Saturday, 08 June 2019 00:00

የዩኒቨርሲቲ ቦርድ ለምን ያስፈልጋል?

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(1 Vote)


              “--እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ የሂሣብ መዝገብ አያያዝ (አካውንቲንግ) የሚያስተምሩና የሚያስመርቁ ዩኒቨርሲቲዎቻችን፤
ለሌሎች አርኣያ መሆናቸው ቀርቶ የፋይናንስ ስርዓታቸው የተበላሸና የሙስና ካምፖች ከሆኑ፤ የሀሪቱን ችግር እንዴት አድርገው ሊፈቱ ይችላሉ? እንደኔ እንደኔ፤ ራሳቸውን በስርዓት ማስተዳደር የተሳናቸው ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት፣ ሀገርን የሚረከብ ብቁና ንቁ ትውልድ ማፍራት ይችላሉ ብሎ መጠበቅ ከንቱ ልፋት ነው፡፡--”
             
              ቀደም ባሉ ጊዜያት “ዩኒቨርሲቲዎቻችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወይስ  ከፍተኛ የዝርፊያ ተቋማት? የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታ በጥድፊያ?! - ሌላ ትውልድ እንዳንገድል! እና የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች አሿሿም አሁንም ሊጤን ይገባዋል!” በሚሉ ርዕሶች የተለያዩ መጣጥፎችን በአዲስ አድማስ ጋዜጣና በማህበራዊ ሚዲያዎች ጭምር ለአንባቢያን አድርሼአለሁ፡፡   
“አንድ ግለሰብም ይሁን ማህበረሰብ ከምር (ከልቡ) ተለወጠ ሊባል የሚችለው ሰውየው ወይም ማህበረሰቡ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ካመጣ ነው” ይላሉ ሊቃውንት፡፡ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ደግሞ እንዲሁ “ልለወጥ” ብለን የምንለውጠው “ተራ” ለውጥ አይደለም፡፡ “የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ በእውቀት (በትምህርት) ላይ የተመሰረተ መሰረታዊ ለውጥ (Paradigm Shift) ነው” ይላሉ ምሁራን:: የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በትምህርት ዙሪያ ተደጋጋሚ መጣጥፎችን በዚሁ በአዲስ አድማስ ጋዜጣና በማህበራዊ ሚዲያዎች ጭምር የሚያቀርብበት ዋነኛ ምክንያትም ትምህርት (እውቀት)፤ ለአንድ ማህበረሰብ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ያለውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባትና ትምሕርት የዘላቂ እድገትና ልማታችን ህብለ-ሰረሰር በመሆኑ ነው፡፡
ኢህአዴግ እስከ “ዘመነ ኃ/ማሪያም” ድረስ ጆሮውን በጥጥ ደፍኖ፣ ሁሉንም ነገር በአልሰማ ባላየ ያልፈው ነበር፡፡ የ“መደመር”ን መፈክር (Motto) በማስተጋባት ላይ ያለው አዲሱ ኢህአዴግ የሚሰማ ስለመሆኑ መቶ በመቶ እርግጠኞች ባንሆንም፤ ዛሬም በአሳሳቢ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጩኸት ማሰማታችንን እንቀጥላለን፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለያዩ ጊዜያት ማነጋገራቸው ይታወቃል፡፡ መምህራንን፣ ባለሃብቶችን፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን፣ በቅርቡም ሀኪሞችን አነጋግረዋል፡፡ የዩኒቨርስቲ መምህራን ወዳጆቼ እንደጠቆሙኝ ከሆነ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዩንቨርስቲ ፕሬዚዳንቶችንና የቦርድ አባላትን በዚህ ሳምንት መገባደጃ ላይ ለማነጋገር አስበዋል፡፡ ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝም ይኸው መረጃ  ነው፡፡
ይህ መጣጥፍ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን (ዩኒቨርስቲዎችን) የሚመራ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በተቋቋመበት ሁኔታ የዩኒቨርስቲ አስተዳደር ቦርድ ማቋቋም አስፈላጊ ነው ወይ? የአሁኑ ቦርድ ትናንት ከነበረው ቦርድ በምን ይለያል? የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት የሚመረጥበት ሂደትስ የዩኒቨርስቲዎችን ነጻነት የሚያረጋግጥ ነው? የሚሉና መሰል ጥያቄዎች ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ከአዋጁ ልጀምር…
ከዚህ በፊት በአንድ መጣጥፌ እንደገለጽኩት፤ ዩኒቨርሲቲዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስለሚመሩበት ሁኔታ በአዋጅ ቁጥር 650/2001 በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ በዚሁ አዋጅ በአንቀጽ 16 ላይ ስለ አካዳሚያዊ ነጻነት በሦስት ንዑስ አንቀፆች ሰፍሯል፡፡ ማንኛውም ከፍተኛ የትምህርት ተቋም፤ በተቋሙ ተልእኮና በአለም አቀፍ መልካም ልምድ መሰረት፣ አካዳሚያዊ ነጻነት እንደሚኖረውም ተጠቅሷል፡፡ በአንቀጽ 17 ላይ ደግሞ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ነፃነት፣ ምን መሆን እንዳለበት ተገልጿል፡፡ በአንቀጽ 44 ላይ የዩንቨርስቲ ቦርድ ኃላፊነቶች በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ በአንቀጽ 45 መሰረት፤ የቦርዱ አባላት የሚመረጡት በሚኒስትሩ መሆኑም ተደንግጓል፡፡ በአንቀጽ 52 ላይ የመንግስት የትምህርት ተቋም ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት አሿሿምን በተመለከተ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡
ስለ ዩኒቨርስቲ ቦርድ…
ዩኒቨርስቲዎችን በበላይነት የሚመራው ዩኒቨርስቲ ቦርድ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 44 እና 45 ላይ ስለ ቦርዱ ስልጣንና ተግባር እንዲሁም ስለ ቦርዱ አባላት አመራረጥ ሰፋ ብሎ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችን የሚመሩ የአስተዳደር ቦርድ አባላት ብዛት 7 ሲሆን አራቱ በሚኒስትሩ በቀጥታ የሚመረጡ ሲሆን ሦስቱ በዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት አቅራቢነት በትምህርት ሚኒስትሩ የሚጸድቅ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ በዚህም መሰረት የትምህርት ሚኒስትሩ ሁሉንም የቦርድ አባላት መርጦ ይሾማል ማለት ነው፡፡
ሚኒስትሩ የቦርድ አባላቱን በምን መስፈርት እንደሚመርጡ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም:: እስከ አሁን ባለው አሰራር፤ በማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት የሚቋቋሙ ቦርዶች አባላት የሚመረጡበት ዋነኛ መስፈርት  አንድም የገዢውን ፓርቲ የአባልነት መታወቂያ መያዝ አሊያም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን መሆን እንጂ እውቀት፣ ብቃትና ልምድን ማዕከል በማድረግ አልነበረም፡፡ የዩኒቨርስቲ ቦርድ አባላትም ከዚህ በተለየ መስፈርት ይመረጡ ነበር ብሎ ለመውሰድ ያስቸግራል:: በአጭር አነጋገር፤ የነበረው አሰራር አካታች መስፈርትን መሰረት ካደረገ ምልመላና መረጣ ይልቅ በድርጅታዊ ኮታ የሚደረግ ምደባ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
የዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ቦርድ አባላትም በተመሳሳይ ሁኔታ በዚህ መልኩ እንዲመደቡ በመደረጉ ምክንያት ለሀገራቸው አስተዋጽዖ ማበርከት የሚችሉ የኢህአዴግ አባል ያልሆኑ ዜጎች እድሉን የሚያገኙበት ሁኔታ ዝግ ነበር፡፡ ስለሆነም፤ ይህ ዓይነቱ ዘርንና የፓርቲ አባልነትን ብቻ “ውስጣዊ መስፈርት” ያደረገ የቦርድ አባላትን የመመደብ አሰራር ቀርቶ ለዩኒቨርሲቲው እድገት አስተዋጽዖ ለሚያደርጉ ዜጎች ሁሉ እድሉ ክፍት ሊሆን ይገባል፡፡ እናም አሁን በስራ ላይ ያለው የመምረጫ መስፈርት ቢመረመር መልካም ነው፡፡
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፤ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ፣ የተለያየ እምነትና ህልም ያላቸው ወጣቶች የሳይንስ እውቀት የሚቀስሙባቸውና ምርምር የሚያደርጉባቸው የእውቀት መቅደሶች እንጂ የፓርቲ ርዕዮተ-ዓለም የሚጋቱባቸው መድረኮች አይደሉም:: እናም፤ የእውቀት መቅደሶችን የሚመሩ ሰዎች የሳይንስ እውቀት፣ የአስተዳደር ጥበብና ልምድ ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ አስፈላጊ ነው እላለሁ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ወቅት እየተነሳ ያለው መሰረታዊ ጥያቄ፤ ለመሆኑ ዩኒቨርስቲዎች የአስተዳደር ቦርድ ያስፈልጋቸዋል ወይ? የሚለው ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶችን ለማሰባሰብ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡
የዩኒቨርስቲ ቦርድን አስፈላጊነት በተመለከተ ያነጋገርኳቸው የዩኒቨርስቲ ምሁራን “ቀደም ሲል የዩኒቨርስቲ ቦርድ እንዲኖር የተደረገው የትምህርት ሚኒስቴር ከመዋዕለ ሕጻናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ የትምህርት ስርዓቱን የመምራት ኃላፊነት ተጥሎበት ስለነበር ሸክሙን ለማቅለል የተነደፈ ስልት ነበር፡፡ አሁን በተፈጠረው አዲስ አደረጃጀት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ብቻ የሚመራ የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተቋቁሟል፡፡ ይህ ሚኒስቴር መ/ቤት በሀገሪቱ ያሉ 45 ዩኒቨርስቲዎችን በቀጥታ ለመምራት አያስቸግረውም” በማለት የቦርዱን አላስፈላጊነት ይገልጻሉ፡፡
እኔ በሙያዬ የኢኮኖሚ ሳይንስ ተምሬያለሁ፡፡ የኢኮኖሚ ሳይንስ ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች አንዱ የሀብት አጠቃቀም ነው፡፡ እናም የቦርዱን አላስፈላጊነት ከሀብት አጠቃቀም አኳያ ማየት ይቻላል፡፡ በዚህም መሰረት፤ አርባ አምስቱ ዩኒቨርስቲዎች እያንዳንዳቸው ሰባት ሰባት የቦርድ አባላት በድምሩ 315 የቦርድ አባላት ይኖሯቸዋል፡፡ ቦርዱ በዓመት አራት መደበኛና ተጨማሪ አስቸኳይ ስብሰባዎችን ያደርጋል፡፡ ለእነዚህ የቦርድ አባላት በአማካይ በዓመት ለእያንዳንዳቸው 200 ሺህ ብር ወጪ ይደረጋል ብለን ብንወስድ፣ በድምሩ 63 ሚሊዮን ብር በጀት መመደብ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ይህ ስሌት የተጋነነ እንዳይመስላችሁ፡፡ እንዲያውም ያሳነስኩት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የቦርድ አባላት ለስብሰባ ተጠርተው ሲመጡ የሚያርፉት በባለ ኮከብ ሆቴል ነው:: በመጓጓዣ ረገድ ከሩቅ የሚመጡት አውሮፕላን ጭምር ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ሾፌርና አጃቢ ይዘው የሚመጡም ይኖራሉ፡፡ በዚህ ላይ የመስተንግዶውን ወጪና በእጃቸው በጥሬ የሚሰጣቸውን ጨምሩበት፡፡ ይሄ ሁሉ ሲደማመር ለእያንዳንዳቸው በአማካይ በዓመት ከ200 ሺህ ብር በላይ ወጪ ይደረጋል ብሎ ማስቀመጥ የተጋነነ ሊሆን አይችልም ብዬ አስባለሁ፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ላለ ድሃ ሀገር 63 ሚሊዮን ብር ብዙ ነው፡፡ ይህንንም በስሌታዊ ንጽጽር እንየው፡፡ ባለፉት ዓመታት ፌዴራል መንግስት ለትምህርት ሚኒስቴር ከመደበው በጀት ውስጥ ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉት የትምህርት ደረጃዎች የተመደበው አንድ ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ 63 ሚሊዮን ከዚህ ጋር ሲነጻጸር 6.3% ይሆናል፡፡ ይህ ገንዘብ ለ63 የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች አንድ አንድ ሚሊዮን ብር ቢመደብ፣ በየዓመቱ በ63 ት/ቤቶች የተሟላ ላቦራቶሪ ወይም ቤተ መጽሐፍት ወይም የኮምፒዩተር ማዕከል ማደራጀት ይቻላል ብዬ አስባለሁ፡፡
ከአደረጃጀት አኳያ የዩኒቨርስቲ ቦርድ፤ ቢሮ የሌለው፣ ጽ/ቤት አልባ፣ የማይጨበጥ የማይዳሰስ ግን ደግሞ ትልቅ ስልጣን የተሸከመ አካል ነው:: የቦርድ አባላትም ከዩኒቨርስቲ ግቢ ርቀው ባሉ ሌሎች መስሪያ ቤቶች በተለያዩ ኃላፊነቶች የሚሰሩ በመሆኑ፣ የቦርድ አባል የሆኑበትን ዩኒቨርስቲ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ በቅርበት አያውቁም፡፡ የሚገርመው ነገር፤ ከማያውቁት ተቋም እጩ ሆነው የቀረቡ ግለሰቦችን በ65% ድምፅ የመመልመል ስልጣን የተሰጣቸው መሆኑ ነው፡፡
ስለ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት…
ዩኒቨርሲቲዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስለሚመሩበት ሁኔታ በአዋጅ ቁጥር 650/2001 የተደነገገ ቢሆንም እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ የአዋጁን መንፈስ በተጻረረ መልኩ ዩኒቨርሲቲዎች ብቃትን ሳይሆን ፖለቲካዊና ዘውጋዊ ማንነትን ባማከለ መልኩ በተሾሙ የገዥው ፓርቲ እንደራሴዎች እንዲመሩ ተፈርዶባቸው ቆይተዋል:: ይህ የተሳሳተ አሰራር በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መተቸቱን ተከትሎ የትምሕርት ሚኒስቴር “በመንግሥት የከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት የአመራሮችና አስተዳዳሪዎችን ምርጫ ሹመት/ምደባ ለመደንገግ የወጣ መመሪያ ቁጥር 002/2009” የተሰኘ ደምብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
እዚህ ላይ መነሳት የሚገባው ጥያቄ፤ የከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት አሿሿም የአፈጻጸም መመሪያ የአዋጁን መንፈስ ተከትሎ የተዘጋጀ ነው ወይ? የሚል ነው፡፡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው በዩኒቨርሲቲ ለረዥም ጊዜ ያስተማሩ ወዳጆቼ እንደነገሩኝ ከሆነ፤ በደንቡ ውስጥ በመስፈርትነት የተቀመጡት አንዳንዶቹ መመዘኛዎች ከአዋጁ መንፈስ ጋር የሚቃረኑ ናቸው፡፡
የአዋጁ መንፈስ ከዩኒቨርሲቲዎቹ ማህበረሰብ ውስጥ ለዩኒቨርስቲዎቹ የላቀ አመራር (Strategic Leadership) ሊሰጡ የሚችሉ ሰዎችን በመምረጥ መሾም ነው፡፡ ይህ የአዋጁ መንፈስ ግን በደንቡ አተገባበር የተጣሰ መሆኑ ይስተዋላል፡፡ ለአብነት ያህል “የዩኒቨርሲቲ አመራሮች አመራረጥና አሰያየም” የሚል ርዕስ ያለው የዚሁ ደምብ አንቀጽ 6/3/ለ፣ ለዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትነት የሚወዳደር እጩን የሥራ ልምድ አስመልክቶ “በከፍተኛ ትምሕርት ወይም ከዚህ ውጭ ባለ መስክ፣ በከፍተኛ አመራርነት የተረጋገጠ የሥራ ልምድ ያለው...” ይላል::
እንዲህ ያለው “ሊበሏት ያሰቧትን ዥግራ ዶሮ ናት ይሏል” ዓይነት አካሄድ በዩኒቨርስቲ ውስጥ ብቻ ሳይሆን “በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነት እየሰሩ ያሉ ካድሬዎችን ወደ ፕሬዝዳንትነት እናሳድግ” ከማለት የዘለለ ትርጉም የለውም፡፡ የዚህ መመሪያ ውጤት የሆኑ በቅርብ ጊዜ በዲላ፣ በጎንደርና በአሶሳ ዩኒቨርስቲዎች የተደረጉ ሹመቶችን መመልከት ይቻላል፡፡
ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት አምስት እሴቶች እንዳሏቸው ይነገራል፡፡ እነዚህም እሴቶች “ተደራሽነት፣ አካዳሚያዊ ነጻነት፣ ተጠያቂነት፣ ግልጽነት እና በሕግ የተገደበ ስልጣን” (access, academic freedom, accountability, transparency and autonomy) የሚሉ ናቸው:: ከአምስቱ የከፍተኛ ትምሕርት እሴቶች አንዱ የሆነው “በሕግ የተገደበ ስልጣን” (autonomy) የሚለውን እንውሰድ፡፡ ይህ እሴት ዩኒቨርስቲዎች የራስ ገዝነት ስልጣን ያላቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህ ማለት ዩኒቨርስቲው የመንግስት ተቋም ቢሆንም በህግ የተገደበ ውስጣዊ የአሰራር ነጻነት ሊሰጠው ይገባል ማለት ነው፡፡
አሁን እየተተገበረ ባለው አሰራር ይህ “ነጻነት” ተከብሯል ለማለት የማያስደፍር መሆኑን ይናገራሉ፤ የዩኒቨርስቲ ማኅበረሰብ አባላት፡፡ “ምክንያቱም አሁንም የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች የሚመረጡት 65% በዩኒቨርስቲው ቦርድ፣ 35% ደግሞ በመራጭ ኮሚቴና በሴኔት ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው በአጭሩ የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች የሚመረጡት በቦርዱ መሆኑን ነው፡፡ የቦርዱ አባላት ደግሞ በፖለቲካና በብሔር ወገንተኝነት የሚመረጡ በመሆኑ ቦርዱ ከመጠን ያለፈ ፖለቲካ የተጫነው (Hyper-politicised) ነው” ይላሉ፡፡ ቀጥለውም “መመሪያው የወጣበት ምክንያት ቀደም ሲል የነበረውን የፖለቲካ ፓርቲ አባልነትንና የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረገ አሰራር ወደ ልምድና ብቃት (ሜሪት) መስፈርት ለመቀየር ነው፡፡ ይህ መርህ ሊከበር ይገባል” ይላሉ፤ አስተያየት ሰጪዎቹ፡፡
እንደ መሰናበቻ…
በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርስቲዎቻችን የተልፈሰፈሱ መሆናቸው ይስተዋላል፡፡ የተልፈሰፈሱ ተቋማት የነገውን ትውልድ በአግባቡ የማነጽ ተልዕኳቸውን መወጣት ቀርቶ የራሳቸውን ተቋማዊ አሰራር በተሻለ ስርዓት መምራት ባለመቻላቸው፣ ዋናው ኦዲተር መ/ቤት፣ በየዓመቱ በሚያቀርበው የኦዲት ሪፖርት፣ በዩኒቨርስቲዎቹ  የሚፈጸመውን የገንዘብ ብክነትና የምዝበራ መርዶ እየነገረን ነው፡፡
እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ የሂሣብ መዝገብ አያያዝ (አካውንቲንግ) የሚያስተምሩና የሚያስመርቁ ዩኒቨርሲቲዎቻችን፤ ለሌሎች አርኣያ መሆናቸው ቀርቶ የፋይናንስ ስርዓታቸው የተበላሸና የሙስና ካምፖች ከሆኑ የሀሪቱን ችግር እንዴት አድርገው ሊፈቱ ይችላሉ? እንደኔ እንደኔ፤ ራሳቸውን በስርዓት ማስተዳደር የተሳናቸው ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት፣ ሀገርን የሚረከብ ብቁና ንቁ ትውልድ ማፍራት ይችላሉ ብሎ መጠበቅ ከንቱ ልፋት ነው፡፡ አካዳሚያዊ ነጻነትና ጥራት “ማሳ እና አዝመራ” ናቸው:: አካዳሚያዊ ነጻነት በሌለበት ሁኔታ ጥራት ያለው ትምሕርት መጠበቅም፣ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው የሚሆነው::
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ 2፤ “ትምሕርት በማናቸውም ረገድ ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካ አመለካከቶች እና ከባሕላዊ ተፅዕኖዎች ነፃ በሆነ መንገድ መካሔድ አለበት” ይላል፡፡ ይህ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ እስከ አሁን መንግስት እየተከተለው ባለው አሰራር ተጥሷል:: ለረጅም ዓመታት በዩኒቨርስቲ ያስተማሩና የተመራመሩ ፕሮፌሰሮች፤ “ዩኒቨርስቲዎች ከመጠን ባለፈ የፖለቲካ ጫና ውስጥ (Hyper-policised) ነበሩ፡፡ የዶክተር ዐቢይ መንግስት፤ ዩኒቨርስቲዎችን ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በማላቀቅ (Depoliticized) ሊታደጓቸው ይገባል” በማለት የረጅም ጊዜ ትዝብታቸውን ይገልጻሉ፡፡
ዩኒቨርስቲዎች የምርምር ተቋማት ናቸው፡፡ ምርምር ሣይንስ ነው፡፡ ሣይንስ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የምንም ነገር ጣልቃ ገብነት አያስፈልገውም፡፡ እስከ አሁን ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻችንን እየመራን የመጣንበት መንገድ ከመጠን ያለፈ የፖለቲካ ጫና (Hyper-policised) የነበረበት መሆኑ አሌ የሚባል አይደለም፡፡ ለራሱ አካዳሚያዊ ነፃነት የሌለው ተቋም፤ ነፃነት ያላቸው፣ ሰብእናቸው የተሟላ ዜጎችን ለማፍራት ይችላል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያት የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶችም ሆኑ የቦርድ አባላት ይሾሙ የነበሩት የፖለቲካ ታማኝነትንና ዘርን መሰረት አድርጎ ነበር፡፡ ይህ አሿሿም ሙስናንና ዝርፊያን አላስቀረም፡፡ የትምህርት ጥራትን አላመጣም፡፡ የመምህራንን ችግር አልፈታም:: ሕዝብንና ሀገርን ተጠቃሚ አላደረገም፡፡
ስለ ዩኒቨርስቲ ቦርድ አንዲት ነጥብ ልጨምርና ልሰናበት፡፡ ስለ ቦርዱ የጠየቅኳቸው አንድ የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሰጡኝን አስተያየት ላስቀድም፡፡ “የፖለቲካ ቦርድነቱ ይቁም፤ አለያም ቦርዱ ከናካቴው እንዳይኖር ቢደረግ ይሻላል” ብለውኛል፤ፕሮፌሰሩ፡፡ ሌላ ምሁር ደግሞ “እንደኔ እንደኔ በአጠቃላይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዴት ይደራጁ? እንዴትስ ይመሩ? የሚለውን የምርምር ጥያቄ አንስተው፤ በጥናት ላይ የተመሰረተ ምክረ ሃሳብ የሚያቀርቡ ምሁራን ቢመደቡና ጥናት ቢያደርጉ፣ ችግሩን በሳይንሳዊ አግባብ ለመፍታት ይቻላል” በማለት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡  
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ግን የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች የምረጡኝ ዘመቻ አድርገው በቀጥተኛ የምርጫ አግባብ (Direct Democracy) በዩኒቨርስቲው ማህበረሰብና በሚመለከታቸው ውስን አካላት እንዲመረጡ ቢደረግ የተሻለ ነው ብሎ ያምናል፡፡
 ከአዘጋጁ፡- ጽሁፉ የሚያንጸባርቀው የጸሃፊውን ሃሳብ ብቻ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢ-ሜይል አድራሻው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1248 times