Monday, 10 June 2019 11:21

የአፍሪካ ህብረት ሱዳንን ከአባልነት አገደ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተፈጸመውን ግድያ አውግዟል

             የሱዳን ህዝባዊ ተቃውሞ  ተባብሶ መቀጠሉንና የወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ወታደሮች በወሰዱት የሃይል እርምጃ ባለፉት ጥቂት ቀናት አንድ መቶ ያህል ተቃዋሚዎች መገደላቸውን ተከትሎ፣ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት፣ ሱዳንን ከህብረቱ አባልነት ማገዱን ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡
የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤቱ በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ በአዲስ አበባ ያካሄደውን አስቸኳይ ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ሱዳንን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ስልጣኑን በሲቪል ለሚመራ የሽግግር መንግስት እስከሚያስረክብ ድረስ ሱዳን በየትኛውም የህብረቱ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳትሳተፍ እገዳ ተጥሎባታል፡፡
በተቃውሞ እየተናጠችና ወደ እርስ በእርስ ግጭት እያመራች የምትገኘዋን ሱዳን ከቀውስ ለመታገድ የሚቻለው በሲቪል አስተዳደር የሚመራ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ሲቻል ነው ያለው የህብረቱ የሰላምና የጸጥታ ምክር ቤት፤ ወታደራዊው ምክር ቤት ይህን አማራጭ በመጠቀም አገሪቱን ከጥፋት እንዲታደግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኡመር አልበሽር ከስልጣን ከወረዱ በኋላ እጅግ አስከፊው የተባለው የተቃውሞ ሰልፍ ባለፈው ሰኞ በካርቱም መካሄዱንና የወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ወታደሮች ባለፉት ቀናት በድምሩ 100 ያህል ተቃዋሚዎችን መግደላቸውን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ ይህን ተከትሎም ተቃውሞው ወደ ሌሎች የሱዳን ከተሞች መስፋፋቱንና ውጥረቱ መባባሱን አመልክቷል፡፡
ከትናንት በስቲያ የተወሰኑ ሰራተኞቹን ከሱዳን ያስወጣውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጨምሮ የተለያዩ የአለማችን አገራት መንግስታት ወታደሩ በሱዳን ተቃዋሚዎች ላይ የሚወስደውን የሃይል እርምጃ እያወገዙት እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው፤ ሩስያ በበኩሏ በሱዳን ላይ የሚደረግን የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት እንደምታወግዝና ችግሩ በብሄራዊ መግባባት መፈታት እንዳለበት ያላትን አቋም አስታውቃለች፡፡ አለማቀፉ ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ፤ ወታደራዊው መንግስት ከሃይል እርምጃዎች እንዲታቀብ አለማቀፍ ጫና ሊደረግ ይገባል ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡
የሱዳን ዶክተሮች ማዕከላዊ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፤ በሳምንቱ በወታደሮች በተፈጸመባቸው ጥቃት ከ108 በላይ ተቃዋሚዎች መገደላቸውንና ከ500 በላይ የሚሆኑትም መቁሰላቸውን ቢያስታውቅም፣ የሱዳን የጤና ሚኒስቴር ግን “ቁጥሩ ተጋኗል፤ የሞቱት 61 ብቻ ናቸው” ሲል ማስተባበሉን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በሱዳን ህዝባዊ ተቃውሞው ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ፣ የቱርክ አየርመንገድን (ተርኪሽ ኤርላይንስን) ጨምሮ ወደ አገሪቱ ይጓዙ የነበሩት የግብጽና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ አየር መንገዶች በጸጥታ ስጋት ሳቢያ በረራቸውን መሰረዛቸውን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡

Read 1137 times