · ለክልሎች ድጎማ የተያዘው በጀት በአብላጫ ድርሻ ይዟል
         · ከታክስ በሚሰበስበውና ለግዥ በሚወጣው ወጪ መካከል የ77 ቢሊዮን ብር ልዩነት አለ


               መንግስት በየዓመቱ የሚመድበውን በጀት ከብክነት ለመከላከል የቁጥጥር ስርአቱን ማጠናከር እንዳለበት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አሳሰቡ፡፡ መንግስት የሃገሪቱን ገቢ እና ወጪ ማመጣጠን ላይ እንዲያተኩርም ጠይቀዋል፡፡
መንግስት ከታክስ ለበጀት በሚሰበስበው እና ለግዢ በሚያወጣው ወጪ መካከል የ77 ቢሊዮን ብር ልዩነት መኖሩን የጠቆሙት በምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁት የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ተመስገን ዘውዴ የሃገሪቱ ዋነኛ የባጀት አመዳደብ ችግር መንግስት የሚሰበስበውን ገቢ ከሚያወጣው ወጪ ማመጣጠን አለመቻሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በየዓመቱ እስከ 3 ቢሊዮን ብር እንደሚባክን የሚጠቁሙት ሌላው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በበኩላቸው ዋነኛ ችግሩ የበጀት አጠቃቀምን ከብክነት መከላከል የሚያስችል ጠንካራ የቁጥጥር ስርአት አለመዘጋጀቱ ነው ሲሉ በየዓመቱ የፌደራል ዋና ኦዲተር የሚያቀርበውን ሪፖርት እና በሪፖርቱ በታየው ጉድለት ላይ የሚወሰድ እርምጃ አለመኖሩን በማሳያነት ጠቅሰው ያስረዳሉ፡፡
ወጪ እና ገቢ እየተጣጣመ ባለመሆኑ መንግስት በመሃል ተጨማሪ በጀትን መጠየቅ ጀምሯል የሚሉት አቶ ተመስገን አሁን ሃገሪቱ እያጋጠማት ላለው የዋጋ ግሽበትም ይህ ተጨማሪ በጀት የመመደብ ሂደት አስተዋፅኦ አለው ብለዋል፡፡
“መንግስት የታክስ አሰባሰብ መሰረቱን በሚፈለገው መጠን አላሰፋም” የሚሉት አቶ ተመስገን ይህም የሃገሪቱ አብዛኛው በጀት ከውጭ በሚኝ እርዳታ እና በብሔራዊ ባንክ ታትሞ በሚቀርብ ብር ላይ እንዲመሰረት አድርጎታል ብለዋል፡፡
ከበጀቱ 30 በመቶ በእርዳታ የሚገኝ ነው ያሉት አቶ ተመስገን ይህ የሃገር ሉአላዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ከመሆኑም በላይ የውጭ እዳዋ የበዛባት ሃገር እያደረጋት ነው ይላሉ፡፡ ለዚህ መፍትሄው መንግስት የታክስ ምንጩን በማስፋት በጀቱ በገቢ ላይ የተንጠለጠለ ማድረግ መሆኑን ያስረዳሉ - ባለሙያው፡፡
መንግስት በአብዛኛው የባጀት ጉድለቱን ከውጭ በመለመን ወይም ብር በማተም ነው ሊሞላው የሚችለው ያሉት አቶ ተመስገን ብር ታትሞ ወደ ገበያ ሲሰራጭ ደግሞ የሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ይፈጥራል፡፡ አሁን በሃገሪቱ እየታየ ላለው የኑሮ ውድነትም አንዱ ምንጭ ይሄው እንደሆነ ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡
በየዓመቱ ሃገሪቱ የምትመድበው በጀት ለከፍተኛ ብክነትና ሙስና የተጋለጠ መሆኑን በአፅንኦት የሚገልፁት የምጣኔ ባለሙያው ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በበኩላቸው ሙስናንና የገንዘብ ብክንትን ለመከላከል አንዱ መፍትሄ ለልማት ስራ የሚመደብ (ካፒታል በጀትን) የመንግስት መስሪያ ቤቶች እጅ እንዳይገባ ማድረግ ነው ይላሉ፡፡ የተደለደለው ባጀትም ለምን ተግባር እንደወጣ የሚቆጣጠር ጠንካራ የቁጥጥር ስርአትም በፓርላማው ሊዘረጋ እንደሚገባ እና ጠንካራ ቁጥጥር በሌለበት አባካኝ ለሆኑ መስሪያ ቤቶች ባጀት መመደብ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
የበጀት አጠቃቀምን ለማስተካከል የቻይናን የበጀት አጠቃቀም ስልት መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡፡
ቻይና እያደገች ያለችው የፋይናንስ ምርምር ተቋማትን፣ የግል ሴክተሩንና መንግስትን የሚያቀናጅ የበጀት ስልት በመጠቀሟ ነው ስለዚህም በኛም ሃገር “መንግስትን ሊያሰራ የሚችል በጀት ሳይሆን ሃገሪቱን እንዴት ማሳደግ ይቻላል የሚል አወቃቀር መፈጠር ይኖርበታል” ብለዋል፡፡ እስካሁን መንግስት ሃገሪቱን እንዴት አድርጎ ነው መቆጣጠር ያለበት ከሚል መነሻ በጀት እንደሚዋቀር ዶክተሩ ጠቁመዋል፡፡
የበጀት እና የፋይናንስ ስርአቱ መበላሸት ሃገሪቱን ላልተገባ የኑሮ ውድነትም እንደዳረገ የሚያብራሩት ባለሙያው የብር የመግዛት አቅም በየዓመቱ በ6 በመቶ እየቀነሰ መሆኑን በማስረዳት ብሔራዊ ባንክ የብር ህትመትና የፋይናንስ ስርአቱን ማስተካከል አለበት ይላሉ፡፡
አቶ ተመስገን በበኩላቸው የፋይናንስ ስርአቱን ለማስተካከልና ስራ አስፈፃሚው እንዳሻው ብር ከማተም እንዲቆጠብና ቁጥጥር ለማድረግ ብሔራዊ ባንክ ለመንግስት ስራ አስፈፃሚ ተጠሪነቱ ቀርቶ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መሆን ይገባዋል ይላሉ፡፡
መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም ዘላቂ መፍትሄውን በባለሙያዎች እያስጠና እስከዚያው በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ድጎማ ማድረግ አለበት የሚሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ይህ ካልሆነ የኑሮ ውድነት በራሱ የህዝብን ብሶት አባብሶ የአረብ ሃገራት እንዳጋጠመው አይነት ቀውስ ሊፈጥር ይችላል ብለዋል፡፡ በኑሮ ውድነት ምክንያት ሱዳንን ጨምሮ በአፍሪካ ውስጥ በ42 ሃገራት ለመንግስት ግልበጣ መነሻ መሆኑንም ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ያስታውሳሉ፡፡
የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም መንግስት አቅርቦትን ማሳደግ አለበት የሚሉት ደግሞ አቶ ተመስገን ዘውዴ ናቸው፡፡
ለቀጣዩ 2012 አመት የተያዘው ረቂቅ በጀት 387.9 ቢሊዮን ሲሆን ከዚህ ውስጥ ለመደበኛ ወጪ (የመንግስት ስራ ማስኬጃ) 109.5 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል በጀት (የልማት ስራዎች ማከናወኛ) 130.7 ቢሊዮን ብር እንዲሁም የበጀቱ አብላጫ ማለትም 140.8 ቢሊዮን ብር ለክልሎች ድጎማ እንዲውል እቅድ ቀርቧል፡፡
የዘንድሮ በጀት ከአምናው ስነፃፀር የ6 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው ሲሆን አምና ከተያዘው በጀት አልበቃ ብሎ በዓመቱ አጋማሽ 18 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መጠየቁም አይዘነጋም፡፡


Read 5933 times