Saturday, 02 June 2012 10:41

የአሜሪካን አይዶል አሸናፊ 9ኛውን ቀዶ ህክምና አደረገ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የዘንድሮ የአሜሪካን አይዶል አሸናፊ ፊሊፕ ፊሊፕስ፤ በመላው አሜሪካ ተዘዋውሮ የሙዚቃ ኮንሰርት እንዲያቀርብ የጤና ሁኔታው መቶ በመቶ አስተማማኝ መሆን እንዳለበት ወላጅ አባቱ ለፒፕል መፅሄት ተናገሩ፡፡ የ21 ዓመቱ ተወዳዳሪው ዓመቱን አሜሪካን አይዶል እየተወዳደረ ያሳለፈ ሲሆን ጎን ለጎን ደግሞ በገጠመው የኩላሊት ጠጠር ችግር ስምንት ግዜ ቀዶ ጥገና አድርጎዋል፡፡ ከአንድም ሁለቴ በጠና ታምሞ ከውድድሩ ለመውጣት ቁዋፍ ላይ  ደርሶ እንደነበርም ታውቁዋል፡፡ ፊሊፕ አሸናፊ ከሆነም በኋላ ሰሞኑን 9ኛውን የቀዶ ህክምና ማድረጉን ቲኤምዜድ ዘግቧል፡፡ በዘንድሮ የአሜሪካን አይዶል ምርጫ ከተመልካቾች 132 ሚሊዮን ድምፅ የተሰጠ ሲሆን በአይዶል ታሪክ ከፍተኛው ቁጥር ተብሎ ተመዝግቧል፡፡ የውድድሩን ፍፃሜ 22 ሚሊዮን የቲቪ ተመልካቾች በመላው አሜሪካ የታደሙት ቢሆንም ከባለፈው ዓመት በ18 በመቶ መውረዱ ተጠቅሶዋል፡፡

በመጨረሻው የውድድር ቀን ፊልፕስ ከ16 ዓመቷ ጄስካ ሳንቼዝ ጋር ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ  ገብቶ እንደነበር የጠቆሙ መረጃዎች፣ሆኖም የጊታር መሳርያ በመጫወቱና የራሱን ዘፈኖች አብዝቶ በማቀንቀኑ ብልጫ ማግኘት እንዳስቻለው አመልክተዋል፡፡ ሁለቱም ድምፃዊያን በማህበረሰብ ሚዲያ አጠቃቀማቸው ንቁ የነበሩ ሲሆን ከፍተኛ ደጋፊዎችና ተከታታዮች ማፍራት ችለዋል፡፡ አሸናፊው ፊሊፕ ፊሊፕስ በትዊተር 317ሺ ተከታታዮች፤ 240ሺ የፌስቡክ ወዳጆች የነበሩት ሲሆን በጉግል የመረጃ አፈላላጊ ድረገጽፅ እስከ 55.9 ሚሊዮን መልሶች ተመዝግቦለታል፡፡ ይሁንና ተሸናፊዋ ጄሲካ ሳንቼዝ በእነዚህ ሶሻል ሚዲያዎች የላቀ ትኩረት ነበራት፡፡

በአሜሪካን አይዶል ወንድ ድምፃዊ ሲያሸንፍ ዘንድሮ ለ5ኛ ተከታታይ ዓመት መሆኑንና በውድድሩ ሁለተኛ ደረጃ ያገኘችው የ16 ዓመቷ ጄሲካ ሳንቼዝ ፣የወትሮውን ሽልማትና የአልበም ስራ እድል ማጣቷ ትችት አስከትሎዋል፡፡ የተበረከተላት የ30ሺ ዶላር የገንዘብ ሽልማት የተወሰኑ ነጠላ ዜማዎችን ብቻ የሚያሰራ መሆኑ ታውቆዋል፡፡ ቀደም ሲል በተደረጉ የአሜሪካን አይዶል ውድድሮች ሁለተኛ ደረጃ ለሚያገኝ ተወዳዳሪ የአልበም ስራ እና እስከ 175ሺ ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ሽልማት ይሰጠው የነበረ ሲሆን ዘንድሮ መቅረቱን ብዙዎች ተችተውታል፡፡ የውድደሩ አሸናፊ ፊሊፕ ፊሊፕስ በበኩሉ፣ በመላው አሜሪካ በመዘዋወር ከሚያቀርባቸው ኮንሰርቶች ባሻገር ሙሉ አልበሙን አስርቶ ከጨረሰ በኋላ 300ሺ ዶላር የገንዘብ ሽልማት ያገኛል፡፡ ሌሎች ተጨማሪ አምስት አልበሞችን ከአሜሪካን አይዶል የሙዚቃ አሳታሚ “19 ሪከርዲንግስ” ጋር ለመስራት ከተስማማ ደግሞ የፊሊፕ የገንዘብ ክፍያ 800ሺ ዶላር እንደሚደርስም ተጠቁሞዋል፡፡

 

 

Read 768 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 10:43