Print this page
Saturday, 08 June 2019 00:00

ጊዜና ተግባሩ ወይስ ሰውና ተግባሩ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)


               “ለሁሉም ጊዜ አለው” ብሏል ጠቢቡ፡፡ ለመምጣትም ጊዜ አለው፤ ለመሄድም ጊዜ አለው … የጥንቱ የኢየሩሳሌም ጠቢብ ምን ለማለት ፈልጎ እንደሆነ ለማስረዳት፤ በርካታ ምሳሌዎችን ዘርዝሯል፡፡ ቢሆንም ግን፤ በተለያየ ጊዜ የመጡና የሄዱ ሌሎች ጠቢባን፣ እንደየሃሳባቸውና እንደየዝንባሌያቸው፣ በተቀራረበም በተራራቀም መንገድ ተርጉመውታል፡፡
“ሁሉም ነገር ለበጎ ነው” በማለት ያስተማረውን ፈላስፋ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አለም ምድሩ ሁሉ፣ ማንም ከሚያስበው በላይ የጠራ፣ ተባረከና የላቀ እንደሆነ ይገልፃል የዚህ ፈላስፋ አባባል፡፡ ካሁን በፊት የሆነው ሁሉ፣ … ማለትም በተጨባጭ የምናየው ነገር ሁሉ (እውነታው)፣ … እንዲሁም አሁን የሆነ ነገር ሁሉ (ሁኔታው)፣… እና ወደፊት እየቀጠለ ያለው ነገር (ክዋኔው …) ሁሉ ለበጎ ነው ይላሉ … የሌብኒዝን ትምህርት ያመኑ ሁሉ፡፡ ነገር ሁሉ፣ ጊዜው ሁሉ ለበጎ ብቻ!   
በእርግጥ ይሄ አባባል የቮልቴር መሳለቂያ ሆኗል፡፡ ካንዲድ በተሰኘው መፅሐፉ፣ ቮልቴር ከጥግ እስከ ጥግ ቀልዶበታል፡፡ እውቀትንና ብቃትን፣ ጊዜንና ጥረትን ይጠይቃል እንጂ፣ ሁሉም ነገር፣ ለበጎ ማድረግ ይቻላል፤ “ሁሉም ነገር፣ በራሱ ጊዜ ለበጎ ይሆናል” ብሎ መጠበቅ ግን ሞኝነት ነው ባይ ነው ጠቢቡ ቮልቴር፡፡
በዚህ የማይስማማ ሌላ ጠቢብ፣ “ሁሉን የሚያቅፍና ሁሉን የሚገዛ መንፈሳዊ ህግ አለ፡፡ መንፈሳዊ ህግ ደግሞ፣ በጎ የእድገት ህግ ስለሆነ፣ … በየመሃሉ ውጣ ውረድ ቢያጋጥምም፣ ጊዜው ቢርቅም ቢዘገይም፣ ዞሮ ዞሮ ሁሉም ነገር በራሱ ጊዜ ለበጎ ይሆናል” ይላል - መለኮታዊ ኃይልን በማጉላት፡፡ “አዎ፣ እድገት አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን በመንፈሳዊ ኃይል አማካኝነት አይደለም፡፡ የተፈጥሮ ህግ፣ … በተፈጥሮው የእድገት ህግ ስለሆነ፣ ሁሉም ነገር በራሱ ጊዜ ለበጎ ይሆናል፡፡” የሚል ጠቢብም አልጠፋም፡፡ ድንጋይ በራሱ ጊዜ ተጠርቦ ግንብ ለመሆን፣ በራሱ ጊዜ ወደ ሲሚንቶ ተቀይሮ ሰማይ ጠቀስ ህንፃ እስኪሆን ድረስ፣ ስንት ጊዜ እንደሚፈጅ ለመገመት ካልሞከራችሁ፤ የዚህን ጠቢብ አባባል ከቁም ነገር አልቆጠራችሁትም፡፡ ለነገሩ፣ የተፈጥሮ ህግ እንደዚህ እንዳልሆነ የሚናገሩ ምሁራንም ሞልተዋል፡። እንዲያውም፣ አንዳንዶቹ የምፅዓት ሟርት የሚሰብኩ ይመስላሉ፡፡  
“የተፈጥሮ ህግማ፣ የማርጀት፣ የመበስስ፣ የመፍረክረክ፣ የመበታተን ህግ ነው” የሚሉ ዘመናዊ ጠቢባንን አድምጡ፡፡ ተራ ስብከት ሳይሆን በምርምር የተረጋገጠ እውነት እንደሆነ የሚነግራችሁ ጠቢብ አታጡም፡፡ “የተፈጥሮ ህግ የመክሰም ህግ” እንደሆነ ለማስረዳት፣ “ኢንትሮፒ” የተሰኘውን ህግ ያስተምራል፡፡ “አዎ፣ ለሁሉም ጊዜ አለው፤ ለመንገጫገጭ ጊዜ አለው፣ ከዚያም ለመፍረክረክ ጊዜ አለው፤ ከዚያም ለመበታተን ጊዜ አለው” በማለትም ያብራራል፡፡ “ለመደብዘዝ፣ ከዚያም ለመጨላለም፣ ከዚያም ድቅድቅ ጨለማ ለመሆን ጊዜ አለው፡፡ ተመልሶ አይበራም፡፡ ሁሉ ጊዜ፣ ሁሉም ነገር ወደ ጨለማ፣ ወደ ከንቱ ያመራል፡፡” - ይላል ዘመናዊው ጠቢብ፤ ሳይንሳዊ ግኝት መሆኑንም አጥብቆ እየገለፀ፡፡
የዛሬ 3ሺ ዓመት ገደማ በኢየሩሳሌም ምድር የተፈላሰፈው የጥንቱ ጠቢብ፣ ይህን ዘመናዊ ትምህርት ከአውሮፓ ቢሰማ ሊደነግጥ ሊያዝን ይችላል፡፡ “ሁሉም ነገር ወደ ከንቱ ያመራል” አላልኩም፣ አልወጣኝም ብሎ ቢያስተባብል አይፈረድበትም፡፡ “ነገር ሁሉ እየፈረሰና እየጨለመ ይሄዳል” አላለም የኢየሩሳሌሙ ጠቢብ፡፡
በእርግጥ፣ “ሁሉም ነገር ከንቱ ነው” ብሏል፡፡ የከንቱም ከንቱ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ነገር ግን “ሁሉም ከንቱ ይሆናል” ብሎ ምፅዓትን አልሰበከም፡፡ ልዩነቱን ለማስረዳት ዕድል እንሰጠውና ያብራራ፡፡ እንዲህ ይላል፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው፤ ይበራል፣ ይጨልማል፣ ተመልሶም ይበራና ለመጨለም ዑደቱን ይቀጥላል፡፡ ፀሐይ በምስራቅ ትወጣለች፤ ፀሐይ በምዕራብ ትገባለች፣ ወደምትወጣበት ወደ ምስራቅም ትቸኩላለች፡፡ ነፋስ ወደ ደቡብ ይሄዳል፣ ወደ ሰሜንም ይዞራል፡፡ በየጊዜው፣ በዑደቱ ይቀጥላል (ዘወትር በዙረቱ ይዞራል)፡፡ … እያለ የጥንቱ ጠቢብ አስረድቷል፡፡
በአጭሩ፣ ሰማይ ምድሩ፣ በማያቋርጥ ዘላለማዊ ድግግሞሽ (በዘወትር ዑደት) የተሞላ ነው፡፡ እናም ሁሉ ነገር፣ ከንቱ ነው … ዞሮ ተመልሶ እዚያው፣ ዞሮ ተመልሶ እዚያው … አዲስ ነገር የለም፤ እድገት የለም፤ … ይመጣል፣ ብዙም ሳይቆይ ይሄዳል፣ እንደገናም ይመጣል፤ … ብዙም ሳይቆይ፡፡
ሁሉም ነገር እንደ ትንፋሽ ጤዛ በእፍታ ይፈጠራል፣ በአፍታ ብን ብሎ ይጠፋል … ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ ሁሉም ነገር ጤዛ … ለዚያውም የትንፋሽ ጤዛ … እንደሆነ ጠቢቡ ይናገራል፡፡ ለምንድነው፤ “ነገር ሁሉ ከንቱ የትንፋሽ ጤዛ” እንደሆነ የሚነግረን? “ነገር ሁሉ የድግግሞሽ ዑደት ነውና” የሚል ምላሽ አቅርቧል ጠቢቡ፡፡ “እንደ ትንፋሽ ጤዛ፣ ነገር ሁሉ ለከንቱ ይመጣል፣ ይሄዳል” የሚል የትካዜ ሃሳብ ነው ከኢየሩሳሌም ጠቢብ የምናገኘው፡፡
የዘመናችን የኢንትሮፒ ትምህርት ግን፣ “ነገር ሁሉ ይፈርሳል” በማለት ነው የከንቱነትን ትርጉም የሚገልፀው፡፡ “ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ ግን ጊዜው፣ ሁሌም ለመሰንጠቅ፣ ብሶበት ለመፍረክረክ፣ ለይቶለት ለመንኮታኮት ነው” እንደማለት ቁጠሩት፡፡
ዶ/ር መሳይ ከበደ፣ ሁለት ዓይነት የጊዜ አስተሳሰብ እንዳለ በገለፁበት ፅሑፍ፣ በአንድ በኩል የጊዜ ሂደት አቅጣጫው ወደፊት ብቻ የሚጓዝ፣ ተመልሶም ወደኋላ የማይመጣ ሂያጅ ነው የሚል አስተሳሰብ እንዳለ ይጠቅሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ “ጊዜ፣ ተመላላሽ የድግግሞሽ ዑደት ነው” የሚል አስተሳሰብ እንዳለ ፅፈዋል ዶ/ር መሳይ፡፡ “ጊዜ ይጥላል፤ ጊዜ ያነሳል” … የሚለውን አባባል በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ ጊዜ፣ እንደገና ተመልሶ ይጥላል፤ ዞሮ እስኪያነሳ ድረስ በትእግስት ማለፍ ወይም ችሎ ማሳለፍ እንደሚሻል መምከርም ከዚህ አስተሳሰብ ይመጣል፡፡ “ያልፍልናል” ይባል የለ! ጊዜ ዟሪ ነው፤ ጊዜ ያመጣል፣ ጊዜ ይወስዳል፡፡
ጊዜ ዟሪ ሳይሆን፣ ሂያጅ እንደሆነ ማሰብስ? ጊዜ ሂያጅ ነው ቢባል እንኳ፣ ብዙ ጥያቄዎችን እያንጋጋ ነው የሚሄደው፡፡ አቅጣጫው፣ ሂደቱና አካሄዱ ቢለያይስ? መላቅጥ የሌለው ቢሆንስ? “የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም” የሚያስብል ይሆናል፡፡ “ዛሬን መኖር እንጂ፣ ነገ የሚያመጣውን ማንም አያውቅም” የሚልም ይኖራል፡፡ “ዛሬን እንቻልበት፣ ነገ ለራሱ አያንስም” በማለት የተስፋ ፍንጣቂ ለመፍጠር መሞከርም ይቻላል፡፡
“እንደፍጥርጥሩ፣ ነገርን ሁሉ ለጊዜ እንተወው” በማለት ከተስፋም ከጭንቀትም ውጭ ለማምለጥ መሞከርስ? ከንቱ መከራ ይመስላል፡፡ ጊዜ፣ የሁሉ ነገር ጌታ ሆኖ አረፈው ማለት ነዋ! ለዚያውም መላቅጥ የሌለው ጌታ!
“የሆነው ሁሉ ሆኗል፤ የሚሆነው ሁሉ ይሆናል፡፡ ለምን ወይም እንዴት ብሎ መጠየቅ፤ በየት እና ወዴት ብሎ ማሰብ በከንቱ ከመልፋት፣ በባዶ ከመባከን ያለፈ ውጤት የለውም” የሚል ማምለጫ የትም አያደርስም፡፡ “አጅሬ ጊዜ፣ ስውር፣ ረቂቅ ሚስጥር፣ የማይጨበጥ፣ መላቅጥ አልባ፣ … አድራጊ ፈጣሪ ገዢ” አስመስለነውኮ፡፡ በእርግጥ፣ “ስውር አይደለም፤ አይተነዋል፤ ጨብጠነዋል፣ ረቂቅነቱ ላይ በመራቀቅ ሚስጥሩን ገልጠነዋል ወይም ተገልጦልናል” የሚሉ ጠቢባን የሉም ማለት አይደለም፡፡
መላቅጡን ደርሰንበታል በማለትም ነው፤ … አንዱ ጠቢብ፣ “ዘመኑ አሸወይና ነው” እያለ እልልታን ይሰብካል፡፡ ሌላኛው ጠቢብ፣ “ዘመኑ ክፉ ነው” በማለት እሪታን ያውጃል፡፡ ሦስተኛው ጠቢብ ከእነዚህ ይለያል፡፡ ድንገት ሳይታሰብ የፌሽታ ርችት እየተኮሰ ሰውን አያስፈነድቅም፡፡ ድንገት ተነስቶ ኡኡታውን እየለቀቀ ሰውን አያስደነብርም፡፡ አስቀድሞ የተስፋ ብስራት ያሰማል፣ ወይም የአደጋ ማስጠንቀቂያ ያስጮሃል፡፡ “መጪው ዘመን ብሩህ” ነው፤ ተሰብሰቡ” ይላል፡፡ ወይም “ክፉ ዘመን ቀርቧል፣ ገለል በሉ” ይላል፡፡ “እሰየው” እና “ወዬው” ያስብላሉ፡፡ ልዩነት ቢኖራቸውም፣ “ጊዜ የሚያመጣውን ማን ይመልሰዋል?” የሚያስብሉ መሆናቸው ግን ያመሳስላቸዋል፡፡
እስካሁን እንዳየነው፣ “ጊዜ ዟሪ ነው” በሚለው አስተሳሰብ ስር፤ “ጊዜ፣ ከንቱ የድግግሞሽ ዑደት ነው”፣ … ወይም “ጊዜ፣ አስተማማኝ የዘላለም ዑደት ነው” … ወይም “ጊዜ፣ በትዕግስት የሚያሳልፉት፣ በተስፋ የሚጠብቁት ዑደት ነው” የሚሉ ሦስት ቅርንጫፎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
“ጊዜ ሂያጅ ነው” በሚለው ስር ደግሞ፣ “አጅሬ ጊዜ፣ ሚስጥሩ አይገለጥ! መላ ቅጥ የለው!”፣… ወይም ደግሞ “መላ ቅጥ ባይኖረውም፣ ክፉና በጎ ዘመን ሲመጣ ሚስጥሩ ይታወቃል”፤ … ወይም “መላ ባይኖረውም፣ ቅጥ አልባ አይደለም፤ እያበበ አልያም እየደረቀ፣ እየጣፈጠ ወይም እየመረረ፣ እየበራ ወይም እየጨለመ ይሄዳል” የሚሉ ሦስት ቅርንጫፎችን አይተናል፡፡
እነዚህን በሙሉ የሚጠቀልል ቅኝት ምንድነው ቢባል፤ “በእውን ነገሮች” እና “በጊዜ” መካከል ያለው ግንኙነት ነው፡፡ “ነገሮች ሁሉ፣ በጊዜ ዘዋሪነት መሪነት የሚሽከረከሩና የሚሾሩ ወይም ጊዜ የሚነዳቸው ናቸው” የሚል የአስተሳሰብ ቅኝትን ያዘሉ ናቸው፡፡
ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ፣ ጊዜ … ልክ እንደ ቁመት ወይም እንደ ስፋት፣ … “የነገሮች ባህርይና ገፅታ ነው” የሚል የአስተሳሰብ ቅኝት አለ፡፡ ቁመትም ሆነ ስፋት፣ “በነገሮች” አማካኝነት ነው ትርጉም የሚኖራቸው፡፡ ርዝመትን ስንለካ፣ በአንዳች መለኪያ “ነገር” ነው፡፡ አንድ ክንድ፣ አንድ ስንዝር፣ አንድ ሜትር … እንላለን፡፡
ጊዜም፣ “በነገሮች የእንቅስቃሴና የለውጥ ሂደት” … ነው ትርጉምና ልኬት የሚኖረው፡፡ ቀንና ማታ፣ ክረምትና በጋ፣ … እነዚህ የጊዜና የወቅት ዑደቶች፣ … ከፀሐይ አንፃር የምድር እንቅስቃሴ ገፅታዎች ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ አዎ፣ ለሁሉ ነገር ጊዜ አለው፡፡ “ጊዜ” ማለት የነገሮች የእንቅስቃሴ ገፅታ ነውና፡፡
እንቅስቃሴያቸው፣ ለእይታ የቀረበ ወይም የቀለለ፣ አልያም ለእይታ የራቀ ወይም የረቀቀ ሊሆን ይችላል፡፡ ድግግሞሽ የጎላበት የዑደት እንቅስቃሴ (ቀንና ማታ፣ ክረምትና በጋ የምንለው ዓይነት የምድር ዙረትና ሽክርክሪት)፣ … ወይም ደግሞ ከተራራ ጫፍ ቁልቁል እንደወረደ ናዳ ወደ ቀድሞው ቦታ ተመልሶ የማይደገም እንቅስቃሴም አለ፡፡ እንደየነገሮቹ ተፈጥሮ ነው እንቅስቃሴያቸው፡፡ እንደየተፈጥሯቸውም፣ ለሁሉነገር ጊዜ አለው፡፡ ምድር ፀሐይን ዞራ እስክትመለስ፣ ክረምትና በጋ ተፈራርቆ እስኪደገም፣ ጊዜ አለው - 365 ቀንና ማታ ነው የዑደቱ ጊዜ፡፡ ይሄ የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡
ተመልሶ የማይደገም ቢሆንስ? ለምሳሌ፣ የተራራ ናዳ ወይም ከፎቅ የወደቀ እቃ፣ ታች ምድር ለመድረስ ጊዜ አለው፡፡ አስቀድሞ መጠንቀቅ እንጂ ብዙ ጊዜ አይሰጥም፡፡ ከ30ኛ ፎቅ ያመለጠ እቃ፣ ታችኛው ወለል ለመድረስ 5 ሰከንድ አይፈጅበትም፡፡ ዘመናዊ ትልልቅ አውሮፕላኖች ከሚበርሩበት፣ ከ10ሺ ሜትር ከሚበልጥ ከፍታ ላይ የተለቀቀ፣ ምድር ለመድረስ ጊዜ አለው - 50 ሰከንድ ገደማ … ይሄም የተፈጥሮ ህግ ነው - ዑደት ባይሆንም፡፡
የፊዚክስ ሊቆቹ ኬፕለርና ጋሊሊዮ፣ … በተለይ ደግሞ አይዛክ ኒውተን፣ … ከፎቅ የተለቀቀ እቃ፣ ወይም ከዛፍ ላይ የሚወድቅ ፍሬ፣ … ከመድፍ ጥይት ወይም በሮኬት ከሚመጥቅ ሳተላይት ጀምሮ እስከ ፕላኔቶች ዑደት ድረስ፣ … ሁሉም ነገር ጊዜ እንዳለው፤ ጊዜውንም እንዴት ማስላትና ማወቅ እንደሚቻል የቀመሩ ጠቢባን ናቸው፡፡ ይሄ ሳይንስ ነው፡፡ ለሰው ሲሆን፣ ስነ ምግባር ይጨመርበታል፡፡
ታላቁ ጠቢብ አርስቶትል፣ አስቀድሞ ብሎታል፡፡ ሁሉም ነገር እንደየተፈጥሮው ነው፡፡ ከዚያ ውጭ አይሆንም፡፡ ሰውም … እንደ ግዑዝ ነገር ወይም እንደሌሎች እንስሳት ሳይሆን፣ … ተግባሩን የመምረጥና የመምራት አቅም ስላለው፣ … ጊዜውን ለበጎ ማድረግ ስለሚችል፣ … ተፈጥሯዊ አቅሙን መጠቀም፣ ስኬትና ብቃትን መቀዳጀት የእያንዳንዱ ሰው ድርሻ ይሆናል፡፡ በዘፈቀደ ሳይሆን፣ እንደተፈጥሮው መሆን ማለት፣ ተፈጥሮአዊ አእምሮውን ተጠቅሞ፣ የሕይወት ጊዜውን ለማሳመር መጣር ማለት ነው - በጊዜ!        

Read 6405 times