Sunday, 16 June 2019 00:00

የመጀመሪያዋ ሴት Gynecology oncologist

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)


             ‹‹…እንደአጠቃላይ ግን የተወሰነ ለውጥም እንደለውጥ የሚታይ እና የህክምና ባለሙያው ሙሉ መስዋእትነትን ለመክፈል ዝግጁ እስከሆነ ድረስ በጣም ከባድ ነው መሰራት አይችልም የሚባል ስራ ነው ብዬ አላምንም፡፡››
ዶ/ር ማሪያማዊት አስፋው ትባላለች፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት በመሆን ስታገለግል የቆየች የህክምና ባለሙያ ነች፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በተጨማሪ የማህጸን ካንሰር ሕክምና እስፔሻሊስት Gynecology oncologist ለመሆን በህንድ አገር ለአንድ አመት ስትከታተል የቆየችውን ትምህርት አጠናቃ በመመለስ አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ትገኛለች፡፡ ዶ/ር ማርያማዊት ወደ ሐገር ቤት የተመለሰችው ከ5/ወር በፊት ነው:: Gynecology oncologist በተባለው ሙያ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ቁጥራቸው እንዲጨምር ገና ጥረት እየተደረገ ያለ ሲሆን እነሱም ወንዶች ናቸው፡፡ ዶ/ር ማርያማዊት አስፋው ግን  Gynecology oncologist በመሆን ስራ ላይ የተሰማራች የመጀመሪያዋ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ባለሙያ ሴት ነች፡፡  
ዶ/ር ማርያማዊት እንዳለችው የማህጸን ካንሰር እስፔሻሊስት መሆን ማለት ሴቶች የሚገጥማ ቸውን የካንሰር ሕመም የሚያክም ሆኖ ግን ሁሉንም አይነት ካንሰር ሕመም ሳይሆን በተለይ  የማህጸን አካባቢ ካንሰርን ማከም ማለት ነው፡፡
ይህ Gynecology oncologist የተባለ ሙያ ከአሁን ቀደም ትምህርቱ በአገር ውስጥ ስለማይሰጥ ሐኪሞቹ በውጭ አገር ተምረው የመጡ ውስን ወንድ ሐኪሞች ብቻ ነበሩ፡፡ በእኛ ሐገር ትም ህርቱ መሰጠት የተጀመረው ምናልባት ከሶስት አመት ወዲህ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው፡፡ ስለዚህ ትምህርቱ አዲስ እንደመሆኑም መጠን በዚህ ሙያ ብዙ የገቡ ሴቶች የሉም፡፡
የካንሰር ሕክምና ትንሽ ከበድ ያለ ነው፡፡ የሐኪሙን ስራ ከባድ የሚያደርገው በቀጥታ ሕክም ናው ብቻ ሳይሆን በመጀመሪያ ካንሰሩ አለ ብሎ ለታካሚው ከመንገር የሚጀምር ነው፡፡ ከቤተሰብ ጋር እንዲሁም ከሕመምተኛው ጋር በምን መንገድ ሕክምናው እንደሚደረግ እና በማዳን ስራው ላይ የሁሉም ድርሻ ምን መሆን እንዳለበት ከመተማመኑ የሚጀምር ነው ክብደቱ፡፡ ስራው ድፍረትን ፤የተሟላ እውቀትን ፤በራስ መተማመንን መፈለጉ እውን ነው፡፡
እንደአጠቃላይ ግን አለች ዶ/ር ማርያማዊት አስፋው፡
‹‹…እንደአጠቃላይ ግን የተወሰነ ለውጥም እንደለውጥ የሚታይ እና የህክምና ባለሙያው ሙሉ መስዋእትነትን ለመክፈል ዝግጁ እስከሆነ ድረስ በጣም ከባድ ነው መሰራት አይቻልም የሚባል ስራ ነው ብዬ አላምንም፡፡››
ስለዚህ ብዙ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ባለሙያዎች ወደመስኩ መግባትና ህብረተሰቡን ማገል ገል ይችላሉ፡፡ በእርግጥ መስዋእትነትን መጠየቁ የማይቀር ቢሆንም ያንን አሟልቶ ወደስራው መግባት ግን እራስን ማሳመንን እና ለሙያው ብቃት እና ትግበራ ዝግጁ መሆንን የሚጠይቅ ይሆናል፡፡   
በሕንድ አገር ቆይታዬ ትምህርቱ በጣም ጥሩ ነበር ያለችው ዶ/ር ማርያማዊት የታካሚዎች ወይንም የህመምተኛው አይነት ግን እኛ ሐገር ካለው በተወሰነ ደረጃ ለየት የሚል ነገር እንዳለው ታዝቤአለሁ ብላለች:: ዶ/ር ማርያማዊት ለትምህርት የሄደችበት ማእከል በተለይ በካንሰር ሕክምና ላይ ስፔሻላይዝድ ያደረገ ሴንተር በመሆኑም ከማህጸን ካንሰር እስፔሻሊስቶች ጋር ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ የካንሰር ሕክምና እስፔሻሊስቶች ጋር አብሮ ለመስራት እድሉን ፈጥሮአል፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ የማህጸን ካንሰር ሕክምና ስራ የሚወሰነው በማህጸን ካንሰር ሐኪሞች ብቻ ሳይሆን የሌሎቹንም እገዛ ስለሚሻ ለተማሪዎች እውቀቱን ለማዳበር ትልቅ እድል ፈጥሮእል፡፡
ዶ/ር ማርያማዊት በማከል እንደገለጸችው በሕንድ አገር ስላለው የካንሰር ታካሚዎች መጠን ለመናገር የሚያስችል ግንዛቤ ባይኖረኝም ለትምህርት የሄድኩበት ማእከል ግን የካንሰርና የልብ ልዩ ሕክምና በግል የተቋቋመ ሴንተር ነው:: ለትምህርቱ ባለሙያዎችን ከየሀገሩ ሲቀበሉም መስፈርቱ ጠበቅ ያለ እና መሟላት የሚገባቸውን ነገሮች በጥንቃቄ ይፈትሻሉ፡፡
ይህንን መስፈ ርት አሟልቼ የሄድኩበት ማእከል ለሕክምና የሚመጡ ታካሚዎች ገንዘብ ከፍለው መታከም የሚችሉ ናቸው፡፡ ከዚያ በመነሳት ግን በአጠቃላይ በአገር ደረጃ ያለውን ሁኔታ ስገምት እና በመረጃ ደረጃ እንደሰማሁት በሕንድ ብዙ የማህጸን ካንሰር ሕመም ታካሚዎች አሉ፡፡ በግል መታከም ለማይችሉት የመንግስት ሆስፒታሎች አገልግሎቱን ይሰጣሉ፡፡
በአንድ አመት የህንድ ቆይታ ቢያንስ በሁለት ቀን አንድ ኦፕራሲዮን በመስራት ከመቶ በላይ ታካሚዎችን ለማከም እድሉን አግኝቻለሁ ያለችው ዶ/ር ማርያማዊት ህክምናው ግን በጨረር፤ በመድሀኒት ጭምር የታገዘና እንዲሁም ከሌሎች የካንሰር ሕክምና እስፔሻሊስቶች ጋር በቡድን በመሆን የሚሰራ ነበር፡፡ ስለዚህ ትምህርቱ ከስራ ጋር የተጣመረ ነበር ፡፡
ዶ/ር ማርያማዊት የዛሬ አምስት ወር ትምህርቷን አጠናቃ ወደሀገር ከገባች በሁዋላ የስራ ፈቃዱዋን በኢትዮጵያ መንግስት በጤናው ዘርፍ ባለው ባለስልጣን ለማጸደቅ ከቆየችበት ጊዜ በስተቀር በቀጥታ ወደሕክምናው ገብታለች፡፡
በአሁኑ ወቅት በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በስራ ላይ ያሉት Gynecology oncologist ባለሙያዎች ጋር በትብብር መስራት እጅግ አስፈላጊ እና የግድ ነው ባለሙያዋ እንዳስረዳችው፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ አይነት ሕክምና አንድ አመት ተምሬአለሁ፤ በቃ በሙ ያው እጅግ ሰልጥኛለሁ፤ ብቃት አግኝቻለሁ ብሎ ለብቻ የሚኬድበት ሳይሆን የሰውን ሕይወት ለማዳን አስፈላጊ የሆኑ ተጨማሪ ስራዎችን ቀደም ሲል ከተመረቁ ባለሙያዎች ጋር መስራት ግድ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ከሙያ ባልደረቦቼ ጋር በመሆን የብዙዎችን ሴቶች ማህጸን ካንሰር ሕክምና በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ እየሰራን እንገኛለን ብላለች ዶ/ር ማርያ ማዊት፡፡
የካንሰር ሕክምና ማለት በመድሀኒት፤ በጨረር ሕክምና፤ በኦፕራሲዮን እና አስቀድሞ ካንሰር እንዳይሆን ለመከላከል የሚሰራ፤ እንዲሁም የካንሰር ምልክት በማሳየቱ ሕክምና የሚደረግ ላቸውን ያጠቃልላል:: ከዚህ ውስጥ በቅዱስ ጳውሎስ የማይሰጠው የጨረር ሕክምናው ብቻ ነው፡፡ የጨረር ሕክምናውን ለመስጠት የሚያስችለው ዝግጅት ስላላለቀ ታካሚዎች የሚላኩት ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው፡፡
የህብረተሰቡን የመታከም ልምድ በተመለከተ ዶ/ር ማርያማዊት የሚከተለውን ነበር የተናገረችው፡፡
‹‹….የህብረተሰቡን ህክምና የማድረግ ልምድ የማገናዝበው ገና የመጀመሪያ አመት የህክምና ትምህርት ተማሪ ከነበርኩበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ሳስታውስ አብዛኛውን ጊዜ የካንሰር ሕመም ታካሚዎች ወደሕክምና ይመጡ የነበሩት መጠኑን ካለፈ በሁዋላ ሕክምና አድርጎ ለማዳን እጅግ አስቸጋሪ ከሆነ በሁዋላ ነበር፡፡ በእርግጥ ካንሰሩ አይነቱ ይለያያል:: አንዳንድ ካንሰሮች በጊዜ ምልክት ላያሳዩ የሚችሉ ሲሆን በተጨማሪም ከብዙ ቀለል ካሉ ሕመሞች ጋር የመመሳሰል ባህርይ ሊኖራቸው እንዲያውም ሕክምናው ጋ ደርሰውም ምንነቱ በጊዜ ላይታወቁ የሚችሉም አሉ:: አሁንም ቢሆን ግን የካንሰር ሕመሙ ደረጃውን ካለፈ በሁዋላ የሚመጡ ታካሚዎች የሉም ለማለት አይደለም፡፡ ቢሆንም ግን ቀደም ባሉት ጊዜያት ይታይ ከነበረው ይልቅ በአሁኑ ወቅት የካንሰር ሕመሙ ገና ሲጀምር የሚመጡት ታካሚዎች ብዙ ቁጥር ያላቸው በመሆኑ ህብረተሰቡ ለጤናው ጥንቃቄ እያደረገ እና ወደሕ ክምናውም በፍጥነት የመሄድ ባህሉ እየተለመደ መምጣቱን ያሳያል:: አሁንም ግን ህብረተሰቡ በሽታን አስቀድሞ የመከላከል ግንዛቤውን እንዲያዳብር ማድረግ እና  የህክምናው መስክም አገልግሎቱን በጥራት እና በብቃት ለማዳረስ ዝግጁ የመሆን ነገርን በተሻለ መስራት ይጠበ ቅብናል:: የህክምናው ባለሙያው የተጣለበትን ግዴታ በአግባቡ ለመወጣት ቃል ኪዳኑን ጠብቆ እና እራሱን አሳምኖ ሁልጊዜ ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ›› ብላለች፡፡


Read 1761 times