Sunday, 16 June 2019 00:00

በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች በገለልተኛ አካል እንዲጣራ መኢአድ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  · ለኮሌራ ወረርሽኝ መንግስት ትኩረት እንዲሰጥ ፓርቲው አሳስቧል
                   · የኑሮ ውድነት ማቃለያ እንዲተለምም ተጠይቋል

             በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች በገለልተኛ አካል እንዲጣራ የጠየቀው መኢአድ፤ በሃገሪቱ የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስቧል፡፡
የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ትናንት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሃገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ህይወት ያለአግባብ መጥፋትና የአካል መጉደል እንዳሳሰበው ገልፆ፤ መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቋል፡፡ ፓርቲው አክሎም፤ የችግሩ ምንጭ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ፣ የተጠናከረ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች የቅድመ ግጭት ክትትል እንዲደረግ ለመንግስት ሃሳብ አቅርቧል::
ፓርቲው በዚህ መግለጫው በአዲስ አበባ ከተማ ህገ ወጥ ቤቶችን ለማፍረስ የተያዘውን ውጥን በተመለከተ መንግስት ለዜጎች አማራጭ ሳያስቀምጥ ቤቶችን ማፍረስ እንደማይገባው አሳስቧል፡፡ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ከተሞች በተካሄደው ተመሳሳይ ቤት የማፍረስ ተግባር በርካታ ዜጎች ያለ አግባብ፣ ለኑሮ ጉስቁልናና ለሰብአዊ እርዛት መጋለጣቸውን በመጠቆም፤ መንግስት ዜጎችን ከማሳቀቅ እንዲታቀብ ጠይቋል፡፡
በሃገሪቱ የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝም በእጅጉ አሳሳቢ ነው ያለው ፓርቲው፤ መንግስት ለበሽታው ትኩረት ሰጥቶ እንዲንቀሳቀስ ያሳሰበ ሲሆን የመኢአድ አባላት፤ ዜጎችን ከበሽታው ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ ሙሉ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሃገሪቱ ዜጎች በኑሮ ውድነት እየተሰቃዩ መሆኑን በመግለጫው የጠቆመው መኢአድ፤ መንግስት የኑሮ ውድነት ማቃለያ መንገዶችን እንዲተልም እንዲሁም በውሃ፣ መብራትና ትራንስፖርት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ እንዲያደርግም ጠይቋል፡፡   


Read 652 times