Saturday, 08 June 2019 00:00

ቃለ ምልልስ ስለ አብን፣ የሽግግር መንግስት፣ የህገ መንግስት ለውጥ --- ኢንጂነር ይልቃል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 የኢትዮጵያውያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ (እሃን) ከተመሠረተ ከአንድ ዓመት በላይ ቢያልፈውም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሲያደርግ አይታይም፡፡ ለምን ይሆን? የፓርቲው መስራችና ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ ያብራራሉ፡፡ አገሪቱ ለገባችበት ውጥንቅጥና የጎሳ ፖለቲካ መፍትሄው፣ ሁሉን አሳታፊ የሽግግር መንግስት መመስረት ነው ይላሉ፡፡ ህገ መንግስቱ የሚሻሻልበት ሦስት መንገዶችንም ይጠቁማሉ፡፡ ስለ ጠ/ሚኒስትሩ አመራርም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንዲህ አጠናቅሮታል፡-

               የኢትዮጵያውያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄን (ኢሃን) ከመሠረታችሁ በኋላ ምን ዓይነት እንቅስቃሴ አደረጋችሁ?
ፓርቲውን መስረተን ወደ ስራ ልንገባ ባልንበት ወቅት በኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲስ ነገር ተፈጥሮ ነበር:: ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ለቀው ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የተሾሙበት ወቅት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የሚከናወኑ ነገሮች በባህሪያቸው ተለዋዋጭና ፈጣን ነበሩ፡፡ ሁሉም ትኩረቱ ቤተ መንግስት አካባቢ በሚፈጠረው አዲስ ነገር ላይ ብቻ ነበር ያነጣጠረው፤ ስለዚህ ለፓርቲ እንቅስቃሴ አመቺ  አልነበረም:: ህዝቡ በወቅቱ የፓርቲዎችን ሃሳብ ለመስማት ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ ድርጅታዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ፈንጠዚያው አመቺ አልነበረም፡፡ ስለዚህ አንዳንድ መግለጫዎችን እየሰጠን፣ ፈንጠዚያው እስኪያልፍ በዚህ ሁኔታ ነው የቆየነው፡፡ አሁን ግን ህዝቡ እየሰከነ መጥቷል፡፡ ሌላ አማራጭ እንዲኖረው እየፈለገ መምጣቱን በግልጽ አመላክቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ድርጅታችንን አጠናክረን፣ አንድ አማራጭ ሃይል ሆነን ለመውጣት  እንቅስቃሴ እናደርጋለን፡፡
እስካሁን አንድም ህዝባዊ ስብሰባ  አላደረጋችሁም፡፡ ለምንድን ነው?
አስቀድሞ ያስቀመጥኳቸው ምክንያቶች እንዳሉ ሆነው በአሁኑ ወቅት የአማራ ብሔርተኝነት አዲስ የፖለቲካ ክስተት ሆኖ መጥቷል፡፡ ስለዚህ የድጋፍ መሠረት ሽሚያ በሚመስል ሁኔታ ፖለቲካውን ማስኬድ አልፈለግንም፡፡ አሁን ያለው ፖለቲካ የፓርቲ መስመርን የተከተለ ሳይሆን ገና ከአገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር የሽግግር ሂደት የማመቻቸት ጊዜ ላይ ነን ብለን እናምናለን፡፡ በመሆኑም ከአማራ ብሔርተኝነት ጋር በአመለካከት ምንም ተቃርኖ የለንም፡፡ እንደውም አንድ የሚያደርጉን ሃሳቦች ይበዛሉ፡፡ እነሱ ህገ መንግስቱ አድሎአዊ ነው፣ ታሪክን የካደ ነው፣ የኢህአዴግ የፖለቲካ ፕሮግራም ግልባጭ ነው፣ የዜጐችን ተዘዋውሮ የመኖር የመስራት መብት ይነፍጋል ይላሉ፡፡ ይሄን እኛም እንስማማበታለን፤ ስለዚህ አብንን የስትራቴጂክ አጋር አድርገን ነው የምናየው፡፡ ከእነሱ ጋር የሚደረግ ፉክክርም አላስፈላጊ ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡ በዚያው ልክ ለአዲሱ አመለካከትም ጊዜ መስጠት ጥሩ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ከእነሱ ጋር ልንፎካከር የምንችለው በመጀመሪያ የዲሞክራሲያዊ ሽግግሩ ተጠናቆ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደ አማራጮች ምርጫ ሲሸጋገር ነው፡፡ ያኔ አብን እና ኢሃን እርስ በእርስ የሚፎካከሩበት ወይም አንዱ ወደ አንዱ የሚመጣበትም ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ግን የምንፎካከርበት ሳይሆን በአጋርነት የምንሠራበት ጊዜ ነው፡፡
ቀደም ሲል ብሔርተኝነትን ይቃወሙ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የአማራ ብሔርተኝነትን እንደሚደግፉ  በግልጽ  እየተናገሩ ነው፡፡ የአማራ ብሔርተኛ ነዎት እንዴ?
እኔ የአማራ ብሔርተኛ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው የአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ በመርህ ላይ የተመሠረተ ትክክለኛ እንቅስቃሴ እንደሆነ አምናለሁ፤ እደግፈዋለሁም፡፡ በብዛት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሃገር እንገንጥል አይሉም:: ኢትዮጵያን የካዱ አይደሉም፡፡ ስለዚህ የአማራ ብሔርተኛ እንቅስቃሴን እደግፋለሁ፡፡ ይሄ ማለት የተለየ አድልኦ ለአማራ ብሔርተኞች አለኝ ማለት አይደም፡፡ ሌሎች ወንድሞቻችን በተበደሉ ጊዜም ሰፊ እንቅስቃሴ አድርጌያለሁ፡፡ አሁንም ቢሆን ከዜግነት ፖለቲካ አልወጣሁም ግን የአማራ ብሔርተኝነትን እደግፋለሁ፡፡ በፊትም ከብሔርተኛ ድርጅቶች ጋር በአጋርነት ስንሰራ ነበር፤ መድረክ የብሔር ፖለቲካ አራማጅ ሃይሎች ያሉበት ነው:: አብረን ስንሰራ ነበር፤ ስለዚህ አሁን ከአብን ጋር ስንሰራ ምንድን ነው የተለየ የሚያደርገው? የአብን መርህ፤ ከኛ መርህ ጋር ብዙም አይጋጭም፡፡
አክራሪ ብሔርተኝነት የሃገሪቱ ፖለቲካ ፈተና ሆኗል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ይህን ሃሳብ ይጋሩታል?
የኢትዮጵያ ፖለቲካን በአትኩሮት ካየነው፣ ኢትዮጵያ በዜጐች አዕምሮ ውስጥ ነው እንጂ በህግ ፈርሳለች፡፡ ኢትዮጵያዊ ዜግነት፤ በህግ፣ የዚህ ሀገር የባለቤትነት ስልጣን የለውም፡፡ ፖለቲካ የሚጀምረው በብሔረሰቦች ቡድን ነው፡፡ በህገ መንግስቱ መሠረት፤ ዜጐች (ግለሰቦች) ሳይሆኑ ብሔረሰቦች ተውጣጥተው የመሠረቷት ሀገር ነች፡፡ የጋራ አንድነት፣ የጋራ ሃገር፣ የሃሳብ ልዩነት ያላቸው ዜጐች ሳይሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን ደምረው፣ ኢትዮጵያ የምትባልን ሀገር እንደ አዲስ እንደፈጠሩ ነው ህገ መንግስቱ የሚነግረን፡፡ በዚህም ሳያበቃ ከፈለጉ እንደሚለያዩም ይገልፃል፡፡ እኛ አሁን ሀገርም የለንም፣ ዜግነትም የለንም፡፡ ግን ኢትዮጵያ ከእያንዳንዳችን አዕምሮ ስላልጠፋች፣እስከ ዛሬ አንድ ላይ ኖረናል፡፡
ለምሣሌ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በርካቶች እየተገደሉ ይፈናቀላሉ፡፡ እኛም እናንተም (ሚዲያዎች)፣ ዜጐች ለምን ይፈናቀላሉ እያልን እንጮሃለን፡፡ ይሄ እንግዲህ ድሮ ባለን ኢትዮጵያዊ ልማድ ነው እንጂ በህግ ያን ያህል ድጋፍ የለንም፤ ምክንያቱም ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በክልሉ ህገ መንግስት መሰረት፤ ባለቤትነቱ የአምስት ብሔረሰቦች ነው፡፡ አንድ አገው ወይም አንድ ኦሮሞ ወይም አንድ አማራ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ሲኖር፣ በክልሉ ውስጥ ከሚኖር አንድ ኬንያዊ የተለየ መብት አይኖረውም፡፡ የመመረጥ መብት የለውም፤ የፖለቲካ ተወካይ አይኖረውም፤ ምክንያቱም የክልሉ ባለቤት ተብለው በህገ መንግስት ከተጠቀሱት ውስጥ የሱ ብሔር የለበትም፡፡ ለዚህ ነው ለኛ የዜግነት ፖለቲካ ለምናራምድ ጉዳዩ ፈተና የሚሆንብን፡፡ ስለዚህ ንቅናቄያችን፣ ህገ መንግስቱን ገምግሞ፣ የሀገሪቱን ሁኔታ በአጠቃላይ የሚያስተካክል የሽግግር መንግስት ያስፈልጋል የሚል አቋም የያዘው፡፡
የዜጐች የሀገር ባለቤትነትም ሆነ የዜግነት መብት የሌለበት ሀገር፣ ሀገር አይደለም፡፡ ይሄ  አካሄድ በመጀመሪያ መቀየር ያለበት፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ የሽግግር ጊዜ ያስፈልገናል፡፡ ያ የሽግግር ጊዜ ግን አሁን እንደሚባለው ሳይሆን ሁሉን ያሳተፈ ሃቀኛ መሆን አለበት፡፡ በሽግግር ጊዜ ውስጥ ከዚህ በፊት የነበሩ የፖለቲካ ቅሬታዎችና ወንጀሎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሽረን የምንሄድበት የእርቅና የእውነት አፈላላጊ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ብሔራዊ እርቅ መደረግ አለበት፡፡  የጋራ ራዕይ ያለው ህገ መንግስት በጋራ መቅረጽ ያስፈልገናል፡፡ ይሄ ምናልባት ሁለትና ሶስት አመት ሊፈጅ ይችላል፡፡ በዚህ መንገድ ነው አሁን ያለውን ሁኔታ ልንወጣው የምንችለው:: አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ አማራጭ ይዞ የሚወዳደሩበት ጊዜ ላይ አይደለንም:: ኢትዮጵያ ካለችበት ለመውጣት ሃቀኛ የሽግግር ጊዜ ያስፈልጋታል የሚል እምነት ነው ያለን፡፡ አሁን የፓርቲ አላማዎችን ይዘን ሶሻሊስት ይሻላል፣ ሊበራል እያልን የምንነጋገርበት ሁኔታ ገና አልተፈጠረም፡፡ በመጀመሪያ ሀገር ሊኖረን፣ የዜግነት መብትም ሊኖረን ይገባል፡፡ ይሄን ሃሳብ ግን እኛ ለውጥ ከተባለው እንቅስቃሴ በፊትም ስንገፋበት የነበረ ነው፡፡
ከጽንፈኛ ብሔርተኝነት ወይም ከዘር ፖለቲካ ለመውጣት መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?
ሁሉን አካታች የሽግግር ጊዜ ነው ወደፈለግንበት ብሩህ ጊዜ ሊያሻግርን የሚችለው፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት ለጠቅላይ ሚኒስትሩም የሚበጃቸው ሁሉን አካታች የሽግግር ጊዜ ተፈጥሮ ህገ መንግስት ማሻሻል፣ ብሔራዊ እርቅና መግባባት መፍጠር ነው፡፡ አሁን በጐሰኝነት ምክንያት ፍትህ ማስፈን አልተቻለም፡፡ ዜጐች ሀገር የላቸውም፡፡ እነዚህ ሁሉ የሚስተካከሉት በሽግግር ጊዜ ብቻ ነው፡፡ አዲስ ሃሣብን ለመቀበልም ክፍት መሆን ያስፈልጋል፡፡      
በእነጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የሚመራውን “የአዲስ አበባ ባለአደራ ም/ቤት” እንቅስቃሴ ፓርቲያችሁ ይደግፈዋል?
አዲስ አበባ ማለት፤ አዲስ አበባን የፈጠሯት ሰዎች ባህል፣ አዲስ አበባ የሚኖሩና የገነቧት ሰዎች ላብ፣ አዲስ አበባ የሚኖሩ ሰዎች ሀብት ነች፡፡ አዲስ አበባ የኔ ነች የሚለው የአንድ ወገን አካሄድ የታሪክም፣ የነባራዊ ሁኔታም፣ የሎጂክም መጣረስ ያለበት ነው፡፡ ስለዚህ የእነ እስክንድርን እንቅስቃሴ እኛም ፖለቲካዊ ድጋፍ የምንሰጠው ነው፡፡ አቋሙ የኛም አቋም ነው፡፡ ለጊዜው በነፃና ገለልተኛ አካል ተይዞ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ቢሆን ይሻላል ከሚል እንጂ ከእነ እስክንድር ቀደም ብሎም ንቅናቄያችን የፖለቲካ አቋም የያዘበት ጉዳይ ነው፡፡
የፓርቲዎችን  ውህደት በተመለከተ አቋማችሁ  ምንድን ነው? ኢሃን ለመዋሃድ አላሰበም?
አሁን ደካሞችን እያበረታታ ጠንካሮችን የሚያባርር አካሄድ የለም፡፡ ስለዚህ ደካማ ሆነው ቀደሞ ሲል ሲበረታቱ የነበሩት ወደ ትክክለኛ ጥንካሬ ለመምጣት፣ በውህደት ከጠንካሮች ጋር ቢካተቱ ችግር የለውም፡፡ 107 ፓርቲዎች አሉ ይባላል እንጂ አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ይሄን እናንተ ሚዲያዎች የምትመሠክሩት ነገር ነው፡፡ እኔ ራሴ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥራ ብትለኝ ከ10 የበለጠ መጥራት አልችልም፡፡ ብዙዎቻቸውን አላውቃቸውም፡፡ አሁን መሰባሰባቸው በመርህ ደረጃ መልካም ነው፡፡ ጥንካሬን ለመፍጠር ይረዳል፡፡ እኛም በተለያየ መንገድ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ የጋራ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ ከአብንም ሆነ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር እንሠራለን፡፡ ኢዜማ ሲመሠረት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አነጋግረውኝ ነበር፡፡ እኔም የማምንበትን ሊሆን የሚገባውንና በሀገራዊ ሁኔታ ላይ ያለን ሁኔታ ሊቀራረብ እንደሚገባ ተነጋግረን ነበር፡፡ ነገር ግን በተለይ በሀገራዊ ሁኔታ ላይ ያለን ምልከታ የተለያየ ስለሆነ መዋሃድ አልቻልንም፡፡ እኛ ይሄ ህገመንግስት እስካለ ድረስ የነፃነት ትግል አላበቃም እንላለን፡፡ እነሱ ደግሞ የነፃነት ትግል አብቅቶ የምርጫ ፖለቲካ እንደተጀመረ አድርገው ለምርጫ የሚዘጋጅ ፓርቲ ነው የምንመሰርተው ይላሉ፡፡ በዚህ ነው የአቋም ልዩነት ያለን፡፡ ለውጡ ላይ ያለን አተያይም ይለያያል፡፡ በአማራ ብሔርተኝነት ጉዳይም ላይ  ያለን ምልከታ  የተለያየ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ በለውጡ ላይ አሉታዊ አስተያየት ሲሰነዝሩ እሰማለሁ፡፡ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር በቅርበት  ተወያይታችሁ ታውቃለችሁ?
በስብሰባ ላይ ከሰዎች ጋር አያቸዋለሁ፤ ሠላምም እላቸዋለሁ፡፡ ከዚያ ውጭ ፖለቲካን በተመለከተ በግል ተነጋግረን አናውቅም፡፡ በተረፈ ግን  እሣቸው ሲተቹ፣ ሰዎች ደስ አይላቸውም፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ለእርስዎ  ምን አይነት መሪ ናቸው?
ይሄን ጥያቄ ልብ ብዬ አጢኜው አላውቅም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ድርጅት ሌላ፣ እንደ ግለሰብ ደግሞ ሌላ ናቸው፡፡  ፖለቲካዊ ለሆኑ ጉዳዮች ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደ መስጠት እሣቸው ግን ሁለት አይነት መልክ ነው ይዘው የሚንቀሳቀሱት:: ለኔ ዶ/ር ዐቢይ የህዝበኝነት ባህርይ ያላቸው፣ ለትችት ስስ የሆኑ፣ በሶሻል ሚዲያ ለተፃፈ ነገር ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ሰው ናቸው፡፡ በግላቸው መጥፎ ሰው አይመስሉኝም፡፡ የግል ሰብዕናቸውን  ከፖለቲካ አቋማቸው ጋር ማደባለቅ  አልፈግልም፡፡ በድርጅት ውስጥ ያደጉ የድርጅት መርህ ተገዥ ሰው ናቸው:: የራሣቸው ፓርቲ በህገ መንግስቱ አልደራደርም ሲል፣ አዲስ አበባ የኔ ናት ሲል፣ ለገጣፎ ያ ሁሉ ቀውስ ሲከተል፣ እሣቸው ዝም ነው ያሉት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከድርጅቱ በተቃራኒ የሆነ ነገር ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ ቃል ከተግባር የገጠመላቸው አይመስለኝም፡፡

Read 1288 times